ከእግዚአብሄር ጋር መስማማት
ቃሉ ተስማምተን ከእግዚአብሄር ጋር ስንኖር የሚሆነውን ሁኔታ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፡-
”የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትጠብቅ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል። የምድር አሕዛብም ሁሉ የእግዚአብሔር ስም በአንተ ላይ እንደ ተጠራ አይተው ይፈሩሃል። እግዚአብሔርም እርስዋን ይሰጥህ ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው በምድርህ ላይ፥ በሆድህ ፍሬ፥ በከብትህ ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ እግዚአብሔር በጎነቱን በላይህ ያበዛል።” (ዘዳ.28:9-11)፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር ለመስማማት የሚወስን ማንም ቢኖር መስማማትን በተግባራዊ መልስ ሊያሳይ እንጂ በአንደበት ንግግር ብቻ ሊያሳወቅ መልፋት የለበትም፡፡ በእርግጥ ከእግዚአብሄር ጋር መስማማት የራስን ፈቃድ መተው ይጠይቃል፡፡ ለሁላችንም ቢሆን መስማማት የሚለው የህይወት መርህ አጠቃላይ የህይወታችን ውሳኔ እንጂ የተወሰነ እኛነታችንን ብቻ የምናቀርበው እንዳይደለ ማወቅ ይገባናል፡፡ መስማማት ከእግዚአብሄር ጋር በመታዘዝ መስማማትን፣ በመገዛት መስማማትን፣ በመላክ መስማማትን፣ በማገልገል መስማማትን ያጠቃልላል፡- ይህም በተባረከው የአገልግሎት መስክ ላይ በመሰማራት የእግዚአብሄርን ስራ መስራት ያስችላል|፡፡
ኢዮ.22:21-26 የመስማማትን መርህ ሲያስረዳ፡-
”አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፤ በዚያም በጎነት ታገኛለህ። ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፤ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥ ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥ የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል። የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ።” ይላል፡፡
ከእግዚአብሄር ጋር የተስማማ ሰላም እንደሚያገኝ ቃሉ ያበስራል፡፡ በረከትም ምህረትም አብሮ ይከተለዋል፡፡ እስራኤል ከእግዚአብሄር ጋር በተጣላ ጊዜ (እግዚአብሄርን በተወ ጊዜ ) ሰላም እንደሚያጣ፣ ተገዝተውለት የነበሩ ጠላቶቹ እንደሚነሱበት፣ እንደሚያጠቁትና እንደሚያሸንፉት በታሪካቸው ግልጽ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡
በዘዳ.28:1-9 ላይ ለእስራኤል የተነገረው የበረከት ቃል ከእግዚአብሄር ጋር መስማማት የሚፈጥረውን ነገር ሁሉ የሚገልጥ ነበር፡፡ ሙሴ ለህዝቡ ሲያስረዳ እንዳለው የእግዚአብሔር አምላክን ቃል እስራኤል በመስማቱና እርሱ ያዘዘውን ትእዛዝ በማድረጉ የእግዚአብሄር ሞገስ በላዩ ላይ ሆኖ በጠላቶቹ ላይ ከፍ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የሰው ልጅ በምድር ላይ መሆን የሚፈልገው ትልቅ ነገር ሲሆን እርሱም ከእግዚአብሄር ጋር አብሮ በመጉዋዙ ያን ዋጋ ያለው ነገር እንደሚያገኘው ቃሉ ያስረዳል፡፡ እንዲህም አለ፡- ”የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል፤ ያገኙህማል። አንተ በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ። የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ቡሩክ ይሆናል። እንቅብህና ቡሃቃህ ቡሩክ ይሆናል።