የእውነት እውቀት[3/3]

የእውነት እውቀት

1.4 የወንጌል መጽሀፍት ስለኢየሱስ ሕይወት የተጻፉ መጻሕፍት ናቸው፡፡

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ፣ ደቀመዛሙርት  የእርሱን ወዲያው መመለስ ይጠባበቁ ነበር፣ በህይወት እያሉ እንደሚከሰት ገምተው ነበርና፡፡በዚህም ምክንያት ለወደፊት ትውልዶች የሚሆን የጽኁፍ መረጃ ለማስቀመጥ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው ቀረ፡፡ ነገር ግን የዐይን ምስክሮች እየሞቱ መሄድና የቤተክርስቲያን የሚስዮናውያን ተልእኮ  ፍላጎት እያደገ ሲሄድ፣ የክርስትና መሰረት የሆነውን ጌታ ህይወት እና ትምህርቶች በፅሁፍ ማስፈር አስፈላጊነቱ ሊጨምር ችሎአል፡፡ የነዚህ ሂደቶች ደረጃ በደረጃ አመጣጥ እንደሚከተለው ተጠቃሎ ሊቀርብ ይችላል፡-

  • በንግግር የተላለፉ ትምህርቶች – ትረካዎች እና ቃላቶች በአብዛኛው በአስተማሪዎች የሚተላለፉ የነበረ ሲሆን ቅደም ተከተልን የጠበቀ አልነበረም፡፡
  • በጽሁፍ የተመዘገቡ የተዓምራት ታሪኮች፣ ምሳሌዎች፣ ቃላቶች ወ.ዘ.ተ. በንግግር ደረጃ ይተላለፉ ከነበሩ ትምህርቶች ጋር አብረው መታየት ጀመሩ፡፡
  • በተከታታይ መልክ የተመዘገቡ ትርክቶች በተደራጀ መልክ መዘጋጀት ያዙ፡፡እነዚህም ሁዋላ ወጥ በሆነ ጽሁፍ ለተዘጋጁት የወንጌል መጽሀፍት ምንጭ ሆነው አገልግለዋል፡፡ለምሳሌ  የሉቃስ ወንጌል መግቢያ በእነርሱ ዘንድ ስለነበሩት በርካታ ቀደምት ዘገባዎች ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡
  • በመጨረሻ በተለያየ ደረጃ ተመዝግበው የነበሩ የጌታ ኢየሱስ ትምህርቶችና ስራዎች፣ታምራቱንና ድንቁን የዘገቡ ጽሑፎችና በንግግር የተላለፉ ትምህርቶችን በማዋሃድ ወንጌላት ሊጻፉ በቅተዋል፡፡

ዛሬም ክርስቲያኖች ወንጌላት የያዙትን እውነት ሲያበስሩ ኢየሱስ ክርስቶስን የምስራች እያሉ ነው ማለት ነው፡፡የምስራቹም ጌታችን ኢየሱስ  ለኃጢያታችን ቅጣት ክፍያን ይከፍል ዘንድ ስለ እኛ መሞቱን ማወጅ፣ ያን ስራውን በማመን  በእርሱ የእግዚአብሄር ልጆች መሆን እንደሚቻልም ፍጥረት እንዲያውቅ ማድረግ ማለት ነው፡፡ በአጭሩ ወንጌል እግዚአብሔር የአዳም ዘር ሁሉ በልጁ ሞትና ትንሳኤ በኩል ይድን ዘንድ  በቅዱሳን መጽሐፍ ውስጥ የገለጸው የደህንነት እውነት ነው፡፡

1.5 የወንጌል መሰረታዊ ይዘት

በ1ቆሮ.15፣1-8 ውስጥ ሀዋርያው ጳውሎስ የወንጌልን መሰረታዊ ይዘት አጠቃሎ ያቀርባል፡-እርሱም የጌታ መሞት፣መቀበር፣ከሞት መነሳትና ከትንሳኤው በሁዋላ መታየትን የሚያጠቃልል ነው፡፡

1ቆሮ.15:1-8 “ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ። እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ። መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።”

