የአገልጋይ ስብራት[1/2]

የእውነት እውቀት

በእግዚአብሄር ፊት በአገልግሎት በቆሙ ሰዎች ላይ ከተፈጠሩት ስብራቶች አንደኛው አስደንጋጭ ክስተት ኦዛ ላይ የደረሰው ስብራት ነበር፡፡ኦዛ በእግዚአብሄር ታቦት ፊት እየሄደ ባለበትና በደስታ እግዚአብሄርን በሚያገለገልበት በዚያች ወቅት ድንገት በስህተት የፈጸመው ድርጊት በመላው እስራኤል መሀል እስከወዲያኛው የሚታወስ መቅሰፍት አምጥቶበታል፡፡ይህን ክስተት ያስተዋለ ሁሉ እግዚአብሄርን እንዴት ማገልገል እንዲገባው ቆም ብሎ ያስባል፡፡ እግዚአብሄርን ማገልገል እንዴትና እስከምን ድረስ የሚለውን ጥያቄ የሙሴና የሀዋርያው ጳውሎስ የአገልግሎት ህይወቶች በበቂ ሁኔታ ይመልሱልናል፡፡ለግንዛቤ እንዲረዳን ስለነርሱ የሚናገሩትን ጥቅሶች እንይ፡-
•”ደካሞች መስለን እንደ ነበርን በውርደት እላለሁ። ነገር ግን በሞኝነት እላለሁ፤ ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍርበታለሁ። ዕብራውያን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የእስራኤል ወገን ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የአብርሃም ዘር ናቸውን? እኔ ደግሞ ነኝ። የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? እንደ እብድ ሰው እላለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ።አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ።ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ።ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።” (2ቆሮ.11:21-28)
•”እነርሱም፡- በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን? አሉ፤ እግዚአብሔርም ሰማ። ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።እግዚአብሔርም ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም፡- ሦስታችሁ ወደ መገኛኛው ድንኳን ውጡ ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወጡ።እግዚአብሔርም በደመና ዓምድ ወረደ፥ በድንኳኑም ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምን ጠራ፥ ሁለቱም ወጡ።እርሱም፡- ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ።ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም? አለ።እግዚአብሔርም ተቈጥቶባቸው ሄደ።ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ፤ እነሆም፥ ማርያም ለምጻም ሆነች፥ እንደ አመዳይም ነጭ ሆነች፤ አሮንም ማርያምን ተመለከተ፥ እነሆም፥ ለምጻም ሆና ነበር።”(ዘኊ.12:2-10)
የእግዚአብሄር አገልግሎት የእግዚአብሄርን ድምጽ እየተከተሉ ፈቃዱን መፈጸም የሚጠይቅ ከባድ ሀላፊነት ነው፡፡አገልግሎቱ ብቃትን ሳይሆን ታማኝነትን፣ ጉልበትን ሳይሆን እምነትን፣ ማየትን ሳይሆን ማመንን፣ መመካትን ሳይሆን ዝቅታን…. እጅግ ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር እርሱንና የእርሱን በማወቅና በመጠበቅ በተሰበረ ልብ እንድንከተለው ይፈልጋል፡፡እሺ ባይና ለቃሉ ገር የሆነ ልብ እንዲሁም ፈቃዱን ለርሱ የተወ ማንነት ይፈልጋል፡፡በእርጋታና በፍርሀት በፊቱ የሚመላለስ፣ የእግዚአብሄርን ድምጽ የሚጠብቅ፣ የአለም የሆነውን ማንኛውንም ረብ የሌለው ነገር የማይፈልግ፣ ነፍሱን በእርሱ ዘንድ ያለውንም ለአምላኩ ያስረከበና የጨከነ አገልጋይ በርሱ ዘንድ ይፈለጋል፡፡እግዚአብሄርና የእግዚአብሄር የሆኑ ነገሮች በሙሉ ቅዱስ ናቸውና ወደ ሰው ነገር ውስጥ መግባት መቀላቀልም የለባቸውም፡፡ ወደ እግዚአብሄር አገልግሎት በምህረቱ የቀረቡ አገልጋዮች እግዚአብሄርን ባለመጠባበቅና የእግዚአብሄር የሆኑትን ባለማክበር መንፈስ ውስጥ ድንገት ዘው ሲሉ ክፍተኛ ጉዳት ይዘው ይወጣሉ፡፡ያንን ጉዳት የሚያሳዩት ክፍሎች ከታች ተዘርዝረዋል፡፡ማን ያውቃል፣ ዛሬ እግዚአብሄርን ማገልገል የፈለጉ እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች ተመልክተው ከጠፉት ሰዎች ታሪክ የሚያተርፍ ጥንቃቄ ቢሸምቱስ? ይሄም አንዱ የትህትና ማሳያ ነው፤ የሚተርፉና የበረከት ሰው የሆኑ አገልጋዮች በትውልዳችን መሀል እጅግ ያስፈልጉናልና፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የምናያቸው አገልጋዮች ቁጣ ያገኛቸው ወይ ቃሉን ባለማክበርና ባለማስተዋቸው፣ ወይ እግዚአብሄር የጠራቸውን ባለመታዘዛቸው ያልያም እግዚአብሄር ለራሱ የለያቸውን ነገሮች ባለማክበራቸው ነው፡፡
