የእግዚአብሄር ቸርነት በአዲስ ኪዳን

የእውነት እውቀት

መዝ.106:1-4 ‘’ሃሌ ሉያ፤ ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ። የእግዚአብሔርን ኃይል ሥራ ማን ይናገራል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ያሰማል? ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ምስጉኖች ናቸው።አቤቱ፥ በሕዝብህ ሞገስ አስበን፥ በመድኃኒትህም ጐብኘን’’
እግዚአብሄር የትውልድ ሁሉ አምላክ ስለሆነ በብሉይ ኪዳን ለፍጥረት ያደረገውን ቸርነት በአዲስ ኪዳንም በተመሳስይ ሁኔታ የቀጠለበት አጋጣሚ ነው አሁንም የሚታየው፣ ያለ እግዚአብሄር ፈቃድ የበላና የጠጣ በየትኛው ዘመን ታይቶአል? ይህ በእንዲህ እንዳለ ከብሉይ ኪዳን በተለየ መንገድ እግዚአብሄር ለሰው ልጆች የሰጠውን ልዩ የቸርነት አሰራር ደግሞ እናገኛለን፣ እንዲህ ስለሚል፦
‘’እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን። ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም’’ (ቲቶ.3:3-5)
በብሉይ ኪዳን ቸርነቱ ሳይቋረጥ ሰውን እየረዳ፣ እያገዘ፣ ጉድለትን እየሞላ፣ በሚያስፈልገው ሁሉ የእግዚአብሄርን እርዳታ ሲያቀርብ ቢኖርም የትኛውም የሰው ልጅ ከነበረበት የማስተዋል ችግር ሊላቀቅ አልቻለም፣ ለእግዚአብሄር የሚታዘዝ አልሆነም፣ ከስጋዊነት፣ ከአለማዊነትና ከመናፍስት ጥቃት ነጻ ሊወጣ አልቻለም፣ በአዲስ ኪዳን ግን ነጻ የሚያወጣ የእግዚአብሄር እርዳታ ተገለጠ።
ይህ በአዲስ ኪዳን የተገለጠው የእግዚአብሄር ቸርነት በስጋ በተገለጠውና አማኑኤል በሆነው በራሱ በአምላካችን ጊዜና አጋጣሚ በኩል ነው። የእግዚአብሄር ቸርነት ያውም የሚያድን ቸርነት፣ እርሱም ዳግም እንድንወለድ የሚያደርግ ቸርነቱ ሲገለጥ በማንነታችን ላይ ፍጹም ለውጥ በማድረግ መንፈሳችንም ዳግም እንዲወለድ አድርጎአል። ይህ የእግዚአብሄር ቸርነት ጸጋ የተባለ ሰውን የሚያድን፣ የሚያግዝ፣ የሚሸከም፣ የሚመራና ለእግዚአብሄር መንግስት የሚያበቃ አሰራር ሰጠን።የእግዚአብሄር ቸርነትና ሰውን የወደደበት መውደድ የተገለጠው እግዚአብሄር በስጋ ተገልጦ በእኛ መሃል በመገኘቱ ነበር። በእኛ መሃል የተገኘው ሰማያዊ ሰው የአዳም መልክና ቁመና ያለው ግን ሰዋዊ ነገር የሌለበት ነበር። እሱም እኛን የሚያድንበት ታላቅ የማዳን ቸርነት ይዞ ተወለደ፣ ቃሉ ይህን ሲያበስር እንዲህ አለ፦
ዮሐ.1:14 ‘’ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።’’
ከእግዚአብሄር አፍ የወጣ ቃል ስጋ ሆኖ ከሴት ማህጸን በወጣ ጊዜ ልጅ ተባለ፣ ይህ ልጅ የተባለው ሰው ክርስቶስ ኢየሱስ ሲሆን በአዳም ልጆች መሃል የተገኘው ከእግዚአብሄር የሆነ ጸጋን፣ እውነትን፣ መንፈስን፣ቃልን በውስጡ ይዞ ስለተግለጠ በእርግጥም በሁሉ ነገር ሰውን መርዳት የሚችል ነው፤ይህ የእግዚአብሄር ልጅ በሰው በኩል ወደዚህ አለም ገብቶ የታየው የተዳሰሰው የእግዚአብሄር የባህሪ ምሳሌና የእግዚአብሄር ክብር መንጸባረቅ እርሱ ነው፤ እርሱም በተወለደ ጊዜ አንድ ነገር ሆነ፣ የመለኮት ክብር ውስጥ የሚታየውን ምሳሌ ሳይሆን የአዳምን ምሳሌ ወሰደና እኛን (የሃጢያት ባሪያ የሆንነውን) መስሎን ተመላለሰ፣ ይህም የሆነው እኛን ያድን ዘንድ የእኛን የሃጢያተኞች ምስል (በመልኩ እንጂ በስጋው ግን ያልሆነውን) በመውሰድ ስለተገለጠ ነው፤ ይሄን እውነት ሃዋርያው ጳውሎስ በፊል 2:4-8 አብራርቶ ይናገረዋል፦
