የመገለጡ ምክኒያት
ስለሰው ጥቅም መሆኑ ዋነኛው ምክኒያት ነው፦
– በእይታ ውስጥ መገኘት
እግዚአብሄርን ያየ አንድ ስንኩዋ የለም የሚል እርግጠኛ የእግዚአብሄር ቃል እያለ እንዲሁ በሆነ ስፍራ ”አየነው” የሚል ተቃራኒ የሚመስል ቃል ብናገኝ ግርታ መፈጠሩና መደናገር ሊሆን ግድ ነው የሚሆነው፤ ሆኖም ከመለኮታዊው እቅድ አንጻር የሚያስደንቅ ሊሆን አይችልም፤ ዋናው ነገር ግን የማይዋሽ እግዚአብሄር የተናገረውን ሁሉ በራሱ መንገድ ሊገልጠው እንዳለው ማወቅና ያን ችሎታውን ማመን ነው፤ የሚገልጠውን ጥበብ በማመን መቀበል እንዲሁም እንደተቀበልነው በማስተዋል መራመድም ጠቃሚ የህይወት መርህ ነው፡፡
”መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።” (ዮሐ.1:18)
ኢዮብ ግን በእምነት እንዲህ ያለው ለምንድነው? ”እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል።”(ኢዮ.19:25-28)
እውነቱ የትኛውም ትውልድ መንፈስ የሆነ እግዚአብሔርን አካል ኖሮት ያላየው መሆኑ ነው፤ ቢሆንም አንድ የሚታይበትን መንገድ እግዚአብሄር እንዳቀደ ደግሞ በመንፈስ ማመልከቱ እርግጥ ነው፤ ይህም እቅድ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ሊተርከው፣ እግዚአብሄር እርሱ ብቻ አምላክ መሆኑን ሊያሳይና ሊገልጠው እንደሚችል ቃሉ በአጽንኦት ይናገራል።
ስለዚህ ለኢዮብ በመንፈስ የተተረከ እውቀት እግዚአብሄር በስጋ እንዲገለጥ፣ ተገልጦ ሊታይ፣ ሊታወቅና ሊታመን እንዳለው የሚያሳይ የተስፋ ቃል ነው፡፡
ዮሐ.14:8-10 ”ፊልጶስ፡- ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው። ኢየሱስም አለው፡- አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፡- አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።”
የእግዚአብሄር ማንነት መገለጫ መንገድ ከክርስቶስ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ አምላክ በልጁ አካል ውስጥ የሚኖር በመሆኑ ከልጁ በቀር ስለእርሱ ባህሪይ መተረክ፣መንገር፣ማሳወቅ፣ማሳየትም የሚችል የለም፡፡
ማቴ.11:27 ”ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።”
እያንዳንዱ እግዚአብሄርን የሚያሳይ መለኮታዊ ባህሪይ በሌላ በማንኛውም ፍጥረት በኩል መገለጥ አይችልም፣ እግዚአብሄር ከወለደው ከራሱ አንድያ ልጁ በስተቀር፡፡ የማይታየው ባህሪይ እርሱም የዘላለም ሀይሉና አምላክነቱ በሌላ በማንም ሳይሆን በክርስቶስ ሰውነት ብቻ የሚገለጥ ነው፡፡
ቆላ.2:9 ”በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና።” ስለተባለ፡፡
እግዚአብሄር በባህሪው አይታይ እንጂ መታያ መንገዶችን እየመረጠ ሲገለጥባቸው ኖሮአል። እግዚአብሄር ካልተገለጠ በስተቀር ሰው ሊያውቀው አይችልም። ኢሳ.40:25፤ እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ። እግዚአብሄር ከክርስቶስ ውጪ በተለያየ መንገድ ቢገለጥም በጊዜያዊነት ተገልጦ ሲሰራ ስለነበር በተገለጠበት አካል በኩል ታይቶአል፤ በተገለጠበት መንገድ ድምጹ ተሰምቶአል።
– በግልጥነት መታወቅ
