አምላካዊ ምክኒያት አለ?
እግዚአብሄር አምላክ በየዘመኑ ላለ ህዝብ እንደ የትውልዱ ቀርቦ ይመጣና የሰውን ልጅ ወደ ራሱ ይጣራል፤ ለጠራው ሰው የጠራበትን ምክኒያት ከማመልከቱ በፊትም የራሱን ማንነት በፊቱ ያውጃል፤ ይህንም በዋናነት አብረሃምና ዘሩ እስራኤልን በጠራው ጊዜ አድርጎአል፡፡ ለእስራኤል አስርቱን ትእዛዝ በሰጠበት ወቅት ራሱን ከማስተዋወቁ ባሻገር ከኔ በቀር ሌላ አምላክ አይሁንላችሁ ሲል አስጠንቅቆ ነበር፡፡ ይህ የጸና አዋጅ በህዝቡ ፊት የሚኖር ህዝቡም ተጠንቅቆ ሊጠብቀው የተገባ ታላቅ ትእዛዝ ነበር፡፡ አዋጁ የእግዚአብሄር ማንነት መሰረት ነው፡፡ እግዚአብሄር ከምንም በላይ በፍጥረት መሀል የገለጠው ክብርና የሰጠው ስም ዝቅ እንዲል፣ ስፍራው እንዲነካበትና ቸል እንዲባል ፈጽሞ አይሻም፤ ያን ያስጠብቅ ዘንድም ከርሱ በፊት አምላክ እንደሌለ ከርሱም በሁዋላ እንዳልተሰራ አጥብቆ ያሳስባል፡፡
እግዚአብሄር በኢሳ.44 ውስጥ የሚያስተላልፈው መልእክት ወደ ባሪያው ያዕቆብ አመልካች ሲሆን ለመንግስቱ የመረጠውን ይህን ህዝብ በአጽኖት ሲጠራ እስራኤል ሆይ፥ ስማ ይል ነበር፡-
ከማኅፀን የሚፈጥር የሚሰራ የሚረዳም እግዚአብሔር ስማ ብሎ ከተጣራ በሁዋላ ” ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ይሹሩን ሆይ፥ አትፍራ።” ይላል፡፡ ይህ ጥሪ ጽናትም መንቂያም ሆኖ በአንድ በድካም ለሚኖር ህዝብና አምላኩን ከማምለክ ለደከመ ትውልድ ማጽኛና ማስተማመኛ ማህተም ነው፡፡ እግዚአብሄር ይምጣ እንጂ ይዞ የሚመጣው መፍትሄ ታላቅ ነው፡፡ እስራኤል ከመንገድ ደክሞ መንፈሱ እንደ ደረቀ የተመለከተ አምላክ በተጠማው ላይ ውኃን በደረቅም መሬት በተመሰለው ህዝቡ ላይ ፈሳሾችን ሊያፈስ፤ መንፈሱን በያእቆብ ዘር ላይ በረከቱንም በልጆቹ ላይ እንደ ውሀው እርካታ በሙላት ሊሰጥ አስቀድሞ ተስፋ ሲልክ እናያለን፤ እግዚአብሄር መንፈሱን ከሰጠ የእስራኤል ህይወት በፈሳሾች አጠገብ እንደሚበቅል እንደ አኻያ ዛፍ (ውሃውን ጠግቦ እንደጎመራው እንደዛፉ) እንደሚሆን ውጤቱን ያበስራል፡፡
በየትውልዱ የተነሳ ህዝብ ግን ለእግዚአብሄር ፈተና የሆነው ከእርሱ ሌላ አማልክትን ተከትሎ በመሄዱ ነው፤ ባለቤት እያለ ባለቤት ወዳልሆኑ ማጋደል፣ አዘጋጅና ፈጣሪ እያለ ምንም ነገር በማይሰጡ ፍጥረታት መቀማት፣ የሚሰማ አምላክ እያለ ወደ ማይሰሙ ጣኦታት መዞር ማጋደል ባለቤቱ ህያው እግዚአብሄርን እጅግ ያስቆጣል፡፡ መንፈሱን በማፍሰስ የሚያለመልም አምላክ በእስራኤል ዘንድ ከእምነት መንሸራተት እንዳይገኝ ”የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም።” በማለት ህዝቡን ለማጽናት አውጆአል፡፡ (ኢሳ.44:6)
ቃሉ በኤር.10:10-16 እንደሚለው፡-
”እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፤ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም። እናንተም፡- ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ ትሉአቸዋላችሁ። ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይሰበሰባሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናቡም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፎአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና። እነርሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው፤ በተጐበኙ ጊዜ ይጠፋሉ። የያዕቆብ እድል ፈንታ እንደ እነዚህ አይደለም፤ እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነውና፤ እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነውና፤ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።”
እስቲ ልብ በሉ የተሻለው ማን ነው? ምድርን በኃይሉ የፈጠረ ወይስ አንጥረኛ የቀረጸው ምስል? ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋው ወይስ በሰው እጅ የተጠፈጠፈ ግኡዝ ቅርጽ? ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ የሚሰበሰቡለት ወይስ ጆሮም ምላስም የሌለው ግኡዝ ነገር? እግዚአብሄር ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፎአል በብልሃተኛ አንጥረኛ ታምኖአልና እያለ ቅሬታውን ይናግራል።
በአህዛብ እምነት፣ ባህልና ልማድ ውስጥ ተቀምጠው እንደሚገዙት አጋንንት ሳይሆን እግዚአብሔር አስተማማኝ የሆነና እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱን ታምኖ ማፈግፈግ፣ ማፈር፣ መረሳት፣ መሸነፍም ሆነ በጣኦታት መደንገጥ የለም። እርሱ ትላንት እንደተነሱ አጋንንት የቅርብ አምላክ አይደለም፣ እርሱ የማይለወጥ፣ የማይናወጥ፣ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው። ጣኦታት ግኡዝ፣ ህይወት አልባ፣ ተጸኖ የሌላቸው፣ በአጋዥ የሚንቀሳቀሱ፣ የማይናገር አፍ ያላቸውና የማይሰማ ጆሮ የተተከለላቸው ግኡዝ ፍጥረታት ናቸውና በህያዋን ላይ ተጽእኖ የላቸውም። የኛ አምላክ ቸር ቢሆንም ያልተገባን ነውር ከፊቱ ፈጽሞ የሚያጠፋና አስጸያፊን ነገር ሁሉ ከፊቱ የሚደመስስ ነው፣ የኛ አምላክ ወዳጅ ቢሆንም ሃይለኛ ነው፣ በሚዘብቱ ላይ ለፍርድ ይነሳል፣ በሚክዱት ላይ በተነሳ ጊዜ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ ከእርሱ ርቀው በሃጢያታቸው ያሉ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም።
እግዚአብሄር የገለጠው ምንድነው?
በዘጸ.33:12-23 ያለው ቃል እግዚአብሄር አንድ ታላቅ ነገር በህዝቡ መሃል ሊያከናውን መጀመሩን ያሳያል፤ በዚያ ስፍራ ሙሴና እግዚአብሔር ይነጋገሩ ነበር። ሙሴ አምላኩ ከተገለጠለት በሁዋላ ሊያሳውቀው የሚፈልገውን ይጠይቃል፦ እነሆ አንተ፦ ይህን ሕዝብ አውጣ ትለኛለህ እንጂ ከማን ጋር ሆኜ ህዝቡን እንደማወጣ አብሮኝ የሚሆነውንም አላሳወቅከኝም ይላል፤ ቀጥሎ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ አለ፤ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን አለ፤ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? አለ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በፊቴ ሞገስ ስላገኘህ በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር አደርጋለሁ አለው።እርሱም፦ እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ። ሙሴ ከእግዚአብሄር ብዙ ነገር ጠይቆ ሊሰጠው ቃል ተገባለት፦ እርሱን ማወቅ ጠየቀ፣ ሞገስ ጠየቀ፣ መንገዱን ጠየቀ፣ የእርሱን ከህዝቡ ጋር መውጣት ጠየቀ፣ እግዚአብሄርም ሁሉን ሊመልስ ቃል ሰጠው፤ ይህን ያረጋገጠው ሙሴ ታላቅ ጥያቄ ላይ ደረሰ፦ ክብርህን አሳየኝ የሚል ጥያቄ።
ዘጸ.33:19-23፤ “እግዚአብሔርም፦ እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምራለሁ አለ። ደግሞም፦ ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ፤ እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፥ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።” አለው።
እግዚብሄርን ሰው ሊያየው አይችልም፣ አይቶም አይድንም። ግን አንድ ምስጢር ጠብቆአል፣ መታያ የሆነ አለት የተባለ። በሰንጠቃነቱ አለቱ ሙሴን ሊያኖርና እግዚአብሄርን ሊያሳይ የሚል ምስጢር ነበር፤ እግዚአብሄርም ሙሴን በርሱ ሊያኖርና በዚያ የማየት ችሎታን ሊቀበል የሚያስደንቅ ቃልኪዳን ሰጠው። አለቱ ግን ማን ነው? ሰንጣቃነቱስ?
