ወሳኝነት አባት የሆነው እግዚአብሄር ለፈጠራቸው የሰው ልጆች ያስተማረው ስልጣን ነው፡፡ ውሳኔ ከትእዛዝ ሰጪ አካል ይወጣል፣ ስልጣን በውሳኔ ተግባራዊነት ይገለጣል፣ እንዲሁም የእግዚአብሄር ውሳኔ ፍጹምና ሊታዘዙት የተገባ ሲሆን የእኛ ግን የሚዋዥቅና አቅም የሌለው ነው (በተለያዩ ምክኒያት ሰው ውሳኔውን ይለዋውጣል)፡፡ ለምሳሌ በዘጸ.9:5-7 ውስጥ ስለእግዚአብሄር ወሳኝነት ሲናገር፡-
”እግዚአብሔርም፡- ነገ እግዚአብሔር ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል ብሎ ጊዜን ወሰነ። እግዚአብሔርም ያንን ነገር በነጋው አደረገ፥ የግብፅም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም። ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።” ይላል፡፡
የእግዚአብሄር ውሳኔ ምንኛ ፍጹምና ቁርጥ ያለ እንደሆነ ስንመለከት ምንም ነገር ተቁዋቁሞ ሊያስቆመው እንደማይችል እናስተውላለን፡፡ እግዚአብሄር በጎን ለማድረግ እንደሚወስን ሁሉ በክፉዎች ላይ ፍርድን ሊያመጣ ደግሞ ይወስናል፡፡
እግዚአብሄር ሰው በፍጥረታት ላይ ወሳኝ ባለስልጣን ይሆን ዘንድ በፈጠረው ላይ ሾሞት ነበር፤ ያን የሚያህል ሀያል ስልጣን በሰይጣን የሽንገላ ቴክኒክ ተነጠቀና ባዶውን ቀረ እንጂ፡፡
እያንዳንዳችን አሁን በዙሪያችን ያለን ወሳኝነት የሁኔታዎች መገጣጠም፣ ግፋ ቢል በመጠበብ ውጤት የመጣ ወይም አንዳችን ከሌላችን በተሻለ አጋጣሚ በተቸረን ምድራዊ ስልጣን ያገኘነው ቢሆን እንጂ ቀድሞ የነበረን ግን በመጀመሪያው አባታችን አዳም ስህተት ምክኒያት ያጣነው መለኮታዊ ሹመት አሁን በእኛ ስለሚኖር አይደለም፡፡
ስለዚህ በትውልድ መሀል እግዚአብሄር ሰውን ጠርቶ በርሱ ላይ ሀላፊነትን ቢያስቀምጥ ከሰውየው ችሎታው ይልቅ እግዚአብሄር በራሱ አሰራር መለወጥና ማብቃት እንደሚችል ስለሚያውቅ ነው፡፡ ማንም ሰው ወደ እግዚአብሄር ቀርቦ ከእግዚአብሄር አሳብ ይልቅ የተሸለ ነገር መስራት አይችልም፣ የተሸለ ስልጣንም አይኖረውም፤ እንዲያውም ከእርሱ የተሰጠውን ሀላፊነት በብቃት መፈጸም አይችልም፡፡ ይሄ በመጀመሪያው አባታችን በአዳም ተሞክሮ የከሸፈ ቀጣይ አባቶችም ያለ እግዚአብሄር እርዳታ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደማይችሉ የታየበት ሁኔታ ነው፡፡
የሚሾምና የሚሽር ጌታ ሰውን ሊያከብር፣ ከፍ ሊያደርግና በቤቱ ላይ ሊሾም የሚጠራው በቤቱና በህዝቡ ላይ ቅን አስተዳደር ተሰጥቶ ትጋት፣ ቅንነትና የጽድቅ ፍርድ በሁሉ ዘንድ እንዲሰፍን ነው፡፡
