የጠላትን መንገድ እወቅ[2…]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

ከጠላት ጋር ፊት ለፊት መተያየት ለሰላም ጉዳይ እንደተገናኙ ያህል በተከፈተ ልብ የሚቀባበሉት አጋጣሚ አይደለም ወይም ለመልካም ጉዳይ እንደተነፋፈቁ ወዳጆች ለመተያየት የሚጉዋጉለት አይደለም፣ የሚያስጨንቅ፣ የማያስደስት፣ ሰላማዊ ያልሆነም ነው፡፡ ጠላትነት ከጥላቻና ከበቀል ጋር ከሆነም ጥፋትን የቁዋጠረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የተገናኘነው ያ የሚጠላን ቂም ቁዋጥሮ፣ በቀል አውጠንጥኖስ ቢሆን? ወይ አዘናግቶ ሊያጠቃ ቢሆንስ? ካልቻለ ሊያሰናክል ከቻለ ሊያጠፋ እንደሚያስብ ማለም ደግሞ ይበልጥ ያስጨንቃል፤ ፊትለፊት ባይጋፈጥ እንኩዋን በቀላል በይቅርታ ሊያልፍ አይችልምና ሁኔታው ሰላም አይሰጥም፡፡ ልብም ቢሆን ያን ስለሚያስተውል መረጋጋት ይችላል ወይም በቀላሉ እርፍ ይላል ማለት አይቻልም፣ ያን እያሰላሰለና እያየ፡፡ ንጉስ ዳዊት ስለጠላቱ በተጨነቀ ጊዜ ጸልዮአል፡-
”አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ ልመናዬንም ቸል አትበል። ተመልከተኝ ስማኝም። በኀዘኔ ተቅበዘበዝሁ ተናወጥሁም፤ ከጠላት ድምፅ ከዓመፀኛም ግፍ የተነሣ፤ ዓመፃን በላዬ ጥለውብኛልና፥ በቁጣም ጠልተውኛልና። ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፥ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ። ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፥ ጨለማም ሸፈነኝ። በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ! እነሆ፥ ኰብልዬ በራቅሁ በምድረ በዳም በተቀመጥሁ፤ ከዐውሎና ከብርቱ ንፋስ ሸሽቼ በፈጠንሁ አልሁ።” (መዝ.55:1-8)
ዳዊት በጸሎት ውስጥ ሆኖ ጠላት የፈጠረበትን ሸክም፣ ሀዘንና መከራ ለአምላኩ ሲያሳስብና እረፍትን ሲለምን እናያለን፡፡ ያኔ ዳዊትን ከምንም በላይ የበረታ የጠላት ድምጽ አስፈራራው፤ ያ የጠላት ቁጣ ልቡን እስኪያናውጥና ልሞት ነው እስኪልም ድረስ ተስፋ አስቆረጠው፡፡ ንጉሱ በህይወት ዘመኑ ብዙ ጠላቶች ተጋፍጠውት ነበር፡፡ እርሱም በእግዚአብሄር እርዳታ አሸንፎአቸዋል ወይም አልፎአቸዋል፡- በእረኝነቱ ወቅት ከቀማኛ አውሬዎች ጋር ተናንቆ በድል መልሶአቸዋል፣ ፍልስጤማዊውን ጀግና ተዋጊ በአንዲት ጠጠር አሸንፎአል፣ በተለያየ የጦር ሜዳ ውሎውም አሸናፊ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ ከንጉስ ሳኦል ፍላጻ ብዙ ጊዜ በአምላኩ ምህረት አምልጦአል፡፡ እንዲያም ሆኖ በራሱ ምኞት ምክኒያት ስቦ ቤቱ ያገባው ውጊያ ግን እጅግ አስለቅሶታል፡- ጻድቁን ወታደር ገድሎ ሚስቱን በመውሰዱ ምክኒያት መቅሰፍት በቤቱ መጥቶአል፣ ልጁ አቤሴሎም ጠላት ሆኖ ተነስቶበታል፣ እምርሮ እንዲያለቅስም አድርጎታል፡፡
ዳዊት እግዚአብሄር እንዲረዳው የታመነ የእግዚአብሄር ሰው ነበር፡፡ ሆኖም የጠላትን አመጣጥና መንገድ ብዙም ሊያስተውል ባልቻለባቸው ወቅቶች ከፍተኛ ጥፋት ውስጥ ሲገባ እንመለከታለን፡፡