አንተም በመግባትህ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ቡሩክ ትሆናለህ። እግዚአብሔርም በላይህ የሚቆሙትን ጠላቶችህን በፊትህ የተመቱ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ መንገድ ይመጡብሃል፥ በሰባትም መንገድ ከፊትህ ይሸሻሉ።”
የእግዚአብሄር ህዝብ በምድር ላይ የሚጎሰቁለው፣ ለጠላቶቹ ተላልፎ የሚሰጠውና የተራቆተ የሚሆነው ይህን በረከት (ከላይ በቃሉ ላይ የተዘረዘረውን በረከት) ቸል ሲል እንዲሁም ሰጪውን አምላክ ሲረሳ፣ የሰጠውን ህግም ንቆ ሲጥል እንደሆነ በቃሉ ተቀምጦአል፡፡ እግዚአብሄርን ቸል ያለ አማኝ ፈጣሪውን ጥሎ በመኮብለሉ ምክኒያት በሚንከራተትበት ስፍራ ሁሉ ከመንገዱ ላይ ተወግዶ የነበረ እርግማን በሙሉ ዳግም አጥምዶ እንደሚይዘው ቀጥሎ በተቀመጠው ቃል ላይ ተብራርቶአል፡-
”ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል። በከተማ ርጉም ትሆናለህ፥ በእርሻም ርጉም ትሆናለህ። እንቅብህና ቡሃቃህ ርጉም ይሆናል። የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ርጉም ይሆናል። አንተ በመግባትህ ርጉም ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ርጉም ትሆናለህ። እኔን ስለ ተውኸኝ፥ ስለ ሥራህ ክፋት፥ እስክትጠፋ ፈጥነህም እስክታልቅ ድረስ በምትሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር መርገምን፥ ሽሽትን፥ ተግሣጽን ይሰድድብሃል።”(ዘዳ.28:15-20)
በጎነቱን ያየ በምህረቱ ምክኒያት ከእርሱ ብዙ የተቀበለ ሰው እንዴት ባለ ህይወት አምላኩን ያከብር ዘንድ ይገባዋል?
ነገር ግን ከእግዚአብሄር ጋር የተጣላ አማኝ ሊሸከመው የማይችለው እርግማን ስለሚጣበቅበት የበጎነቱን ዘመን እስከሚረሳ ድረስ ጎብጦ ይቀራል፤ ከእግዚአብሄር ጋር የተስማማ ግን በሰላም ይኖራል፤ ሰላሙም ዋስትና ስለሆነ በእረፍት ያድራል፡፡
በየዘመኑ የተነሳው ያለፈው ትውልድ እግዚአብሄርን በማስቆጣት ለተለያየ ነገር ተላልፎ ሲሰጥ እንደኖረ ሁሉ ከችግሩ ሰብአዊነት የተነሳ ሰንሰለቱ ሳይቆረጥ አሁን ድረስ ያ ቀጥሎአል፡፡ በታሪክ እንደምናየው እስራኤል ከግብጽ ምድር ሲወጣ የግብጽ በሽታ ዳግም ላያገኘው ከእግዚአብሄር ቃል ተገብቶለት የነበረ ቢሆንም ያዳነውን አምላክ በተወ ጊዜ ከምድር የሚያጠፋ ከባድ ቸነፈር እየደጋገመ ሲጣብቅበት ነበር። እግዚአብሄር እንዳለው አማጺው ህዝብ በክሳት፥ በንዳድም፥ በጥብሳትም፥ በትኲሳትም፥ በድርቅም፥ በዋግም፥ በአረማሞም ሲመታ የኖረበት አጋጣሚ እጅግ የበዛ ነበር፤ ለጠላቶቹ አጋልጦ ስለሚሰጠውም እስኪጠፋ ድረስ ይሰደድ ነበር። ይሄ ሁሉ እግዚአብሄር ያደረገውን በጎነት ቸል በማለቱ፣ በማናናቁና ጣኦትን በመከተሉ የሆነበት ስለነበር ለእስራኤል መንፈሳዊም ቁሳዊም ድቀት ሊሆን በቅቶአል፡፡ በእኛ ዘመን የሰው ልጆች ከእግዚአብሄር ርቀውና እርሱ ያልፈጠራቸው እስኪመስል በሌላ አማልክት (በቅርብ በተነሱ ጣኦታት) ሲያሳዝኑት ለተመሳሳይ ጉስቁልና ሲጋለጡ ይታያል፡፡