‘’እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።’’
ጌታ ክብሩን በመጣሉ እርሱ ተጎድቶ እኛን የጠቀመ ነገር አውጥቶአል፦ደሙ ፈስሶ ስጋው ተቆርሶአል፣ የርሱ መከራ የኛን መዳን አምጥቶአል፣ ከዚያም አልፎ የዘላለም ህይወትና መንግስቱን በሰጠን ጸጋ በኩል እንድንውርስ ተስፋ ሰጥቶናል።
ይህ ባለጸጋ ጌታ ሳይወለድ በፊት የምስራች ድምጽ የሰማ ነቢይ ነበር፣ የእግዚአብሄር ቸርነት ከጥልቅ ፍቅሩ ውስጥ የሚያወጣው መዳን ይገለጥ ዘንድ እንደምን በራሱ ልጅ ላይ (መገለጫ ሰውነት ላይ) ታላቅ ፍርድ እንዳሸከመው ( በርሱ ላይ ጭከና ያለበት ውሳኔ፣ ስለእኛ ከመርገም መትረፊያ ጸጋን እንቀበል ዘንድ ሆኖ) የተመለከተው ነቢይ ይህን ታላቅ ትንቢትና ራእይ በኢሳ53 ላይ ሊያሰፍረው በቅቶአል፣ በትውልዱ ባይገለጥም የዚህ ታላቅ መዳን ትንቢት በዚያ የመጽሃፍ ክፍል ላይ ለሚመጡ ትውልዶች ምስክር እንዲሆን ተቀመጠ፤ እኛስ ዛሬ ላይ ያንን እንዴት እናየዋለን?
ሮሜ.2:4-7 ’’ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ። እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤ በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል’’
የደህንነት ስጦታ እግዚአብሄር ሲሰጠን ከነበረው እጅግ የበዛ ስጦታ መሃል ልዩ ሆኖ የተገለጠ ስጦታ ነው፤ ይህ የደህንነት ስጦታ የክርስቶስ ጸጋ ነው። ይህ ስጦታ ከሰው ልጆች ህይወት ጋር የተያያዘ ነው፤ ምክኒያቱም ጸጋ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ከእግዚአብሄር የተገለጠ በመሆኑ ነው። ጸጋ የተቀበለ ማንም ሰው ህይወቱ ይለወጣል፣ እለት በእለት ወደ ፍጹም ሙላት ያድጋል፣ ክርስቶስን እስኪመስልም ይለወጣል።
ስለዚህ የሰውን ህይወት የሚለውጥ አስደናቂ ስራ የሚገለጥበት ይህ ጸጋ እግዚአብሄር ለሰው ልጆች የሚሰጠው ያልተቆጠበ እርዳታ፣ አድሎ የሌለበት ስጦታ፣ ምላሽ የማይፈልግ ገጸ-በረከት፣ ኢፍትሃዊነት የማያውቀው የእግዚአብሄር ቸርነት፣ የእግዚአብሄር ፍቅር የተሞላ ስጦታ ነው። የጸጋ መሰረታዊ ይዘት የእግዚአብሄር ፍቅር ነው፤ በዚህ መሰረት በጸጋው ውስጥ ፍቅሩ ማዳኑና ምህረቱ ለሰው ልጆች ተገልጦአል። ጸጋ እግዚአብሄር ከሰው ልጆች የታረቀበትን መንገድ ይዞአል፣ እግዚአብሄር ለሰው ይቅርታውን ገልጦበታል፣ በጽድቅ የመኖር ሃይልንም በጸጋው በኩል ሰው ተቀብሎአል። በጸጋው ምክኒያት የሰው ልጅ ከእግዚአብሄር ታላላቅ በረከትን አግኝቶአል፤ በጸጋው ምክኒያት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ወርዶአል።
ጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ብቻ ይገኛል፤ ይህም የእግዚአብሄር አሰራር ነው። ማንም ሰው ጌታ ኢየሱስ ጸጋን እንደሚሰጥ ቢያምን ከእርሱ በሚወጣው መንፈስ በኩልና ባመነው ልክ ይቀበላል።
