የጠፋው ልጅ ሰቆቃ

የእግዚአብሄር ፈቃድ

የጠፋሁት ልጅ ነኝ፤ የኮበለልኩና የተራቆትኩ፣ ርቄ ተጉዤም በዚያው የተሰወርኩ ነኝ፣ራሴን በእርያዎች መሀል ደብቄ ከመልካሙ አባቴ የተገለልኩ አመጸኛ፡፡ዛሬ በዚያ ባለሁበት ሆኜ አባቴ ሊያየቸው እንኩዋን ከሚጸየፋቸው ጋር ተወዳጅቻለሁ፡፡ማድረግ የሌለብኝን እያደረግኩ በመኖር ላይም እገኛለሁ፡፡ ለዛሬ ኑሮዬ የዳረገኝ እምቢተኝነቴ ሲሆን ያ ያለመታዘዜ ምክኒያት ሆኖ ከአባቴ ለይቶ አርቆኛል፡፡ የመጣሁበት አገር ኑሮ ገና ከሀገሬ ሳልነሳ በፊት እንደገመትኩት አልሆነልኝም፡፡ ከባእድ አገር አመል መላቀቅ ስላልቻልኩ ቆይታዬ ከባድ ህይወትም መራር ሆኖብኛል፡፡በአባቴ ቤት ያደግኩበት ማንነት ተሸርሽሮ የባእድ ሰዎችን ልማድ እየኖርኩበት እገኘለሁ፡፡ ከድሎት ቤቴ ከወጣሁ ሰንብቻለሁ፡፡ ስወጣ በትምክህት ነበር፤ ያኔ ማንንም ሳላማክርና ሳላስከትል ስላደረግኩ ዛሬ ከእኔ ጋር ሆኖ የሚደግፈኝ፣ አይዞህ ሲል የሚያጽናናኝ፣ የሚያበረታኝ ወይም ጉድለቴን የሚካፈል የልብ ወዳጅ የለኝም፡፡ወዳጆቼን ከሁዋላ ትቼ ወጥቻለሁ፤ ቤተሰቤን ላለመስማት ጠፍቻለሁ፤ ስለዚህ ዛሬ ብቻዬን እቸገራለሁ፡፡ከቤቴ ይዤ የወጣሁት የአባቴ ገንዘብ ብዙ ነበር፡፡ ያን ገንዘብ እንደልቤ ስላባከንኩ አሁን በእጄ ላይ ምንም እስካይቀር ሆኖአል፡፡በመልካም ጊዜ ማንንም ስላልፈለግኩ በችግሬ ወቅት ፈላጊ የለኝም፤ ስለዚህ በረሃቤ የሚያበላኝ በጥማቴ የሚያጠጣኝ የለም፡፡ ባለኝ ወቅት አባካኝ እንጂ ቸር ስላልነበርኩ ቸርነት የሚያደርጉልኝን አላገኘሁም፡፡ማንንም አልፈለኩም፣ ስለዚህ ዛሬ ፈላጊዎቼ ከኔ ጋር የሉም፡፡ድሮ የሚንከባከቡኝ የአባቴ ባሪያዎችም ቢሆኑ አይፈልጉኝም፡፡ ከገንዘቤ ያቁዋደስኩዋቸው ባእዳን ስለሆኑ ዛሬ ተቸግሬ ቢያዩም ቸል ብለውኛል፡፡
የብቸኝነቴ ኑሮ የጎዳኝ በአካል ብቻ ሳይሆን በልብ ስብራትም ነው፡፡ አሁን ባለሁበት ሁኔታ ብቸኝነቴን የሚሞላና የሚያበረታኝ እውነተኛ ባልንጀራ የለኝም፡፡ ከአባቴ ቤት መራቄ ደህንነቴን ጭምር አደጋ ላይ አውሎታል፤ስለዚህ ሁልጊዜ ስጋትና ሀዘን ይሰማኛል፡፡ልቤ በትእቢት ምክኒያት ከቤት ሸፍቶ ሲወጣ አባቴን አሳዝኜ ወደ ምኞቴ ተለየሁ፡፡ያኔ ከወጣሁ ጊዜ አንስቶ የህይወቴ ሁኔታ አስደሳች አልሆነም፡፡ጥፋቴ በታየኝ ጊዜ እንኩዋን ወደ ሁዋላ የምመለከትበት አቅም አልነበረኝም፡፡አንዴ ላልመለስ አባቴን አሳዝኜ ወጥቼአለሁ፣ ንብረቱን ነጥቄአለሁ፣ ሁሉንም ለባእዳን በትኜበታለሁ፡፡ ዛሬ ላይ ተቸግሬ አለሁኝ፣ ግን በደሌ ያሸማቅቀኛልና ወደ ሁዋላ ወደ መጣሁበት መመልከት አቅም የለኝም፡፡