ኢሳ.22:15-19 ”የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በቤቱ ውስጥ ወደ ተሾመው ወደዚህ አዛዥ ወደ ሳምናስ ሂድ እንዲህም በለው፡-መቃብር በዚህ ያስወቀርህ ከፍ ባለው ስፍራ መቃብር ያሰራህ በድንጋይም ውስጥ ለራስህ መኖርያ ያሳነጽህ በዚህ ምን አለህ? በዚህስ በአንተ ዘንድ ማን አለ? እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይል ወርውሮ ይጥልሃል፥ አጠንክሮም ይጨብጥሃል። ጠቅልሎም ያንከባልልሃል ወደ ሰፊይቱም ምድር እንደ ኳስ ይጥልሃል፤ አንተ የጌታህ ቤት እፍረት! በዚያ ትሞታለህ በዚያም የክብርህ ሰረገላዎች ይሆናሉ። ከአዛዥነት ሥራህ አሳድድሃለሁ፥ ከሹመትህም ትሻራለህ።”
ይህ ቃል እግዚአብሄር ታማኝ አገልጋይ እንደሚፈልግ ያሳያል፡፡ የታመኑትን ሰዎች የሚያስጠጋ አምላክ ያልታመኑትን ከቤቱ በእፍረት እንዴት እንደሚያባርራቸው እንመለከታለን፡፡
ሀላፊነት፣ ስልጣን፣ ትእዛዝና ውሳኔን የመሳሰሉ ተግባራትን ለመመልከት አንዳንዶቹን አቅርቦ መመርመር ጠቃሚ ነው፡-
መወሰንና ውሳኔ
መወሰን በእግዚአብሄር ነገር ላይ ሲሆን የውሳኔው ውጤት ወሳኙን ሰው ራሱ የሚሰራውና የሚለውጠው ነው የሚሆነው፡፡ በበጎ ለወሰነ የበጎነቱ ፍሬ በውሳኔው ውስጥ እንደሚመጣ ሁሉ እንደ እስራኤል አዘዦች በእግዚአብሄር ፈቃድ ያልሆነና ክብር የሌለበት ተግባር ውስጥ ያለው እርሱ መራር ፍሬ እንደሚያፈራ ከላይ ያለው ቃል አሳይቶናል፡፡
– ለራስ ፈቃድ ከመገዛት ይልቅ ወደ እግዚአብሄር መቅረብ
ይህ ውሳኔ በራስ ላይ የሚደረግ ውሳኔ አካል ነው፡፡ ፈቃዳችንን ወደ ሁዋላ የእግዚአብሄር ግን ወደፊት ስናመጣ ከእርሱ ፈቃድ ጋር አብሮ የሚቀድም የእግዚአብሄር ነገር ሁሉ ይመጣል፡፡ ይህን የእግዚአብሄር አሰራር ማስተዋል ሲኖረው ብዙ ትርፍ እንደሚያስገኝ ቀጥሎ እንይ፡-
”ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።” (ማቴ.10:37-39)
በዚህ ጥቅስ መሰረት የእግዚአብሄር ፈቃድ ከእኛ ፈቃድ እንዲልቅና እንዲቀድም ተጠይቀናል፡፡ የእኛ ፈቃድ አባትን፣ አናትን፣ ወንድምና እህትን እንዲሁም ልጆችንና ባለቤትን ከሌላው ይልቅ ማስቀደም ይመርጣል፡፡ ፈቃዳችን የኛ ካልነው ፊት ማንም እንዲቆም አይሻም፡፡ ሆኖም እግዚአብሄርን አይተን ይህን ፈቃዳችን ስንሽርና የሚሰማንን ብርቱ የስነልቦና ህመም ቻል አድርገን እርሱንና ፈቃዱን ለማስቀደም ስንወስን ከርሱ ዘንድ የነፍሳችን ዘላለማዊ ደህንነት እንደሚመጣ ጌታ ገልጦ ይናገራል፡፡
እርሱ በሉቃ.9:23 ለሁሉም እንዲህ አላቸው፡- በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ።
በኋላው ሊመጣ የሚወድ ይወስን፡- ዘላለሙን አስቦ ይወስን፣ አምላኩን በምድር ላይ አስከብሮ ማለፍ ክብር እንደሆነ አስተውሎ ይወስን፣ ክርስቶስ መከራን የተቀበለው ለፍጥረት ሁሉ መሆኑን አስተውሎ ያን በአለም ለማወጅ ይወስን፣ የራሱን ፈቃድ ይካድ የርሱንም ፈቃድ ያስቀድም፡፡
– እግዚአብሄርን የማምልክ ዋጋ ተመልክቶ በፍጹም ልብ መቅረብ
እግዚአብሄርን ማምልክ፣ መጠጋትና ማወቅ ምን ዋጋ አለው? እርሱ ቀርበው በቤቱ ለሚያመልኩት ከበረከቱ አትረፍርፎ ይመግባል፡፡ ቤተመቅደሱ አካባቢ የሚያገለግሉ እስራኤላውን ሌላ ስራ አልነበራቸውም፣ ግን ምን እንበላለን እንጠጣለንስ ብለው አይጨነቁም ነበር፤ ምክኒያቱም በቤቱ የሚገለገል አምላክ ሀላፊነት ወስዶ አሰማርቶአቸዋልና፡-