ከላይ ጥቅሱ የሚያመለክተው በቀደመችው ቤተክርስቲያን ውስጥ አጽንኦት ተሰጥቶት እየተመሰከረ ስለነበረው የወንጌል ማእከላዊ ትምህርት ነው፡፡ይህ ትምህርት ዛሬም የወንጌሉ ማእከላዊ ትምህርት ሆኖ መቀጠል ያለበት ነው፡፡ ወንጌሉ የሚገልጠው ሁለት ገጽታ ያለው እውነት አለ፡- የመጀመሪያው ክርስቶስ ስለ እኛ ሀጢያት መሞቱን 2ኛ ደግሞ ከሙታን መነሳቱና ለእኛ ትንሳኤን ማጎናጸፉን ነው፡፡በቃሉ የተነገረው ስለመቀበሩ ዜና በእርግጠኝነት ስለመሞቱ ሲያመለክት ከተቀበረ በሁዋላ ለብዙዎች መታየቱ ትንሳኤውን ያበሰረ ድርጊት ነው፡፡በብሉይ ኪዳን ስለእርሱ የተነገሩት እውነታዎች በዚህ መፈጸማቸውንም አሳይቶአል፡፡(መዝ.16፡10፣ኢሳ.53፡8-10) እነዚህም የቃሉና የድርጊት ምስክሮች አማኞችን በማስረጃ የሚደግፉ የጌታ ስራ ምስክሮች ናቸው፡፡

1.6 ተጨማሪ ምልከታዎች

ወንጌል በመሰረቱ የእግዚአብሄርን ታላቅ ስራ አመልካች ሆኖ በራሱ የቆመ የደህንነት አዋጅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ነገር ግን ወንጌሉ የሚኖረውን ተዛማጅነት ለማመልከት ከቃሉ ጋር አብረው የሚጨመሩ  ቃላት ይኖራሉ፡፡ስለዚህ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የሚከተሉትን ቃላት እናገኛለን፡-የእግዚአብሄር ወንጌል (ማር.1፡14፣ሮሜ.15፡16)፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል (ማር.1፡1፣1ቆሮ.9፡12)፣ የልጁ ወንጌል(ሮሜ.1፡9)፣ የመንግስቱ ወንጌል (ማቴ.4፡23፣9፡35፣24፡14)፣ የጸጋው ወንጌል (ሐሥ.20፡24)፣ የክርስቶስ የክብር ወንጌል (2ቆሮ.4፡4)፣ የሰላም ወንጌል (ኤፌ.6፡15)፣ የዘላለም ወንጌል (ራእ.14፡6)፡፡ከላይ የተዘረዘሩት ቃላት አንዱ ወንጌል የገለጣቸውን እውነታዎች በአጽንኦት የሚያሳዩና የሚናገሩ እንጂ ሀዋርያው ጳውሎስ በገላትያ 1፡6-11 እንዳለው ከአንድ በቀር የተለያዩ ወንጌሎች ስለመኖራቸው የሚናገሩ አይደሉም፡፡ወንጌል ታላቁን የእግዚአብሄር ምስጢር የሚገልጥ የምስራች ነው፡፡ ወንጌል የአምላክን አሳብ ማመልከቻና ለሰው ልጆች ያለውን ፈቃድ መግለጫ ብርሃን ነው፡፡ወንጌል እግዚአብሄር በልጁ መገለጡን፣ ጸጋውን መስጠቱን፣ በልጁ ደም ሰላም ማምጣቱን፣ የዘላለምን ህይወት መግለጡን፣ የመንግስተ ሰማይን ምስጢር ወደ ብርሀን ማውጣቱን ሁሉ አውጆአል፡፡  ስለዚህ እንዲህ ወንጌል ተጠርቶአል፦    

