ካለፈው የቀጠለ…
– እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ… ይላል (1ቆሮ.14:9)
በፍቅሩ ምክኒያት የተቀበልነውን ደህንነት በፍቅርና በሸክም ድህንነት ለተገባችው የሰው ልጆች ሁሉ ማሳለፍ ምህረት ካገኘ ወገን ይጠበቃል። ስለመዳን እያወሩ አዳኙን ያለመንገር አይቻልም፣ የተሰጣቸውን እያስተዋወቁና በሰፊው እየተናገሩ ሰጪውን ያለማስተዋወቅ ንፉግነት ነው። አይሁድ የአለም ሁሉ አዳኝ ጌታን ሊቀበሉ እጅግ አንገራግረዋል፤ ምህረትና ፈውሱን ከተቀበሉም በሁዋላ የተሸሸጉ አልጠፉም፤ በላያቸው የነበረው ነቀፌታ ከብዶባቸው አፍረው ያለተሰወሩ ያዳነና ነጻ እንዲመላለሱ ያደረጋቸውን ጌታ ሲሰውሩት ነበር፤ ይህ ችግር በእኛም ዘመን አለ፤ ያዳናቸው ግን ይናገሩ ዘንድ ስለፍቅር ግድ ነው፦
ዮሐ.9:13-22 “በፊት ዕውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዓይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ ፈሪሳውያን ደግሞ እንዴት እንዳየ እንደ ገና ጠየቁት። እርሱም፦ ጭቃ በዓይኖቼ አኖረ ታጠብሁም አያለሁም አላቸው። ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ፦ ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም አሉ። ሌሎች ግን፦ ኃጢአትኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶች ሊያደርግ እንዴት ይችላል? አሉ። በመካከላቸውም መለያየት ሆነ። ከዚህም የተነሣ ዕውሩን፦ አንተ ዓይኖችህን ስለ ከፈተ ስለ እርሱ ምን ትላለህ? ደግሞ አሉት። እርሱም፦ ነቢይ ነው አለ። አይሁድ የዚያን ያየውን ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ ዕውር እንደ ነበረ እንዳየም ስለ እርሱ አላመኑም፥እነርሱንም፦ እናንተ ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል? ብለው ጠየቁአቸው። ወላጆቹም መልሰው፦ ይህ ልጃችን እንደ ሆነ ዕውርም ሆኖ እንደ ተወለደ አናውቃለን፤ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም፥ ወይም ዓይኖቹን ማን እንደ ከፈተ እኛ አናውቅም፤ ጠይቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ ራሱ ይናገራል አሉ። ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህን አሉ፤ እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና።”
– የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው (ገላ.5:19)
የጽድቅ ነገር ሰውን እንደሚለውጥ ሁሉ የስጋ ስራም እንዲሁ ሰውን ከብርሃን ወደ ጨለማ ይለውጣል።የስጋ ስራ ሲገለጥ በእኛ ላይ ተገልጦ ሲመራን የነበረ መንፈሳዊ ነገር እየተዋጠ ይሄዳል፤ የስጋ ስራና መንፈሳዊ ፍሬዎች በአብሮነት በህይወታችን መገለጥ አይችሉም፤ አንዱ ሌላውን ከህይወታችን ገፍቶ ያስወግደዋል። ዛሬ የትኛው እንዲሰለጥንበት እንደምንሻ ፍላጎታችንን መመርመር አለብን።
ገላ.5:13-6 “ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ።ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው።ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።”
– የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው (1ጢሞ.5:24)