እግዚአብሄር የሚገለጠው በአላማ ከሆነ መገለጡ የሚያመጣው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ምንጊዜም ቢሆን እግዚአብሄር የሚገለጠው መልካምነቱን ሊያውጅና ለጠራው ህዝብ እንደ ቸርነቱ መጠን አብዝቶ ሊሰጥ ነው፤ የመረጠው ህዝብና ባሪያው እንዲያውቁት፣ እንዲያምኑበት፣ ከእርሱ በፊት አምላክ እንደሌለ ከእርሱም በሁዋላ ሊሆን እንደማይችል እንዲያተውሉ ይህንንም ለፍጥረት ሁሉ እንዲመሰክሩም ነው (ኢሳ.43:10)፡፡እግዚአብሄር ግን የማያውቁትን አይልክም፣ ለምን ይልካል አያውቁትማ፣ በትክክል እሱን አያሳዩማ!
ቸሩ አምላክ እግዚአብሄር በመገለጡ ውስጥ ግን የሚሰጠው ነገር አለው፡- መገለጥን ሲፈጥር በእይታ ውስጥ መገኘት ያለበት ነገር ወደ መታየት እንዲመጣ ያደርጋል፣ በግልጥነት መታወቅ ያለበት ሁሉ በገለጠው እውቀት ውስጥ እንዲታወቅ ይሆናል፣ ማስተዋል እንዲመጣ ሲያደርግ በገለጠው ነገር የሰው ልብና አእምሮ ያን እንዲያገኝም ያደርጋል፣ በተጨበጠ ማስረጃ ግልጥ መሆን ያለበትም ነገር ሲገለጥ የተገለጠለት ሰው በማስረጃው በኩል እምነቱ እንዲጠነክር ለመርዳት መንገድ ይሆነዋል፡፡ ሙሴም እርሱን የማወቅ ጥማት ነበረውና እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ።
የተገለጡ ምስጢራት
እግዚአብሄር እናውቅ ዘንድና አውቀንም እናስተውል ዘንድ ወደ ብርሃን የሚያመጣቸው ምስጢራት ብዙ ናቸው፣ ቃሉ
ከሚያሳያቸው ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
– ከእግዚአብሔር የተገለጠ ሰው …(ሐዋ.2:22)
ይህ የተገለጠ ሰው የሚለው ቀድሞ ያልነበረ ወይም በታየበት ሁኔታ ቀድሞ የማይታወቅ የነበረ መሆኑን ሲያመለክት፣ እግዚአብሄር ግን ለእርሱ አላማ ማስፈጸሚያነት እንደገለጠው የሚያሳይ ነው።
የእስራኤል ሰዎች አንድ ወደ እነርሱ የመጣ ልዩ ሰው በመሃላቸው እንዳደረ ሊያስተውሉ ይገባ ነበርና ይህን ልብ እንዲሉ ሃዋርያው ጴጥሮስ በበአለ ሃምሳ ቀን በመካከላቸው ቆሞ ሲያውጅ እናያለን፤ ስሙ ይላቸዋል ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ፤ እርሱ በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ አላቸው። ይህ ሰው በአዳም ልጆችና በእግዚአብሄር መሃል ሆኖ (እንደ ቤተመቅደሱ መጋረጃ ለምህረት የቆመና ወደ መለኮት እንድንደርስ መስዋእትን ያደረገ) በመስዋእቱም ያዳነን ሰው ነው።
– በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ የተገለጠው ልጁ …(ሮሜ.1:3-4)
ሉቃ.1:31-38 “እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው።መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።ማርያምም። እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ።”
ይህ ለእስራኤል የተገለጠው ሰው በመለኮት ሃይል የተሞላና ከእግዚአብሄር የወጣ በልደት በኩል የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ መሆኑን ያሳያል። የእግዚአብሄር ልጅ እስኪወለድ ድረስ ወገኖቹ የሆኑት የአብረሃም ዘሮች በጨለማ ይኖሩ ነበር፤ ወደ ገዛ ወገኖቹ የጸጋ ሃይልን ተሞልቶ መጣ።