የእግዚአብሄር ህዝብ ከሚደርስበት የብዥታ ህይወት እንዲወጣ እግዚአብሄር ለህዝቡ ሊታወቅ ያስፈልግ ነበር፡፡ አህዛብ ማንነቱ ያልታወቀ ጣኦት (ህይወት የሌለው ግኡዝ ቅርጻ ቅረጽና ምስል) ይገዛቸዋል፣ ስለሚፈሩት ይሰግዱለታል፣ ሰይጣንም ፍርሀታቸውን መግቢያው አድርጎ በዚያ በኩል የራሱን ፈቃድ የፈጽማል፡፡ የትኛውም የአህዛብ ሰው የሰይጣንን ክፋት በትክክል ተረድቶ እርምጃ አይወስድም ወይም አውቆ አይራመድም፤ ይልቅ እንደሚሰጠውና እንደሚጠብቀው አምኖ ይከተለዋል እንጂ ወደ ዘላለም ሞት እንደሚነዳው አያሰተውልም፡፡ የተገለጠለት ህዝብ ግን የሚያመልከው አምላክ ህያው መሆኑን ይመሰክራል፡፡
ዘዳ.4:7-10 ”አምላካችን እግዚአብሔር በምንጠራው ጊዜ ሁሉ እንደሚቀርበን፥ አምላኩ ወደ እርሱ የቀረበው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው? በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንደማኖራት እንደዚህች ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ፍርድ ያለው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው? እግዚአብሔር፡- ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፥ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ ልጆቻቸውንም ያስተምሩ ዘንድ ቃሌን አሰማቸዋለሁ ብሎ በተናገረኝ ጊዜ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በኮሬብ በቆምህበት ቀን ዓይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አስታውቀው።”
ከላይ ቃሉ እንደሚያሳየን እግዚአብሄርን በማወቅ ለሰዎች የሚመጣ የህይወት ልምላሜና በረከት አለ፤ እግዚአብሄር በድንግዝግዝ እንዲመለክ አይፈልግምና፤ ታውቆና ታምኖበት እንዲመለክ ይሻልና፡፡ ድንግዝግዝ አምልኮ የጥፋት አምልኮ ነው፣ የተለመደውም ለአማልክት ማቅረብ ሲሆን እግዚአብሄርን ለማወቅ የሚከተሉ ግን ከማስተዋል ጋር በእርሱ መገለጥ የሚያመልኩት ነው፡፡ እስራኤል ከግብጽ ወጥተው በሚጉዋዙበት ወቅት ቆም ብለው ወደ አህዛብ የተመለከቱበትን ወቀት አይረሱትም፤ ብዙ ጥፋት ይዞ የመጣባቸው ቀን ነበርና፡፡ በዚያን አጋጣሚ ከእስራኤል መሀል ብዔልፌጎርን የተከተሉት ሰዎች ተገኙ፣ እነዚህን ሰዎች እግዚአብሔር ከህዝቡ መካከል አጥፍቶአቸው ነበርና ህዝቡ በብዔልፌጎር እግዚአብሄር ያደረገውን አዩ፤ አይተው የተመለሱት አምላካቸውን እግዚአብሔርንም የተከተሉ እስከ ከነአን ድረስ በሕይወት ኖሩና ምድሩን ወረሱ።
እነዚህ አስተውለው የተጉዋዙ እስራኤላውያን እግዚአብሄርን አመለኩ፣ ስሙን በመቃናቸው አድርገው፣ በግንባራቸውም ምልክት አድርገው ሳይረሱ እለት እለት እያስታወሱ ተከተሉት፣ ማንነቱን ተረድተው ነበርና፡፡
ዘጸ.3:15-17” እግዚአብሔርም ደግሞ ሙሴን አለው፡- ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ፡- የአባቶቻችሁ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፥ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው። ሂድ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ሰብስብ። እግዚአብሔር የአባቶቻችሁ አምላክ የአብርሃም የይስሐቅም የያዕቆብም አምላክ፡- መጐብኘትን ጐበኘኋችሁ፥ በግብፅም የሚደረግባችሁን አየሁ፤ ከግብፅም መከራ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ያቡሳውያንም አገር ወተትና ማር ወደ ምታፈስስ አገር አወጣችኋለሁ አልሁ ብሎ ተገለጠልኝ በላቸው።”
– ማስተዋል እንዲመጣ መታየት
ምስጢርን የሚገልጥ አምላክ በመገለጡ የሰጣቸው ብዙ እውቀቶች አሉ፡፡ በኤፌ3:8-9 ውስጥ ያለው ቃል ያን የሚያስረዳ ነው፡-
” ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ፥ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘላለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለኔ ተሰጠ”
ጌታ ኢየሱስ የመረጣቸውን ሃዋርያት የእውቀት ብርሀን በመንፈስ ቅዱስ ከሞላ በሁዋላ በአሕዛብ፣ በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሙን እንዲሸከሙ፣ የመለኮትን ምስጢርም እንዲያሳውቁ የላካቸው ስለእርሱ ይሰሙ ዘንድ ያላቸው ሁሉ እርሱን በማወቅና በመረዳት እንዲያምኑ ነው፡፡
እንዲሁም በሮሜ.16:25-26 ውስጥ:-
”እንግዲህ እንደ ወንጌሌ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ተሰበከ፥ ከዘላለም ዘመንም የተሰወረው አሁን ግን የታየው በነቢያትም መጻሕፍት የዘላለም እግዚአብሔር እንደ አዘዘ ለእምነት መታዘዝ ይሆን ዘንድ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው፥ ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።” የሚል ቃል አለ፡፡
ጌታ ኢያሱስ የሰጠው ወንጌል ለህዝብ ከመገለጡ አስቀድሞ የባሪያዎቹን ህይወት ለውጦአል፤ ጸጋውን በጥበብና በአእምሮ ስላበዛላቸውም የጌታ ደቀመዛሙርት ሊሆኑ ችለዋል። ቀጥሎ ጌታ ወደ እርሱ የሚጠራቸውን ነፍሳት በጸጋው አስተዋይ ሆነው ያድጉ ዘንድ አደራው ለሀዋርያት የተሰጠ ነበር፡፡ በዚያም መሰረት እግዚአብሄር በክርስቶስ ለማድረግ የወደደውን ምስጢር ለፍጥረት በሙሉ ከኢየሩሳሌም አንስቶ በሰማሪያ እስከ ምድር ዳር ድረስ እንዲደርስ ሰርተዋል፡፡ እርሱ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር ባስታጠቃቸው መጠን ይሰብኩ ዘንድ ብዙ ደክመዋል፡፡ በሄዱበት ሰፍራ ሁሉ የዳኑበትን የመጀመሪያ ትምህርት ማሳወቅ ብቻ ሳይሆን በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡን እርሱም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ያቀደውን በግልጥ ይሰብኩ ነበር (ኤፌ1:8-10) ፡፡
በ2ጢሞ.1:9-11 ሲናገሩ ”ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። ” ብለዋል፡፡
እግዚአብሄር በጠራቸው ወገኖች ዘንድ ስለመንግስቱ እውቀት ማስተዋል እንዲገኝ ከሁሉ አስቀድሞ ክርስቶስ እንዲገለጥ ተገብቶታል፤ ያን የሚያደርግ አምላክ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታችም የተወለደውን ይህን ልጁን ላከ፤ በዚያም የዘላለም አሳቡ በነበረው ቅዱስ አጠራር ያመኑትን ተቀብሎ እንደ ልጆች ይሆኑ ዘንድ፥ ከሕግ በታች የነበሩትን ሁሉ የሚዋጅ ስራ ይሰራ ዘንድም ያን አከናውኖአል።
– በተጨበጠ ማስረጃ ግልጥ መሆን
እግዚአብሄር ሊገለጥ ያስፈለገበት ሌላው ምክኒያት የርሱን አምላክነት፣ ኤልሻዳይነት፣ የህይወት ምንጭነት… በአጠቃላይ በብሉይ ኪዳን ዘመን ስለ እርሱ የተነገሩትን ቃሎች በሙሉ በተጨባጭ ማስረጃ ለሚጠባበቁት ወገኖች ግልጥ ያደርግ ዘንድ ነው፡፡ ያን በተመለከተ ሃዋርያው ዮሀንስ እንዲህ ሲል ተናግሮአል፡-
1ዮሐ.1:1-2 ”ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን”
ተስፋ የተጨበጠ ማስረጃን ይቀድማል፣እንደ ጥላና አካል ሆኖ፤ እግዚአብሄር ሊያደርግ ያቀደውን ስራ ተናግሮ ብዙ መቶ አመታት ሊያልፉ ይችላሉ፡፡ይሁን እንጂ የተናገረው ሳይፈጸም ጨርሶ አይቀርም፡፡እግዚአብሄር በብሉይ ኪዳን ይታወቅ ዘንድና መልእክቱ ለህዝቡ ይደርስ ዘንድ በመላእክት አፍ ደጋግሞ ተናግሮ ነበር፤ ስራውንና ሊያደርግ ያለውን በብዙ ማስረጃ እየመሰከረ ቢቆይም የራሱን ባህሪ ግን በሙላት ሊገልጥበት የሞከረበት ፍጥረት የለም፡- ፍቅሩ፣ ርህራሄው፣ መድሀኒትነቱ፣ አምላክነቱ፣ የዘላለም ሀይሉ መገለጥ ካለበት የሚገለጠው በባእድ አካል ሊሆን አይችልም፣ ከቃሉ ካዘጋጀው ስጋ/ ሰውነት፣ ከአንድያ ልጁ በስተቀር በሌላ በማንም ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚያ ነው እግዚአብሄር በስጋ የሚገለጥበት ጊዜ ሲደርስ ስለመገለጡ ማረጋገጫ ብስራቶች/ ምስክሮች ወደ እስራኤል ይመጡ የነበረው፡-
ሚል.3:1-3 ”እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል፤ እናንተም የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል፤ የምትወዱትም የቃል ኪዳን መልእክተኛ፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።ነገር ግን እርሱ እንደ አንጥረኛ እሳትና እንደ አጣቢ ሳሙና ነውና የሚመጣበትን ቀን መታገሥ የሚችል ማን ነው? እርሱስ በተገለጠ ጊዜ የሚቆም ማን ነው? እርሱም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያጠራ ሰው ይቀመጣል፥ የሌዊንም ልጆች ያጠራል፥ እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያነጥራቸዋል፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር በጽድቅ ቍርባንን የሚያቀርቡ ይሆናሉ።”
ሉቃ2:10-14”መልአኩም እንዲህ አላቸው፡- እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፡- ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።”
የእግዚአብሄር አማኑኤል መሆን ለአህዛብ ንጉስ ጭምር ይታወቅ ዘንድ ለሄሮድስ ተገለጠ፤ ምስክሩም በእንዲህ ሁኔታ ወደ እርሱ መጥቶ ነበር፡-
ማቴ.2:1-7 ”ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል፡- የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤ የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም፡-አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት።
ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፥”
እግዚአብሄር እንደቃሉ ሲፈጽም መታየቱ ተስፋውን ሲጠባበቁ ለኖሩ ለህዝቡ እረፍት ስለመሆኑ ቃሉ ያሳያል፡-
ሉቃ2:25-32” እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ።በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር።በመንፈስም ወደ መቅደስ ወጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ።ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፣ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።”