የጠላትን መንገድ እወቅ[3…]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

የነህሚያ ተግዳሮት
ነህሚያ ለእግዚአብሄር ህዝብና ለመቅደሱ የቀና አገልጋይ ነበር፡፡ የኢየሩሳሌም ፈርሳ መቅረትና የመቅደሱ ስርአት መቆም እያስጨንቀው በባእድ አገር ለብዙ ዘመናት ኖሮአል፡፡ በእግዚአብሄር ሰአት ከሚኖርበት የምርኮ ምድር ተነስቶ ወደ ገዛ ምድሩና ህዝቡ በመጉዋዝ አገሩ ደረሰና ቀጥታ ወደ ስራ ገባ፡፡ የነህሚያ ተግዳሮት የሚጀምረው ገና እግሩ ኢየሩሳሌምን ከረገጠ ጊዜ አንስቶ ነበር፡፡ ጠላቶች በእግዚአብሄር አምልኮና ስርአት ስለማይደሰቱ የከተማይቱና የመቅዱስ ዳግም መሰራት አስቆጥቶአቸዋል፡፡ እነዚያ ጠላቶች የነህሚያ ትጋት አስጨነቃቸው፣ ስለዚህ በቅንአት ተነሱበት፡፡ ጠላቶች ከውጪ የሚያደርሱት ጫናና ጉዳት ሳያንስ በውስጥ በተቃውሞ የተነሱ ወገኖች ለጠላት በር ሆነው ነበር፡፡ በህዝቡ መሀል ከሰፈነው በራእይ እየሆነ ካለ እንቅስቃሴ ውጪ አንድ አጥፊ መንፈስ ተንቀሳቅሶ ሊያናውጣቸው እንደሞከረ መረዳት እንችላለን፡፡
ነህሚያና ወገኖቹ በብዙ ትጋትና ድካም ቅጥር መገንባቱን እያጠናቀቁ ቢሆንም በሩ ተሰርቶ አልተፈጸመም ነበር፡፡ ስራው የነበረበት ደራጃ ለነህሚያ እንዲሁም ለእግዚአብሄር ስራ እጅግ ወሳኝ ሰአት ነበር፡፡ ጠላቶቻቸውም ያ ሰአት የመጨረሻ የማሰናከያ ምክር አጋጣሚ እንደሆነ የተገነዘቡበት ወቅት ነበረ፡፡ ስለዚህ ጠላቶች ያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቆም ካልቻሉ የግንባታው እቅድ ያለምንም ክልከላ መጠናቀቁ አይቀሬ እንደሆነ ስላወቁ የመጨረሻ እንቅስቃሴ በህብረት ማድረግን መረጡ፡፡
በተሰበሰቡ ጊዜም ጠላቶች አንድ ሴራ ወጠኑ፤ ነህሚያን ምስጢራዊ ስፍራ ቀጥረው ማጥመድ አቀዱና ምክራቸውን ጨረሱ፡፡ ሊያጠምዱት በቀረቡ ጊዜ የወዳጅነት በሚመስል ማባበያ ተናገሩት፣ ቢሆንም ነህሚያ ጉዳዩን ጠንቅቆ ተረድቶ ነበርና አልተታለለላቸውም፡፡
ቀጠሮው ለስምምነት ምናልባት ለእርቅ በሚመስል ሁኔታ ወደ ነህሚያ ተልኮአል፡፡ ነህሚያ ግን በመልእክቱ ውስጥ የተቀበረውን ወጥመድ ተመልክቶ ስለነበር ሰንበላጥ በዚያ ግብዣ ውስጥ የቀበረውን ተንኮል ሾለከና አመለጠ፡፡ ያ ብቻ አልነበረም ከሴራው ባሻገር ሁሉን በመታገስ ለጠላቱ በመልካም ቁዋንቁዋ መልሶለታል፡፡ ወዳጅ ሆኖ በሽንገላና ተአማኒነት በሌለው ሁኔታ ጠላት እንደነሰንበላጥ ሊያጠምድ ሲቀርብ ባለመደናገር፣ ባለመቻኮልና ባለመዘናጋት መቆጣጠርና መቁዋቁዋም እንደሚገባ የነህሚያ አካሄድና ልምምድ ያስተምራል፡፡
የእስራኤላውያን ጠላቶች ነህሚያን ነጥለው የሚመቱበት የጥፋት ጥበብ ቢኖራቸውም ነሂምያ ግን በእግዚአብሄር አመልካችነት ቀድሞአቸዋል፡፡ ከውጪ የነበረው ወዳጅ መሳይ አመለካከት ውስጡ ጥፋት የተሞላ አካሄድ ቢኖረውም እግዚአብሄር ባስታጠቀው ጥበብ ያን ሊያስተውል ችሎአል፤ ምስጢር ገላጭ አምላክ በመንፈሱ አስቀድሞ አመልክቶታልና ራሱን፣ ህዝቡንና ስራውን ከጥፋት አተረፈ፡፡
እግዚአብሄር ሰው እንደሚያይ አያይም፡- ሰው ፊትን ሲያይ እግዚአብሄር ልብን ያያል፡፡ የሰው ችሎታ ውስን በመሆኑ ምክኒያት በምስጢር እየሆነ ያለውን የክፉ ሴራ ሳያስተውል ሁሉ ሰላም ነው ብሎ ከቂመኛው ጋር ይኖራል፡፡ እንደ ነህሚያ ሆኖ በእግዚአብሄር የታመነና በእርሱ ጥበብ የተመራ ስብእና ሲኖር ግን ከጠላት ወጥመድ ማምለጥና በእግዚአብሄር ፈቃድ ተጠብቆ መኖር ይቻላል፡፡
