የጠላትን መንገድ እወቅ[1…]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

ጠላትን ፊት ለፊት ተጋፍጦ በሰራው መንፈሳዊ ስራ ድልን ያገኘው ነህምያ እግዚአብሄር ረድቶት ያሸነፈበትን ጥበብ ሲተርክ እንዲህ ይላል፡-
ነህ.4:1-9 ”ሰንባላጥም ቅጥሩን እንደ ሠራን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፥ ተበሳጨም፥ በአይሁድም አላገጠ። በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊትም ፊት፡- እነዚህ ደካሞች አይሁድ የሚሠሩት ምንድር ነው? ይተዉላቸዋልን? ይሠዋሉን? በአንድ ቀንስ ይጨርሳሉን? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን? ብሎ ተናገረ።አሞናዊውም ጦብያ በአጠገቡ ቆሞ። በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል አለ። አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤ በምርኮ አገር ለብዝበዛ አሳልፈህ ስጣቸው። በደላቸውንም አትክደን፥ ኃጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፤ በሠራተኞች ፊት አስቆጥተውሃልና። ቅጥሩንም ሠራን፤ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኵሌታው ድረስ ተጋጠመ፤ የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ። ሰንባላጥና ጦብያም ዓረባውያንም አሞናውያንም አሽዶዳውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያሸብሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተማማሉ። ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን።”
በቅድሚያ ሰንበላጥና ጦብያ የሚባሉ ባለስልጣኖች የህዝቡን በጎነትና ልማት የማይወዱ እንዲያውም ህዝቡ በከፋ ችግር ውስጥ ሆኖ እንዲኖር የሚመኙና ለዚያ የሚሰሩ ነበሩ፡፡ ድንገት ባልተጠበቀ ሰአት ለህዝቡ ተሙዋጋችና የፈረሰውን መቅደስ ጠጋኝ ሰው ብቅ ሲል ቁጭታቸውን መቆጣጠር እስኪሳናቸው ተናዘዙ፡፡ ሰዎቹ ስጋ ቢሆኑም የተስፋ ቃል የነበረውን ህዝብ የተቃወሙበት መንፈስ ሲታይ አነሳሳቸው ከስጋ ባለፈ የክፉ መናፍስት ቅንጅት እንደነበረበት ማየት ይቻላል፡፡
ስለ ጠላት እንደሆነ፣ የጠላ በጠላው ሰው ላይ ምንም አይነት ፍቅር እንደማያሳድር ግልጽ ነው፤ ፍቅሩም ስለሌለው ሊጎዳው፣ ሊያዳክመው ወይም ሊያጠፋው ያደባበታል፡፡ እርሱ የጠላውን ሰው ጥፋት ስለሚያፈላልግም በጎ የሆነ ነገሩን ፈጽሞ ሊያበላሽ ይዋጋል፡፡
የእኛም ጠላት (መንፈሳዊ ጠላት ስላለን) እኛን ይጎዳ ዘንድ ጥቅማችንን በሞላ በእርሱ ጥቃት ኢላማ ስር ያስገባል፡፡ በዚህ አካሄድ ከእግዚአብሄር የተቀበልነውን ለህይወታችን እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ ለማበላሸት ዘወትር ይተጋል፡፡
አደገኛው ጠላት መንገዱን እየቀያየረ፣ ዱካውን እያጠፋና ዘዴውን እየለዋወጠ ይሹለከለክና በቀናው እለት ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይቻኮላል፡፡
ክፍተት በህይወታችን ሲኖር ያጋልጠናል፤ መንፈሳዊው ጠላትም ሴራውን እንዲያሾልክ ያመቸዋል፡፡ ስለዚህ ወገኖች አስተውለው በፍቅር ካልተባበሩ፣ በህብረት ሆነው ዙሪያቸውን ካላጠሩ፣ ልባቸውን ከሚከፋፍል አሳብ ካልጠበቁትና በመንፈስ ጉልበታቸውን ወደ ማጠናከር ካልመጡ በርሱ ኢላማ ውስጥ በቀላሉ ይገባሉ፡፡ ይህ ክፉ ጠላት ህዝቡን ሊያጠቃ መንገድ ሲቀይስ የተለያዩ ብልሀቶችን ይጠቀማል፤ ከነርሱም መሀል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-
• በማስፈራራት ይመጣል