እግዚአብሄርን የሚያምን ቢኖር ግን ደግሞ ደጋግሞ ከእርሱ ጋር የሚስማማበትን መንገድ እርሱም ከአፉ ሕጉን መቀበልና መጠበቅ፣ በልቡም ቃሉን ማኖር፣ ከእግዚአብሄር አሳብ ጋር መሄድ፣ ለቃሉ ልቡን የዋህ ማድረግና ሁሉን ወደሚችል አምላክ መመለስ፣ የባዘነበትን ዘመን ማስመለስ፣ የጠፋበትን የእግዚአብሄር መገኘት ዳግም መቀበልና ከእግዚአብሄር ጋር ግንኙነቱን ማደስ የመሳሰሉትን የሚያቀርቡ ፍለጋዎች መሻት ይገባዋል፡፡ ለተግባራዊ እርምጃ እንደሆን ሌላ አቁዋራጭ መንገድ ሊኖር አይችልም፡- ቃሉ እንዳለው በፊቱ መዋረድ፣ ኃጢአትን ከድንኳን ማራቅ፣ ሰዋዊ ክብርን መጫን ሳይሆን መለኮታዊ ሞገስን ለመጎናጸፍ ሁሉን ማድረግ እንጂ፡፡ ”የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ።” የሚለው የጌታ ቃል ከመታዘዝ ቀጥሎ ያገኘዋል፡፡
እርስ በርስ መስማማት
ከእግዚአብሄር ጋር መስማማት ለሰው ልጅ ደህንነት ብቸኛው መፍትሄ ነው፣ ይህን ሊተካ የሚችል አማራጭ ሊኖር አይችልም፡፡ በሌላ በኩል ሰው በእግዚአብሄር ቤት ሲኖር ከወገኑ ጋር በሰላም እንዲኖር ተጠርቶአል፡፡ ህያውን አምላክ ማመን በሰላምና በእርጋታ ያኖራል እንጂ ሁከተኛ አያደርግም፡፡
1ቆሮ.14:33 ”እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው።”
ሰላማዊ ወገኖች በህብረት ያመልካሉ፣ ያገለግላሉ፣ የእግዚአብሄርን ምህረትና ጸጋ እንደ አካል በአንድነት ይቀበላሉ፡፡ ሁከት ሲመጣ ግን ሰይጣን አብሮ ይመጣል፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ስም የተጠራ ማንም ሰው ሊዋደድና ሊከባበር የተጠራ መሆኑን መረዳት አለበት፡፡
ያዕ.3:13-18 ”ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።”
የስምምነት መስፈን
በወንጌል ምክኒያት፡-
ስምም በእግዚአብሄርና በሰው ልጆች መሃል ሆኖአል፣
ስምም በአይሁድና በአህዛብ መሃል ሆኖአል፣
ስምም በማህበር መሀል ሆኖአል፣
ስምም በባልና ሚስት መሀል ሆኖአል፣
ስምም በቤተሰብ መሀል ሆኖአል፣
ስምም ከጎረቤት ጋር ሆኖአል፡፡
ኤፌ2:10-15 ”እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ”
መስማማት ዋናና አስፈላጊ ጉዳይ ሆኖ ሳለ የስምምነታችን ይዘት ካለመስማማት በላይ የሚያሳስብ ነው፡፡ ፍጥረት በሙሉ ቢያብር፣ ቢስማማ፣ አንድ ቢሆን ወይ ለበጎ ይስማማል ያልያም ለክፉ አንድ ይሆናል፤ እና የመስማማሚያችን ሁኔታ የሚከተለው ይዘት ይኖረዋል ፡-
በበጎ መስማማት
ማቴ.18:15-17 ”ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።”
ከወንድም ጋር የሚፈጠር አለመስማማት መንፈሳዊ ህይወትን እንዳይጎዳ ግንኙነት በቅድመ-ጥንቃቄ ውስጥ ሊያልፍ ይገባዋል፤ እርቅና ስምምነትም ዋና የቅድመ-ጥንቃቄ አካል ናቸው፡፡ ሁለት የተለያየ አሳቦችን አንድ ማድረግ የተሳናቸው የአንድ መንገድ ተጉዋዦች ቢኖሩ (ጥንዶች ወይም ባልንጀራሞች) ሄደው ሄደው በስተ መጨረሻ ወደ አንድ አሳብ ሊመጡ ወይም ሊስማሙ ግድ ነው፣ አብሮነት ስምምነት መሰረቱ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ በአንድ አሳብ ባይስማሙ ወይ የተሸለውን አንዱን ሊወስዱ አይሆንም ካሉ ሁለቱን እርግፍ አድርገው ሊተዉ ምርጫ አላቸው፤ ግን ከዚያ አስከትሎ (ከውሳኔያቸው በመከተል) በወዳጅነታቸው ላይ ቁርሾ እንዳይፈጥሩ እጅግ መጠንቀቅ ይገባቸዋል፡፡ ሙከራ ባይሳካ/በሰላም ባይፈጸም አለመግባባት ሊካረር ይችላልና ያን ለማስወገድ መካከለኛ ወደሚሆን መንፈሳዊ አካል ብቅ ማለት