የዳዊት መዝሙር።
‘’ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ለቅኖች ምስጋና ይገባል። እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፥ አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት። አዲስ ቅኔም ተቀኙለት፥ በእልልታም መልካም ዝማሬ ዘምሩ፤ የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና። ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፤ የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች።’’(መዝ.33:1-5)
እግዚአብሄር በበጎነቱና በሰጪነቱ የታወቀ አምላክ ነው፤ ከሰጪነቱ ታላቅነት የተነሳ ቸር አምላክ ይባላል፤ ሰጪነቱ ህያው አድርጎ ለፈጠራቸው በሙሉ ቢሆንም በሰው ልጆች አንጻር ስንመለከተው ልዩ እንደሆነ እንገነዘባለን፣ያም በመሆኑ ለሰው ልጆች፦
የምንበላውን ሰጠን
የምንጠጣውን ሰጠን
የምንለብሰውን ሰጠን
የምንኖርበትን ምድር ሰጠን
ከክፉ መናፍስት ጠበቀን
ከአደጋ ጠበቀን
ምድር እንድትጸና አደረጋት
በውስጥዋ ያመቀውን እሳት የሰው ልጆችን እንዳያጠቃ ተከላከለ
ውሃ ዳግመኛ እንዳያጥለቀልቀን ባህርን አጸና፣ ዝናብን መጠነ
ሃሩር እንዳይፈጀን የጸሃይን ትኩሳት ገደበ
የምንተነፍሰውን ሰጠን.. የሚያስፈልገንን ሁሉ ከርሱ ተቀበልን፣ የሆነው ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ሆነልን፤ እናም አያልቅ ሆኖ ነው እንጂ አስተውለን እለት ተእለት እንኩዋን የሚደረግልንን ብንቆጥር የአምላካችን የምስጋና ባለእዳዎች እንደሆንን እናውቃለን። እግዚአብሄርን ስለቸርነቱ ማመስገን ከህዝቡ በተለይ ይጠበቃል፣ በእውቀት ከአምላኩ ጋር ስለሚኖር፣ የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ስላገኘ ጭምር፤ እግዚአብሄር እስራኤላውያንን በታላቅ ቸርነት ከግብጽ ባወጣ ጊዜ የሙሴ ሚስት አባት ሰምቶ ደስ አለው፦
ዘጸ.18:9 ‘’ዮቶርም እግዚአብሔር ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ፥ ከግብፃውያንም እጅ ስላዳናቸው ደስ አለው።’’
ዮቶር እግዚአብሄር እስራኤላውያንን በያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው እንደረዳቸውና በብዙ ቸርነት እንዳወጣቸው ሰምቶ ነበርና ያን አስተውሎ እግዚአብሄርን አመሰገነ። ዮቶር የልጁ ባል ሙሴና ወገኖቹ እንደምን ባለ ድህነት፣ ጉስቁልና፣ ባርነት፣ ጭቆናና በሚደርስባቸው በደል በብዙ ምሬት ውስጥ እንደነበሩ ከሙሴ ሰምቶ ሳያውቅ አልቀረም፤ አሁን ግን ሆኖ ባየው ተቃራኒ ነገር ተገረመ፦ ከግብጻውያን መሪር በትር የተነሳ ሃዘንተኛ የነበረው ህዝብ አሁን ተደስቶአል፣ ፈሪ የነበረው ህዝብ በእግዚአብሄር ድፍረት አግኝቶአል፣ ደሃው ህዝብ ባለጠጋ ሆኖአል፤ እናም ያን ሲያስተውል ከአዘቅት ህዝቡን ያወጣውን አምላክ አመሰገነ። እግዚአብሄር ህዝቡን የሚመግበው ከሰማይ በሚያዘንበው የመላእክት ምግብ እንደሆነ ሲያውቅ፣ ሲጠሙም ይጠጡ ዘንድ ከአለቱ ውሃ እያፈለቀላችው እንደሆነ ሲያስተውል፣ የአምላካቸውን ድምጽ እንዲሰሙ በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሄር በክብር እንደተገለጠላቸው ሲያውቅ እጅግ ደስ አለው፤ ባህሩን እንደከፈለላቸው፣ ጠላቶቻቸውን በጥልቁ እንዳሰጠመላቸው፣ ቀን በደመና ሌት በእሳት አምድ በምቾትና በጥበቃ እየመራችው እንዳለ ሁሉ አየ ሰማናም ቸሩን እግዚአብሄርን አመሰገነ። እስራኤላውያን ቢያስተውሉ ኖሮ ስለቸርነቱ እዚአብሄርን ከዮቶር አልቀው ባመሰገኑ ነበር፣ የተደረገላቸው እነርሱ ነበሩና።