ልንሰራ ያሰብነውን እንዳንጀምረው የጀመርነው ካለም እንድናቆመው ያስፈራራል፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብ ጠላቶች እነ ነህምያ የእግዚአብሄን ስራ እንዳይሰሩ ያን አድርገዋል፡፡ ጠላት ሁልጊዜ በጽድቅ ስራ ላይ ይዘምታል፤ ከሚዘምትበት መንገድ አንደኛው ማስፈራራት ነው፡፡ እግዚአብሄርን ተስፋ ያደረጉ ግን በእጁ ላይ ፈጽሞ አይወድቁም፤ ጠላት ያስፈራራ እንጂ አሸናፊው ህዝቡ ነው፡፡ ስለዚህ መፍራት ካለብን ከእግዚአብሄር ፊት እንዳንጠፋ እንጂ በሰይጣን ድንፈታ መሆን የለበትም፡-
ዘጸ.15:6-13 ”አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ። በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰድደህ፥ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ። ጠላትም፡- አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ። አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው።”
ይህ የእግዚአብሄር ህዝብ ዝማሬ የመጣው ከከፍተኛ የጠላት ማስፈራሪያ በሁዋላ ነበር፤ ከብዙ አስጨናቂ ውጊያ ተርፈው፣ እግር ለእግር ተከታትሎ ከሚያስጨንቃቸው ጠላት በእግዚአብሄር ክንድ አምልጠው የጠላትን ሬሳ ባዩ ጊዜ ነበር፤ በብዙ ጭንቀትና መከራ ከገቡበት ሁኔታ ከተረፉ በሁዋላ በእግዚአብሄር ተዋጊነትና ድል ሰጪነት ሀሴት አድርገው የዘመሩትም ነው፡፡ ስለዚህ ”አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ” የሚል ቅኔ አቀረቡለት።
• በማስደንገጥና በማሸማቀቅ ይመጣል
አቅም የለኝም ብለን እንድንሰበሰብና እንድንተሳሰር ወደፊት እንዳንወጣም ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሴራው በኩል ጀምሬ ባይሳካልኝስ የት እገባለሁ? ብለን እንድንሳቀቅ ያደርጋል፡፡ ልባችንን በፍርሀት በመወጠር የተሸለ መፍትሄ እንዳናስብም መንገዳችንን ይሰውራል፡፡
ሀጢያት የሰይጣን ቀይ ካርድ ነው (ማስፈራሪያና መክሰሻው ስለሆነ)፡፡ ህይወት ከእግዚአብሄር በራቀች ቁጥር ሀይል አልባነት ስለሚወርሰን በጸሎት ውስጥ ገብተን ሀይል መለመን አንችልም፣ ወደ እግዚአብሄር መቅረብም አንችልም (ከሳሽ ስለሚያጣድፈንና ስለሚያስፈራራን የእግዚአብሄር ምህረት ሩቅ ይሆንብናል)፡፡ እግዚአብሄር ራሱ የንሰሀ በር ከፍቶ፣ ልባችንን ደግፎና ወደ እርሱ አቅርቦ እስክንፈወስ ድረስ የአጋንንት መጫወቻ ነው የምንሆነው (የኢየሱስ ማላጅነት ደሙን ወደ እኛ አቅርቦ የህሊና ክስ እስኪወድቅልን ሰይጣን እንዲያ ያሸማቅቀናል)፡፡ ስለዚህ በእርሱ ላለመደንገጥና ላለመሸነፍ የጽድቅ ህይወትን ምርጫ ማድረግ ብቻ ይበጃል፡፡
1ጴጥ.5:7-9”እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።”
• ማባበልን ይጠቀምና ያዘናጋል
ወዳጅነት የሚሻ በማስመሰል ልብን ሊሰርቅ ይሞክራል፤ አመቺ ቀን ካገኘም ያጠቃል፡፡ ብዙ ምኞቶቻችን ወደ ጥፋት ይመሩናል፤ በተመኘነው ልክ ፍላጎታችንን መስፋትና ማስተካከል ደግሞ እርሱ አጥብቆ ያውቅበታል፡፡ ሶምሶን የሚባል ልጅ ለቤተሰቡ ሲወለድ እግዚአብሄር በዋነኛነት ለእስራኤል መፍትሄ ፈጣሪ እንዲሆን ለየው፡፡ ሶምሶን ግን በተሰጠው ጸጋ የእግዚአብሄርን አገልግሎት ከማገልገል ይልቅ የተጠራበትን አላማ ስቶ ጠላት አካባቢ መሽከርከር ያበዛ ነበር፡፡ ጠላቶቹም የሚወድቅበትን ስስ ባህሪውን አፈላልገው ደረሱበትና በምታባብል ሴት እጅ እንዲማረክ አደረጉት፡፡ ሶምሶን በዚያ ጥፋቱ ምክኒያት የተወለደለትን አላማ ማሳካት ይቅርና እራሱን ከጠላት መንጋጋ ማውጣት ሳይችል አሰቃቂ ሞት ሞተ፡፡
ገላ.5:7-10 ”በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው።”
የዲያቢሎስ ማባበል በጽድቅ ከጠራን ጌታ እጅ ለማውጣት ነው፡፡ አስተማማኝ ደህንነት ካለበት እጅ ውስጥ አንዴ ከሾለክን የተሻለ ደህንነት ጠላት ዘንድ ይገኛል ብለን ለምን ተስፋ እናደርጋለን? በሬ ካራጁ እንደሚባለው ካልሆነብን በስተቀር ሌላ ምን ይተርፈናል?
