የዮሴፍ በረከት ያግኝህ (1…)

የእግዚአብሄርን ቃል የሚያውቅ ሁሉ የዮሴፍን በረከት በደስታም በጥንቃቄም ያስተውላል፤ በእርግጥ እግዚአብሄር የረዳው፣ በባእዳን ምድር ከፍ ከፍ ያደረገው፣ በባለጠግነትና በማረግ ያገነነውም እንደርሱ ያለ ሰው የለምና። ዮሴፍ እዚህ ከፍታ እስኪደርስ ግን ምን ገጠመው፣ እንዴት ባለስ ሁኔታ ውስጥ አለፈ? ብሎ የሚጠይቅ ከዚህ ትሁት ሰው ህይወት የሚቀበለው ማስተዋል አስተሳሰቡንና እምነቱን ደግሞ ደጋግሞ እንዲቃኝ ያደርገዋል።
በእርግጥ እንደ ዮሴፍ ያለ በረከት ያገኝ ዘንድ የሚመኝ ማንም ቢኖር መልካም ተመኘ፣ ሆኖም እርሱ ያለፈበትን ረጅምና ውስብስብ መንገድ በትግስት ይጓዘው ዘንድ ግን አምኖ ይቀበል። ህይወት እንደ ንግግር ፈጽሞ አይቀልም፣ የህይወት ልምምድ እስከነፍስ ድረስ የሚጠልቅ የስሜትና የአስተሳሰብ ግብግብ የሚያሳልፍ የሰው ልጅ የዘመን መንገድ ነውና።ጊዜን በሚጠይቅ ጉዳይ ላይ እግዚአብሄርን ፈጽሞ መጠበቅ ቀላል ነገር አይደለም፣ ወደ ኋላ እንድናፈገፍግ የሚያስገድድ ሰዋዊ ግፊት በኛ እያለ ያን መቋቋም ያውም በራሳችን ማንነት ውስጥ ሆኖ የሚሞግተን እንደመሆኑ ያን ሁሉ ተግዳሮት አስቀድሞ የአምላካችንን እርዳታ ፈጽመን ማግኘት የግድ አስፈላጊ ያደርገዋል።
በዚህ መረዳት ዮሴፍን ስንመለከት ብዙ የምንደነቅበትን የህይወቱን መንገድ አካሄድ እናስተውላለን፤አስቀድሞ ከእግዚአብሄር ጋር የነበረውን ልምምድ ስንመረምርም ይህን አስደናቂ ነገር ከእግዚአብሄር በተቀበላቸው የብላቴንነት ራእዮች እንደጀመረ እናያለን።ያ ሲሆን ግን እነዚያ ራእዮች ከመነሻው የወደፊቱ ዮሴፍ ማንነት መስታወቶች ቢሆኑም ከቤተሰብ በኩል በበጎ የተቀበላቸው ማንም አልነበረም። በእግዚአብሄር በኩል ለአንድ ከፍ ያለ ነገር የተጠራውን ብላቴና ስናገኝ በሌላ በኩል በወገኖቹ መሃል በጥርጣሬ የሚታይን አንድ ትንሽ ልጅ እናገኛለን። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚቀጥለው የዮሴፍ ህይወት ብዙ ዳገቶችንና ቁልቁለቶችን ተጉኡዞአል፤ ትንሹ ብላቴና ትልቁና የፈርኦን ምክትል የሆነውን ባለብዙ ክብር ዮሴፍ እስኪያገኘው በችግር አፋፍ፤በፈተና አፋፍ፣ እንዲያውም በሞት አፋፍ ላይ እየደረሰ እንዲመለስ አድርጎታል።በእግዚአብሄር በኩል ግን ጠርቶ የማይጸጸት አምላክ በመሆኑ አንዴም ፊቱን ሳይመልስበት እስከፍጻሜው ከርሱ ጋር ሆኖአል። እንግዲህ የዮሴፍ በረከት ብቅ ጥልቅ ስትታየው የኖረችው በአምላኩ የማይለወጥ የተስፋ ቃልና በጠላት ፍጹም ፈተና መሃል አሳልፋዋለች፤ ሆኖም እርሱ እስከ መጨረሻው በአምላኩ ስለጸና በብላቴንነት ዘመን ያጣቸውን በሙሉ በጊዜው አግኝቶአቸዋል።