በክፉ ይሁን በደግ ፍሬያማነት በየትኛውም መልኩ የሰውን ህይወት የሚገልጥ ነው። የተገለጠው ነገር ማንነታችንን ያሳያል፤ ህይወታችንም የሚነበበው በእኛ ላይ በተገለጠው ነገር ነው። ማንም በስውር የሰራው የተከደነ ቢመስለው ፈጥኖ ካልተነቀለና በህይወቱ ስር ከሰደደ እያደር ፍሬው ይታይና የዚያን ሰው ምስጢር ይገልጣል። የሰው ባህሪ የርሱን የልብ ዝንባሌ ይገልጣል፣ አካሄዱም በውስጡ የሞላውን ለአለም ይገልጣል፤ በሰው ፊት የተሰወረ ቢሆን እንኩዋን በእግዚአብሄር ፊት ሁሉ ግልጥ ነው። ጤናማ ትምህርትን የማይከተልም እንዲሁ ከርሱ አመጽን ስለሚወልድ የትምህርቱ ፍሬ ሃጢያት ይሆናል።
– እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው (1ጢሞ.5:25)
ለቃሉ ልባቸውን ገር ያደረጉ ግን በህይወታቸው የሚያፈራው የጽድቅ ፍሬ ይገልጣቸዋል። መልካም ስራ በራስ ችሎታ የሚጸና ሳይሆን በእግዚአብሄር እርዳታ ሰው በህይወቱ የሚለማመደው በመሆኑ በአምላኩ ላይ ያለው ተማጽኖና ትምክህት ህይወቱን ከተግባራዊ እንቅስቃሴው ጋር በውጤታማነት ያቆራኘዋል፣ ውጤታማነቱም ለሌላው ይተርፋል።
– የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ መገለጥ… (ቲቶ3:4)
መድሃኒታችን እግዚአብሄር ሊያድነን የፈቀደው የህይወታችን ይዘት በጎና ጤናማ ሆኖ አልነበረም፤ ይልቅ በቅዱሱ አምላክ ፊት ስራችንና ህይወታችን አጸያፊ ሆኖ ሳለ በርሱ ዘንድ የነበረው ለሰው ልጅ ያለው የልቡ ፈቃድ ማንም እንዳይጠፋ መማር፣ መታገስና ማዳን በመሆኑ ያን ፈቃዱን ወደ ተግባር ለውጦ አለሙን በሙሉ የሚታደግበትን መፍትሄ ገልጦአል። ለክፉው አዳም የተገለጠው መልስ ቸርነት ሆነ፣ ለአመጹ የዘላለም ሞት መጨረሻው ሆኖ ሳለ ከፈጠረው አምላክ ጋር ለዘለአለም እንዳይቆራረጥ ሲል በጸናው ፍቅሩ ሰውን የሚታገስና የሚጎበኝ ሆነ፤ ይህ መሃሪ አምላክ በተገለጠው ቸርነቱና መውደዱ በኩል ለሚመጣ ሁሉ በስሙ የሚደገፍበትን ጸጋ ሰጥቶ ያን ቅዱስ ስም እየጠራ የሚድንበትን የእግዚአብሄር የልጅነት ስልጣን የሚቀበልበትንም መንገድ ከፈተ። በቲቶ3:5-7 ላይ ለእኛ የተደረገውን ሲያሳስብ እንዲህ አለ፦
“እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው።”
– የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ (1ዮሐ.4:9)
የእግዚአብሄር ፍቅር በአለም በግልጥ የታየ፣ የታወቀና የታመነ እንዲሆን ያደረገው አምላክ በልጁ ሰውነት በመገለጡ ነው፤ ሰዎች በሃጢያት ምክኒያት ከእግዚአብሄር ክብር መራቃቸው የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ እግዚአብሄር ግን አማኑእል (እግዚአብሄር ከእኛ ጋር) ሆነ፤ ይህን የምስራች ህዝቡ በደስታ ለአለም እንዲያበስሩ ድፍረት የሰጣቸው የአባቶቻቸው አምላክ በመሃከላቸው አዳኝ ሆኖ በመገለጡ ነው።
2ቆሮ.5:17-19 “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።”
– የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ… (ራእ15፡3)
የጽድቅ ስራ የሚታየው ጽድቅን የሰጠን አምላክ በህይወታችን መስራት ሲቀጥል ነው፤ አማኞች ጽድቃችን ኢየሱስን በህይወታችን ስናነግስ በእኛ የነገሰው እርሱ በሚታይ ስራ ህይወታችንን ለአለም ይገልጣል። ይህ የመንፈሳዊ ህይወት መርህ ሲሆን ሰው በራሱ ጥረት (በሚሄድበት በራሱ መንገድ ላይ ሆኖ) የጽድቅ ፍሬ የሚባለውን እግዚአብሄር ያረጋገጠውን መልካም ነገር ያደርጋል ማለት የማይታሰብ ነው። ምክኒያቱም ሰው ያን ማድረግ ስላቃተው ነው እግዚአብሄር በስጋ እንዲገለጥ የተገደደው። ሰዎች ከእግዚአብሄር ምህረትን ከተቀበሉ በሁዋላ እግዚአብሄር ያደረገላቸውን ረስተው በራሳቸው ስራ መታመን ሲጀምሩ ከፍ እያሉ ሳይሆን እየተንሸራተቱና ለውድቀት ራሳቸውን እያጋለጡ መሆኑን እንዲያውቁ ቃሉ አጥብቆ ያሳስባል፤ እንዲህ ሲል፦