የጠላትን መንገድ እንዴት እንለይ?
የጠላትን አካሄድ እንዴት መመዘን እንችላለን? ነህሚያ የጠላትን አካሄድ የማስተዋል አቅም እንደነበረ አይተናል፡፡ የነሰንበላጥን አካሄድ ቀድሞ በማስተዋሉ ምክኒያት ነበር ጥንቃቄ ውስጥ ሊገባ የቻለው፣ በዚያ ማስተዋሉ ታላቅ ጥፋትን አስቁሞአል፣ እስራኤልን ከዳግም ውድቀትም አስመልጦአል፡፡ ይህ ታላቅ ነገር ነው፡፡
እኛስ የጠላትን መንገድ መለየት አያስፈልገንም? ያስፈልገናል ያለምንም ጥርጥር፡፡ ግን በዘፈቀደ ወይም እንደኛ ምኞት በሆነ አካሄድ ሊሆን ግን የሚችል አይደለም፡፡ መንፈስን መመዘን/መለየት፣ አካሄድን መለየትና የጠላትን ታክቲካዊ አቀራረብ (በተለይ ሽንገላውን) ማስተዋል የሚባል ብቃት ከእኛ ይፈልጋል፡፡ ይሄ የሰው አእምሮአዊ ችሎታ ውጤት ሊሆን ይችላል ብለን አንገምት፣ ብቃቱ የሰው የጥበብ ሀይል የሚፈጥረው ሳይሆን በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ ሆነን በመንፈሱ ሀይል የምንቀበለው የእግዚአብሄር ችሎታ ነው፤ ጥበቡ ከእግዚአብሄር በመሆኑ የጠላትን መንገድ ፍንትው አድርጎ ማሳየት ይችላል፡፡ በዚህ ብቃት ብንታጠቅ የውጪን መልክ ዘልቀን የውስጥ መንፈሳዊ ይዘትን የምናይ፣ በተቀባባ አቀራረብ የታጀበን ምስጢር ከውስጥ ፈልፍለን መግለጥና ከጠላት ማምለጥ የምችል ያደርገናል፡፡
1ቆሮ.2፡12-15 ”እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም። ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።”
ስለዚህ ወዳጆችና ወንድሞች በውጫዊ አቀራረብ ብቻ ከተወሰኑ፣ ሁኔታዎችን ከገመገሙና ውሳኔ ከሰጡ በአካሄድ የተሳሳቱ ናቸው ማለት ነው፡፡ ሌላም አለ፡- በውጪ ታይታ ብቻ ህይወት ሲጠመድ የማስመሰል ሁኔታ ላይም ሲያተኩር ውስጣችን ከእውነተኛው ድምጽ እየሸሸ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ መልካም እንዲያደርጉ የሚያምኑ ሰዎች ለመንፈሳቸው እየተናገረ ያለውን ምክር ቸል ብለው ሲያልፉ እየተጠመዱ እንደሆነ ያስተውሉ፡፡ ከመልካሙና በጎው የጌታ ትምህርት የሚንሸራተት አካሄድ ለጠላት በር ይከፍታልና ያን የሚለይ ማስተዋል ሊኖረን ይገባል፡፡ ሁሉን ትምህርት በጭፍን መቀበል የተሳሳቱ አካሄዶችንና ሰዎችን መቀበል ይፈጥራል፡፡ ክርስቲያን የዋህነቱ በእግዚአብሄር ቃልና በአምላኩ ፈቃድ ላይ እንጂ በአለም፣ በስጋና በአጋንንት ወጥመድ ላይ አይደለም፡፡ አማኝ መንፈሳዊ ሁኔታዎችን መለየት ካልቻለ ከውጪ ያለውን ሁኔታ ስለሚቀበል ከውስጥ ያለውን የነገሮች መንቀሳቀሻ መንፈስ አይረዳም፤ በዚህ ምክኒያት ይሳሳታል፡፡ በአታላይቱ አለም ለዚያውም በዚህ መጨረሻ ዘመን ነገሮችን መመርመር ያለመቻል አደጋ እያመጣ ነው፡፡ አካሄዳችንን በጌታ እናጽና፣ ውስጣችንን በእርሱ እናጽና፣ ነገሮችን ከውጫቸው ብቻ አንገምግም፣ የነርሱ አድራጊ ሀይል ከወዴት እንደሆነም እንወቅ እንጂ፡፡ ፈጽመን በእግዚአብሄር እንመካ፣ መልካሙ መንገድ ይሄ ነውና፡፡