ጉዞ ብርቱ ተስፋን በሚታገል ተግዳሮት ላይ በተንጣለለ ጉርብጥብጥ መንገድ፦
በዘፍ.41:39 ላይ ‘’ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ እንደ አንተ ያለ ብልህ አዋቂም ሰው የለም፥ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ገልጦልሃልና። አንተ በቤቴ ላይ ተሾም፥ ሕዝቤም ሁሉ ለቃልህ ይታዘዝ፤ እኔ በዙፋኔ ብቻ ከአንተ እበልጣለሁ። ፈርዖንም ዮሴፍን፦ በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾምሁህ አለው። ፈርዖን ቀለበቱን ከእጁ አወለቀ በዮሴፍ እጅም አደረገው፥ ነጭ የተልባ እግር ልብስንም አለበሰው፥ በአንገቱም የወርቅ ዝርግፍን አደረገለት፤የእርሱም በምትሆን በሁለተኛይቱ ሰረገላ አስቀመጠው፥ አዋጅ ነጋሪም፦ ስገዱ እያለ በፊት በፊቱ ይጮኽ ነበር፤ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ተሾመ።ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ እኔ ፈርዖን ነኝ፤ በግብፅ አገር ሁሉ ያለ አንተ ማንም እጁንም እግሩንም አያንሣ።’’
እንዲህ ያለ ሞገስና ክብር እንዴት ያስደስታል? ግብጻዊ ሳይሆን የግብጽ ገዢነት ላይ መድረስ፣የፈርኦን ዘር ሳይኖረው የርሱ ከፍተኛ ባለስልጣን መሆን በተለይ ለአይሁዳዊ መጻተኛ ሰው ከአእምሮ በላይ የሆነ ግርምት የሚፈጥር ነው፤ ለባርነት ተሽጦ ወደ ባእድ አገር ገብቶ ሳለ ቆይቶ ወደ ንጉስ ቀኝ እጅነት ድረስ መድረስ ተአምር አይሆንምን?
ለመንፈሳዊ ሰው ግን ከእግዚአብሄር በረከት ደጅ ላይ ቆሞ የሚጠብቅ የጠላት በቀለኛ እንዳለ ማስተዋል ይግባል። ዮሴፍ ፍጹሙ በረከት አጠገብ ሳይደርስ (የፈተናው ፍጻሜን ያገኘበት የሚመስለው የባለስልጣንነት ደረጃ) ከርሱ በፊት ብዙ ሞገስና በረከት የሚጨምሩለት አጋጣሚዎችን ተቀብሎ ሳለ ወዲያው በሚያጨነግፍ የጠላት አሰራር ተጠቅቶ ወደኋላ ሲል እንመለከታለን።