በዘኊ.18:31 ውስጥ ሲናገር ”እናንተም ቤተ ሰቦቻችሁም፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የማገልገላችሁ ዋጋ ነውና በሁሉ ስፍራ ትበሉታላችሁ።” ሲል ሌዋውያንን አሳስቦአል፡፡ ለእግዚአብሄር የቀረበው መስዋእት በእስራኤል ዘንድ እንደ እርኩስ የማይነካ ቢሆንም ለቅርቦቹ አገልጋዮች በረከት ሆኖ የየእለት ምግብ ነበር፡፡
– ከከንቱ የህይወት መንገድ ለመመለስ
ለመመለስ መወሰን ሁልጊዜ ከራስ አካሄድ ወደ እግዚአብሄር ፈቃድ መመለስን የሚጠይቅ እንደመሆኑ ውሳኔውን አንድ አማኝ ያለመታከት ደግሞ ደጋግሞ ሊተገበር መፍቀድ እንዳለበት አመልካች ነው፡፡ ሰው በራሱ ዋስትና ሳይሆን በእግዚአብሄር ትምክህት ዘላቂና አስተማማኝ ህይወት እንደሚመራ እስከተገነዘበ ድረስ ይህን የህይወቱ መመሪያ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ያ የውሳኔ እርምጃ የራስን አካሄድ ባጤነ መልኩ ሲሆንና መንገዱን በማወቅ ሲከናወን የእግዚአብሄር አብሮነት ይኖራል ማለት ነው፡፡
ሐዋ.24:25 ”… እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኵነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ፡- አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ብሎ መለሰለት።”
አንድ ንጉስ ራስን የመግዛት ውሳኔ ላይ ለመድረስ እንዴት እንዳዳገተው ከላይ ባለው ታሪክ ውስጥ ይታያል፡፡ ንጉሱ ስለ ኢየሱስ የማዳን ስራ ሲሰማ ደስ እያለው ነበር፤ ሰባኪው ሃዋርያ ወደ እርሱ መለስ ብሎ ሊወስነው ስለሚገባው ነገር ሲነግረው አቅማማ፣ ከሰማው የጽድቅ ውሳኔ ለማምለጥ ሲልም በዘዴ ከሰባኪው ሊርቅ ሲሞክር ይታያል፡፡ ቃሉ ግን ቸል በማለት ሳይሆን በጽናት ጽድቅን ቀን በቀን በመጨመር ማደግን ያበረታታል፡፡ በ2ጴጥ.1:6-7 ውስጥ፡-
”በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።” ሲል ያበረታታናል፡፡
– ህይወታችንን በቃሉ እንዲቃኝ መፍቀድ
በቃሉ ተጠርተን፣ በቃሉ ተፈውሰን፣ በቃሉ ድነን ለርሱ ልንሆን ስለበቃን ቀጥሎ በቃሉ እየተመላለስን ለመኖር እንድንችል ከተፈለገ እንደነገረን ለመሆን ከመቁረጥና ራስን ለህያው ቃሉ አሳልፎ ከመስጠት ሌላ የተሸለ አማራጭ የለም፡፡ ውሳኔው ተግባራዊ ሲሆን መንፈሳችን ቃሉን ይወዳል፣ ልባችን ቃሉን ያሰላስላል፣ ነፍሳችን ለቃሉ ትገዛለች፣ ሁለንተናችን በቃሉ ፍርሀት ይጠበቃል፡፡
1ጴጥ.2:7-8 ”እንግዲህ ክብሩ ለእናንተ ለምታምኑት ነው፤ ለማያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የዕንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ፤የማያምኑ ስለ ሆኑ በቃሉ ይሰናከሉበታልና፤ ለዚህ ደግሞ የተመደቡ ናቸው።”