ጊዜያት እየተቆጠሩ ቀናት ብዙ አልፈዋል፤ በጽኑ ረሀብ ተመትቼ ስሰቃይ እንዲሁም ችግር ሲያስጨንቀኝ አሳቤ ወደ ቤቴ መናፈቅ ጀምሮአል፤ እንቅልፍ አጥቼ ከእርያዎች ጋር ማደር ሲበዛብኝ የቤቴን የቀድሞ ምቾት ወደ ማሰብ እየገባሁ ነው፤ አባቴ ያደርግልኝ የነበረውን እንክብካቤ ደጋግሜ ማሰላሰል አልተውኩም፡፡የአባቴ ቤት ምቾት ነበረው፤ ምንጣፉ ምቾት ነበረው፤ የሚመግበኝ ከመልካም ገበታው ነበር፤ልብሴ የተመረጠ፣ውሎዬ የተመቸ ነበር፡፡ አሁን ምን ቀረኝ? ምንም፡፡ አሁን ምን አለኝ? ምንም፡፡ ይሄን ሳስተውል አባቴ ሆይ ምንም አልበደልከኝም እያልኩ ለብቻዬ ሆኜ አነግረዋለሁ፡- ሁሉን አደረግክልኝ፣ እኔ ግን በምላሹ መልካም ሳይሆን በደልን ሰጠሁህ፡፡ ምንስ ላድርግ? እንዴት ደፍሬ ልጥራህ? ፊትህንስ እንዴት ልይ? አባቴ ተጨንቄያለሁ – ልበለው? መልእክተኛ ልላክበት?
ያን ለማለት ቢያሳፍረኝና ድፍረት ባይኖረኝም ያለሁበት ህይወት ግን ከዚያ በላይ የከፋ እፍረት እንደሆነ አስባለሁኝ፡፡ እርያ መሀል ነው ኑሮዬ፣ ከክፉ ሽታቸው፣ ከእዳሪያቸው፣ ከምግባቸው፣ ከውሎአቸውስ ጋር አይደለሁም ወይ? የተዋረደ የኔ ህይወት ከዚህ የከፋ ምን ያገኘዋል?
የአባቴ ምህረት ቀርቦኛል፤ ስለዚህ በሀዘን ከተቀመጥኩበት ተነስቼአለሁ፡፡ የከረምኩት ከጸጸት ጋር ነው፡፡ ብዙ ጭንቀት፣ምሬትና እንቅልፍ አጥቼ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ተነስቼአለሁ፡፡ አንድ ነገር ላደርግ ወስኜአለሁ፡፡ ያ ውሳኔዬም ውስጤን እረፍት እንዲሰማኝ እያደረገ ነው፡፡ ልዩ ሰላም ይሰማኛል፤ ውስጤ አባቴን ይጣራል፤ ፊቱን ናፍቆአል፡፡ ልመና ያለው ድምጽ ውስጤ ይመላለሳል፤ የንሰሀ መንፈስ መጥቶብኛል፡፡ ወደ አባቴ የምሄድበትና እርሱን የማገኝበት ሰአት የደረሰ መሰለኝ፤ ሳገኘው ምን እላለሁ? አዎ በፊቱ ተደፍቼ በንሰሃ አለቅሳለሁ፣ እለምነዋለሁ በሰማይና በፊትህ በደልሁ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ…..፡፡
ሉቃ15:11-24 ” … ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው።ልጁም፡- አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው።አባቱ ግን ባሪያዎቹን አለ፡- ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር።”
የጠፋው ልጅ ምሳሌ ከእግዚአብሄር ፊት የኮበለለን አማኝ ፈተና፣ ምሬትና የንሰሀ ጩሀት የሚያሳይ ነው፡፡ ምሳሌው ጌታ በንሰሀ የሚመለሱትን በርህራሄና በፍቅር እንደሚቀበልና እንደሚባርክ አመልካች ትምህርትም ነው፡፡የእግዚአብሄር እገዛ ሲመጣ ተነሥተን ወደ እርሱ የምንገሰግስበት ጉልበት እንደምናገኝ እንማራለን፡፡ መሻታችን ወደ እርሱ ብቻ ያዘንብል እንጂ እርሱ ገና ሩቅ ሳለን አይቶ በማዘን ሊያድነን ይወስናል፡፡ነገር ግን የሀጢያተኞች ታላቁ ስህተታችን ከእግዚአብሄር ዘንድ የሚላክልንን መልካም መልእክት ላለመቀበል ልባችንን መዝጋታችን ነው፤ ይህ የሚያጠፋ እንቅፋት መንገዳችን ላይ ሲኖር ትልቅ መሰናክል ይሆናል፡፡እግዚአብሄር ግን ባሪያዎቹን ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም ሲል ምህረትን ያውጃል።