ዛሬ መንፈሳዊውን በረከት ሊቀበል የተዘጋጀ ምን ምን ይታየው? በእግዚአብሄር መንገድ ላይ በረከት ብቻ ሳይሆን መንገዱ አቅራቢያ፣ በዙሪያውም ሆነ በርሱ ላይ ይገባና ይነጥቅ ዘንድ አድብቶ የሚጠባበቅ መንፈሳዊ ጠላት እንዳለ ያለማሰለስ ይታየው። በእርግጥ አመጣጡ ባለ አንድ አቅጣጫ ሳይሆን ፈርጀ ብዙና ፈጽሞ የማይገመት ሲሆን ልክ ዮሴፍ ላይ በተለያየ መንገድ ይገለጥ እንደነበረው በኛም ዘንድ ያን እንደሚያደርግ መገመት ያስፈልጋል።በአብዛኛው የጠላት ፈተና እንደ ህይወት ይዘታችን የተለያየና የተለዋወጠ ነው።ነገር ግን ለሁሉም ሰው ጠላት እስኪመጣ ድረስ አመቺ ጊዜና ስፍራ ይጠብቃል፤ የተዘናጋንበትን ሁኔታ ይጠብቃል፤ የዛልንበትን ሰአት ይፈልገዋል፤ማምለጥ የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ እስክንገባ ይታገሳል።
ለማንኛውም ግን ማንም ሰው በእግዚአብሄር ፈቃድ የማይኖር ሆኖ ሳለ በጠላት ተፈተንኩ ማለት ከቶ እንዳይችል ይወቅ፤ የዚህ ዋና ምክኒያት ከእግዚአብሄር ክልል ውጪ ያለው ሰው ሁሉ ወትሮም በዲያቢሎስ መንፈሳዊ ክልል ውስጥ ያለ በመሆኑ በገዢው ዲያቢሎስ ፈቃድ ሊኖርና ሊገዛ ግድ በመሆኑ ነው፤ በርሱ መንገድ ላይ ወዲያና ወዲህ እየተላተመ ቢኖር የገዢው ፈቃድ ነው፣ አትችልም፣እምቢ ይል ዘንድ ስልጣን የለውምና። እንዳሻው ሊያደርገው ስልጣን ስላለው በርሱ ተፈተንኩ የሚልበት ሰበብ ከቶ አይኖረውም፤ ማንም ሰው በገዛው ጌታ ስር ሆኖ ጌታው ያሻውን ቢያደርግበት ፈተነኝ ሊል መብትም የለውም።
አንድ የእግዚአብሄር ሰው (በእግዚአብሄር መንፈስ የሚመራ ሰው) ግን በጌታ ነጻ ሆኖ ሳለ በሚያስበው የራሱ አሳብ ሊፈተን ይችላል፤ ልቡን በሞላው እውቀት፣ በሚሰማው ስሜት፣ በሚታመንበት ነገር፣ በሚወደው ነገር፣ልቡ ባዘነበለበት ጉዳይ፣ ባስከፋውም ሆነ ልቡን በሞላው ሃዘን ያልያም ሃሴት ባደረገበት ነገር ሁሉ በክፉው ሊጥመድበት ይችላል።ይሁዳን እናስታውሳለን፤ ይህ ሰው ከጌታ ጋር ሆኖ ሳለ አሳቡ ግን ከርሱ ጋር ባለመሆኑ ሰይጣን አሳብ ሲያገባበት እናያለን፤ይህ ሰው የራሱን አሳብ ተተግኖ በገባበት ሰይጣን ቁጥጥር ስር እንደነበረ ስላላስተዋለ ቀጥሎ የመጣውን የዲያቢሎስ አሳብ (አሳልፈህ ሽጠው የሚለውን አሳብ በፍጹም ልብ ተቀበለው)። ሰው ግን የመጣበት የሚያናውጥ አሳብ፣ ሃይል፣ ፍርሃት፣ መጥፎ ስሜትም ሆነ ፈተና ሲያገኘው በጭፍን ወዲያና ወዲህ ከማለቱ፣ ለማምለጥም ከመጣደፉ በፊት ልቡን አስቀድሞ ወደ እግዚአብሄር ነገር ቢመለስ (ይሁዳም ልቡን ወደራሱ አሳብ ሳይሆን ወደ ጌታ ድምጽና ትእዛዝ ቢመልስ) በተያዘበት ሁኔታ በዚያ ወቅት ላይ ፈጣን መፍትሄ፣የልብ መጽናናት ወይም የመፍትሄ ምክርም ሆነ ተግሳጽ ይቀበል ነበር።እንግዲህ የክርስቶስ የሆነ ሰው ከሚመጣ ድንገተኛ ገጠመኝ ያመልጥ ዘንድ ጌታን በፍጥነት ይፈልግ፣ ወደ ቃሉ ዞር ይበል፣ በእምነት የሚደግፈውን ቃሉን ይዞም ወደ ጸሎት መንፈስ ውስጥ ይግባ።
