የእግዚአብሄር የተሻለው ነው (2…)

የመጨረሻ ዘመን

የአብረሃም አምላክ የሆነ እግዚአብሄር ብርቱ አምላክ ሲሆን ለሰው ደግሞ ያለው አሳብ በጎ ነው፣ የሰው አሳብ ወደ ጥፋት እየሆነ ባለበት በዚህ ዘመን እንኩዋን በመንገዱ ሁሉ በጎ ነው፣ በሚያደርግልን በስጦታው በጎ ነው፣ በራሳችን አውቀናል እያልን በምርጫዎች ብንሞላም ከኛ ይልቅ የተሻለውን የሚያውቅልን እርሱ ብቻ ነው። በእምነት ማጣት ምክኒያት እግዚአብሄር በገለጠልን እውነት ያለመርጋት ስለሚታይብን እንጂ ከርሱ የምንቀበለው እውነት ትልቅ መንፈሳዊ ስፍራ የሚያደርሰን ነበር። ለራሳችን አሳብና ጉዳይ አብዝተን ስፍራ የምንሰጥ፣ ውስጣችንን በጣም የምናምንና የምንደገፍበት፣ ለእውቀት ልብን በራስ አጥር የምናፍንና ለእግዚአብሄር ነገር ክፍተት የማንሰጥ ሰዎች በሁሉም ዘርፍ ተጎጂዎች ነን፤ ምክኒያቱም ከእኛ የላቀ አምላክ ከእኛ ውጪ አለና፤ ስለዚህ ውስጣችንን በመዝጋት እርሱ ህይወታችንን እንዳይመራ ከፈቃዳችን መሃል ስለምናስወጣው መልሰን እኛው ተቸጋሪዎች እንሆናለን። ዛሬ በብቸኝነት ችግር የሚሰቃየው የትኛው ትውልድ ነው? የየትኛውስ ማህበረሰብ አባል ነው? ራሱን የትጋ እያስቀመጠስ፣ ምንስ ጋ ተገኘ? ብዙ መታወስ ያለባቸው ነገሮች አሉ፣ ሁሎቹም ግን መያያዝ ያለባቸው ከእኛ የህይወት ደረጃ ጋር ነው፣ ክፈጠረን አምላክ ጋር የላላ ብሎም ምንም ግንኙነት ስለሌለን ነው።
የእኛን ነገር በዚህ ትውልድ አንጻር እንድናስተውል ከግብጽ የወጡትን የእስራኤል ህዝብ መለስ ብለን እናስባለን ፦ የህዝቡ ከግብጽ አወጣጥ፣ የጉዞ ሂደት፣ በጉዞአቸው የገጠማቸው ድካም እንዲሁም የእምነታቸው መነቃቃት ታሪክ ሁሉ ለእኛ ዘመን ሰው መንፈሳዊ እውቀትን የሚሰጥ ነው። የሰው ልጅ ያለ እግዚአብሄር ምሪት በምድር ላይ መኖር ቢችልም ኑሮውን በጽድቅ ሊመራው ግን ከቶ አይችልም፤ ይህም ማለት ሰው በራሱ ጻድቅ እንዳይሆን የጥፋት መንገድ ተሰርቶበታል ማለት ነው፤ ይህን ያደረገ የሰው ዘር ጠላት አለ፤ ባለጋራ የሆነ ሰይጣን ይህን ክፋት በሰው ልጅ ላይ ከማድረጉ በተጨማሪ ሌሎች መሰል ጥፋቶችን ሰው እንዲቀጥላቸው ወደ እርሱ አስተላልፎአል።
ሰው ግን ምንም ቢደነቃቀፍ፣ አንካሳ በመሆን ከአምላኩ ጋር መጓዝ ቢሳነውም የእግዚአብሄር ቸርነት ወደ ሁዋላ ሳይል በሃይሉ እየመጣ የህይወት መንገዱን ይቃኛል።
በተመሳሳይ ከግብጽ ምድር ያወጣውን ወገን ሲመራ የህዝቡ ስነልቦና እምን ድረስ እንደሚጓዝ እግዚአብሄር በማየት ደግፎአል፣ በድካማቸው ረድቶአል፣ በጥፋታቸው ደግሞ ቀጥቶአቸዋል። ያኔ የህዝቡን ልብ ስለሚያውቅና ያስተምራቸው ዘንድ ረጅም ዘመን እንዲያስፈልጋቸው በማየት የ40 አመት ትምህርትና የህይወት ተሞክሮ እንዲኖራቸው በምድረ-በዳ መርቶአቸዋል።
‘’እግዚአብሔርን ብትፈሩ ብታመልኩትም፥ ቃሉንም ብትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ባታምፁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ፥ መልካም ይሆንላችኋል።ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ብታምፁ፥ በእናንተና በንጉሣችሁ ላይ የእግዚአብሔር እጅ ትሆናለች።አሁንም ቁሙ፥ እግዚአብሔርም በዓይናችሁ ፊት ወደሚያደርገው ወደዚህ ታላቅ ነገር ተመልከቱ።’’ (1ሳሙ.12:14-16)