አስፈላጊ ነው፤ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን የሁለቱ ወገኖች አዎንታዊ ውሳኔ ይፈለጋል፤ የሂደቱ አስፈላጊነት መስማማትን ለመፍጠር ነው (በምርጫችን አንድ መሆን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አቀራረብ ውስጥም ሆኖ መስማማትን መፍጠር ስለሚቻል)፡፡ የኔ ካልሆነ ወይም እኔ ያላልኩት ካልሆነ አይሆንም አልስማማምም የሚል አይነት ውሳኔ ነገሮችን ማጥበቅና ማካረር በስተመጨረሻም ጥልን/ያለመታረቅን ስለሚፈጥር መንፈሳችንንም ስለሚያኮመጥጥ (መራሮች ሊያደርገን ስለሚችል) ቅድመ-ጥንቃቄ የተባለው ነገር ሁሌም መረሳት የለበትም፡፡
ሮሜ.15:5-6 ”በአንድ ልብ ሆናችሁ በአንድ አፍ እግዚአብሔርን፥ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት፥ ታከብሩ ዘንድ፥ የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ፈቃድ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ መሆንን ይስጣችሁ።”
እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ የሆነ አሳብ የሚመጣው የጌታ ፈቃድ በህይወታችን ገዢ ሲሆን ስለሆነ ለግንኙነታችን መሰረት እርሱን ቅድሚያ ማድረግ ተገቢ ነው ፡፡ ግንኙነታችን ሰላማዊ ከሆነ ከእኛ አልፎ ለቤተሰብ፣ ሲልም ለጎረቤትና ለማህበረሰብ በበጎነቱ የሚተርፍ ይሆናል፣ ከሰው ሁሉ ጋር ያለነቀፋ ሆኖ ለመገኘት፣ ምሳሌያዊ ኑሮንም ለመግለጥ አስቀድሞ እንዲህ መሆን ይጠበቃልና፡፡
ማቴ.5:23-25 ”እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥
በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ። አብረኸው በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራ ለዳኛ እንዳይሰጥህ ዳኛም ለሎሌው፥ ወደ ወህኒም ትጣላለህ”
ለክፉ መስማማት
በአመጽ መተብተብ ለክፋት የመስማማት ውጤት ነው፡፡ ባልተገባ ግንኙነት ውስጥ መጣመር ለክፋት ስራ መወዳጀትን ይፈጥራል፣ መጨረሻውም ጥፋት ይሆናል፡፡ ደግሞ ወዳጅነታችን በመሃላችን በጎ ነገርን የሚያጸና እንዲሆን እንጂ ክፉ ምክርን የሚያበረታታ እንዳይሆን መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ እውነተኛ ወዳጅ ሌላውን ከስህተቱ ገስጾ የሚያስተካክል ነው፣ ነገር ግን የአመጹ ተባባሪ ቢሆን ራሱም ከአጥፊው ጋር ይመደባል፡፡ ይህ ስህተት በእግዚአብሄር ቤት ውስጥ የተገኘ እንደሆነም ስህተቱ ጥልቅ መንፈሳዊ ስብራት ላይ የሚጥል ይሆናል፡፡ ቀጥሎ ያለው ታሪክ ይሄንን ችግር በግልጽ ያሳያል፡-
ሐዋ.5:9 ”ጴጥሮስም:- የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለ ምን ተስማማችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው አንቺንም ያወጡሻል አላት።”
እነዚህ አማኝ ባልና ሚስት ጅማሬአቸው በጎ ስምምነት ሆኖ ሳለ (መሬታቸውን ሸጠው ያገኙትን በታማኝነት ሊያስረክቡ ተመካክረውና ተስማምተው ነበርና) በክፉ ምክር ላይ ድንገት በወደቁ ቅጽበት ግን ስምምነታቸው ወደ አመጽ ተቀየረ፤ በምክራቸው ክፋት ያገኛቸው ቅጣት እንደዚያው የከፋ ሆኖም ተገኘ፡፡
ሮሜ.12:16 ”እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ።”