የማይጋፉት ጠላት መምጫ መንገዱም ሆነ የሚከሰትበት ጊዜ አይታወቅም፣ ሳኦል በዳዊት ላይ እንደሆነበት ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ጠላት ብርቱ በሆነበት እንዲያ ባለ አጋጣሚ እንደ ዳዊት ዝቅ ብሎ በጸሎት ወደ እግዚአብሄር መቅረብ በአሳብ ከመዋለልና በጭንቅ ከመወጠር መዳን፣ የአእምሮ እረፍትና የደህንነት ተስፋ ማግኘትም ያመጣል፡፡
ከዚህ ሰዋዊ ሁኔታ እልፍ ብለን ስንመለከት ደግሞ አንድ ለየት ያለ ጠላትና መንገድ እንገናኛለን፡- ሰው ጠላቴ ያኛው ወይ ይሄኛው ሰው ነው እያለ ከሚቆጥረው ሰብአዊ ፍጡር በላይ የላቀና ምድርን በክፋት እያስጨነቀ የሚገኝ መንፈሳዊ ጠላት እንዳለው ሰው አይዘንጋ፡፡ ይህ መንፈሳዊ ጠላት ከስጋውያኑ ሰዎች ይልቅ መራራ ነው፡፡ ሰው እርስ በርሱ ቢጣላ ጥሉ በስጋ መሀል ብቻ የሆነ ነው፣ ደግሞም በይቅርታ፣ በመሀል በሚወርድ ሰላምም የሚፈታ ጥል ነው፤ የሰውና የአጋንንት ጠላትነት ግን በረቂቅ መንፈስና በግኡዝ አካል መሀል የተፈጠረ በመሆኑ የማይመጣጠን የበላይነት ያለበት ነው፡፡ መንፈሳዊው ጠላት ለምን የከፋ ይሆናል? አስቀድሞ ያለው እውነታ የሚያሳየው መንፈሳዊው ጠላት ሰው የማያየው፣ የማይዳስሰውና የማያሸተው ጠላት መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የሚከተለውን ብልሀት፣ አታላይ ዘዴና የማጥቂያ መንገዱን ሰው በስጋ አእምሮው ፈጽሞ አይገነዘበውም ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክኒያት ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ ክፋት የሚመነጨው ከጨለማው መንፈስ መሆኑን ልብ አይልም፣ ተንኮሉንም አይደርስበትም፣ አወቅኩ ቢል እንኩዋን ብዙ አጥፍቶና ከሰው ማስተዋል ርቆ ከተለየ በሁዋላ ነው፡፡ ይህ ክፉና አደገኛ ጠላት ቅርጹ ስለማይገባን፣ የሀይሉ መጠን ስለማይታወቀንና ስለማንዳስሰው ብቻ እንደ አንድ ደቃቃ ነገር ለዚያውም ተራ ነገር አድርገን እንቆጥረዋለን፣ ያልያም ሰው ለክፉ አሳብ የሚሰጠው ስም እስኪመስለን ያንስብናል፡፡ እንዲያውም ሰለጠነ በተባለው አለም ለክፉ ሰው የሚሰጥ ባህሪ ብቻ ወይም ሰው በአእምሮው የፈጠረው ማንነት ተደርጎ ይወሰዳል፡- የሰይጣን ህልውና፡፡ ይህ መንፈስ የማይዳሰስ፣ የማይቆረቁር፣ ለስለስ ያለ ድምጽ ያለው፣ ፍላጎትን የማይጋፋ፣ ደግና ሩህሩህ መሳይ ሲሆን አልታወቀም እንጂ ሲጥልና ሲያጠፋ ዱካ ሳያስቀር የሚያጠፋ መንፈስ ነው፤ ግን የጠፋው እንደጠፋ፣ ያጠመደውም ተሰናክሎ ባለበት ሁኔታ እርሱ ሳይታወቅ ይሰውራል፡፡ ስለዚህ ነገሮቻችን ሲጠፉ ወይም ሲሞቱብን ገዳዩንና የሞተውን የቀብር አድራሻ ሳናውቅ ነገራችን አካባቢ ሆነን በተሳሳተ አድራሻ ላይ እናማትራለን፣ የሞተውም ገና በእጃችን ህያው ሆኖ ያለ እየመሰለን በስህተት ውስጥ እንመላለሳለን፤ በመታለል የጠላታችን ውጤት ሳይገለጥልንም እንኖራለን፡፡
የሰይጣንን ዱካ የሚገልጥ የጌታ ኢየሱስ ማሳሰቢያ በሚያሳየን ልክ እኛም ቢታየን ኖሮ እንደምን ስራው ፍንትው ብሎ ይበራልን ነበር? በዮሐ.10:8-10 ውስጥ ሲናገር፡- ”ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።” ይላል፡፡
ይህ ከጌታ አስቀድሞ የሚሹለከለክን ጠላት በምን እርዳታ እናግኘው፣ እንወቀው፣ እንከላከለውስ? ባይዳሰስ ባይታይም ማንነት ስላለው፣ ባህሪው በተግባሩ የተገለጠ ስለሆነና ስራውም ስለሚታይ ተሰውሮ አይቀርምና ረቂቅ እውቀቱን የሚገልጥ የእግዚአብሄር አሰራር በገለጠው ልክና እንደተጻፈው ሆኖ በመጋፈጥ ድል እናድርገው፡፡
”ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው፡- ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት። እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።” (ሉቃ10:17-21)
የጠላትን መምጫ በጌታ እውቀት ያስተዋሉ ደቀመዛሙርት እንደምን እንደተዋጉት በቃሉ ተገልጦአል፡፡
ኤፌ2:1-3” በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።
በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።”
ለጠላት ጥቃት መፍትሄ አለው
ዘዳ.33:27-29 ”መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፡-አጥፋው ይላል። እስራኤልም ተማምኖ፥የያዕቆብም ምንጭ ብቻውን፥እህልና የወይን ጠጅ ባለባት ምድር ይኖራል፤ ሰማያቱም ጠልን ያንጠባጥባሉ። እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው? እርሱ የረድኤትህ ጋሻ፥ የከፍተኛነትህም ሰይፍ ነው። ጠላቶችህም ይገዙልሃል፤ አንተም ከፍታቸውን ትረግጣለህ።”
ከሩቅ የሚያስፈራራውም ይሁን ሾልኮ መሃል የገባ ጠላት አላማው ሰውን በሞት ወጥመድ ላይ መጣልና በዘላለም ፍርድ ውስጥ መቀርቀር ነው፡፡ በእግዚአብሄር የዳነ ግን በረድኤቱ ጋሻ ይከለላል፣ ከፍታን የሚማርክበት ሰይፍ ይቀበላል፡፡ የሚያጠቃው ጠላትም ተሸንፎ ይገዛለታል፣ የጠላቶቹን ዋና ስፍራ ይረግጣል፡፡ እግዚአብሄር እስራኤልን በክንዱ ላይ አኑሮ ጠላቱን ግን ፊቱ ከጣለለት በሁዋላ በለው፣ ገስጸው አጥፋው ይለዋል፡፡ ጠላታችንን የሚያይ ጌታ አስቀድሞ መንገዱን አጋልጦ ባሳየን ጊዜ በዚያ መረዳትና እውቀት ጠላትን ድል እንነሳለን፡፡ ነገሮች ሳይሳኩና ራእይ ወደ መደብዘዝ ሲመጣ የተስፋ ማጣት ለቅሶ እንጂ መታመን አይሆንልንም፡-
”ልቤ ተስፋ በቈረጠ ጊዜ ከምድር ዳርቻ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በድንጋይ ላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ። ጽኑ ግንብ በጠላት ፊት ተስፋዬም ሆነኸኛልና መራኸኝ። በድንኳንህ ለዘላለም እኖራለሁ፤ በክንፎችህም ጥላ እጋረዳለሁ”(መዝ.61:1-4)
ጠላት የምንጉዋዝበትን ዱካ ሲያጭበረብር ከእግዚአብሄር እንደ ምድር ዳርቻ ያለ ርቀት እንርቅና በርሱ ላይ እንጮህበታለን፣ የርሱ ምህረት ስለሚልቅ ያቀርበንና በተስፋ ይሞላናል እንጂ እንደ ክፉው ጠላት አሳብ ቢሆን ኖሮ ለጥፋት ተጋልጠን እንጠፋ ነበር፡፡ ይህን ምስጢር ያስተዋለ ከዚህ መነሻ ጀምሮ መንፈሳዊ ጠላትን አምርሮ መዋጋት ይገባዋል፡፡ ዛሬ እያንዳንዳችን የከሰርነው የማንነቱ መሰወር በፈጠረብን ተጽእኖ ምክኒያት ነው፤ ያለመዋጋታችን ከበታቹ ስለሚያስቀረን፣ ባሪያ አድርጎ ለፈቃዱ ስለሚያስገዛንና የሀጢያት ባሪያ ስለሚያደርገን እንጂ ስራውና ማንነቱ ሲገባን እኮ ዝም አያሰኘንም፡፡ እርሱ ከላይ እስከታች በሚደርስ የጦር ተዋረድ ተሰልፎ እያጠቃን ካለ እኛስ በኢየሱስ ጸጋ፣ ስምና ሀይል መከላከልና መዋጋት አስፈላጊያችን አይደለም ወይ? ”ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው፡- ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል” ያሉት የውጊያ ስልቱ ገብቶአቸው ነው፡፡ በ2ቆሮ.2:11 ቃሉ ሲናገር” በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና።” ይላል፡፡