በመነሻና መዳረሻ መሃል ያለ ጉዞ
እግዚአብሄር በጠራን መጀመሪያ ላይ ይናገራል፣ ተስፋ ይሰጣል፤ መዳረሻችንን እያሳየ በደስታ እንድናምነው ያደርጋል። እግዚአብሄር ለጉዞ እንድንነሳ በሚያሳስበን ወቅት አብሮ የሚደግፈንን ተስፋ ይሰጣል፤ ተስፋው መዳረሻችንን የሚያስናፍቅ፣ የሚያሳይና በዚያን ጊዜ ሊሆን ያለውን ሽልማት ያበስራል። በተስፋው ቃል እየተመራን እግዚአብሄር ወዳሳየን ስንገሰግስ ጉዞአችንን በእምነት እያበረታን ልንሄድ፣ ጉዞውም አስቸጋሪ እንዳይሆን ያስችላል። በመሃል ያለው ሂደት ግን ለእኛ የሚነገረን ሳይሆን እንድንኖረው እርሱ የተተወልን የጉዞ ሂደት ነው፤ በዚያን በምናልፍበት ወቅት መሃል እንደ አጀማመራችን ያልሆነ የማንጠብቀው ነገር ሊገጥመን ይችላል፣ የሚያስደነግጥ ገጠመኝ፣ ተስፋ አስቆራች ፈተናም ድንገት ሊከሰት ይችላል፣ ፤ ሆኖም ተስፋ የሰጠውን አምላክ በማመን ምሪቱ ላይ ትኩረታችንን ካደረግን በድል ወደ ፍጽሜ እንደርሳለን።
ለምን እግዚአብሄር ይታመናል? እግዚአብሄር እስከ መጨረሻው ይመራናል፣ ይሸከመናልም በሚል ተስፋ አይደለምን? እንዲያ ከሆነ መነሻችንን እንዲያስጀምር የእስራኤል ህዝብ እንዳደረገውም እግዚአብሄርን መጠበቅ ተገቢ ነው። ተስፋው መጨረሻችንን አሳይቶ በደስታ ሙላት እግዚአብሄርን እንድንከተል ያደርጋል፦
‘’አምላክህም እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሰጠህ ምድር ላይ እግዚአብሔር በእውነት ይባርክሃልና አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመህ ብትሰማ፥ ታደርጋትም ዘንድ ዛሬ የማዝዝህን ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቅ፥ በመካከልህ ድሀ አይኖርም። አምላክህም እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠህ ይባርክሃል፤ ለብዙ አሕዛብም ታበድራለህ፥ አንተ ግን አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብንም ትገዛለህ፥ አንተን ግን አይገዙህም።’’ (ዘዳ. 15:5-6)
እግዚአብሄር ተስፋ ይሰጣቸው በነበረ ሰአት ህዝቡ አንዱም ነገር በእጃቸው የሌለ ባሪያ የነበሩ ህዝቦች ናቸው፤ ጭራሽ ሃብት የማያውቁ፣ ምቾት የማያውቁ፣ እረፍት የማያውቁ የተጨቆኑና የተናቁ ነበሩ፤ እግዚአብሄር ግን ከዚያ የኑሮ ይዘታቸው ባሻገር ዛሬ ላይ እያሉ ከአርባ አመት በሁዋላ የሚሆነውን ትልቅ ነገር ይነግራቸው ነበር፤ ያም ይፈጸምላቸው የነበረው ግን ሲያምኑት፣ ሲሰሙትና ሲከተሉት ብቻ ነበር። እስራኤል ስማ፣ ገና ለገና መንገዱ ስለረዘመ ተስፋ አይጣልም፣ ጊዜው ስለሚረዝምም ከእርሱ ፈቀቅ ማለትና ሌላ መንፈስ መከተልም አያዋጣም፤ በምንም መልኩ እግዚአብሄር የመረጠው መንገድ በጎና የተሻለ ነውና።