በቃሉ የተሰናከሉ መደብ ውስጥ እግዚአብሄር ጎትቶ ነው ወይ ያስገባን? ወይስ አለማመናችን ከሚሰናከሉ መሀል አስገባን? የዚህ መልስ ይበልጥ የሚበራልን ለራሳችን መወገን ስንተውና ወደ ስሜታችን ሳናደላ በቃሉም ለመወቀስ ስንፈቅድ ነው፡፡
– እንዳቀደው ለመከተል፣ እንደፈቀደው ለመገኘት
እግዚአብሄር የሚሰራው ከዘላለም ያቀደውን ስራ ስለሆነ እርሱ ድንገተኛ አምላክ እንደሆነ አድርገንና ከነገሮች መከሰት ሁዋላ መፍትሄ ሊሻ የሚመጣ አድርገን ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ ያቀደውን በጊዜው የሚፈጽም ከሆነ አሰራሩን ብቻ ተከትለን በእምነት ልባችንን በእርሱ ላይ ልናሳርፍ ተገቢ ነው፡፡
በጥጋብ ወራት በደስታ ስንባርከውና ስናመልከው ቆይተን ወደ ሸለቆ የሚያስገባ ሁኔታ ሲፈጠር ምነው ስንጠፋ ግድ አይልህም? እያልን ማጉረምረም በእምነታችን የዛልን ምስጋናችን ከጥቅማችን ጋር የሚነፍስ በእርሱ ስራ ላይ ተደግፈን መጽናት ያቃተንም መሆኑን አመልካች ነው፡፡
በእምነታችን የዛልን ከሆንን በእምነት ከእግዚአብሄር የምንቀበለው ነገር አይኖረንም፤ የምናመሰግነው ጥቅማችን ሲከበር ከሆነ የሚነፍስ ነገር ሁሉ ያወዛውዘናል፤ በአጠቃላይ በእርሱ ስራ ላይ ተደግፈን መጽናት ካቃተን ህይወታችን በእምነት መጽናት ያቃተው ስለሆነ ነው ማለት ነው፡፡
ህያው አምላክ ግን ሁኔታችንን ያለፈ የእርሱ ፍቅር በማይለወጥበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሳለ፣ ከእርሱም ጋር ከሆንን የምናልፍበት የገጠመኝ ውጣ ውረድ የሚያጸናን ሆኖም እያለ ያንን በማስተዋል ፈንታ ድንግርግር ብሎን በመናወጣችን ምክኒያት የተፈጠረው ያለማመን ውሳኔያችንን ሊያስቀይረው ባልተገባ ነበር፡፡ ቃሉ በሮሜ.8:39 ሲናገር፡-
”ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” ይላል፡፡
ከፍታም ቢሆን ከፍታው በእኛ ዙርያ ላለ ነገራችን ብቻ ነው፣ ዝቅታም ቢሆን ዝቅ ያለው ለእኛ እንጂ ለእግዚአብሄር አይደለም፡፡ ግን የርሱ ፍቅር የእኛን ሁኔታ አልፎ ይሰራል ያጸናናልም፡፡
– ለመቀደስ መወሰን
ለመቀደስ የምንወስነው ለእርሱ እንደተቀደስን ለመኖር፣ በእርሱ ወደ ሙላት እያደግን ለመሄድና እግዚአብሄር ባኖረን ስፍራ ለመጽናት ነው፡፡ በጽድቅ ህይወት ማደግ በራሱ ሂደት ሲኖረው ሂደቱ ቀጣይነት ያለው በውሳኔና በጽናት ነው፤ ታዲያ እግዚአብሄርን በእኛ ሁኔታ ውስጥ እንዴት እናስገባ? ዘወትር/አረፍ ሳይባል ትጋት በተሞላ ህይወት ውስጥ ለእግዚአብሄር ጸጋ ቅድሚያ ሰጥቶ፣ አክብሮና ትሁት ሆኖ በመገኘት ነው፡፡
1ጢሞ.4:14-15”…ከሽማግሌዎች እጅ መጫን ጋር የተሰጠህን፥ በአንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል። ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፥ ይህንም አዘውትር።”