ነህሚያን ደግመን ብናይ፡- እርሱ ከጠላቶች ምክር ይልቅ የእግዚአብሄርን ምክር በመከተሉ ከነሰንበላጥ አደገኛ ሴራ እንዳመለጠ በታሪኩ ውስጥ ተገልጦአል፡፡ በምሳ.27፡6 ውስጥ የሚናገረው መንፈስ በእርሱ ዘመን ጥበብ ሆኖለት አካሄዱን እንዳጸናው የምንመለከተው እውነት ነው፡፡ እንዲህ የሚለው፡-
”የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል። የወዳጅ ማቍሰል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው።” (ምሳ.27:5-6)

የጠላትን አካሄድ መለያ መንገድ
የጠላት አካሄድ አንዱ የሰይጣንና አጋንንቱ መንፈሳዊ ጥቃት መገለጫ መንገድ ነው፡፡ የሚታወቀው፣ የሚመረመረውና የሚገለጠውም በቃሉ እውቀትና በመንፈሱ ሀይል ነው፡፡ ቃሉ በጽድቅና በእውነት ሲሰበክና መንፈሱ በሀይል ሲመጣ የተሰወሩ አጋንንት ይወጣሉ፣ ይናዘዛሉ፣ ይለፈልፋሉ፤ ቃሉ ሲበራ እንዲሁ በመጽሀፍ የተዘረዘሩ የጠላት ባህሪያት ወደ መታወቅ ይመጣሉ፡፡ ሀይል በሌለበት ስፍራ/አምልኮ አካባቢ/ የሚጋለጥ የጥፋት አሰራር ያለመኖር ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በተቃራኒ አጋንንት ሁሉን ገዝተው ወንጌላዊ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ቃል እውቀት ለመሞላት የጠላትን አካሄድ ከማስተዋል ፊት የምንጠየቀው መንፈሳዊ እርምጃ የሆነውን ወደ እውነተኛው አምላክ የመቅረብ ልምምድ ነው፡፡
እንዲሁም በመንፈሳዊ ህይወት እያደግን በምንሄድበት ሁኔታ ውስጥ ስለጠላት አካሄድና ስለመንፈሳዊ አሰራሮች ማስተዋል ዋነኛ ነገር በመሆኑ ያን እያገኘን እንድንሄድ፤ ማደጋችን በነገሮች ሁሉ እንዲሆንና መንፈሳዊ ነገሮች በቃሉ ማስተዋል እንዲበሩ መጽናትና መገዛትን በእግዚአብሄር ብቻ እናድርግ፡፡
ዕብ.5:11-14 ”ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው። ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።”
በመንፈሳዊ ህይወት ሕፃናት የሆኑ አማኞች መንፈሳዊውን ህይወትና አሰራር ስለማያስተውሉ ብዙ ይቸገራሉ፡፡ ሕጻን የሚነካውን እንደማያስተውል (ደጉና ክፉውን እንደማይለይ) እና በሚያደርገው ነገር በቀላሉ እንደሚደናቀፍ በመንፈሳዊ ህይወት ያልበሰሉ ሰዎች በነገሮች ስህተት ውስጥ በቀላሉ መውደቅ ይቀናቸዋል፡፡ መልካሙንና ክፉውን ያለመለየት ለጠላት አሰራር በቀላሉ ያጋልጣል፤ የተጋለጡትም ሲወድቁና ሲሰባበሩ ታይተዋል፡፡
በሌላ በኩል ማስተዋልና የጠላትን አካሄድ መለየት በእግዚአብሄር መንፈስ በምንቀበለው ስጦታ በኩል እንደሚቻል የታመነ ነው፡፡ ይህን ስጦታ ግን አጥብቀን መጠየቅና መፈለግ አለብን፡-
1ቆሮ.12:10”ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል”
መንፈስን ባለመለየት ምክኒያት የጠላትን መንገድ ለማስተዋል የምንቸገር ብቻ ሳይሆን የራሳችንን አካሄድ ማወቅ የማንችል ስለምንሆን (እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ የሆነ አኑዋኑዋር ስለማናውቅ) በገዛ ራሳችን ውሳኔ መፈተን ይደርስብናል፡፡