ሲነሱ እስራኤላውያን የሰሙትን አመኑና ወጡ፣ መንገዳቸውንም ተጓዙ፣ ነገር ግን በመሃል የሆኑትን ሁኔታዎች ባዩ ጊዜ መልሰው ፈሩ፣ አጉረመረሙም፤ ከውስጥም ከውጪም የነበረው ውጥረት እንዳይረጋጉ አድርጉዋቸውም ነበር። በዚህ መሃል በተጨነቁ ጊዜ በመጸለይ ፈንታ አጉረመረሙና በአምላካቸው ላይ ስንፍና ቃል ተናገሩ፣ ከርሱ ጋር ተቀያየሙ። ከግብፅ እንድንወጣ ለምን አደረግክ? ብለው ሙሴ እንዳጠፋ ያህል ተቆጡ። ሙሴም እንዲረጋጉ በመሞከር ቁሙ የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ አላቸው። በሰው አይን ከሆነ ምንም ማድረግ ወደ ማይቻልበት የጥፋት ደረጃ ደርሰዋል፤ በእግዚአብሄር እቅድ ውስጥ ግን በጉዞአቸው ውስጥ ማዳን ነበረ፤ እግዚአብሔርም ወደዚያ ወደ ባህሩ ባመጣቸው ጊዜ ለእስራኤላውያን መዳኛ ለጠላቶችቸው መቀበሪያ ስፍራ ነበር። ስለዚህ ቢፈሩም አንድ ነገር መጠበቅ ይገባቸው ነበር።
ኤር.21:8-10 ‘’ለዚህም ሕዝብ እንዲህ በል፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በፊታችሁ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ አድርጌአለሁ። በዚህች ከተማ ውስጥ የሚዘገይ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወጥቶ ወደ ከበቡአችሁ ወደ ከለዳውያን የሚገባ ግን በሕይወት ይኖራል፥ ነፍሱም ምርኮ ትሆንለታለች። ለመልካም ሳይሆን ለክፉ ፊቴን በዚህች ከተማ ላይ አድርጌአለሁና፤ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ትሰጣለች፥ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል።’’
የእግዚአብሄርን ሁሉን ቻይነት በዚህ ጥቅስ ላይ እናያለን፤ ጠላት ብለህ በልብህ የፈረጅከው ዞሮ ለመትረፊያህ መንገድ የሚሆንበት አጋጣሚ እግዚአብሄር ሊፈጥር ይችላልና፤ ደግሞ የሚያድነኝ አለ ብለህ በልብህ ስፍራ የሰጠሀው ሰው ለክፉ አሳልፎ ሊሰጥህ ይችላል፤ እግዚአብሄር ግን ለርሱ ለሆነው ሁሉ ለበጎ የሚቆም፣ ለክፋት የገጠመውን ሁኔታም ቀይሮ ለበጎ አላማ የሚያውል ነው።
እግዚአብሄር እስራኤላውያን በሚኖሩበት ምድር ላይ የሞት መንገድንና የህይወት መንገድን አኑሮ ነበር፤ ያን ባደረገ በዚያ ወቅት እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ተከበው በዛቻቸው ጫና የሚጨነቁበት ጊዜ ነበር፤ በዚያ ህይወት ውስጥ እያሉ ነባራዊውን ሁኔታ ያላማከለ እንዲያውም ለከበባቸው ጠላት አሳልፎ የሚሰጥ የሚመስል አሳብ እግዚአብሄር አቀረበላቸው፤ ህዝቡን ወደ ከበቡህ ጠላቶችህ ሄደህ እጅ ብትሰጥ ከመጥፋት ይልቅ ታመልጣለህ፣ ባለመታዘዝ ብትዘገይ ግን በሶስት የጥፋት መሳርያ ውርጅብኝ (ማለትም ሰይፍ፣ ራብና ቸነፈር) ትጠፋለህ አላቸው። ይህን ስንመለከት ስለ እግዚአብሄር ፈቃድና ውሳኔ ምን እንላለን? ምንስ እናስተውላለን? የርሱን ውሳኔ በትክክለኛ አይን ልንመለከት የምንችለው የኛ የራሳችን የህይወት ይዘት ከገባን ብቻ ነው። ለማንኛውም እግዚአብሄር ባመጽንበት ጊዜና ምክኒያት እንኳን መዳን የሚገለጥበት ትንሽ ቀዳዳ ከፍቶ በዚያ እንድናመልጥ እንደሚመክረን ያን የማምለጫ አጋጣሚ ሳንጠቀም ድምጹን ቸል ካልን ግን ያዘጋጀውን መልካም አጋጣሚ ስለማንጠቀምበት በጥፋታችን ላይ እንወዳቃለን፤ የተስፋው ህዝብ ምን ደረሰበት?