ጌታ ኢየሱስ በሃይል የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ ይገለጥ ዘንድ በልኡል ሃይል ጽንሱ መዘጋጀት ነበረበት። ጌታ ኢየሱስ በመለኮት ሃይል የተጸነሰ፣ በመለኮት ሃይል የእግዚአብሄር ልጅ ሆኖ በአጋንንትና በሰው ልጆች ፊት የተገለጠ፣ በመለኮት ሃይል አጋንንትን ያወጣ፣ የፈወሰ ፣ ታምራትን የሰራ ነው፤ እርሱ የአባቱ የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።
ማርያም እግዚአብሄር በህይወትዋ ሊሰራው የነበረውን ስራ አስተውላ እንዲህ ብላለች፦
ሉቃ.1:48-55 “የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።”
ማርያም ስታስተውል በእርስዋ እየሆነ ያለው ታላቅ ስራ አስደንቁዋታል፤ ስትመሰክርም በህይወትዋ ታላቅ ሥራ ያደረገው ስሙ ቅዱስ የሆነው አምላክ በክንዱ ሃይል የገለጠው (በልጁ በክርስቶስ የገለጠው) ምሕረት ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ እንደሚኖር በማመን ነበር።
– ሳሙኤል ግን ገና እግዚአብሔርን አላወቀም ነበር፥ የእግዚአብሔርም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበርና (1ሳሙ.3:7)
መገለጥ ከእድገት በሁዋላ የሚመጣ የእግዚአብሄር ቅርርብ መንገድ ነው፤ ወደ እግዚአብሄር የተጠጋ እግዚአብሄር ሳይገለጥለት አይቀረም፤ ይህን አሰራሩን በብላቴናው ሳሙኤል ህይወት እንመለከታለን። ሳሙኤል ለእግዚአብሄር የተሰጠ ልጅ ቢሆንም እግዚአብሄር እስኪገለጥለት ጊዜ ይጠብቅ ነበር፤ እግዚአብሄር ልጆቹን የሚያሳድግበት መንገድ አለው። ሳሙኤል ግን በእድሜ፣ በአስተሳሰብና በእግዚአብሄር ቃል ጸጋ ሲያድግ በእስራኤል ምድር የታወቀ ነቢይ ሆነ።
1ሳሙ.3:1-3 “ብላቴናውም ሳሙኤል በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር፤ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ፤ ራእይም አይገለጥም ነበር።በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ ጀምረው ነበር።ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ፥ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ሳለ፥ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ጠራው፤ እርሱም፦ እነሆኝ አለ።”
– ለአሕዛብ ምሥጢር ተገለጠ… (ሮሜ.16:25-26)
አህዛብ ከእውነተኛው የአብረሃም አምላክ ጋር ትውውቅ የነበረው ወገን አልነበረም፤ በዚህ ምክኒያት ከእግዚአብሄር መንግስት የራቀ፣ ከጽድቅ የራቀ፣ ከተስፋው ቃል የራቀ፣ ከሰማይ እውቀት የራቀ፣ በአጠቃላይ ያለክርስቶስ የነበረ ህዝብ ነበረ። የአህዛብ እጣ ፋንታ አሳዛኝ ነበረ። እኛ አህዛብን የሚገልጥ ጥቅስ እንዲህ ይላል፦
“እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን። ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው። ቃሉ የታመነ ነው።” (ቲቶ3:3-8)
እግዚአብሄር አህዛብ የሆንን እኛን ሊያድን ስለወደደ የደህንነት ምስጢር ክርስቶስን ገለጠልን፤ ይህም የርሱን ፍቅር የሚያሳይ ታላቅ ስራ ነው።
ሮሜ.16:25-27 “እንግዲህ እንደ ወንጌሌ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ተሰበከ፥ ከዘላለም ዘመንም የተሰወረው አሁን ግን የታየው በነቢያትም መጻሕፍት የዘላለም እግዚአብሔር እንደ አዘዘ ለእምነት መታዘዝ ይሆን ዘንድ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው፥ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።”