የውሳኔና ስምምነት አግባብ (3…)

የእግዚአብሄር ፈቃድ

ወስኖና ተስማምቶ መኖር
ንጉስ ዳዊት ስለ እግዚአብሄር ማንነት ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ስነለነበር ከእርሱ ጋር ተስማምቶ ለመኖር (ሲሳሳት እንኩዋን ፈጥኖ በይቅርታ ለመስማማት) የማያቅማማ ሰው ነበር፡፡ ይህ ፍላጎቱም የተሳካለት ሰው ነበር፡፡ በመዝ.130:3-8 ውስጥ ሲናገር፡-
”አቤቱ፥ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፥ አቤቱ፥ ማን ይቆማል? ይቅርታ ከአንተ ዘንድ ነውና። አቤቱ፥ ስለ ስምህ ተስፋ አደረግሁህ፤ ነፍሴ በሕግህ ታገሠች። ከማለዳው ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ነፍሴ በእግዚአብሔር ታመነች። ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን ነውና እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን። እርሱም እስራኤልን ከኃጢአቱ ሁሉ ያድነዋል።” ይላል፡፡
ንጉሱ ዳዊት ወስኖ ሌላው እንዲወስን ሲጋብዝ በእግዚአብሄር ታመን፣ ማዳኑ ብዙ ስለሆነ፣ ከሀጢያትም ስለሚያድን ይላል፡፡
ስለዚህ ከጥፋትም ሆነ ከስህተት መዳኛው መንገድ ውሳኔ ነው ማለት ነው፡- ውሳኔ በራስ ላይ (ለበጎ ስራ)፣ ውሳኔ በነገሮቻችን ላይ፣ ውሳኔ በግንኙነታችን ላይ፡፡ በራስ ላይ ስንወስን በተለይ በእግዚአብሄር ቃል ላይ መስማማት ለማኖር ይሁን፡- ራስን ለእግዚአብሄር አሳልፎ ለመስጠት፣ ለራስ ቃል በመግባትና ቃሉን ያለምንም ማቅማማት ለመቀበልም ጭምር፡፡
የራስን ለመተውና የእግዚአብሄርን ለማንሳት ወይ የራስን ባህሪ ለማክሰም፣ ወይ ደግሞ የእርሱን ብቻ ለማሰራጨት፡- የእግዚአብሄርን ነገር በሙሉ እንደ አላማ ከፍ አድርጎ መያዝና እርሱን እያዩ መጉዋዝ ተገቢ ነው፡፡ የሃዋርያው ጳውሎስን ጠንካራ ውሳኔ ጭብጥ እንመልከት፡-
1ቆሮ.2:1-4 ”እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና። እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።”
ይህ ተገቢ የእግዚአብሄር አገልጋይ ውሳኔ ነው፤ ለእኛም ምሳሌ የሚሆን ማለት ነውና፡፡ ወንድሞችን ሲያሳስብ አመጣጤ በውሳኔ ነው ይላል፤ ውሳኔው የግል ንግግርን ወይም አመለካከትን የመግልጥ ፍላጎት ያለው ግን አልነበረም፡፡ የሰው ጥበብን በሚያሳይ የፍልስፍና ንግግር ለማውራት አልመጣምና (ሌሎች እንደሚያደርጉት ያለ ኣካሄድ የተከተለ ስላልነበረ)፡፡ የእግዚአብሔር ምስክርቱ በስጋ እውቀት የተቀባ እንዳልሆነም ለማመልከት እንዲዚያ አለ፡፡
ዋናው ውሳኔ ምን ላይ ያተኮረ ነበር? ካዳነንና በቅዱስ አጠራረ ከጠራን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም ሀጢያታችንን በደሙ ሊያጥብ፣ ጥልን በመስቀል ይገድል ዘንድ ለእኛ እንደተሰቀለ እንጂ የእኛን ነጻነት ካበሰረ ጌታ ውጪ ያለን ነገር ላይ እንዳላውቅ ቆርጬ ነበር አለ። የሃዋርያው ውሳኔ ለምንና እንዴት እንዲህ የጨከነ ሆነ ስንል እምነታችን በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን ስለሚያስፈልግ፣ የእርሱ ቃልም ሆነ ስብከት መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ እንጂ፥ በሚያባብል ሰዋዊ ንግግር ወይም ፍልስፍናን በሚገልጥ በጥበብ ቃል ሊሆን እንዳላስፈለገ ስለወሰነ ነበር።
-የተወሰነን ማስፈጸም
የእግዚአብሄር ህዝብ እግዚአብሄር ለርሱ የወሰነውን ምህረትና በረከት መቀበል እንዲችል ዝግጅት ሊያደርግ ይገባዋል፤ ይህን አስተውሎ በመንፈስም በነፍስም መዘጋጀት እንዲችል ከቃሉ ጋር መገናኘትና መተዋወቅ፣ ከቃሉ ምሪትም ሁዋላ በመከተል ውሳኔን በትክክል ማስፈጸም ይገባዋል፡፡
