ዝምታ ምን አይነት ድምጽ ሊያሰማ ይችላል? ወይም ዝምታና ድምጽ እንደምን ይገናኛሉ? ዝምታ ያለ ድምጽ የሆነ ክስተት ሲሆን ድምጽ ከሚሰማ ቃል ጋር በመሆኑ ሁለቱ በተቃራኒ በኩል ሳሉ በአንድነት ትርጉም ያላቸው እንዲሆኑ ተደርገዋል፤ የቻሉት ግን የእግዚአብሄር አሰራር በመሆናቸው ነው፡፡
በዝምታ ውስጥ ምን ልንሰማ እንችላለን? ምን አይነት ድምጽስ በዝምታ ውስጥ ሊሰማ ይችላል ብለን መጠበቅ እንችላለን?
እንደ ሰው ግን ዝምታን ለማግኘት ወስነን ከሆነ ጸጥ ወዳለ ስፍራ እንሄዳለን ወይም ጸጥታን የምንፈጥርበት ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡ በዚያም ጸጥ ባለው ሁኔታ ውስጥ የውስጥ የልባችንን ማዳመጥ እንጀምራለን፡፡ በጸጥታ ውስጥ ቅድሚያ የምንሰማው ሰውነታችን ውስጥ የሚካሄደውን ስራ ነው፡- የልብ ምታችንን በጉልህ እንሰማለን፤ ውስጣችንን ዘልቀን ስንፈትሽ የደም ዝውውራችንን እናስባለን፣ ጨጉዋራችን ለስራ እንደሚንቀሳቀስ በአይነ ህሊናችን እናያለን፣ ነርቮቻችን መልእክት ሲቀበሉና ሲሰጡ እናስባለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ስርአታቸውን ጠብቀው ሳይዛነፉና ሳይሳሳቱ እንዲያከናውኑ ማን አደረጋቸው ወደሚለውም እንመጣለን፡-እግዚአብሄር ነው ያንን የሚያደርገው፣ እና ይህንን ስናረጋግጥ እናመሰግናለን፡፡ እግዚአብሄርን ስናስብ በእኛ ስለሚያደርገው ታላቅ ነገር ማስተዋል እንችላለን፡፡ ዘለቅ ብለን ካሰብን ደግሞ እኛ በእርሱ ፊት ማን መሆናችንን እንጠይቃለን፣ መልሱን በሰጠ ጊዜም በነፍሳችን ላይ ወዳለው አላማው እንደርሳለን፡፡
ሰው በእግዚአብሄር ፊት በጽሞና ሲቀርብና እንዲናገረው ሲለምን በዚያ ውስጥ ወደ ልቡ የሚመጣ የርሱ ድምጽ አለ፡፡ እግዚአብሄር ይናገራል፣ ይመራል፣ ያጽናናል፡፡ በመጽሀፍ ውስጥ በተቀመጠ ቃል ልብን ያንኩዋኩዋል፡፡ አስበነው ወይም አስተውለነው በማናውቀው መንገድ ቃሉ ድምጽ ሆኖ ሲናገር ይሰማናል፤ ወደ ንሰሀ ያስገባናል፣ ያላየነውን እንድናይ፣ የወደቅንበትን እንድናስተውል፣ የተላለፍነውንም እንድናውቅ ያደርጋል፡፡ የልቦና አይናችንን ሲከፍት መንፈሳዊ ስፍራችንን እናያለን፣ ከፍ ያለ ስፍራውን አውቀን ራሳችንን እስክንንቅ ድረስ ያለንበትን ውድቀት እንመለከታለን፡፡ ደግሞ ብድግ ሲያደርግ ክብሩን እናያለን፡፡ ሆኖም ንጉሱ በዙፋኑ ላይ ሆኖ የሚታይበት የመንፈስ ከፍታ እንደምን ያለ መለኮታዊ ጉብኝት ይሆን?
ዝምታን ስንለማመድ በውስጥ የምናስበውንና የሚሰማንን ማድመጥ ልማድ እናዳብራለን፡፡ በዝምታ ውስጥ ብቻ ሆኖ ከራስ ጋር በሙግት/በወቀሳም በሉት/ እንዲያ መቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡
መዝ.39:1-6 ”በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ። ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ ቍስሌም ታደሰብኝ። ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ፤ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ። አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ። እነሆ፥ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው፤ አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ብቻ ነው። በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጣላ ይመላለሳል፤ ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም።”
እኛም ብንጠይቅ ጥሩ ነው፡- ምን እያደረግኩ ነው? የት ነው ያለሁት? ህይወቴ ምን ይመስላል? እንቅስቃሴዬን የእግዚአብሄር ቃል እንዴት ያየዋል? አካሄዴን የእግዚአብሄር ቃል ይደግፈዋልን? ብዙ ብዙ የሚታዩ (በራስ ላይ የሚከናወኑ ፍተሻዎች) ይኖራሉ፣ ዋናው ልማዱን ማዳበር እንጂ፡፡ የዳዊትን ፍተሻ አስተውለን ስንመለከት ከእለት ተእለት ያለፈ የራስ ፍተሻ ሲያካሂድ እናያለን፡፡ አረ እንዲያውም አምላኩን ከአንድ ዘመን አልፎ እስከፍጻሜው በሚደርስ ኡነት ውስጥ ያለውን እርሱነቱን እንዲመለከትለት፣ እንዲፈትሽለትና እንዲያስታውቀው ይጠይቃል፡፡ንጉስ በማሰላሰል ብዛት የገጠመውን ሁኔታ ሲያመለክት ”ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ” አለ፡፡
አንዳንዴ በራስ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከመንፈሳዊ ህይወት አንጻር በሚል በጸጥታና ለብቻ ለመሆን መሻት ለመነጠል ከመሻት ወይም ከብቸኝነት ስሜት ጋር እንዳይያያዝ ያስፈልጋል፡፡
በዝምታ ውስጥ ሆኖ ራስን ከውስጥ ድምጽ በማሳረፍ ከእምነት ጋር መተባበርና የእግዚአብሄርን ነገር ማሰብና ማሰላሰል ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ቃሉን በማሰብ ማስተወል፣ ምህረቱን በመቁጠር ማመስገን፣ አምላክነቱን በማሰብ ማምለክና ራስን በመፈተሽ ንሰሃ መግባት በህይወት ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ከሁካታና ጫጫታ ርቆ በጽሞና ጸሎት ውስጥ በመሆን መንፈሳዊነትን ማዳበር ይቻላል፡፡ ኤልያስ በእግዚአብሄር ተራራ ላይ በቆመ ሰአት ብዙ የሚያናውጡ ነገሮችን አየ፣ ሰማም፡፡ በዚያን ወቅት ራሱን መፈተሽ መቻል ሳይሆን ፍርሀትና ድንጋጤ ላይ ወድቆ ነበር፡፡ ያ ሁከት አልፎ ዝምታ ሲከተል በዚያ ውስጥ የእግዚአብሄር ድምጽ መጣለት፡-
1ነገ.19:9-13 ”እዚያም ወዳለ ዋሻ መጣ፥ በዚያም አደረ፤ እነሆ፡- ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። እርሱም፡- ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።
እርሱም፡- ውጣ፥ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ ዓለቶቹንም ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ። ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፥ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ፡- ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።”