ምስኪኖቹ እስራኤላውያን በአንድ ቀን በሃብት እንዴት ተጥለቀለቁ? ይሄን ቸርነት ማን አሳያቸው? የግብጾችን ወርቅና ጌጣጌጥ እንዴት እንዳሸከማቸው ባይረሱ ኖር ያመሰግኑት ነበር፣ በጭካኞችና አስፈሪዎች አማሌቃውያን ላይ እንዴት ያለ ድል እንደሰጣቸው ባይረሱ ኖሮ ድምጻቸውን በምስጋና ከፍ ባደረጉ ነበር፣ በሙሴ እጅ እንዴት ከፍ ያለ አምላካዊ ህግ እንደተቀበሉ ሁሉ ቢያስተውሉ እጅግ ባመሰገኑ፣ ደግመው ደጋግመው በዘመሩ ነበር። ከተደረገለት ይልቅ ታምራቱ ለሌሎች ሲደረግ ሰምቶ ያመሰገነው ግን እንዲህ አለ፦
‘’ዮቶርም፦ ከግብፃውያንና ከፈርዖን እጅ ያዳናችሁ፥ ከግብፃውያንም እጅ ሕዝቡን ያዳነ እግዚአብሔር ይባረክ። ትዕቢት ባደረጉባቸው ነገር እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አሁን አወቅሁ አለ። የሙሴ አማት ዮቶርም የሚቃጠል መሥዋዕትንና ሌላ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ወሰደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከሙሴ አማት ጋር እንጀራ ሊበሉ አሮን የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ።’’ (ዘጸ.18:10-12)
እግዚአብሄር የሰጠን ስጦታ ከርሱ ውጪ የሆነ አይደለም፣ ደግሞም ከርሱ በቀር ያቀርበው ዘንድ ቻይ ስለሌለ መመኪያችንና መደገፊያችን የሚሆንበት ምክኒያት ይህ ነው፤ ከነዚህ አንዱ ቢጎድል የመኖር ዋስትናችን ይቆረጣልና።
መዝ.25:5-11‘’አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና። የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ።እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።ገሮችን በፍርድ ይመራል፥ ለገሮችም መንገድን ያስተምራቸዋል። የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው። ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ።አቤቱ፥ ኃጢአቴ እጅግ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ።’’
የእግዚአብሄርን ማንነት ያስተዋለ ንጉስ ዳዊት የአምላኩን ቸርነት አጥልቆ ሲመለከት ይህ አምላክ ከእለት ተእለት አቅርቦት ያለፈ ስጦታ እንዳለው ተረድቶአል፣ ባየውአምላካዊ እጅ ውስጥ፦
አምላክ በቸርነቱ በእውነት እንደሚመራ አውቆአል
ይህ አምላክ ቸርነት አድርጎ መለኮታዊ ትምህርት እንደሚሰጠው አውቆአል
ይህ ቸር አምላክ አሻግሮ ለሰው ልጅ የሚያደርገውን ያሳውቅ ዘንድ ተስፋ እንደሚሰጥ አውቆአል
ይህ ቸር አምላክ ምህረትን የሚሰጥ አምላክ እንደሆነ አውቆአል፦ ከምህረቱ የተነሳም ኃጢአትና መተላለፍን እንደሚተው አውቆአል፣ እንደ ቸርነቱ ብዛት በምህረት እንደሚያስብና ከሃጢያት ፍርድ እንደሚታደግም አውቆአል
ይህ ቸር አምላክ ቅን ስለሆነም ኃጢአተኞችን በደህንነትና ቅን በሆነ መንገድ ይመራቸዋል የሚል መረዳት ይዞአል
ይህ ቸር አምላክ ገሮችን በፍርድ እንዲመራም አውቆአል
በዚህ ሁሉ እግዚአብሄር የሚገልጠው መንገድ መሰረቱ ቸርነትና እውነት መሆኑን ጨምሮ ተረድቶአል። የዚህ ልዩ ቸርነት ተቋዳሾች ግን የትኛውም ፍጥረት ሳይሆን እግዚአብሄር በተለይ የሚያያቸው በጽድቅ የሚከተሉትና የሚገዙለት ሰዎች ብቻ ናቸው። በመዝ.31:19 እንዲህ ተብሎአል፦
‘’በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት፥ ቸርነትህ እንደ ምን በዛች!’’