ነህ.10:34 ”እኛም፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ ሕዝቡም፥ እንደ አባቶቻችን ቤቶች በተወሰነ ጊዜ በየዓመቱ ወደ አምላካችን ቤት አምጥተን በሕጉ እንደ ተጻፈ በአምላካችን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይቃጠል ዘንድ ስለ እንጨት ቍርባን ዕጣ ተጣጣልን”
የነህሚያ ታሪክ ከእስራኤላውያን የስደት መልስ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው፤ እስራኤላውያን ወደ ባእድ አገር ተሰድደው ከኖሩበት ስፍራ የመመለሻቸው ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሄር ነህሚያን ቀሰቀሰው፡፡ የነህሚያ ህይወት ለጉዞው እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት ከእግዚአብሄር ዘንድ ሞገስን ተቀብሎ እርሱም ህዝቡን ይዞ መንቀሳቀስ ቻለ፡፡ ያም ሆኖ ግን የህዝቡ ልብ ወደ እግዚአብሄር መቅረብ እንዲችል ዝግጅት ያስፈልግ ነበር፡፡ በዝግጅቱ ውስጥ ከተከናወኑት ተግባራት መሃከል ካህናቱና ሌዋውያኑ ሕዝቡም በሙሴ ህግ እንደተሰጠው ትእዛዝ ተዘጋጅተው ቁርባኑን እንዲያቀርቡ ማድረግ ነበር፡፡
-የተወሰነን ጭንቅ ጊዜ በጥበብ ማሳለፍ
እግዚአብሄር ለእኛ የሚስባት አሳብ በረከት፣ ህይወትና ምህረት ያለባት እንደሆነች ከልባችን ካመንን አንዳንዴ ወደ ህይወታችን የሚያመጣው ከባድ የሆነብን ፈተና እንዴት ነው ከእምነት የሚያንሸራትተን? ተስፋስ የሚያስቆርጠን? ሰው እንደመሆናችን የሚገጥመን ይህ ፈተና ያስጨንቀናል፣ ስቃዩ ተስፋ ያስቆርጠናል፣ መኖር የሚባል ቀጥሎ ያለ የማይመስለን ደረጃ ላይ ያደርሰናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ተወን ብለን እናለቅሳለን፣ እንተክዛለን፡፡ ሆኖም የመከራችን ጊዜ ረዝሞ ሁሉን ነገራችንን ከእምነታችን ላይ ባራገፍን በዚያች የመጨረሻችን ባልንባት ወቅት ምህረቱ እንደ ወገግታ ይገለጣል፣ እኛም በዚያ ሀሴት እናደርጋለን፣ ወዲያው መከራ ተሸንፎ በደስታ እንዋጣለን፡፡ ሁሉም አልፎ ልባችን በሰከነና ማስተዋል በሆነልን ጊዜ ያኔ የእግዚአብሄርን አሰራር ማስተዋልና ልብ ማለት ይገባናል፤ እግዚአብሄር ለምን ያሰበውን ወሰነና አደረገብን? ከሆነው ነገር በሁዋላ በህይወታችን የተፈጠረው ለውጥ የቱ አሳድጎናል? ይሄንንና ሌሎች ከመንፈሳዊ ህይወታችን ጋር የተያያዙትን የእግዚአብሄር ፈቃዶች በማስተዋል ምስጋና ከእኛ ይጠበቃል፡-
ኢዮ.7:2-5 ”አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥ ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥ የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ። በተኛሁ ጊዜ፡- መቼ እነሣለሁ? እላለሁ። ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥ እስኪነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ። ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፤ ቁርበቴ ያፈከፍካል እንደ ገናም ይመግላል።”
እግዚአብሄር በኢዮብ ህይወት ሊገልጥ የፈለገውን ትምህርት በጨረሰ ጊዜ ያጣውን ነገር ሁሉ እጥፍ አድርጎ መልሶለታል፤ ተወሰነችልኝ ያላት ያች የድካም ሌሊት ስላለፈች ሞገስና ብርሀን በህይወቱ ወጣና የደስታ ዘመን ከአምላኩ ጋር ሆነለት፡፡ መከራው ባለፈ ጊዜ እንዲህ አለ፡-