 (1) የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል (ማርቆስ 1 1; 1 ቆሮ 9 12) እና የልጁ ወንጌል (ሮሜ 1 9)፣በነዚህ ሁለት መግለጫዎች በኢየሱስ ክርስቶስ  ሥራ  ለሰው ልጆች የመጣውን ደህንነት የምሥራች እናያለን፡፡ በተጨማሪ በክርስቶስ መከራ መቀበል ሰዎች ከኃጢአት ቅጣትና ከሞት ኃይል ነጻ ስለመውጣታቸው የምስራች ይላሉ፡፡
(2) የእግዚአብሔር የጸጋ ወንጌል (ሐዋ 20 24)፣ የሚያመለክተው አማኞች ደኅንነትን የተጎናጸፉት በከፈሉት ዋጋ ወይም በሰሩት ስራ ሳይሆን እግዚአብሄር በሰጣቸው ጸጋ ምክኒያት መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡
(3) የመንግሥቱ ወንጌል (ማቴ .4 23; 9:35; 24:14)፣ እግዚአብሔር በልጁ ስራ የሚገልጠውን መንግሥቱን የሚያመለክት የምሥራች ነው፡፡

4) የሰላም ወንጌል(ኤፌ.6፡15)፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠን ደህንነት በሁሉም አቅጣጫ እንዴት ያለ ሰላም እንዳጎናጸፈን የሚያመለክት ነው (ሰላም ከእግዚአብሄርና ከሰዎች ጋር፣ የእግዚአብሄር ሰላም ለነፍሳችን፣በአለም ውስጥ ለምንኖርበትም ጊዜና ስፍራ ሁሉ) 

5)የዘላለም ወንጌል(ራእ.14፡6)፣ወንጌል ከእግዚአብሄር የምናገኘውን ዘላለማዊ ሽልማት ይዞአል፡፡ጌታ በመስቀል ላይ መሞቱ መቀበሩና መነሳቱ በእኛ ህይወት ሰርቶ የሚያጎናጽፈን ህይወት የዘላለም ህይወት፣ የሞተልንን በጉንና መንፈስ የሆነውን የዘላለም አምላክ በሰማይ በስጋው መቅደስ ሆኖ የምናመልክበት የመጨረሻ መዳረሻችን በዚህ ወንጌል ውስጥ ተገልጦአል፡፡

ከላይ እንዳየነው ወንጌል አንድ ሰው የዘላለም ሕይወትን በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን እንደሚቀበል የሚገልጽ መልእክት የያዘ ነው፡፡ከዚህ በተጨማሪ ወንጌል የሚገልጻቸው እውነቶች አሉ፡- ለምሳሌ  ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 1 ከቁጥር 16  እስከ 17 እንዲህ ይላል “በወንጌል አላፍርምና ፣ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፣ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና፡፡ ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና።”

ወንጌል የመለኮትን አሰራር በሙሉ በመያዙ የእግዚአብሄር ሀይል መሆኑ ተመልክቶአል፡፡በጥቅሱ ውስጥ የሚታየው እውነት  ወንጌል እንደ እምነት መጽደቅ (ሮሜ.3-5)፣ በመንፈስ ቅዱስ መቀደስ (ሮሜ.6-8)፣ እና የእግዚአብሔር እስራኤልን (ሮሜ9-11) የመሳሰሉትን እንደሚጨምር ያሳያል፡፡ በእርግጥም፣ ወንጌል በሮሜ መጽሀፍ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ሁሉ በአንድ ላይ አጠቃሎ ይይዛል፡፡ ስለዚህ፣ በሮሜ 1-16 ውስጥ፣ ጳውሎስ የሚገልጸው የእግዚአብሄር ሀይል ጽድቅን፣ ቅድስናን እና መክበርን እርሱም በደህንነት አሰራሩ ከኃጢአት ባርነት መላቀቅንና የእግዚአብሄር ልጅ መሆንን  ሁሉ ወንጌል አጠቃሎ እንደያዘ ያሳየናል፡፡.

ሀዋርያው ጳውሎስ ጌታ እንደገለጠለት ያስተማረው ወንጌል (ስለዚህ ወንጌሌ ያለው) እግዚአብሄር ከዘላለም ያቀደው እቅድ በክርስቶስ ተፈጽሞ ሳለ እርሱ እየሰበከው ባለው ወንጌል አሁን እንደሚሰበክ  ይናገራል፡፡(ሮሜ16፡25-27)