የጠላትን መንገድ ስለማያስተውሉ ጠላት የሚያቀርበውን ግብዣ የፍቅር መግለጫ አድርገው ወስደው ወጥመዱ ውስጥ የገቡ ብዙ ናቸው፡፡ አንድ የዋህ የአይሁድ ንጉስ እንዲያ ነው የሆነው፡፡ ለትምህርታችን በተጻፈው መሰረት ከእርሱ ለመማር መሞከር አለብን፡-
የእስራኤል ንጉሥ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሳይጠይቅ ብድግ ብሎ ከባሪያዎቹ ጋር ሶርያን ለመውጋት ይማከራል። በዚያ ሳያቆም ምክሩን በይሁዳ ንጉሥ በኢዮሣፍጥ ላይ ያጋባና ይዞት ወደ ውጊያ ስፍራ ያንደረድረዋል፡፡ በጉዞ መሀል የይሁዳ ንጉስ ወደ ማስተዋሉ ሲመለስ ለእስራኤል ንጉስ እግዚአብሄርን አስቀድሞ መጠየቅ እንደሚገባ መከረው፡፡ የእስራኤል ንጉሥ ሳይፈልግ የግዱን ነቢይ ጠራ፡፡ ነቢዩ ግን አትሂዱ እግዚአብሄር ብሎአልና አላቸው፡፡ የአይሁድ ንጉስ የሰማውን ቃል ታዝዞ በጊዜ መመለስ ሲገባው ከአመጸኛው የእስራኤል ንጉስ ጋር ተባበረና ወደ ፊት ተጉዋዘ፤ በዚያ ሳቢያ ግን ሞት አፋፍ እስኪደርስ ራሱን አደጋ ላይ ጣለ፡፡ ይህ ሁሉ ለምን ሆነበት? ስንል ከእስራኤል ንጉስ የቀረበለት ጥያቄና ግብዣ ስለፍቅር የተደረገ ስለመሰለው ነበር፡፡ (1ነገ.22:4-18)
”የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፡- እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የይምላ ልጅ ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ አለው። ኢዮሣፍጥም፡- ንጉሥ እንዲህ አይበል አለ።…ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር? አለው፤ እርሱም፡- ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል ብሎ መለሰለት። ንጉሡም፡- ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ? አለው። እርሱም፡- እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፡- ለእነዚህ ጌታ የላቸውም እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ ብሎ ተናገረ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፡- ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁህምን? አለው” አለውናም አባበለው፣ ወደ ውጊያ ውስጥ ከተተው፣ ሞት አፋፍም አደረሰው፡፡
የክፉው ግብዣና ዝግጅት ልዩ ሲሆን ጥሪውም ትህትና ያለበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ቃሉ በኤፌ4:14 ላይ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ የሚነግረን፡-
”እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም”
1ቆሮ.14:20 ላይም ሃዋርያው ጳውሎስ ወንድሞች በአእምሮ ሕፃናት እንዳይሆኑ ይልቁን ለክፋት ነገር ሕፃናት እንዲሆኑ፣ አድገውም በአእምሮ መብሰል ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አሳስቦአል፡፡