ኢዮ.42:1-6 ”ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፡- ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ።ያለ እውቀት ምክርን የሚሰውር ማን ነው? ስለዚህ እኔ የማላስተውለውን፥ የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ።እባክህ፥ ስማኝ እኔም ልናገር፤ እጠይቅህማለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፤ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ።”
-በእግዚአብሄር ውሳኔ ላይ ምንም ማድረግ አይቻልም
አንዳንዴ በመንፈሳዊ እውቀት እጥረት ምክኒያት እንስታለን፣ እንስትናም እኛ መወሰን ካለብን ገደብ አልፈን ወጥተን በእግዚአብሄር ስልጣን መከናወን በሚገባው ነገር ላይ እናርፋለን፣ ታዲያ ይህ ጥፋት አይሆንም? የምንወስነው እስከምን ድረስ እንደሆነ ማሳሰቢያውን ሳንገነዘብ ወደ ሁሉ ባለቤት እግዚአብሄር ስንዞር የእረሱን ውሳኔ በራሳችን ልንፈጽመው እንደፍራለን፤ እውቀት በማጣት ወይም የእርሱን ማንነትና ችሎታ ባለማወቅ የሚመጣ ስህተት በፈንታው የተሳሳተ ውሳኔ ላይ ይጥላልና፡፡
ኢዮ.14:5 ”የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው የወሩም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፥ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት።”
የኢዮብን ማስተዋል ተመልክተን እንደሆነ ማስተዋሉ በሰዎች ልጆች የዘወትር ጥያቄ ላይ ያተኮረ እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ የሰው ልጆች ነገን ማወቅ ይጉዋጉዋሉ፣ የነጋቸውን ነገር ሊገምቱ ይሻሉ፣ በምድር ለመኖር የሚቀራቸው ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ያውቁ ዘንድ ይጉዋጉዋሉ፡፡ ግን ያ የሰጪው እውቀት ጉዳይ ነው፣ በእርሱ ውሳኔ ላይ የተመሰረተም ነው፡፡ እርሱ ከወሰነው ወደ ግራም ወደ ቀኝም ፍንክች ማለት አይቻልም፡፡ኢዮብ ስለዚህ እንዲህ አለ፡-
”በእኔ ላይ የተወሰነውን ይፈጽማል፤ እንደዚህም ያለ ብዙ ነገር በእርሱ ዘንድ አለ።” (ኢዮ.23:14) የኢዮብ እውቀት ጥቅሙ ብዙ ነው፤ ከነዚያም ውስጥ ዋነኛው የራስን መንገድ ለማወቅ፣ ሰዋዊ ልክን ለመረዳት(የሰው ልጅ ማድረግ ያለበት ነገር ምን ምን መሆኑን ለማስተዋል) የሚያግዝ ነው፡፡
-እግዚአብሄር የወሰነውን በረከት ይሰጣል
በቤቱ የሚኖሩ፣ ከፊቱ ያልጠፉና ምህረቱ ያጠራቸው ልጆቹ ከእርሱ ዘንድ የሆነ በረከት ያገኛቸዋል፤ አስቀድሞ ጽድቁ ሌላው ጽድቅ አጃቢ ሆኖ ኑሮን ሊሞላ የተፈቀደ ነው፡፡ የእግዚአብሄር በረከት የምድሩም ሰማዩም ሰስለሆነ ህይወትን ኑሮንም የሚባርክ ነው፡-
መዝ.84:4-7 ”በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፤ ለዓለምና ለዘላለምም ያመሰግኑሃል። አቤቱ፥ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት፥ በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው። በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና። ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል።”
ዋናው ነገር እግዚአብሄር አደርገዋለው ካለው ስፍራ አንጥፋ እንጂ እንደተናገረው ሆኖ እናገኛለን፡፡
-ለፍጻሜ የተወሰነው ይሆናል
በእግዚአብሄር የተወሰነው ቅጣት መምጣቱ፣ መገለጡና መፈጸሙ የግድ ነው፣ የተናገረው እግዚአብሄር ስለሆነ፡-
ዳን.8:19 ”እንዲህም አለኝ፡- እነሆ፥ በመቅሠፍቱ በመጨረሻ ዘመን የሚሆነውን አስታውቅሃለሁ፤ ይህ ለተወሰነው ለፍጻሜ ዘመን ነውና።”
የእግዚአብሄር ቁጣ በስፍራ የተወሰነ ብቻ ሳይሆን በተቆረጠለት ሰአትም የሚሆን ነው፤ ችግሩ ግን ጥፋቱ አስቀድሞ እየተነገረ ሳለም የሰው ልጆች ፍርሀት ያለው ልብ ማጣታችን ነው፡-
