እውነተኛ እረኛ ወደ በረቱ በበሩ የሚገባ ነው፡፡ሾልኮ የሚገባ ወንበዴን ይከላከላል፡፡ሌባው እንዳያገኘንና በመንገድ፣ እንዳንቀር አወጣጥና አገባቡን የሚያሳየን አርሱ ብቻ ነው፡፡እውነተኛ እረኛ ድምጹን ያሰማና በጎቹን ያነቃል፡፡የበጎች እረኛ በህይወት በር በመግባት ወደ መኖርያችን በደህንነት ያስገባናል፡፡በልባችን ያድራል፡፡ያኔ ልባችንን ወደ እረፍት ያቀናዋል፡፡ወደ ቀናው የህይወት ስርአት ሊያመለክተን በእርሱም እንድንኖር ያጸናናል፡፡
እግዚአብሄር እረኛችን ነው፡፡እንዲያ በመሆኑ ከእርሱ ብዙ ይደረግልናል፡፡ለምሳሌ፡- ስጋችንና መንፈሳችን የሚያስፈልጋቸውን ነገር በጊዜው ያቀርባል፡፡እጅግ ስለሚታገሰን ሳይታክት ይጠብቀናል፡፡ስንወጣ ይቀድማናል፡፡ወደ ወጣንበት ይሄዳል፣ ወደ ገባንበት ይከተለናል፡፡ክፉው በቁጣው እንዳያገኘን ይከላከልልናል፡፡ስንሳሳት ይመልሰናል፡፡የእሳት ቅጥር ሆኖ የክፋትን ነበልባል ያጠፋልናል፡፡በክፉው አሰራር ነድደን እንዳናልቅ ማብረጃውን ያበጅልናል፡፡አለታችን እርሱ በመሆኑ ከክፉው ፍላጻ ያስመልጠናል፡፡
ዮሐ.10:7-17 ኢየሱስም ደግሞ አላቸው፡- እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እኔ የበጎች በር ነኝ።ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም።በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፥ ይገባልም ይወጣልም መሰማሪያም ያገኛል።ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል።ሞያተኛ ስለ ሆነ ለበጎቹም ስለማይገደው ሞያተኛው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ፥ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል።
ወደ እግዚአብሄር ህዝብ ጎራ የሚሉ ባእድ መናፍስት ህዝቡን እንዳይነጥቁና ከመንገዱ እንዳያስቱት እግዚአብሄር ዘወትር ይጠነቀቃል፡፡እንዳሰብነው ያልሆነው እግዚአብሄር ለፈቃዳችን አሳልፎ ስለማይሰጠን ነው፡፡ፍቃዳችን እንዳያስተን፣ለጠላት አሰራር ተላልፈን እንዳንሰጥ እረኛ የሆነው አምላክ ያስተካክለናል፡፡ሌቦችና ወንበዴ መናፍስቶች ነፍስን ይናጠቃሉ በመንገድ ለማስቀረት ያደባሉ፡፡እውነተኛው እረኛ ግን ለወጥመዳቸው አሳልፎ አይሰጠንም፡፡
ወደ እግዚአብሄር መንግስት የምንገባበትን በር እርሱም ክርስቶስን አግኝተናል፡፡በተናወጠች ከተማ፣በወንበዴ መናፍስት በተሞላች በዚህች አለም ሳንጠፋ የመኖራችን ምስጢር የጌታ የኢየሱስ በእኛ የማደር ምስጢር ነው፡፡ሰዎች በተሳሳተ እረኛ እጅ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ይህ እረኛ የበጎቹን ድምጽ የማይሰማና ግድ የሌለው ነው፡፡የነርሱ ረሀብና ጥማት ግድ ስለማይሰጠው በምድረበዳ በጥማት ምድር ለአውሬ አጋልጦ የተዋቸዋል፡፡እውነተኛው እረኛ ግን ነፍሱን ለበጎቹ አሳልፎ እስከመስጠት የታመነ ሆኖአል፡፡መልካም እረኛ በበጎቹ የታወቀና እርሱም በጎቹን የሚያውቅ ነው፡፡ለልብ የቀረበ እጅግ ውድ ጌታ የተጠጋጋ ወዳጃችን ነው፡፡ድምጹን በሩቅም በቅርብም የሚሰሙ ሁሉ ወደእርሱ በመንፈሳቸው ይገሰግሳሉ፡፡ወደ ጸጋው ዙፋኑ ይመጣሉ፡፡በዚያም ንጉሳቸውን ያመልኩታል፡፡በዚያም ባርኮቱን ይቀበላሉ፡፡ በዚያም ክብሩን ያያሉ፡፡በዚያም ከእርሱ ጋር ይነጋገራሉ፡፡በጠፋችው አለም ውስጥ ሰጥመው ሳይጠፉ በጸጋው መርከብ እየተንሳፈፉ በባህሩ የተበሉትን ይታደጉ ዘንድ ቀንና ሌሊት በጸሎታቸው ያስሳሉ፡፡ነፍስ አድን ጥሪን ይጮሀሉ፡፡በምልጃቸው የእረኛውን ማዳን ያሳስባሉ፡፡የአምላካቸውን ጥሪ ይሰማሉ፣” አለሁኝ ለምታዘኝ ስራ ሁሉ” ይላሉ፡፡
ዕብ13:20-21 በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ያወጣው የሰላም አምላክ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን በእናንተ እያደረገ፥ ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ፍጹማን ያድርጋችሁ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።
1ጴጥ.2:24-25 ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።
በሌላ በኩል እግዚአብሄር ነፍስ በአቅርቦት እጥረት እንዳትጎሰቁል ሁልጊዜ ይሞላታል፡፡ሌሎች ከሚሰጡን ይልቅ የተሸለ ስጦታ ከእግዚአብሄር ብቻ ይገኛል፡፡ለእኛ አቅርቦታችን ያጠረ የሚመስለን ራሳችንን ከሌላ ወገኖች ጋር ስናጻጽር ብቻ ነው፡፡እስራኤል ከግብጽ ወጥተው በአህዛብ መሀል ሲያልፉ የተመለከቱዋቸው በላያቸው ካለው ከእግዚአብሄር ሞገስ የተነሳ ፈርዋቸው ፣ቀኑባቸውም፡፡እስራኤል ግን በእግዚአብሄር አምላኩ እጅ እየሆነለት የነበረውን ሳይመለከት አህዛብ እየሆኑ በነበረው ተነሳስቶ መጎምዠት ውስጥ ገባ፡፡ያም መጎምዠት ሀጢያት በላዩ ላይ አመጣበት፡፡እያንዳንዳችን ግን “ለእኔ አባት የሆነኝ አምላኬ የሚያሳጣኝ የለም” የሚል ሙሉ ትምክህት ቢኖረን እንዳልነው ይሆንልናል፡፡