እግዚአብሄር ያመለከተንን አይተን ባንወደውም፣ ከፊታችን ያኖረውን ትእዛዝ ሰምተን ባንመርጠውም፣ ሃሌሉያ አሰኝቶ ባናመሰግንበትም እርሱ ያዘዘውና የተናገረው ነገር በሙሉ በጎ ውጤት አለው።
የእግዚአብሄር ንግግር የተሻለ መንገድ አመልካች ነው፣ የተሻለ ህይወት አለው፣ የተሻለ መጨረሻም አለው። እግዚአብሄር ነገሮች ከመምጣታቸው አስቀድሞ ይናገራልና፣ ሁኔታዎች ከመድረሳቸው አስቀድሞ ስለ እነርሱ ያመለክታልና፣ የድርጊቶቻችንን ውጤት እንድናውቅም ያመለክታልና፦ ስለዚህ እምቢታ ካሳየን ያለማስተዋላችንና ድምጹን ለመቀበል ያለመፍቀዳችን እጅግ ብዙ ጉዳት ያስከትላል።
የእስራኤል ህዝብ ከግብጽ መውጣት፣ በኤርትራ ባህር ማቁዋረጣቸውና ድል አድርገው መውጣታቸው ለእስራኤል ስለተነገረ የሆነ ብቻ ሳይሆን በእርሱ አይኖች አስቀድመው የታዩ ክንውኖች ስለሆኑም ነበር። ያን እውነት እስራኤል ጠንቅቀው አውቀው ቢሆን ኖሮ በጠላት ፊት ማልቀስ ባልነበር፣ በእግዚአብሄር ባርያ በሙሴም ላይ ማጉረምረም ባልነበር፣ ከምንም በላይ በእግዚአብሄር በአምላካቸው ላይ የስንፍና ቃል ባላወጡም ነበር።
‘’እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። ተመልሰው በሚግዶልና በባሕር መካከል፥ በበኣልዛፎንም ፊት ለፊት ባለው በፊሀሒሮት ፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ ከእርሱም አጠገብ በባሕር ዳር ትሰፍራላችሁ። ፈርዖንም ስለ እስራኤል ልጆች፦ በምድር ይቅበዘበዛሉ፥ ምድረ በዳም ዘጋቻቸው ይላል። እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ እርሱም ያባርራቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ።’’ (ዘጸ. 14:1-4)
ከግብጽ እስከ ከነአን በነበረው የእስራኤል ጉዞ ውስጥ የእግዚአብሄር ምሪት ነበር፤ በዚያም በቀን ክፍለ-ጊዜ አካሄዳቸው ምን መምሰል እንደነበረበት፣ በሌሊትም ምን መሆን እንዳለበት፣ ለጉዞአቸውም የእርሱ አቅርቦት ምን እንደሚመስልና ምን ሊያደርግ እንደሚገባው በእርሱ ዘንድ አስቀድሞ የተወሰነ ነበር፤ እሥራኤል ግን ሲያስቡ በልባቸው የተመላለሰው ያሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ፣ ሲያዩ ፊትለፊታቸው ድቅን ይል የነበረውም የእርሱ እቅድ ሳይሆን የከበባቸው ጠላት ነበር፤ ይህም ፈጥኖ ሁለንተናቸውን የተቆጣጠረና ልባቸውን ያቀለጠ ስለነበር ከእምነት አስቀርቶአቸዋል፦ ስለዚህ እግዚአብሄር ቀን በደመና አምድና ሌሊት በእሳት አምድ ሊመራቸው፣ ይህንም አሰራር እንዳዘጋጀ አይተውና ተረድተው ሊያመሰግኑት አልፈቀዱም፤ ነገር ግን የፈርኦን ፈረስና ሰረገላ አራዳቸው፣ የበረሃው ወላፈን ታስቦአቸውም እጅግ አማረሩ፣ ስለሚበሉትና ስለሚጠቱት ተመኝተው ክፉ ንግግር ከአንደበታቸው አወጡ፤ ይመራቸው ዘንድ እግዚአብሄር የሾመውንም ሰው ረገሙ። በመጨረሻ ግን መልካም የነበረውን የእርሱን ፈቃድ በመቃወማቸው ከግብጽ ከወጡት ከሁለት ሰዎች በቀር ሁሎችም ባጉረመረሙበት ምድረ-በዳ ወድቀው ቀሩ።
1. እግዚአብሄር ተጓዙ ሲል ምን አቅዶ ነበር?