ንጉሱ ዳዊት በዚህች ቸርነት እግዚአብሄር ሰውን የሚባርክበት ምክኒያት በርሱ ላይ ባለ እምነትና አምላክነቱን በመቀበሉ እንደሆነ ተናግሮአል፤ የመንግስቱ ርስት በንጉሱ በእርሱ ዘንድ ሳይሆን በአምላኩ እጅ መሆኑን ስለተረዳ፣ ምንም ሃያል ቢሆን ዋናው ተዋጊና የድል ምንጭ እግዚአብሄር ብቻ መሆኑ ስለገባውም ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ ሲል ሊጣራ ችሎአል። ከዚህ ማስተዋል በመነሳት ሲናገር፦
‘’በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት፥ ቸርነትህ እንደ ምን በዛች!በፊትህ መጋረጃ ከሰው ክርክር ትጋርዳቸዋለህ፥ በድንኳንህም ከአንደበት ክርክር ትሸፍናቸዋለህ። በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን በእኔ የገለጠ እግዚአብሔር ይመስገን። እኔስ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፥ በድንጋጤ አልሁ፤ አንተ ግን ወደ አንተ በጮኽሁ ጊዜ የልመናዬን ቃል ሰማኸኝ። ሁላችሁ ቅዱሳኑ፥ እግዚአብሔርን ውደዱት፤ እግዚአብሔር እውነተኞችን ይፈልጋል፥ ትዕቢተኞችንም ፈጽሞ ይበቀላቸዋል። በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ፥ በርቱ ልባችሁም ይጥና’’ (መዝ.31:19-24)
አስቀድሞ እንደተባለው ይህችን ልዩ መለኮታዊ ቸርነት ለመቀበል ቅርበት፣ መታመን፣ እርሱን መውደድ፣ መፍራትና በፊቱ በእውነት መመላለስን ይፈልጋል። በዚህ መንገድ ላሉ ቸርነቱ ብዙ ነው፣ ቸርነቱ ሁሌ የደህንነት መንገድን ሰጥታ ልጆችን ትመልሳለች፣ ታቀናለች፣ ታድናለችም። የአብረሃም ዘሮች በመንገዳቸው ሁሉ እጅጉን በድለው ሳለ በእያንዳንዱ የፍርድ መንገዳቸው ላይ ቸርነትና ምህረቱን በትግስት ሲያስቀድም እናያለን፤ ነህ.9:15-20 እንደሚለው፦
‘’ለራባቸውም ከሰማይ እንጀራ ሰጠሃቸው፥ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃ አመጣህላቸው፤ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው ይወርሱ ዘንድ አዘዝሃቸው።ነገር ግን እነርሱና አባቶቻችን ታበዩ፥ አንገታቸውንም አደንደኑ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ለመስማትም እንቢ አሉ፥ ያደረግህላቸውንም ተአምራት አላሰቡም፤ አንገታቸውንም አደንደኑ፥ በዓመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ይመለሱ ዘንድ አለቃ አደረጉ፤ አንተ ግን ይቅር ባይ፥ ቸርና መሐሪ አምላክ፥ ለቍጣም የምትዘገይ፥ ምሕረትንም የምታበዛ ነህ፥ አልተውሃቸውም። ቀልጦ የተሠራውንም እምቦሳ አድርገው። ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው ባሉ ጊዜ፥ እጅግም ባስቈጡህ ጊዜ፥አንተ በምሕረትህ ብዛት በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ በመንገድም ይመራቸው ዘንድ የደመና ዓምድ በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ ያበራላቸው ዘንድ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከእነርሱ አልራቀም።ያስተምራቸውም ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፥ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፥ ለጥማታቸውም ውኃ ሰጠሃቸው።’’