ሰው በህግ ምክኒያት መተላለፉና ሃጢያቱ ተገልጦ ባለበት ሁኔታ፣ ከእግዚአብሄር መገኛ አካባቢ ጠፍቶም ሳለ ጸጋ በመምጣቱ ምክኒያት በህይወቱ አዲስ አሰራር ተገለጠ፤ ከእግዚአብሄር ጋር ጥል ውስጥ የነበረው የሰው ዘር ሁሉ ወደ እግዚአብሄር መቅረብና ከእርሱ ጋር መኖር የሚችልበትን አቅም ተቀበለ።
(ዮሃ.1:14-17) ‘’ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።’’
ጸጋ በሰው ህይወት ውስጥ ሲገለጥ እንደ ባለጠግነቱ መጠን ህይወታችን ውስጥ የርሱ የጽድቅ ስራ ይገለጣል፤ ሰዎች እንዳይችሉ ሆነው መንፈሳቸው በሃጢያት ቢሰበርም ጸጋው በህይወታቸው ገብቶ የማስቻል ስራን ይሰራል፤ ሰዎች ጸጋ ሲሞሉ ከአምላካቸው የተቀበሉትን በጎነት ለሌላ ሰው ያሳያሉ፣ በአምላካቸው ተምረዋልና እነርሱም ምህረት ያደርጋሉ፤ ጌታ ኢየሱስ ስለወደዳቸው በውስጣቸው የፈሰሰው የጸጋ መንፈስ ሰውን እንዲወዱ፣ በፍቅር ሰውን እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል፣ በጸጋው መንፈስ የተቀበሉት ወንጌል እንዳዳናቸው ሁሉ ለሌሎች የእርሱን በጎነት ያካፍሉ ዘንድ ይወዳሉ። ይቅር ያላቸውን አምላክ ስለሚያከብሩ ጸጋው ይቅር ባይ ያደርጋቸዋል።
ጸጋ በቤተ-ክርስቲያን ህብረትን ይፈጥራል፤ አማኞች በአንድነትና በፍቅር እንዲኖሩ እርስ በርስ ያስተሳስራቸዋል። ጸጋ እያንዳንዱ የአካሉ ብልት አንዱ ሌላውን እንዲቀበል በማድረግ በፍቅር ያዋህዳል። በሰዎች መሃል የሚሰፍን መልካም አመለካከት በጸጋ ብቻ የሚፈጠር ነው፤ ወንድማማችነት፣ መቀባበል፣ መተሳሰብ፣ ራስ ወዳድነት የሌለበት የፍቅር ህይወት በጸጋው መንፈስ አማካይነት በቤተክርስቲያን እንዲኖር ያስችላል።
ሰዎች ክፉን ከክፋቱ ነጥለው ደካማውን በርህራሄ እንዲመለከቱ የሚያስችላቸው በህይወታቸው ጸጋ ሲሰራ ብቻ ነው፤ ደካማን አንድ ቀን ይበረታል ብለው አርቀው የሚያዩለት፣ በዚያ ሸክም የሚሸከሙት ጸጋ ሲኖራቸው ነው። ጸጋ ከሰው ልጆች ህይወት ውስጥ መሰላቸት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ መድከም፣ ያለማመንና የመሳሰሉ በጎነትን የሚገድሉ ነገሮችን ከውስጥ በማውጣትእየሆኑ ያሉትን ማናቸውንም ነገሮች በእግዚአብሄር የተስፋ ቃል መነጽር በኩል የሚመለከቱ በጎ ሰዎች ያደርጋል።
ሃስ.4:3233 ‘’ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም። ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው።’’
የጸጋ ስጦታን ስናስብ ከእግዚአብሄር በመንፈሱ አማካኝነት የምንቀበለው አንድ ከሰው ልጆች ነባራዊ አመለካከት፣ አኗኗር፣ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር አውጥቶ ወደ እግዚአብሄር አሳብ ውስጥ የሚያስገባ አስቻይ ጉልበት ሆኖ እናገኘዋለን። ጸጋ ከእኛ፣ ለእኛና በእኛ ከሚሆን እውቀት፣ ጉልበትና አመለካከት ውጪ በሆነ አሰራር ልናደርጋቸው የማንችላቸውን በእግዚአብሄር አሳብ ውስጥ ያሉ ለሰው ልጆች ግን ሊሆኑ የተገባቸውን ነገሮች እንድንቀበል፣ እንድናከናውንና እንድንኖርበት የሚያስችል ጉልበት ነው።
ማርያም ከእግዚአብሄር ስለምትቀበለው ጸጋ ከመላኩ የተነገራት ቃል አስደናቂ ነው፦