ሰዎች ስለሀጢያት ያለን አሳብ ቀለል እንዳይል እንጠንቀቅ፡፡ሀጢያት እንደ ወህኒ መቆለፊያ ብርቱ መከርቸሚያ ነው፡፡በርሱ ውስጥ የታሰረ ሰው የትኛውንም ሰብአዊ ሀይል ቢጠቀም ሰብሮ መውጣት አይችልም፡፡ስለዚህ በሀጢያት የተያዝንበት ወቅት ማለት በወህኒ ታስረን ከጌታ የምንለይበትና የምንርቅበት ወቅት ነው፤ የተቀበልነውን በረከት የምናባክንበትም ጊዜ ማለት ነው፡፡በሀጢያት በተያዝን ጊዜ አሳባችንንና ሀይላችንን ለማይገባ ጉዳይ እናውለዋለን፣ይደክመናልም፡፡ ሀጢያተኝነት የባዶነት ስሜት የሚጫነን የህይወት ይዘት ነው (የእግዚአብሄር ቃል ከእኛ ውጪ የሚሆንበት፣ እኛም ከርሱ ምሪት ውጪ የምንሆንበት ክስተት ነው)፡፡በሀጢያት ወጥመድ ከተያዝንበት ቅጽበት አንስቶ ውስጣችን መሸሽና ማፈግፈግ ውስጥ ሲገባ ይታወቀናል፤ አንድም በሰይጣን ክስ ምክኒያት አንድም በሀጢያት ሀይል ግፊት፡፡ ቃሉ ግን መለኮታዊ እርዳታን ሲያመለክት፡-
መዝ.6:4-10 ”አቤቱ፥ ተመለስ ነፍሴንም አድናት፥ ስለ ቸርነትህም አድነኝ።በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው?በጭንቀቴ ደክሜያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ።ዓይኔ ከቍጡ ዕንባ የተነሣ ታወከች፤ ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ።ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ፥ ከእኔ ራቁ፥ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ቃል ሰምቶአልና።እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማኝ፤ እግዚአብሔር ጸሎቴን ተቀበለ።ጠላቶቼ ሁሉ ይፈሩ እጅግም ይጐስቍሉ፤ ወደ ኋላቸው ይመለሱ፥ በፍጥነትም ይፈሩ።” ይላል፡፡
ሀጢያተኝነት መንፈሳዊ ብክነት ነው፤በሀጢያት ምክኒያት ከታማኙ እግዚአብሄር ክልል የሚወጣ ሰው ልክ በተበሳ እቃ ውሀ ተሸክሞ እንደሚጉዋዝ ሰው ከእግዚአብሄር የተቀበለውን ጸጋ እያፈሰሰ ፊት ፊቱን የሚል ነው፡፡ውሀው ከእቃው ውስጥ ፈስሶ እንደሚያልቅ የከበረው የእግዚአብሄር ነገር ከውስጡ ተሙዋጥጦ ይወጣና ይህ ሰው ባዶ ይሆናል፡፡ባዶ ቢሆንስ ምን ይሆናል? ባዶ መሆኑ ብቻ አይደለም ችግሩ፣ባዶውን ህይወት ፈጥኖ የሚሞላ ምትክ መኖሩ፣ ይህ ነው የሚያስጨንቀው፡፡ የጠፋው ልጅ ከአባቱ ቤት መውጣቱ ብቻ ሳይሆን የአባቱን ምትክ ማግኘቱ ላይ ነበር ሌላው ፈተናው፡፡ስለዚህ እርሱ ምን ሆነ? ከመልካሙ ምንጣፍ ወደ እሪያ ጉሮኖ ተዛወረ፤ውሎው ተለወጠ፣ስለዚህ ሽታው (በቤተሰቡ የነበረው ተቀባይነት/ታማኝነት) ተለወጠ፡፡ውሎው አኑዋኑዋሩን ለወጠው፡-ለውጡ በሁለንተናው የተንጸባረቀ ስለነበር የደረሰበት ኪሳራ ብዙ ነበር፡፡
ሀጢያተኞች በህይወታቸው ውስጥ ለነፍሳቸው እርካታ የሚሆን መንፈሳዊ ምግብ አይኖራቸውም፡፡ ሀጢያት በተቆጣጠረን ወቅት ባዶነትና ፍርሀት ስለሚያጠቃን ደካሞች እንሆናለን፡፡በደከምንም ጊዜ መጸለይ አንችልም፤ማመስገን፣ማምለክም ሆነ መለመን አንችልም፡፡ ደስታ ይርቀናል፣እንደርቃለን፣እንጨነቃለንም፡፡