የእስራኤል ህዝብ ለ400 አመት ያህል ተገዝተውበት ከነበረው ምድር በእግዚአብሄር ትእዛዝ ነቅለው እንዲወጡ የተደረገው በዋናነት የእግዚአብሄር የተስፋ ቃል ፍጻሜ እንዲያገኝ ነበር። ለዚህ ፍጻሜ መሳካት የእግዚአብሄር ፈቃድ መንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን ቃል-ኪዳን የተገባለት ህዝብም የእግዚአብሄርን እቅድ ይቀበል ዘንድ ፈቃደኛ መሆን ነበረበት። እስራኤላውያን ግን ምን አሉ?
‘’ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግስው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ። ሙሴንም፦ በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና። ተወን፥ ለግብፃውያን እንገዛ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? አሉት።ሙሴም ለሕዝቡ፦ አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው።’’ (ዘጸ. 14:10-14)
እግዚአብሄር ከናንተ ጋር እወጣለሁ ያለው መላኩን ልኮ፣ በቀን የደመና አምድና በሌሊት የእሳት አምድ ለእነርሱ አዘጋጅቶ ነው። ስለዚህ ጉዞአቸውን በጀመሩበት ምሽት አምዱ በነርሱ ላይ ተገልጦአል፤ የደመናው አምድ በተገለጠበት በዚያ ወቅት ደግሞ የግብጽ በኩሮች ተገድለዋል። የተገለጠው የርሱ ክብር ስለነበረ ስራው ታላቅ ነበር። በእግዚአብሄር እቅድ ውስጥ የነበረው ተጓዙ የሚለው ትእዛዝ ሲከበር በጠላቶቻቸው ላይ የማያዳግም ፍርድ ሊካሄድ በነርሱ ላይ ደግሞ የምህረት እጅ ሊንቀሳቀስ የተወሰነ እንደነበር ማየት እንችላለን። የእግዚአብሄር የደመና አምድም ሙሴ የመገናኛውን ድንኩዋን እስከሰራበት ጊዜ ድረስ በፊቱ ይገለጥ ነበር።
የደመናው አምድ መታየት የእግዚአብሄር አብሮነት፣ ክብር፣ ሃይልና ማዳን ምልክት በመሆኑ ህዝቡን በሞላ ከአስቸጋሪ ሁኔታ ይጋርዳቸው ነበር። የደመናው እንቅስቃሴ የህዝቡን እረፍትና እንቅስቃሴ የሚወስንም ነበር፤ ምክኒያቱም ዳመናው በተነሳ ጊዜ ህዝቡ ለጉዞ ይዘጋጃሉ፣ በተንቀሳቀሰ ጊዜ መጓዝ ይጀምሩም ነበር፤ ደመናው በቆመበት ስፍራ ሊቆሙ በቆየበት ጊዜ ልክም ህዝቡ በአንድ ስፍራ ሊከርሙ ቁርጥ ነበር። ከዚህ የጉዞ ዝግጅት፣ እንቅስቃሴም ሆነ እረፍት አንድም ሰው ሊዘገይ ወይም ሊፈጥን አይፈቀድለትም፣ ብቻ በምንም መልኩ እንደ ትእዛዙ መንቀሳቀስ የተሻለ ስፍራ ያደርስ ነበር እንጂ በመቃወምና በቸልተኝነት የተሻለ ነገር የሆነበት አንድም ጊዜ አልነበረም።
2.ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ውስጥም የእግዚአብሄር ፈቃድ አለ
የእስራኤል ሰዎች ወደ ሲና በረሃ በገቡ ጊዜ እጅግ አስፈሪ የጸሃይ ግለት፣ የምድር ንዳድ፣ አውሎነፋስ፣ የምሽት ቅዝቃዜና የሚያንገበግብ ውሃ ጥም ቢጠብቃቸውም የጠራቸው እግዚአብሄር ግን ለነዚህ ሁሉ የተሻለ መፍትሄ በዚያ ጉዞ ውስጥ ነበረው፤ ህዝቡ ትእግስቱን ቢያሳይ፣ እግዚአብሄርን መጠበቅ ቢያውቅ፣ በእርሱ ቢተማመንና እግዚአብሄር ያውቃል ቢል ኖሮ ብዙ ተከታታይ መልካም ነገሮች ያለጥርጥር ይጎርፉ ነበር። አንድ ደመና ከሰማይ እስከ ምድር በአምድ መልክ በበረሃው የግለት ማእበል ውስጥ ሊጋርድ ሲቆም እግዚአብሄር የህዝቡ ጥላ ሆኖ (ለ3 ሚሊዮን የሚያክል ህዝብ) እንደቆመ በግልጥ ያመለክታል፤ መደገፊያነቱን በጉልህ በማሳየት በሙቀት እንዳይሰቃዩ የሚያደርግ የእግዚአብሄር የጥንቃቄ መገለጫ እንደሆነ አሳይቶአል። ያ አምድ በምሽት እንደ እሳት መልክ ሆኖና የምድረ-በዳውን ጨለማ ገፍፎ የህዝቡን ከባቢ ሁኔታ ሲያደምቅ የእርሱን አብሮነት፣ እንክብካቤም አብስሮአል። ሆኖም ያን ቢረዱ፣ ቢያደንቁና ቢያመሰግኑ ጉዞው አጭር ሰላማቸው የተጠበቀ በሆነ ነበር፣ እልፍ ሲሉ የሚጠብቃቸው የውሃ አለት፣ ሲርባቸው የመልአክት ምግብ… እረፍቱ ሁሉ ከሰማይ እንዲወርድ የአምላክ ዝግጅትና ፈቃድ ነበር።
በታሪካቸው ውስጥ እንደታየው የደመናው አምድ ህዝቡን ከጠላቶቻቸው ተከላክሎአል፤ ጠላት ሊያጠቃቸው በመጣ ጊዜ በዙሪያቸው ከለላ ሆኖ፣ በፊታቸውም ቢወጣ ብርሃን ሆኖ፣ በጠሉዋቸው ላይ ደግሞ ድቅድቅ ጨለማ በመሆንም ጭምር ሰርቶአል። እግዚአብሄር ፊቱን ለህዝቡ እንዲያ እያበራ ለጠላቶቻቸው ደግሞ አስፈሪ በሆነ መንገድ እየተገለጠ በምድረ- በዳ ከነርሱ ጋር ተጉዞአል። ቃሉ ሂደቱን ሲያመለክት እንዲህ ይላል፦
‘’በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ፥ በግብፃውያን ሰፈርና በእስራኤል ሰፈር መካከልም ገባ፤ በዚያም ደመናና ጨለማ ነበረ፥ በዚህ በኩል ግን ሌሊቱን አበራ፤ ሌሊቱንም ሁሉ እርስ በእርሳቸው አልተቃረቡም። ሙሴም በባሕሩ ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ሌሊቱን ሁሉ ጽኑ የምሥራቅ ነፋስ አምጥቶ ባሕሩን አስወገደው፥ ባሕሩንም አደረቀው፥ ውኃውም ተከፈለ። የእስራኤልም ልጆች በባሕሩ መካከል በየብስ ገቡ፤ ውኃውም በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ሆነላቸው።’’ (ዘጸ. 14:19-22)
የክብሩ ደመና ከህዝቡ ጋር በመጓዝ እስከ ተስፋይቱ ምድር አብሮአቸው ነበር፤ ደመናው በህዝቡ ፊት ከመቆም አልፎ በመገናኛው ድንኩዋን ላይም ይገለጥ ነበር፤ ህዝቡን አስጉዞ የተስፋይቱን ምድር በረገጡ ጊዜም በዚያ ታይቶአል። ይህ ደመና ከመገናኛው ድንኩዋን ወደ ሰለሞን መቅደስ በማለፍ በዚያ ውስጥ ተገልጦ በህዝቡ ፊት ታይቶአል፤ የክብሩ ደመና ከሰለሞን ቤተ-መቅደስ በኋላ ወደ ህያው መቅደስ ወደ ቤተክርስቲያን መጣ። እኛም ዳግም በተወለዱ የእግዚአብሄር ልጆች ላይ ተገልጦ በሚሰራበት የአዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ ተገኝተናልና፣ ዛሬ ማንም ክብሩን የሚፈልግ ቢኖር የእግዚአብሄር ክብር ሊገለጥለት ይችላል።
የክብሩ ደመና የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ በመሆን እግዚአብሄር በመጨረሻው ዘመን በሃይል ይሰራ ዘንድ ከሰው ህይወት ዙርያ አልፎ በህይወት ውስጥ በመዝለቅ፣ መንፈሱን በማፍሰስም እየሰራና ህዝቡን በድል እየመራ ይገኛል።
3.የሚጓዘው ህዝብና የጉዞው ባህሪ