• ቅጥረኛ ይመለምልና መሀል ይገባል
ለከፍተኛ ችግርና ፈተና ከሚዳርጉ ስህተቶች መሀል አንዱ ከጠላት ጋር (ከክፉ አሳብ ጋር) መወዳጀት ነው፡፡ ክፉ ባልንጀራ የዲያቢሎስ ምልምል ነው፡፡ ሰይጣን ቅንነትን የሚያጠፋ አመል በባልንጀራ በኩል በቀላሉ ያስተዋውቃል፡፡ በፍቅር የታሰረ ወዳጅ የባልንጀራው ስህተት ስለማይታየው ባለው ቀረቤታና ፍቅር ምክኒያት ይታወራል፣ ወደ ገደልም ያመራል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል እንዲህ አይነቱን ግንኙነት አጠንክሮ ይገስጻል፡-
1ቆሮ.15:33” አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ።”
አሳቡ የሸፈተን ሰው ጠላት በገንዘብና በጥቅማጥቅም በማባበል ይጠቀምበታል፡- ምስጢር በማውጣጣት፣ በማዘረፍ፣ በማጥፋት፣ ወሬ በማስነዛት፣ በማዳከም፣ ስለጠላት መልካም እንዲያወራና ህዝቡን እንዲከፋፍል ያደርግበታል፡፡ በነዋይ መታለል ምክኒያት እውነትን መሸጥ ይመጣል፤ የሰው ድካም መነገጃ ማድረግ (ለሌላው ስላቅ ማድረግ)፣ ህይወትን ማስበዝበዝ የመሳሰሉ ውድቀቶች ይከተላሉ፣ በጠላት ከተማረክን፡፡ ነህምያ የእግዚአብሄርን ስራ እንዳይሰራና በጠላቶች እጅ እንዲወድቅ የገዛ ወንድሞቹ ለጠላት አሳብ አጋልጠውት ነበር፡-
ነህ.6:10-13 ”እኔም ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ቤት ገባሁ፤ እርሱም ተዘግቶ ነበርና። በእግዚአብሔር ቤት በመቅደሱ ውስጥ እንገናኝ የመቅደሱንም ደጆች እንዝጋ፤ እነርሱ መጥተው ይገድሉሃልና፥ በሌሊትም ይገድሉህ ዘንድ ይመጣሉና አለ። እኔም፡- እንደ እኔ ያለ ሰው የሸሸና፥ ነፍሱንስ ያድን ዘንድ ወደ መቅደስ የገባ ማን ነው? እኔስ አልገባም አልሁት። እግዚአብሔርም ልኮት እንዳልነበረ፥ በእኔ ላይ ግን ትንቢት እንደ ተናገረ፥ እነሆ፥ አወቅሁ፤ ጦብያና ሰንባላጥም ገዝተውት ነበር። ይህንም ነገር አደርግና እበድል ዘንድ፥ በእኔም ላይ ክፋት እንዲናገሩና እንዲያላግጡ ያስፈራራኝ ዘንድ ተገዝቶ ነበር።”
• በመመሳሰል ተሰውሮ ያጠቃል
በዚህ ስልት ብዙ ጉዳት ያደርሳል፣ ይህ ከፍተኛ የጥፋት ስልቱ ነው፤ ወዳጅና ጠላቱን የማይለው የዋሁን በቀላሉ ያጠምደዋል፡፡ የሰው የከፋ ጠላቱ ያልተጠበቀ አሳቡ ነው፡፡ አሳባችን ግድብ፣ ጥብቅና ጥንቁቅ ካልሆነ ብዙ ስፍራ እያካለለ የጠላት መጠመጃ መሬት ያደርገናል፡፡
2ቆሮ.11:3 ”ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።”
አሳብ እንዴት እንዲህ ከፋ? አሳብ የድርጊት ጅማሬ ጥንስስ እንደመሆኑ ገና እንደታሰበ ሳይቆረጥ ካደገ የሚመኘውን ከመሆን የሚያግደው አንዳች ነገር አይኖርም፡፡ በክርስቶስ ደም ነጽተን ያገኘነውን ቅንና ንጹህ ህሊና በጠላት አሳብ ካበላሸን ድርጊታችን ሁሉ ወደ ክፉ ፍሬ የማይደርስበት ምንም ማስተማመኛ የለም፡፡ ስለዚህ ቅጥርን መቅጠር ሲያስፈልግ አእምሮን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
ቆላ.1:21-22 ”እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ።”
ነገሮች ግልጽ ከሆኑልን ዘንድ በሰይጣን እንደተጠመድንና እንደወደቅን ሳናውቅ አሰባችን በሙሉ ከእግዚአብሄር አሳብ በተቃራኒ አቅጣጫ እየሄደ ጠላትነትን እንዳተረፍነው ጊዜ ሳይሆን ሸንጋይነቱን አውቀን እግዚአብሄርን የተጠጋን ወዳጅ መሆን ይገባናል፤ በቃሉ ካስተዋልን የዲያቢሎስን ሽንገላ የምናውቅ፣ አሳቡንም መቃወም የምንችል፣ የጦር እቃውንም የታጠቀ እንዲያ ያለ ሰው መሆን እንችላለን፡፡