በራሱ ፈቃድ የተሸነፈ እንዲህ ያለ ሰው ለስጋዊ ምኞት የሚመች አቅርቦት በማሰናዳት ላይ ይጠመዳል፡፡ስለዚህ ሀጢያት ህይወቱን በቀላሉ ተቆጣጥሮ እርካታ/ይበቃኛል የሚል መንፈስ ከህይወቱ እንዲጠፋ ያደርጋል፡፡መርካት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ መሻት ዳግም አይመጣም፡፡
ኤር.31:20 ”በእውነት ኤፍሬም ለእኔ የከበረ ልጅ ነውን? ወይስ የተወደደ ሕፃን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አስበዋለሁ፤ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።”
በእውነት ኤፍሬም ለእኔ የከበረ ልጅ ነውን? ለሚለው የእግዚአብሄር ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ሊሰጥ የሚደፈር አይኖርም፡፡ምክኒያቱ ደግሞ እንደ ኤፍሬም ያለ አስቸጋሪና አመጸኛ ነገድ የተወደደ የእግዚአብሄር ልጅ ተብሎ ሊጠራ ስለማይቻል ነው፡፡ነገር ግን ከእግዚአብሄር ዘላለማዊ ፍቅር አንጻር አመጸኛው ኤፍሬም ወደ እግዚአብሄር በተመለሰበት ቅጽበት እግዚአብሄር ውድ ልጁ አድርጎ እንደሚያየው ቃሉ ያመለክታል፡፡ ቃሉ እግዚአብሄር በንሰሀ የሚመለሱትን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አመልካች ነው፡፡እግዚአብሄር ለኤፍሬም አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ በማለት ለሀጢያተኛው ጥልቅ ፍቅር እንዳለውና ከሀጢያቱም ያድነው ዘንድ ፍቃዱ በመሆኑ በርህራሄ እንደሚያየው ያመለክታል፡፡
ኤፍሬም በሀጢያቱ ምክኒያት አለቀሰ፣ ስለሀጢያቱና ስለስንፍናው በራሱ ላይ አዝኖአልና፡፡በራሱ ሀይል ራሱን ወደ እግዚአብሄር ማስጠጋት እንደማይችል ተረድቶም ነበር፡፡ስለዚህ እያለቀሰ መልሰኝ እመለሳለሁ አለ፡፡እንደዚህ የራሱን ፈቃድ ለእግዚአብሄር አስገዛ፡፡
ሁልጊዜ የእግዚአብሄር መንፈስ አስተምሮ ሲያስተካክለን ይሄ ልሳን ይኖረናል፡፡በመከራችን ውስጥ አልፈን የእግዚአብሄር መጽናናት ሲሆንልን እርፍ እንላለን፡፡በእግዚአብሄር ጎተራ ያለው እጅግ የበዛ ምህረት ሁልጊዜ ልቡን በቅንነት ወደ እግዚአብሄር ላዘነበለ ሀጢያተኛ ያለመከልከል የሚሰጥ ነው፡፡ይህን ታላቅ መዳን በመመለስ ማግኘታችን እግዚአብሄር የከፈተልን የንሰሀ በር እንዴት ባለ ምህረትና በጎነት እያኖረን እንዳለ አመልካች ነው፡፡
ሐዋ.3:19-20 ”እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን አንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም።”
በመመለስና በእውነተኛ ንሰሀ ኃጢአታችንን እናስደምስስ፣ በልባችን ጌታ ነግሶ የመጽናናት ዘመንም ትቀበለን፣አሜን፡፡