‘’መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና፦ ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።’’ (ሉቃ1:28-31)
ቃሉ የሚያሳየን የእግዚአብሄር ጸጋ የሰው ልጅ ሊኖር የሚገባውን የህይወት ጥራት የሚያጎናጽፍ አምላካዊ ስጦታ መሆኑን ነው፣ ያም ክርስቶስን በህይወታችን እንዲኖር ያደርገዋል። የሰው ልጆች ከእግዚአብሄር ጋር ከታረቁ በኋላ በስምምነት ከርሱ ጋር መኖር የሚችሉት እንደተማሩበት ምህረት በመኖር ብቻ በመሆኑ ከዚያ የህይወት ጥራት እንዳይወድቁና ወደቀድሞ የጥፋት አሰራር ውስጥ እንዳይገቡም በጸጋው ይደገፋሉ።
አምላካዊ በጎነት የሰውን ህይወት ወደ መልካም ጎዳና የሚመራ ነው፣ ይህ የእግዚአብሄር በጎነት የሰውን ልጅ ማንነት በአዲስ መንገድ የሚገነባና መንፈሳዊ ህይወቱን የሚያሳድግ ነው። የሰው ልጅ በሙሉ አምላኩን ሲጠጋና ሲከተል በህይወቱ የሚገለጥ ልምላሜ ምክኒያቱ በቀጥታ እግዚአብሄር ከሚሰጠው ጸጋ ጋር የተገናኘ ነው።
የሰማይ አምላክ የጸጋ አምላክ ሲሆን ሰባዊ ማንነትን ከፍ ወዳለ ባህሪና አስተሳሰብ የሚያወጣበት አሰራርን ሲገልጥ ጸጋን ሰጠን። ወሰን በሌለው በዚህ አምላክ የእኛ እጅግ የደከመ ባህሪ ከገባበት ውድቀትና የሰይጣን የክፋት ውርስ ተነጥቆ እንዲወጣ የእግዚአብሄር በጎ ስጦታ ያስፈልገዋል። መለኮታዊ እርዳታ እያንዳንዱን የሰው ልጅ የህይወት አቅጣጫ ሊያስለውጥና ወደ እግዚአብሄር መገኛ አቅጣጫ እንዲመራ ማወቅ ብቸኛው ማምለጫ ነው።
የእግዚአብሄር ስጦታ ፈጽሞ ክፍያ አይፈልግም፤ ምትክ አይፈልግም፤ ምላሽም አይፈልግም። በክርስትና ውስጥ ጸጋ ወደ እግዚአብሄር ለመቅረብና ለመታረቅ፣ ለሃጢያት ስርየትና በደህንነት ለመኖር መሰረት ነው። በማስተዋል ሆነን ብንፈልገውና ብንመኘው ከቸር አምላክ ልንቀበል የምንችለው ነው፤ ሩህሩና ፈቃር አምላክ ሊቀርበን እንደሚፈቅድ ካላወቅን ግን እንዲጠጋን አንፈልግምና የርሱን ቸርነት ቸል እንለዋለን፤ እግዚአብሄር ኤልሻዳይ መሆኑ ካልተገለጠልን ደግሞ የፍጥረታት ባለቤት መሆኑንም አንቀበልም፤ ቸር መሆኑን እንዲሁ ካላስተዋልን አንጠይቀውም፣ እንዲያውም የምንጠይቀውም ይጠፋናል፤ እንደሚበልጠን በቃሉ ካላረጋገጥን እንንጠራራና እኩያ እናደርገዋለን፤ ባህሪውን አልለየንምና እንዳፈረዋለን፤ መንፈሳዊ አስተውሎ ስላልተጎናጸፍን ፈቃዱን አንረዳም ስለዚህ ክአሳቡ ጋር ትውውቅ የለንም፣ አንከተለውም፣ አናምነውም፣ የዚህ አደጋ ደግሞ ዞሮ ጥፋት ላይ የሚጥለን ነው የሚሆነው።
በኛ ዘንድ ያለ ውስንነትና የሞራል ውድቀት ከገዛን ግን እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ያዘጋጀውን በጎ ምኞት፣ ወሰን የሌለው ፍቅርና ምህረት ከማስተዋል እንገደባለን። ተስፋ የሚሰጠው ግን የእግዚአብሄር ጸጋ በውስጣችን የገነገነውን እምቢተኝነት በመንፈስ ሃይል የሚሰበር መሆኑ ነው። ይህ መለኮታዊ ስጦታ በክርስቶስ ኢየሱስ መከራ መቀበል፣ መሰቀል፣ መሞትና ከሙታን መነሳት ምክኒያት የመጣ ነው። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስን ለተቀበልን የጸጋው ስጦታ ተጠቃሚ ሲያደርገን በተቃራኒው ጌታ ኢየሱስን ያላመንን ጥፋት ውስጥ እንደሚጥለን እርግጠኞች መሆንና ማስተዋል አለብን። ቸሩ ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን።