የእውነት እውቀት[2/3]

የእውነት እውቀት

1.2 ወንጌል ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ስራና ትምህርት የተፃፈ ዘገባ:

​​​​​​በዮሐ.21:24-25 ውስጥ ቃሉ ሲናገር “ስለ እነዚህም የመሰከረ ይህንንም ጽፎ ያለ ይህ ደቀ መዝሙር ነው፥ ምስክሩም እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።​​​​​​​ ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል።” ይላል፡፡በእርግጥ ወንጌል ብቸኛው የክርስቶስ ስራ የመረጃ ምንጭ ነው፡፡በየእለቱ፣በየሰአቱ፣በየደቂቃውና፣በየሽርፍራፊው ጊዜ ሳይቀር የሰራው ድንቅና ታምራት ከቁጥር በላይ ስለነበር ሃዋርያቶች መቁጠር እስኪያቅት የበዛ እንደነበር መስክረዋል፡፡በብሉይ ኪዳን እግዚአብሄር ነብያትን ያናግር ነበር፡፡በአዲስ ኪዳን ሊያደርገው ያለውን ስራ አስቀድሞ ሲያመለክት ስለራሱም በመንፈሱ ሲገልጸው የኖረውን ጌታ ሊፈጽመው በአዲስ ኪዳን ወደ ምድር ወርዶአል፣ ቃሉንም በተግባር አሳይቶአል፡፡በነቢዩ ኢሳያስ መጽሀፍ ውስጥ አስቀድሞ የተነገረ የትንቢት ቃል እንዲህ ይላል፡-

​​​​​​​​”ፈሪ ልብ ላላቸው። እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው።በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል፤ የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል።በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፥ የድዳም ምላስ ይዘምራል፤ በምድረ በዳ ውኃ፥ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና።” (ኢሳ.35:4-6)

እናንተ በፍርሀት ምክኒያት ከእምነት የምታፈገፍጉ ልባችሁን አበርቱ፣ እጃችሁን ወደ ጌታ ለመዘርጋት አንሱ፣ ተስፋ የገባው አምላክ የዲያቢሎስን ስራ በበቀል ሊያፈርስ ይገለጣል አላቸው፡፡እስራኤላውያን እንዲያምኑ የእግዚአብሄር ቃል ተስፋን ሰጥቶ አበረታቸው፡፡እግዚአብሄር ይመጣል መጥቶም ያድናችሁዋል ተባሉ ፡፡ለማዳን በተገለጠ ጊዜ ድንቆችና ታምራቶች በህዝቡ መሀል እንደሚያደርግላቸው ያስተውሉ ዘንድ ቃሉ ማበራታቻ ድምጹን ሰጣቸው፡፡

ልክ እንዳለው መንፈስ የሆነ እግዚአብሄር አብ ሰውነትን ከቃሉ በማዘጋጀት በርሱ ሆኖ ወደ እስራኤል መጣ፡፡ያ የእግዚአብሄር ሰውነት የበቀል ደም፣ ውሀና መንፈስም ነበረው፡፡እግዚአብሄር በዚያ በፈሰሰ ደም የዲያቢሎስን ስራ (ሰውን በሀጢያት መንፈስ ተይዞ እንዲሞት የሰራውን የተንኮል ስራ) አፈራረሰበት፣ከስፍራው አስወገደው፡፡የእውሮች አይን መብራት ፣የደንቆሮዎች ጆሮ መከፈት ፣የአንካሳዎች ሙሉ መሆንና መራመድ መቻል፣ የዱዳው መከፈት ሁሉም የኢየሱስን ክብር የገለጠ የታምራት ስራ ነበር፡፡በእርሱ ያመኑ ሁሉ የህይወት ውሀ ፈለቀላቸው፣ምድረበዳ ህይወት ውሀ ሞላ፡፡ጸጋ በሰው ውስጥ ተትረፍርፎ ሀጢያተኛ ነፍስን ነጻነት ሊያወጣ ቻለ፡፡ከድካም መበርታት ፣በሀጢያት ላይ መሰልጠን፣ አጋንንትን ማውጣትና ነፍሳትን ወደ መንግስቱ ማፍለስ ተቻለ፡፡ሀዋርያው ሲመሰክር ድንቅም ቢሆን፣ ታምራትም ቢሆን በእጃችን በእኛ ሲሆን ተመለከታችሁ እንጂ በውስጣችን ሆኖ ያንቀሳቀሰንና የሰራው እሱ ብቻ ነው አሉ፡፡በዚህም ትውልድ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ ነው፡፡በትላንትናው ትውልድ የሰራ ጌታ እጁ አላጠረችም ጆሮውም ከመስማት አልደነቆረችም፡፡በየትኛውም ትውልድ ራሱን ለጌታ አሳልፎ የሰጠ ካለ እምነቱም በሀዋርያትና በነብያት መሰረት ላይ ከታነጸ ጌታ ሁሌም በዚያ  ሰው አድሮ ይሰራል፡፡እንዲህ ስለሚል፡-

​​​​​​​​ዕብ13:7-8 የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።

ትላንትና በሀዋርያት የሰራ ዛሬም በባሪያዎቹ ሊሰራ ነገ ደግሞ እስከ ምጽአቱ ድረስ ስራውን ሊቀጥል የታመነ ጌታ ነው፡፡

1.3 ወንጌል ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ መከራ፣ሞትና ትንሳኤ ያበሰረ ዜና ነው፡፡

ጌታ ኢየሱስ ሲናገር መጽሀፍት ሁሉ ስለእኔ የሚናገሩ ናቸው ብሎአል፡፡ነቢያት ጥንት የተናገሩት ስለ እርሱ ነው፡፡ከአብረሀም ጀምሮ ትውልድ ሁሉ በእርሱ መገለጥ ምክኒያት  የሚገኘውን ደህንነት ለማግኘትና ለማየት እየተመኘ ሳይሳካለት አልፎአል፡፡

​​​​​​​​1ጴጥ.1:10-12 “ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤​​​​​​​​በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር።​​​​​​​​ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን ባወሩላችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፤ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።”

ከጥንት  ጀምሮ  ስለ መሲሁ መምጣትና  መከራ ስለመቀበሉ የትንቢት ቃላት በነብያት መነገሩ ብቻ ሳይሆን እነርሱ ራሳቸው የተናገሩት የእግዚአብሄር ቃል በነርሱ ዘመን ይፈጸም እንደሆነ በጉጉት ተጠባብቀው ግን ሳየገኙት አልፈዋል፡፡ነቢያት የተናገሩትን የትንቢት ቃል ፍጻሜ መላእክ ሊያዩ እስኪመኙ ድረስ የጌታ መወለድ አስደናቂና ጉጉትን የፈጠረ ነበር፡፡

​​​​​​​​ዮሐ.1:46­-52 “ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፦ ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል አለው።​​​​​​​ናትናኤልም፦ ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው። ፊልጶስ፦ መጥተህ እይ አለው።ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፦ ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ።ናትናኤልም፦ ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው።​​​​​​​​ናትናኤልም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው።​​​​​​​​ኢየሱስም መልሶ፦ ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው።​​​​​​​​እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው።”