ቢሆንም አንፍራ፣በእግዚአብሄር እጅ ያለ ሰው የትም ይሁን የት አይጠፋም
እግዚአብሄርን በፍጹም ልቡ የሚያምን ሰው (በአማራጭነት የሚከተለው ሳይሆን እሱንና እሱን ብቻ ቅድሚያ ምርጫ ያደረገ ሰው) ምንም ሁኔታ ይፈጠር፣ ማናቸውም ነገር ይምጣ በትግስት እርሱን በመጠበቁ ከእግዚአብሄር ዘንድ ምህረትን ያገኛል።እንዲህ ያለ ሰው በተመቸ ሁኔታ ሊኖር ይችላል (ልክ ዮሴፍ በአባቱ ፊት ይኖር የነበረበትን ሁኔታ የመሰለ ተድላና ሞገስ ያለው ህይወት ውስጥ ሊኖር ይችላል)፣ ያልያም በአሳነባሪ ሆድ ውስጥ እንደነበረ እንደ ዮናስ በአስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እየጸለየም ይሆናል (እንደ ሲኦል በሚያስፈራ ስፍራ ውስጥ ሊገኝ ይችላል)።ሁሉም ሁኔታዎች በእግዚአብሄር ፊት ነበሩ።
ዮሴፍ በአባቱ ቤት ሳለ በወላጆቹ መሃል በሰላም የተከበበ ከእግዚአብሄርም ዘንድ ሞገስን የተቀበለ ብላቴና ነበር፤ ከአምላኩ ጋር የተጣበቀም ስለነበር በህልምና በራእይ በኩል ከአምላኩ ጋር ግንኙነት ነበረው። ብዙም ሳይቆይ ግን በክፉ አጋጣሚ ውስጥ ገባና መከራን ይጋፈጥ ያዘ። በዚህ የህይወት ሁኔታ ውስጥ ሆኖና የከፋ ሁኔታን እየተጋፈጠ ሳለ እግዚአብሄር ከርሱ ጋር መሆኑን በተለያየ መንገድ ያይና ያስተውል ነበር።ስለዚህ በወንድሞቹ ጥላቻና በቀል ምክኒያት ለባርነት ተሽጦ የህይወት አዘቅት ውስጥ ገባ፤ ይህ ለአንድ ለግላጋ ልጅ በቤተሰቡ ልዩ እንክብካቤ ስር ለነበር እንዲህ ላለ ልጅ ከባድ ቅጣት ነበር። ይህ ልጅ በዚያ ፈተና ውስጥ ቢሆንም እግዚአብሄር ግን ፍጹም ሳይለየው ከርሱ ጋር ሆኖ ወደ ወረደበት ወደዚያ መንፈሳዊ አዘቅት ወዳለበት ስፍራ ወርዶ ነበር። ወደ ግብጽ ከገባ በኋላ ለጋው ዮሴፍ እግዚአብሄርን መፍራት ስላላቆመ በባርነት ቤት ሆኖም የእግዚአብሄር ሞገስ ከርሱ አልተለየም።ፈተናው እየቀጠለ እየቀጠለ በሄደ ጊዜ ከባርነት ኑሮ በላይ ወደ ሚከፋው ወህኒ የመጣል እጣ ገጠመው።ዮሴፍ በዚያ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሳለም እግዚአብሄር አምላኩ ከርሱ ጋር ነበር (ብላቴናውም ይህን አስተውሎ ከአምላኩ ጋር ተጣብቆ መኖርን መርጦአል)።የአባቶቹ አምላክ እንዲህ ያለው ቃል ይከተለውም ነበር፦
ዘፍ.28:15፤ ‘’እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።’’