ከግብጽ የወጣው ህዝብ ብዛት ምን ያህል ነበር? ወንዶች ተቆጥረው 600,000 ያህል ሲገመቱ አጠቃላይ ከሴቶችና ከህጻናት ጋር ከ2 -3 ሚሊዮን ይደርሱ ነበር። ከነርሱ ሌላ አብረው የወጡ ድብልቅ ህዝብም ነበሩ፤ እነዚህ ያልተገረዙ ህዝብ ሲሆኑ በጉዞ ውስጥ እያደር ለእስራኤል ፈተና ሆነው የተገለጡ ወገኖች ነበሩ።
‘’የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ፤ ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህል እግረኛ ነበረ። ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ። ከግብፅም ከእነርሱ ጋር ያወጡትን ሊጥ ጋገሩ፥ አልቦካም ነበርና ቂጣ እንጎቻ አደረጉት፤ ግብፃውያን በመውጣት ስላስቸኰሉአቸው ይቈዩ ዘንድ አልተቻላቸውም፥ ስንቅም አላሰናዱም ነበር። የእስራኤልም ልጆች በግብፅ ምድር የተቀመጡት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነው።’’ (ዘጸ. 12:37-40)
እስራኤላውያን የጉዞአቸውን መነሻ ያደረጉት ራምሴ ከሚባል ስፍራ ሲሆን ህዝቡ አስቀድሞ ጌሴም ምድር ይቀመጡ ነበር። እግዚአብሄር ህዝቡን ከተቀመጡበት አገር አንቀሳቅሶ ወደ ራምሴ የሰበሰባቸው በአላማ ነበር። እነርሱ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚያደርጉትን ረጅም ጉዞ አንድ ብለው ከራምሴ ጀመሩ። ራምሴ የባርነት ዘመናቸው መታሰቢያ ግንባታ ያለበት ስፍራ ነበርና፤ ከዚያም የባርነት ዘመን መታሰቢያ ስፍራ ወደ ነጻነት ስፍራ ጉዞን አንድ ብለው ጀመሩ፤ የነጻነታቸው ብስራት መባቻ በዚያ ሆነ። እግዚአብሄር ከእስራታችን ስፍራ ወደ ነጻነት ስፍራ ሊያስቀይረን ሲመጣ ጉዞአችንን ካደቀቀን፣ ከገዛንና ካሳፈረን ሰፈር በማውጣት እንደሚጀምር ማስተዋል መልካም ነው።
‘’እንዲህም ሆነ፤ ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ ምንም ቅርብ ቢሆን እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ምድር መንገድ አልመራቸውም፤ እግዚአብሔር፦ ሕዝቡ ሰልፉን ባየ ጊዜ እንዳይጸጽተው ወደ ግብፅም እንዳይመለስ ብሎአልና። ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን በዙሪያ መንገድ በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መራቸው። …ከሱኮትም ተጓዙ፥ በምድረ በዳውም ዳር በኤታም ሰፈሩ። በቀንና በሌሊትም ይሄዱ ዘንድ፥ መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሊያበራላቸውም ሌሊት በእሳት ዓምድ እግዚአብሔር በፊታቸው ሄደ።’’ (ዘጸ. 13:17 -21)
እስራኤል ወደ ነጻነታቸው ምድር እንደሚወጡ ይወቁ እንጂ የጉዞአቸው ፕላን በእግዚአብሄር እጅ ላይ ነበር፤ በፊታቸው መውጫ የሚሆኑ፣ መጉዋዝ የሚችሉባቸውም ሶስት መስመሮች ቢኖሩም የትኛውን መያዝና መጓዝ እንዳለባቸው የሚወስነው የጉዞው ባለቤት እግዚአብሄር ነበርና የሚያመለክታቸውን አቅጣጫ እስከሚያውቁ መጠበቅ ይገባቸው ነበር፤ አዎ ለምን አንደኛውን አይመርጡም ነበር፣ ሁለተኛውንና ሶስተኛውንስ ቢሆን? ቢሉ ወሳኙ እግዚአብሄር ብቻ ነውና እስኪያሳውቃችው ድረስ መጠበቅ፣ ሲናገርም መስማት የግድ ነበር፤ ቃሉ እንደሚያሳየውም ከግብጽ ራምሴ ተነስተው ወደ ከነአን ሊጉዋዙ ከሚችሉባቸው ዋና መስመሮች የመጀመሪያው ከባህሩ ዳር የሚነሳው መንገድ ነበር፤ መንገዱ ከዚያ በመነሳት የፍልስጤም ምድርን አቁዋርጦ ያልፋል፤ ይህ መስመር ቀጥተኛና አጭሩ መንገድ ነበር። ቅርቡ መንገድ እርሱ ቢሆንም እግዚአብሄር በዚያ በኩል እንዲጉዋዙ ለምን አልፈቀደም ብለን መጠየቃችን አይቀርም፤ እግዚአብሄር የተሻለውን አቁዋራጭ እያወቀ በዚያ እንዲጉዋዙ ለምን አልፈቀደም ማለት ይቻላል? ደግሞስ የህዝቡን ድካም ለምን አልተረዳም ብለን ማሰብስ እንችላለን? ወይስ እርሱ በድካማቸው የሚደሰት ነበር? ሊበቀላቸው ይፈልግ ነበርን? እንዲህ ያለ ብዙ ነገር ህዝቡም ሊያስቡ ይችሉ ነበር፤ እርሱ ግን ያን ያደረገው እነርሱ ያላዩትን ስላየ፣ እነርሱ ያልተጠነቀቁትን እርሱ ሊጠነቀቅላቸው ስለፈቀደና የማይቋቋሟቸው ባለጋራዎች እንዳይጎድዋቸው ወይም ወደ ዳግም ባርነት እንዳይመልሷቸው ስላዘነላቸው ብቻ ነበር፦ ያኔ በፍልስጤም ምድር ምን እየሆነ እንደነበር እግዚአብሄር አይቶአል፤ ፍልስጤማውያን ተዋጊዎችና በጦርነት የሰለጠኑ በመሆናቸው በወቅቱ በዙሪያቸው የተፈሩ ነበሩ፣ ስለዚህ እስራኤላውያን አይተዋቸው እንዳይፈሩ፣ ተስፋ እንዳይቆርጡና እጅ እንዳይሰጡ፣ እምነት እንዳያጡና እንዳይማረኩ እግዚአብሄር ወደ እነርሱ ምድር አልመራቸውም። ሁለተኛው መንገድ በመካከለኛ ስፍራ ከመጀመሪያው መንገድ አለፍ ብሎ የተቀመጠ ነበር፤ መንገዱም በቀጥታ በረሃውን አቁዋርጦ የሚያልፍ ነበር። እስራኤላውያን ጉዞአቸውን በዚያ በኩል ጀምረው ሳለ ኋላ ትተውት ነበር፤ በዚያ ስፍራ በግብጻውያንና በኬጢያውያን መሃል እየተደርገ ያለ ጦርነት ነበር። ግብጻውያንም መንገዱን ለመቁረጥ ረጅም ግንብ ገንተውበት ነበር፣ ግንቡ መጠበቂያ ነበረው፣ በዚያ ግንብ ዙሪያ የታጠቁ ወታደሮችም ነበሩ። እግዚአብሄር በፈርኦን ላይ ያቀደው ታላቅ ቅጣት ስለነበረው ያን መንገድ ከግብጻውያን አስለቅቆ እስራኤልን በዚያ በኩል ሊመራቸው አልወደደም። ሶስተኛው መንገድ ዙሪያ መንገድ የነበረ በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ በኩልም የተዘረጋ ነበር። እስራኤላውያን በግብጻውያን መከላከያ ግንብ ጎን አልፈዋል፣ ከዚያም ወደ ሲና ምድረ-በዳ አምርተዋል። በዚህ መንገድ በሄዱ ጊዜም የተቋቋማቸው አንዳች ሰራዊት አልነበረም፤ ስለዚህ የእግዚአብሄር ምሪት በዚያ መንገድ በነጻነት እስከ ሲና ተራራ ድረስ እንዲጉዋዙ ረድቶአቸው ነበር። እግዚአብሄር ይህን መንገድ ለሙሴ ባሳወቀው ጊዜ እንዲህ ብሎአል፦
‘’ሙሴም እግዚአብሔርን፦ ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ? አለው። እርሱም፦ በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም እንደ ላክሁህ ምልክትህ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ ለእግዚአብሔር ትገዛላችሁ አለ።’’ (ዘጸ. 3:11-12)
እግዚአብሄር የፈቀደው በሚያደክም መንገድ እንድንጓዝና እንድንደክም ነበር ሲሉ ህዝቡ ያስቡ እንጂ እርሱ የመረጠው መንገድ ለነርሱ ለዘለቄታ የሚበጃቸው እንዲያውም የተሻለ ነበር።