ለመቀደስ መወሰን እግዚአብሄርን የመውደድ መንገድ ነው፤ ያለቅድስና እግዚአብሄርን ማየት ካልተቻለ ሌላ አማራጭስ ከየት ይገኛል? ተአምራቱ ደግሞ ጸጋ የሚሰጥ አምላክ የሚያግዝ መሆኑ ነው፡፡
– ለእግዚአብሄር መሰጠት
ለእግዚአብሄር መሰጠት የራስ ፈቃድን ለእግዚአብሄር መተውና በርሱ ፈቃድ መወሰን ይጠይቃል፤ ያን ያስተዋለ የእግዚአብሄር አገልጋይ ንጉስ ዳዊት እረፍት ለሰጣቸው አምላክ ራሳቸውን እንዲሰጡ ይጠይቃል፡-
”አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈልጉ ዘንድ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ስጡ፤ ለእግዚአብሔርም ስም ወደሚሠራው ቤት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ታመጡ ዘንድ ተነሥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።” (1ዜና.22:19)
የዳዊት ልጅ ንጉስ ሕዝቂያስ እንደ አባቱ ያመለከውን አምላክ ህዝቡ ይከተሉ ዘንድ ጥሪ ለነርሱ ያስተላልፋል፡-
2ዜና.30:8 ”አባቶቻችሁም እንደ ነበሩ አንገተ ደንዳና አትሁኑ፤ እጃችሁንም ለእግዚአብሔር ስጡ፥ ለዘላለም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱም ግቡ፥ ጽኑ ቍጣውም ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ።”
– እንደፈቃዱ መኖር
እኛ እንዳሰብነው ሳይሆን እሱ እንዳለው ለመኖር፣ እኛ ለራሳችን እንዳወጣነው እቅድ ሳይሆን እርሱ እንደተናገረው ለመኖር ፈቃዳችንን መተውና የእርሱ ባሪያ መሆን የግድ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ሰውን ሊገዛ፣ አሳቡንና ፈቃዱን ሊጭንበት አንዲሁም ባርያ ሊያደርግ ከርሱ ስልጣን በታች ያደርገዋል፤ አግዚአብሄር ግን ሰውን የሚገዛው (ገዢ ቃሉንም ለማህበሩ የሚሰጠው) ስለእያንዳንዱ ህይወት ሃላፊ ሊሆን በሚያስፈልገው ሊረዳውና እንደ አባት ሊንከባከበው ነው፡-
”እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”(1ጴጥ.5:6-7)
አባት ብለን እግዚአብሄርን ከጠራን በሙሉ ልብ በእርሱ ላይ መደገፍ ራስን ለእርሱ አሳልፎ መስጠት ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የመናፍስትን አገዛዝ እንመልከት፡- አጋንንት ሰውን እያሰቃዩ ይገዛሉ፣ በማስመረርና በማስለቀስ ይገዛሉ፣ በመቀሰፍ ይገዛሉ፣ በደዌና በቁስል አየመቱ የገዙት ሰው ቀና እንዳይል አጉብጠው በመራራ ቀንበር ስር ያኖራሉ፡፡ ዛሬ ለማን ፈቃድን መስጠት ይሻላል? ውሳኔው የእኛ ነው፡፡
ያዕ.4:7-10 ”እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ።በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።”