ዳን.11:29 ”በተወሰነውም ጊዜ ይመለሳል ወደ ደቡብም ይመጣል፤ ነገር ግን ኋለኛው እንደ ፊተኛው አይሆንም።”
ዳን.11:35 ”እስከ ተወሰነውም ዘመን ይሆናልና ከጥበበኞቹ አያሌዎቹ እስከ ፍጻሜ ዘመን ይነጥሩና ይጠሩ ይነጡም ዘንድ ይወድቃሉ።”
-ለሰው ልጆች የወሰነው ሰማያዊ ነገር
የእግዚአብሄር ውሳኔ በቀደመ- እውቀቱ ምክኒያት የሚሆንና የሚገለጥ ነው፤ አንዳች በፊቱ የማይሰወር አምላክ ሁሉን ያያል፣ ምንም ነገር የማይታጣው አምላክ ሁሉን ያውቃል፤ የሚያይ የሚያውቅ አምላክ ሁሉን ማድረግ ይችላል፤ የወደፊቱን የሚያይና የሚያውቅ ትላንትንም ዛሬንም በዚያው ቅጽበት አይቶአል አውቆአል፡፡ እግዚአብሄር የሚወስናቸው ነገሮች አንዳንዴ ግራ የሚያጋቡን የእርሱን ጥልቅ እውቀት በሰው አእምሮ ሆነን ስለማንረዳ በመሆኑ በእርሱ የሆኑት ሁሉ ግራ ያጋቡናል፤ ለምሳሌ ከቃሉ ባስተዋልነው መሰረት ክርስቶስን የከዳው ደቀመዝሙር እርሱን ለጠላቶቹ አሳልፎ እንደሰጠው አይተናል፡፡ በዚያን ወቅት የሆነውን ብቻ ተመልክተን የይሁዳን አሳልፎ መስጠትና በእርሱ ምክኒያት ተሰቅሎ መሞቱን እንናገራለን እንጂ የጌታ በዚያ መከራ ውስጥ ማለፍ አለም ሳይፈጠር በፊት ዲዛይን ተደርጎ ያለቀ ክስተት ነበር በሐዋ.2:23 ላይ ያንን እውነት ያሳያል፡-
” እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።”
እግዚአብሄር አስቀድሞ ማየት፣ መስማትና ማወቅ በሚችል ችሎታው ህዝቤ ብሎት ወደ እርሱ በመጣው አይሁድ ተክዶና በዓመፀኞች እጅ እንዲሰቅሉት ሆኖ ተገደለ። የእርሱ ውሳኔ ከምንም በላይ ለእኛ ሰዎች ደህንነት ሆነልን፣ መትረፊያ ሆነን፡፡ ይህንን የተረዱት የእርሱ ደቀመዝሙርት የሆኑት ሃዋርያት በሐዋ.10:42-43 እንዲህ ብለዋል፡-
”ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን። በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።”
-ለህይወትና ለፍርድ የተወሰነው
ጌታ ኢየሱስ መከራና ፍርድን ስለእኛ ተቀብሎ ሁሉን በዚያ አልዘጋም፤ ይልቅ የእርሱ መከራና ሞት ትንሳኤውም ለፍጥረት ሁሉ እንዲሰበክና የሰው ልጅ በእርሱ መስዋእት ተጠቅሞ የዘላለምን ህይወት እንዲቀበል ፈቀደ፡፡ እግዚአብሄር የሚወደው ልጁ የሰውን የሞት ጽዋ (ለሰው ልጆች የተገባን ፍርድ) እንዲቀበል ከጨከነ፣ ይህንን ውሳኔ ደግሞ የሰው ልጅ ይቀበለው ዘንድ ለህዝብ ሁሉ ይሰበክ ሲል ወሰነ፡-
ሐዋ.10:42-43 ”ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን። በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።”
1ቆሮ.2:7 ”ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።”
-እግዚአብሄር ስልጣንን ሰጠ
የወሰነውን ለደቀመዛሙርት ከሰጠ በሁዋላ በህዛብ ሁሉ መሀል እንዲያውጁት ደግሞ ወሰነ፤ ነገር ግን ወንጌሉ የራሱ እውቀት እንጂ የሰው አይደለምና ጉልበትና ችሎታውን እንደያዘ በሰዎች መሀል እንዲገለጥ ለሰዎች የሚሰጥ አንድ ብርቱ ስልጣን ያስፈልግ ነበር፤ ያለ እርሱ ስልጣን ወንጌል የሰዎች ትረካ ይሆን ነበር፣ ግሪካውያን እንዳሰቡትም አዲስ የሰዎች የጥበብ ቃል ብቻ ይሆንና ያረጅ ነበር፡፡ ወንጌል ግን ሀይል አለው፡- ኢየሱስ ስለሚሰበክበት፣ ስሙ ስለሚጠራበት፣ መንፈስ ቅዱስ ስለሚወርድበት፣ የኢየሱስ ደም ስለሚሰራበት! ሀጢያትም ስለሚነጻበት፣ ሰው ዳግም ስለሚወለድበት፣ የአጋንንትም ቀንበር ስለሚሰበርበት…. ስለዚህ፡-
”አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው።” (ማቴ.10:1)
ሰዎችን በወንጌል ሊያድን የወሰነ አምላክ ከዘላላም እስከ ሰዘላለም ይባረክ!