ተራሮችን የሚሰነጥቅ ዓለቶችንም የሚሰባብር ትልቅና ብርቱ ነፋስ በኤሊያስ ፊት ሲያልፍ እግዚአብሄር የት ነበረ? ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሲከተል እግዚአብሄር የት ነበረ? ከምድር መናወጥ በኋላም እሳት ሆኖአል፣ በዚያም ግን እግዚአብሄር አልነበረም፡፡ ከእሳቱ በኋላ ግን የዝምታ ድምፅ ሆነ፣ በዚያ ዝምታ ውስጥ እግዚአብሄር ወደ ኤሊያስ መጣ፣ ድምጹንም አሰማው፡፡
ብዙ ግርግሮች፣ የሚያናውጡ ክስተቶች ወይም ህይወትን የሚነቅሉ ፈተናዎች መጥተው ስንናጥ የእግዚአብሄር የመልስ ጸጥታ ደርሶ ሊሆን ስለሚችል ያን ጊዜ በትእግስት መስማት ይገባል፡፡
ሁከት በውስጣችን ያለውን በጎ ነገራችንን ያናጋል፣ በሁከት ውስጥ መቀበልም መስጠትም አይቻልም፤ ዝምታ ግን (በመንፈስ የሆነው ግን) የሌለውን ወደ ህይወታችን ያመጣል፡፡ የዝምታ ድምጽ ጸጥ ያለና የተረጋጋ መንፈስ ካላገኘ አይሰማም፡፡
ለእግዚአብሄር ያለን ፍቅር በግርግር ሳይሆን በፊቱ ጸጥ ብለን በመጠበቅ፣ በእምነትና እርሱን አጥብቆ በመፈለግ የምንገልጸው ነው፡፡ ኤልያስ እግዚአብሄርን በመተማመን ብቻ ወደ ሚያስፈራው ዋሻ ወደዚያ መጣ፤ የእርሱን መገኘት በመጠባበቅ አስፈሪዎቹን ክስተቶች አሳለፈ፡፡ የዝምታው ድምጽ ሲጠይቀውም አለ፡-
”ኤልያስ ሆይ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ? የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። እርሱም፡- ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና…” ሲል መለሰ፡፡
ጸጥታን በመለማመድ ማንነትንና በህይወትም ውስጥ የሚመላለሱትን የኑሮ ፍልስፍናዎች መገምገም ይቻለናል፡፡ በጸጥታ እንጂ በግርግር ውስጥ የባህሪ ሽግግር ማድረግ አዳጋች ስለሆነ ጸጥታን መምረጥና ከእግዚአብሄር መማርን መለማመድ ይበጃል፡፡
ኢዮ.4:12-16 ”ለእኔም በምሥጢር ቃል መጣልኝ፥ ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች። በሌሊት ሕልም አሳብ ሲነሣ፥ የከበደም እንቅልፍ በሰው ላይ ሲወድቅ፥አጥንቴን ሁሉ ያናወጡ ድንጋጤና መንቀጥቀጥ ወደቁብኝ። መንፈስም በፊቴ አለፈ፤ የሥጋዬ ጠጕር ቆመ። እርሱም ቆመ፥ መልኩን ግን ለመለየት አልቻልሁም፥ ምሳሌም በዓይኔ ፊት ነበረ፤ የዝምታ ድምፅ ሰማሁ።”
ኢዮብ በመከራ ውስጥ ሆኖ ሳለ በዝምታ ውስጥ የእግዚአብሄር ድምፅ በጆሮው እንደ ሹክሹክታ ሆኖ ተሰማው፣ በሰማው የዝምታ ድምጽ ነቅቶም መልክ እስኪያይ አይኖቹ ተከፍተው ራእይ ውስጥ ገባ፡፡ የነገንና የዘላለማችንን ጉዳይ የሚወስነውን ራእይ ለመቀበል የዝምታ ድምጽ በብቃት በህይወታችን መስራት እንደሚችል ማመን ይገባል፡፡
የዝምታ ሂደቶች፡-
በመንፈስ በጸጥታ ውስጥ ስንሆን የእግዚአብሄርን ቃል ብቻ በማሰላሰል በአእምሮአችን የሚመላለሱ የማያስፈልጉ አሳቦችን እናስወግዳለን፣ እንጫናቸዋለን፣ ያልያም በመለኮታዊ አሳቦች (በቃሉ ምክሮች) እንዲዋጡ ማድረግ እንችላለን፡፡ ከንቱ አሳቦችን ከውስጣችን ገስጸን ማውጣት፣ በእንቅስቃሴያችንም ጥንቁቅ መሆን ያስፈልጋል፤ ይህን ለማሳካት ከሚያውኩ ምክኒያቶች ገለል ማለት፣ ከማያንጹ ግንኙነቶች መራቅ፣ ነጻ መሆንና ልብን ለርሱ ብቻ መለየት ይገባል፡፡ ትግስት ባጣ ሁኔታ መንቀሳቀስም ሆነ ማንቀሳቀስ ከውስጣችን መራቅ አለበት፣ በጽሞና ሆኖ ለመጠበቅ ይቻል ዘንድ፡፡