እንደው እንደቃሉ አተያይ በሰይጣን የማይታለሉ እነማን ናቸው እንላለን? የማይታለሉት እርሱን በብቃት የሚያውቁት ብቻ ናቸው፡፡ በብቃት ሲባል በፊደል ደረጃ ማለት አይደለም፣ በስሚ ስሚም ሆነ በተራ ፉከራም አይደለም፡፡
2ቆሮ.10:3-6 ”በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል።”
ጠላትን በሰው ልማድ አንዋጋም ወይም እንደ ሰው ልማድ የጦር መሳርያ ጨብጠን አንቁዋቁዋመውም፣ መንፈስ ነው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት መንፈሳዊና ሙሉ የሆነ የጦር መሳሪያ እግዚአብሄር አስታጥቆናልና አንፈራም፤ መንፈሳዊው መሳሪያ የሰውን አሳብ በማሸነፍና የጠላትን አሳብ በማፍረስ ነጻ የወጣ አእምሮን ለእግዚአብሄር ይማርካልና።
የታጠቀ ሁለንተናዊ ዝግጅት ያደርጋል
መንፈሳዊ ውጊያ እግዚአብሄርን ከማወቅና የጠላትን ተንኮል ከማስተዋል ይጀምርና የእግዚአብሄርን መንፈሳዊ የጦር እቃ መታጠቅና ለውጊያ ዝግጁ መሆን ላይ ያተኩራል፡፡ ከእግዚአብሄር ያገኘነው መንፈሳዊ ዝግጅት ጠላት ባይቁዋቁዋመውም በቸልተኝነት ከተመላለስን ግን ሙሉውን ትጥቅ ያስጥለናል፣ ይማርከዋልም፡፡ እናስተውል፡- እግዚአብሄርን ማወቅ፣ የጠላት ባህሪንና የጠላትን መንገድ ማወቅ፣ መንፈሳዊውን የጦር እቃ መታጠቅም፣ በጠላት ፊት መቆምንም በደንብ መረዳት! ያን እውቀት ያለማወቅ ውድቀት ነው፡፡
ያ አካሄድ ከማሰናከሉ በፊት ምን ማድረግ ይበጃል?
በአንድ ልብ እንሰማራ፡- ህብረት በእግዚአብሄር ለዳኑ ልጆች ወሳኝ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን በመደገፍ ሲቆም የጠላትን አሰራር ያዳክማል፣ እንዲህ ለማደርግ ክፍተት የሚፈጥር አካሄድ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ፣ ያለመነቃቀፍ ያለመጣላት ጠላት የሚገባበትን ቀዳዳ ያለመፍጠርም ያስፈልጋል፡፡ ትውልዱ የተቸገረው አንዱ ከሌላው ጋር እየተያየ ስለሆነ ነው፣ በፉክክር፡፡ የሚፎካከር ህብረት የቅናት ጉባኤ እንጂ የፍቅር ጉባኤ አይደለም፣ ሀሜት ስለሚያበዛ፣ መነቃቀፍና መፎካከር ስለሚያበዛም፡፡ ቃሉ እኮ አንዱ ሌላውን የተሸለ ወዳጅ አለኝ ብሎ እንዲቆጥር ነው የሚመክረው፡፡ የእኔ ነገር ደግሞ ወርዶ በበላሁትና በለበስኩት ወይም በመሳሰለው የእጄ ኮተት የክርስቶስ ደም የተቀባን የእግዚአብሄር ልጅ ልብ አጎሰቁላለሁ(አስቀናለሁ ወይም አባብላለሁ)፣ በእውነት ያስጨንቃል ድርጊቱ ለሚያስተውለው፡፡ ማናችንም ብንሆን ይህን አለማዊ ፈሊጥ እስካልጣልን፣ እስካልሻርንና አድገን እስካልተጸየፍን ድረስ በፍቅር ጉባኤ መሀል ሁሌም ጉድፍ ነው የምንሆነው (ህብረት አጠናካሪ ሳንሆን በታኝ ነንና)፣ በዚያም የጠላት በር በወገኖቻችን መሀል ከፋች እንሆናለን፡፡
ቃሉ በፊል1:27 ውስጥ ሲናገር” ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።” ይላል፡፡
ስለዚህ ማህበሩ በአንድ ልብ ሊወጣና ሊገባ ታዝዞአል ማለት ነው፣ በአንድ ልብ ስለወንጌል አብራችሁ እየተጋደላችሁ ስለሚል፡፡ በዚህ ማስተዋል ውስጥ ስንኖር እርስበርስ መደጋገፍ፣ መሸካከምና መበረታታት ይቻላል፡፡ ይህም የአዲስ ኪዳን ማህበር ወግ ነው፡፡