– እስራኤል ግን እግዚአሄርን አልሰማም ብሎ በምድረ-በዳ 40 አመት እየተንከራተተ አለቀ፣
– እስራኤል እግዚአሄርን አልሰማም ብሎ ነቢዩ ኤርሚያስ ላይ ፊቱን ባዞረ ጊዜ ከምድሩ ተነቅሎ 70 አመት በባእድ ምድር እየተንከራተተ አለቀ፣
– እስራኤል እግዚአሄርን አልሰማም ብሎ በጻድቁ ላይ ስላመጸ 2000 አመት ለሚሞላ ዘመን ከምድሩ ተነቅሎ በባእዳን አገር እየተንገላታ አለቀ።
እንግዲህ የእስራኤል ፍጻሜ ከወደየት ነው?
የሚሻለውን መወሰን ያለበት አሁንም ህዝቡ ራሱ ነበር፤ እግዚአብሄር የፈቀደው የተሻለ ነገር ከሆነ በእሺታ መንፈስ መቀበል ያስፈልጋል፤ እውቀት በህይወት ሊገለጥ አስፈላጊ ነውና። ስለዚህ በመመለስ መትረፍ፣ እይታን በማስተካከል ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረስና በእግዚአብሄር ፊት ንሰሃ መግባት አስፈላጊ ነው።
የተሻለው የእግዚአብሄር ፈቃድ ከእኛ ተጽእኖ ክልል ውጪ ስለሆነ ህዝቡ ወደ ራሱ መለስ ቢል ያን በማስተዋል ይጠቀማል፣ ያን በማስተዋል ውስጥ ደግሞ፦
– ከራሱ ከእስራኤል ህይወት፣ ኑሮ፣ ባህል፣ ማንነትና ወግ ውጪ ህያው ሆኖ ያለው እግዚአብሄር ብቻ መሆኑን ያውቃል፣
– እስራኤል የሚጠቅመውን አስተውሎ የተሻለውን የእግዚአብሄር አሳብ ሲመርጥ እንደሚበጀው ይመለከታል፣
– የራሱ አሳብ ማስቀደም መተው እንደሚገባው ይደመድማል፣
– ከአለም ጋር ያለውን የጠበቀ ዝምድና ፈጽሞ ሲቆረጥና የፈጠረውን አምላክ ሲከተል እርሱ እንደሚረዳው ይገባዋል፣
– ቃልኪዳኑን ሲያነሳ ተስፋው ወደ እርሱ እንደሚነሳ ያውቃል።
‘’እግዚአብሔርም ይሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ ወረሱአትም፥ ተቀመጡባትም። እግዚአብሔርም ለአባቶቻቸው እንደ ማለላቸው በዙሪያቸው ካሉት አሳረፋቸው፤ ጠላቶቻቸውም ሁሉ ይቋቋማቸው ዘንድ ማንም ሰው አልቻለም፤ እግዚአብሔርም ጠላቶቻቸውን ሁሉ በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም።’’ (ኢያ. 21:43-45)
ከተስፋው ህዝብ የተረዳነውን ይዘን ወደ ራሳችን ስንመልሰው ትልቅ ነገር እናያለን፣ የእግዚአብሄር እይታ ከፍ ያለ ነውና እኛ ስለራሳችን ከማየትና ከማለም ይልቅ እግዚአብሄር በቃሉ ያየልንን እንወቅ፣ እግዚአብሄር የነገረን አስቸጋሪ ቢመስልም አለም ከምትሰብከን፣ ሰይጣንም ከሚያንሾካሹከን የጥፋት ምክር የርሱ የተሻለና የሚበጀን ነው እንበል፤ እስራኤላውያን እግዚአብሄር ሊያጠፋን ነው ባሉ ሰአት እርሱ ግን በበጎ ምክር መልሶአቸዋል፣ እግዚአብሄር አያይም ወይም አይሰማም ባሉበት ስፍራ እግዚአብሄር ቀድሞ አይቶ እርምጃ ሲወስድም አይተናል። እንዲህ ብሎአቸውም ነበር፣ እርሱን ለራሳችንም ብንጠቀምበት?
‘’እንዲህም ይሆናል፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ ብትጠብቅም አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል፤ ያገኙህማል።አንተ በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ።የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ቡሩክ ይሆናል።እንቅብህና ቡሃቃህ ቡሩክ ይሆናል።አንተም በመግባትህ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ቡሩክ ትሆናለህ።እግዚአብሔርም በላይህ የሚቆሙትን ጠላቶችህን በፊትህ የተመቱ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ መንገድ ይመጡብሃል፥ በሰባትም መንገድ ከፊትህ ይሸሻሉ። እግዚአብሔር በረከቱ በአንተ ላይ በጐተራህ በእጅህም ሥራ ሁሉ እንዲወርድ ያዝዛል፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ይባርክሃል።የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትጠብቅ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል።የምድር አሕዛብም ሁሉ የእግዚአብሔር ስም በአንተ ላይ እንደ ተጠራ አይተው ይፈሩሃል።’’ (ዘዳ. 28:1-10)