ነህሚያ በህዝቡ ላይ ሲመሰክር አንተ ‘’ያደረግህላቸውንም ተአምራት አላሰቡም አንተ ግን ቸርና መሐሪ አምላክ፥ ለቍጣም የምትዘገይ፥ ምሕረትንም የምታበዛ ነህ፥ አልተውሃቸውም’’ ይላል። አዎ እግዚአብሄር በምህረቱ ቸር ነው፤ በቸርነቱ ምክኒያት ምህረቱ አያልቅም፤ የእኛ ድካም፣ ሃጢያት፣ በደልና መተላለፍ አያበቃምና፣ ሰዎች ስለሆንን፣ ደካሞች ስለሆንን፣ ስጋ ስለለበስን ከዚህም በላይ እየሆንን እጁ ሰፊ የሆነ አምላክ ይፈልገናል፣ ጥፋታችንን ስለማይፈልግም እስክንመለስ ይታገሰናል። ይህን የሚያውቅ አምላክ በእኛ ላይ ተስፋ ቆርጦ ምህረቱን አያቋርጥም፣ ይህ ህልውናችን በመሆኑ ፈጽሞ አይተወንም፤ እንዲያ ባይሆን ኖሮ ከእርሱ ውጪ እንዴት መቆየት እንችል ኖሮአል? ነገር ግን በበደልን ቁጥር እንደቸርነቱ ብዛት ምህረቱ ሳታቋርጥ ከእርሱ ዘንድ ወጥታ እኛን ታገኘናለች ለኛም ማምለጫ ይሆናል።
መዝ.57:2-3 ‘’ወደሚረዳኝ እግዚአብሔር ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጮኻለሁ።ከሰማይ ልኮ አዳነኝ፥ ለረገጡኝም ውርደትን ሰጣቸው፤ እግዚአብሔር ቸርነቱንና እውነቱን ላከ።’’
ከሰማይ የሚላክ ቸርነትና እውነት የሚመጣው የሰው ልጆችን ለመርዳት ነው፤ ይህ እውቀት ለአማኞች ዋስትና ነው፤ በዚህም እግዚአብሄር እጅግ ሊመሰገን ይገባል።
1ዜና.16:34-35 ‘’ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ። የመዳናችን አምላክ ሆይ፥ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ ሰብስበህ ታደገን በሉ።’’
በደግነቱ፣ ባልተቆጠበ ስጦታው፣ በምህረቱ፣ በማዳኑና በርህራሄው የሚታወቀውን የእስራኤል አምላክ ቅዱሳኑ ለቀረው አለም ያሳዩ ያሳውቁም፤ አለምም በእርሱ ቸር ስጦታ ይባረክ ዘንድ ልቡን ወደዚህ አምላክ ያዘንብል፣ ምህረቱ ከስጋዊ በረከት ባለፈ ለነፍስና ለመንፈስ የሚተርፍ ነውና፣ ወዳጆቹም በዚህ የተባረኩ ናቸውና። እግዚአብሄር እንደልቤ የሆነ ያለው ንጉስ ዳዊት የእግዚአብሄር ቸርነት እንደምን የበዛችና ለየትኛውም ነገሩ የተስፋው ምንጭ እንደሆነች ያስተዋለ ሰው ነበር፤ በእውቀቱም ተጠቅሞአል። እናስታውስ ከሆነ እግዚአብሄር ይህንን ሰው የጠራው ገና በብላቴንነቱ ጊዜ፣ ማንም ልብ ሊለውና ሊመለከተው በማይችልበት የእረኝነት ምድረ-በዳ ሳለ ነበር፣ እግዚአብሄር ግን ከዚያ አንስቶ ቀባው፣ ባረከው፣ ተጠነቀቀለት፣ ከእርሱ ጋር በየስፍራው ተመላለሰ፣ ከጠላትም እጅ ብዙ ጊዜ አስጣለው፣ ጠበቀው፣ በመጨረሻም ቃል እንደገባለት አነገሰው፣ ቃል እንደገባለትም ከእርሱ ዘር ነገስታት ወጡ፣ እንደነገረውም የነገስታት ንጉስና የጌቶች ጌታ የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ በርሱ የዘር ግንድ ውስጥ አልፎ በስጋ መጣ። ቸር ነውና፣ ምህረቱም ለዘላለም ነውና፣ ቃል ኪዳኑን አይረሳምና፤ ስለዚህ እርሱ እንዲህ አለ፦
‘’እግዚአብሔርን ከእኔ ጋር ታላቅ አድርጉት፥ በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ። እግዚአብሔርን ፈለግሁት መለሰልኝም፥ መከራዬም ሁሉ አዳነኝ። ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፥ ፊታችሁም አያፍርም። ይህ ችግረኛ ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ሰማው፥ ከመከራውም ሁሉ አዳነው። የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል። እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው።’’ (መዝ.34:3-8)