ኤር.9:23-24 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ነገር ግን የሚመካው ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር።”
የሚገለጥ የእግዚአብሄር ማንነት
እግዚአብሄር ማንነት አለው፤ ሃይል ያለው፣ ፈቃድ ያለው/ በራሱ የሚወስን፣ ፈጣሪና ህያው አምላክ ነው። የአለም ፈላስፋዎች እግዚአብሄርን እንደ አንድ የተለየ ሃይል ወይም ተጽእኖ የሚያሳድር አካል ብቻ ይቆጥሩታል፣ ያልያም ውሉ የማይታወቅ ዝም ብሎ ሃይል ብቻ አድርገው ይቆጥሩታል ወይም እግዚአብሄር ብለው ሳይሰይሙ አንድ ከነርሱ አእምሮ በላይ የሆነ ሃይል ብቻ እንደሆነ ገምተውታል። እግዚአብሄር ግን ሃይልና ስልጣን ያለው ብቻ ሳይሆን ህያውና ክፍጥረቱ ጋር መቀራረብና አብሮ መጉዋዝ የሚፈለግ ልዩ አምላክ የሆነ እንጂ እንደገመቱት ግኡዝ ነገር አይደለም። እግዚአብሄር የሚሰማ የሚናገርም አምላክ ነው፣ ስለዚህ እንደሚገምቱት እርሱ እንደ አንድ የተፈጠረ ነገር፣ በሃይሉ ብቻ እንደሚገለጥና ማንነት እንደሌለው ተደርጎ የሚታሰበው አመለካከት ከንቱ ነው። እግዚአብሄርስ ቸር፣ መሃሪ ይቅር ባይ፣ የሚምር፣ የሚራራ፣ ተስፋ የሚሰጥ፣ የሚፈልጉትን የሚያገኝ፣ ሰውን ከጥፋት የሚጠብቅ፣ የቅርብ አምላክም እንጂ ሃይል ብቻ ሆኖ እንደተፈጠረችው ጸሃይ፣ ብርሃናቸውን እንደሚፈነጥቁትም ከዋክብት፣ ደግሞ በሰው ጥበብ እንደተፈጠረው የኤሌክትሪክ ሃይል ሆነ የኒዩክሌር ሃይል እርሱም በራሱ አንድ የሃይል ምንጭ ብቻ ሆኖ ከፍጥረታት ጋር ከተነጻጸረ ይህ እውቀት በራሱ የደህንነታችን ጠንቅ እንደሚሆን አይጠረጠርም።
”ሙሴም እግዚአብሔርን፦ እነሆ፥ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ፦ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ፦ ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ፥ ምን እላቸዋለሁ? አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ <ያለና የሚኖር>እኔ ነኝ አለው፤ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ <ያለና የሚኖር> ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው።” (ዘጸ.3:13-14)
የእግዚአብሄር በተለያየ መንገድ የመገለጡ ነገር አንድ ነገር ሆኖ መገለጥ የተገባው ማንነቱ ግን ሌላ ነው። ግን እግዚአብሄር ለምን ይገለጣል? የባህሪው ሁኔታ ነው ዋናው ምክኒያቱ፤ አምላክና የሁሉ ፈጣሪ ባለቤት እንደመሆኑ ከፍጥረቱ ጋር በተለይ ከሰው ልጅ ጋር በቅርበትና በአብሮነት መጉዋዝ ይሻል። እግዚአብሄር ከፍጥረቱ ውጪ ብቻውን መኖር እንደማይችል መቆጠር የለበትም፤ ፍጥረት ከመምጣታቸው አስቀድሞ እርሱ ብቻውን አልነበረም ወይ? ብቻ በእጆቹ ስራዎች ደስ ተሰኝቶአልና ወደ እነርሱ አዘውትሮ ይመለከታል፤ በተለይ ወደ ሰው መቅረብ ስለሚሻ አንድ አስደናቂ ነገር በርሱ ዘንድ ያደርጋል፤ ይህንም በመገለጡ አሳይቶአል፤ እግዚአብሄር ሲገለጥ እንዲታወቅለት የሚፈልጋቸው ዋና ባህሪዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦
እግዚአብሄር መንፈስ መሆኑ
እግዚአብሄር መንፈስ መሆኑ ምን ማስተዋል ይሰጠናል? መንፈስ ያለመታየትና ያለመዳሰስ ብቻ አይደለም። በስጋ አእምሮ ሊገመት፣ ሊቀረጽ፣ ሊተነበይ ወይም ሊሰላ አይችልም ማለትም ነው።
”እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።” (ዮሐ.4:24)
እግዚአብሄር ወሰን የሌለው፣ ዘላለማዊና የማይለወጥ ፍጹም መንፈስ የሆነ አምላክ ሲሆን ጥበብ፣ ሃይል፣ ስልጣን፣ ቅድስና፣ መልካምነትና እውነት ያለው አምላክ ነው። እርሱ የሁሉ ምንጭ ነው፤ ሁሉን ደግፎ የያዘም ነው፤ የሁሉም ነገር ፍጻሜ እርሱ ነው። እግዚአብሄር የነገሮች መጀመሪያ፣ ምክኒያትና የሁሎቹም መጨረሻ/ ወሳኝ ነው። እግዚአብሄር ጊዜያቸውን ጠብቀው ለሚገለጡ ማናቸውም ክስተቶች ምንጭ ሲሆን እነርሱ ጊዜያዊ እርሱ ግን ዘላለማዊ ነው።
እርሱ ህያው መንፈስ ነው፣ መንፈስ በመሆኑ የማይታይ ነው። መንፈስ ምንድነው? መንፈስ እንደ ስጋና ደም መዳሰስ የማይችል ህያው ማንነት ነው።
”እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው።” (ሉቃ24:39)
መንፈስ አካል የለውም፣ የሚዳሰስ ወይም የሚጨበጥ ግኡዝ ነገርም አይደለም።
”መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።” (ዮሐ.1:18)
እግዚአብሄር ብርሃን መሆኑ
”ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት፦ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።” (1ዮሐ.1:5)
እግዚአብሄር ፍቅር መሆኑ
”ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።” (1ዮሐ.4:8)
እግዚአብሄር የሚበላ እሳት መሆኑ
”አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና።” (ዕብ.12:29)
እግዚአብሄር በራሱ ህያው መሆኑ
እግዚአብሄር በማንም አይደገፍም፣ በራሱ ህያውና ሙሉ ነው። የእኛ የሰዎች መደገፊያችን እርሱ ነው፣ እርሱ ግን በማንም አይደገፍም። የእኛ መገኘት ምክኒያት እግዚአብሄር ሲሆን እግዚአብሄር ህያው እንዲሆን ምክኒያት የሆነው ግን ማንም የለም። እግዚአብሄር ትላንት ነበር ዛሬም ሳይለወጥ አለ፣ ወደፊትም ያለመለወጥ የሚኖር ነው። በእርሱ ህያውነት ውስጥ ጊዜና ስፍራ ተጽእኖ የላቸውም፣ እኛ ሰዎች ግን በሁለቱ የታጠርን ነን። የእኛ ህይወት ምንጩ ከውጪ ያለ ነው፣ ያም እርሱ ነው። እኛ ህያው ሆነን መኖር የጀመርነው በሆነ ወቅት ነው፤ ያን አድራጊው እግዚአብሄር ነው።
እግዚአብሄር ወሰንና ዳርቻ የሌለው መሆኑ
በመለኮት ባህሪ ውስጥ ወሰን የለም፤ እግዚአብሄርን በምንም ሁኔታ ውስጥ ልንገድበው አንችልም። ለእኛ ገደብ የሆኑ ነገሮችም ለእርሱ እንደእኛ አይሆኑም።
”ጌታችን ታላቅ ነው፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ ለጥበቡም ቍጥር የለውም።” (መዝ.147:5)
”ምነው እግዚአብሔር ቢናገርህ! በአንተም ላይ ከንፈሩን ቢከፍት!የጥበቡን ምሥጢር ቢገልጥልህ! ማስተዋሉ ብዙ ነውና። እግዚአብሔር ለበደልህ ከሚገባው አሳንሶ እንደሚያስከፍልህ እወቅ።የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክ ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን?ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ?ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል።እርሱ ቢያልፍ፥ ቢዘጋም፥ ጉባኤንም ቢሰበስብ፥ የሚከለክለው ማን ነው?ምናምንቴዎችን ሰዎች ያውቃልና፥ በደልንም ሲያይ ዝም ብሎ አይመለከትም።የሜዳ አህያ ግልገል ሰው ሆኖ ቢወለድ፥ ያን ጊዜ ከንቱ ሰው ጥበብን ያገኛል።” (ኢዮ.11:5-12)
”የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም። የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው?ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” (ሮሜ.11:33-36)