አማኝ በህይወቱ የሚመላለሱ ጣልቃ ገብ ( አላስፈላጊ) ስጋዊ አሳቦችንና የሚያውኩ የጸጸት ክሶችን (ትውስታዎችን) በጸጥታና በተከታታይ ጾም ጸሎት ህይወት ማሸነፍ ይችላል፡፡ ከእግዚአብሄር የሚያስፈልገንን መፍትሄ ማግኘት ካለብን ተገቢው ነገር በዝምታ ውስጥ ወደሚያሰማን ድምጹ መጠጋት ነው፡፡ ጾምና ጸሎት ወደ እግዚአብሄር ለመቅረብ ዋና መንገድ ነው፡፡ ጾምና ጸሎት ድምጹን ሰምተን ለመታዘዝ፣ ለመሰራትና ፈቃዱን ለማስተዋል እንጂ በርሱ አሳብ ላይ ለውጥ ለማካሄድ መቼም አይደለም፡፡
ኢዮ.13:15-16 ”እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ። ዝንጉ ሰው በፊቱ አይገባምና እርሱ መድኃኒት ይሆንልኛል።”
ኢዮብ በከፍተኛ ፈተና ውስጥ ሆኖ ይህን ተናግሮ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ቀርቦ እስኪናገረው የመጽናናት አምላክ ወደ እርሱ እስኪመጣ ድረስ ”እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ” ሲል ለራሱ ቃል ይገባል፤ መንገዱን በፊቱ በማጽናት ዝንጉ ሰው ከሚያገኘው ጥፋት ጨክኖ ሊያመልጥ እንደወሰነም ተናግሮአል። ለኢዮብ መፍትሄ የእግዚአብሄር መጽናናት ቃል ብቻ እንደሆነ ገብቶት ነበርና እስኪናገረው ጠብቆአል፡፡
ዘዳ.30:20 ”እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፥ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።”
በዝምታ ውስጥ ከእግዚአብሄር የሚመጣ ድምጽ እንዳለ ሁሉ ወደ እግዚአብሄርም በጸጥታና በጽሞና ነፍሳችንን በፊቱ በማፍሰስ መጸለይ ምህረቱ ፊት ያቀርበናል፡-
1ሳሙ.1:12-17 ”ጸሎትዋንም በእግዚአብሔር ፊት ባበዛች ጊዜ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር። ሐናም በልብዋ ትናገር ነበር፤ ድምፅዋም ሳይሰማ ከንፈርዋን ታንቀሳቅስ ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች ቈጠራት። ዔሊም፡- ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው አላት። ሐናም፡- ጌታዬ ሆይ፥ አይደለም፥ እኔስ ልብዋ ያዘነባት ሴት ነኝ፤ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር ነገር አልጠጣሁም፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤ኀዘኔና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ድረስ ተናግሬአለሁና ባሪያህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ ብላ መለሰችለት። ዔሊም፡- በደኅና ሂጂ፥ የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ ብሎ መለሰላት።”
የሳሙኤል እናት ሐና ልጅዋን ሳትወልድ በፊት ብዙ ሀዘን በህይወትዋ አልፎአል፡፡ ልጅ ለመውለድ ብዙ አምጣለች፤ እግዚአብሄርን ብዙ ተማጽናለች፡፡ አንድ ወቅት በተሰበረ ልብ ሆና መቅደስ ገባች፣ ጸሎትዋንም በእግዚአብሔር ፊት አበዛች፤ ካህኑ ዔሊ ሐና በዝምታ ሆና በተሰበረ ልብ በውስጥዋ ወደ እግዚአብሄር ስትጸልይ አፏን ብቻ ይመለከት ነበር። እርስዋ ድምፅዋ ሳይሰማ ከንፈርዋን ታንቀሳቅስ ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች ቈጠራት። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍስዋን እያፈሰሰች ስለነበረ ኀዘንና ጭንቀትዋን ሁሉ ሰምቶ እግዚአብሄር መለሰላት፡፡ ዔሊ፡- በደኅና ሂጂ፥ የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ ብሎ እንደመለሰላት እግዚአብሄር ሐናን በዚያ የጸጥታ ልባዊ ጩሀትዋ ያለችውን ሰማት፡፡ ታላቁ ነቢይ ሳሙኤልንም ወለደች!