1ቆሮ.1:10 ”ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።”
ወንድሞች አንድ ንግግር ከተነጋገሩ፣ በአንድ ልብና በአንድ አሳብ ከተባበሩ መለያየት በመካከል ስለማይኖር ለጠላት ክፍተት አይኖርም፣ ያለክፍተትም የተንኮሉ መንገድ አይገለጥም፡፡
በጸሎት አጥር እንስራ፡- አንዱ ለሌላው መንፈሳዊ ውጊያ በመዋጋት የእግዚአብሄርን እርዳታ ማቅረብ፣ በምልጃና በጸሎት ውስጥም ሀይልን መሻት ይገባዋል፡፡ መንፈሳዊ ህይወት መደጋገፍ የሚያገኘው በዚያ መንገድ ነው፡፡ የቀረበ የራቀውን ሲስብ፣ ከራቀው ድካም ሲርቅ፣ በህብረት የጠላትን ምሸግ ለማፍረስ ሲዋጉ ሁሉም በእግዚአብሄር የምህረት ጥላ ውስጥ ሲያድሩ ታላቅ ድል ይሆናል፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብ በጽድቅ ህይወት ሲመራ በቤቱ በህብረት ቢጸልይና ቢለምን በአምላኩ ፊት ሞገስ ሲያገኝ በጠላቱ ፊት ማስፈራትን ይላበሳል፡፡
1ነገ.8:33-36” ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላቶቻቸው ፊት ድል በተመቱ ጊዜ፥ ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥አንተ በሰማይ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው። አንተን ስለ በደሉ ሰማይ በተዘጋ ጊዜ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኃጢአታቸው ቢመለሱ፥ አንተ በሰማይ ስማ፤የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብ ስጥ።” ይላልና፡፡
የመናፍስት አሰራር እየረቀቀ ሀይላቸውም እየጨመረ በሄደ መጠን የእግዚአብሄር ህዝብ በአምላኩ ሀይል ተግዳሮትን ማራቅ አለበት፡፡ ነፍሳት ይድኑም ዘንድ በአንድ ልብ መዋጋትና የሲኦል ደጆችን መጋፈጥ ግድ ይላል፡፡ የጌታ ኢየሱስን ራእይ በምድር ላይ ማስፈጸም እንዲቻል አንድ ሆኖ መመላለስ፣ መጾምና መጸለይ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
ሀዋርያው ጳውሎስ የህብረትን ነገር ሲያጎላ እንዲህ ይላል፡- ”በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤ ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ።” (ኤፌ6:18-20)
መደጋገፍን እናዳብር፡- አንዱ የሌላውን ጉድለት መሸፈን፣ ለማህበሩ መጠንቀቅ፣ እለት እለት ሁኔታዎችን መከታተልና ጉድለትን መሸፈን ከእርስበርስ ግንኙነት መሀል ዋናው ነው፡፡
2ቆሮ.1:10-11 ”እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፥ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል።” ይላል፡፡
በሮሜ.12:4-7 ላይ ሲናገር፡- ”በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ” ይላል፡፡
ውጊያ ማቀጣጠል፡- መንፈሳዊ ጦር ሆኖ መዘጋጀትና የጠላትን ሀይል ለመስበር መንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ መሰለፍ የሚጠበቅብን ተግባር ነው፡፡
ኤፌ6:11-17” የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ። እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።”