የዖዛ ስብራት
2ሳሙ.6:5-9 ”ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር።ወደ ናኮንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ።የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ድፍረቱ በዚያው ቀሠፈው፤ በእግዚአብሔርም ታቦት አጠገብ በዚያው ሞተ።እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ሰበረው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያ ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ተብሎ ተጠራ።በዚያም ቀን ዳዊት እግዚአብሔርን ፈራና፡- የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል?” አለ።
እግዚአብሄር በዘሁ.4፡15 ላይ አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና የመቅደሱን ዕቃ ሁሉ ከሸፈኑ በኋላ፥ የቀዓት ልጆች ሊሸከሙት ይመጣሉ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን አይንኩ ሲል አዝዞአል፡፡ኦዛ ግን በእግዚአብሄር ታቦት አካባቢ ቸልተኝነት አሳይቶ ነበር፡፡ ማስተዋል በሌለው ሁኔታ የእግዚአብሄር ታቦት የሚንቀሳቀስበትን መንገድ ሳይጠነቀቅ ቀረ፤ ታቦቱን ማጉዋጉዋዝ ስለነበረባቸው ሰዎች ምንም እስከማይመስለው ቸል አለ፡፡ኦዛ ታቦቱ በአባቱ ቤት በመቀመጡና እርሱም ብዙ ጊዜ አብሮት በመቆየቱ ምንነቱን ፈጽሞ ዘነጋ፡፡ስለዚህ እስከዚያች የመቅሰፍት ሰአት ድረስ አግዚአብሄር ለራሱ ነገር የሚጠነቀቅ እስካይመስለው ስርአቱን ረሳ፡፡ኦዛ የተቀሰፈው በታቦቱ አካባቢ ሲከናውን ስለነበረው አገልግሎት ሳይሆን የአገልግሎቱን ስርአት ባለመጠበቁና ለእግዚአብሄር ቃል ባሳየው ቸልተኝነት ነበር፡፡
ንጉስ ዳዊት የታቦቱ ወደ ስፍራው መመለስ አስፈላጊነት ስለገባው በብዙ ምስጋናና ደስታ ወደ ማረፍያው እየወሰደው ነበር፡፡በኦዛ ላይ የተፈጠረው ስብራት ግን ወደ ሀዘንና ፍርሀት ውስጥ ከተተው፡፡እንዲህ ከሆነ እንዴት ታቦቱ ከእኛ ጋር መጉዋዝ ይችላል ሲል ታቦቱን ከመውሰድ ተገታ፡፡ የእስራኤልን ደስታ በቅጽበት ያጠፋው ያ አስፈሪ የእግዚአብሄር ቅጣት በአገልግሎት አካባቢ ለሚኖር እንቅስቃሴ ማስጠንቀቂያ ይልካል፡፡ለእግዚአብሄር የተቀደሱትን ነገሮች በቸልተኝነት መመልከት፣ጥድፊያ በሚገፋው የራስ ውሳኔ ቃሉን ያላማከለ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ እግዚአብሄርን ባለመፍራት ስጋዊ የሆኑ ውሳኔዎች ውስጥ መግባት የኦዛ ስብራትን የመሰለ ቅጣት ያስከትላል፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ባለን ህብረት ልባችንን አጥብቀን መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር አውቀዋለሁ በሚል ልበ-ሙሉነት ቸልተኝነትን ማንጸባረቅ ከባድ ጥፋት እንደሚያስከትል የኦዛ አገልግሎት ላይ የተፈጠረው ሁኔታ ያስተምራል፡፡ ሁላችንም እግዚአብሄር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡በተመሳሳይ የናዳብና የአቢዩድ ህይወት በአገልግሎት አካባቢ ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ያስገነዝባል፡፡
ዘሌ.10:1-5 ”የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ።እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ።ሙሴም አሮንን፡- እግዚአብሔር፡- ወደ እኔ በሚቀርቡ እቀድሳለሁ፥ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከብራለሁ ብሎ የተናገረው ይህ ነው አለው፤ አሮንም ዝም አለ፡፡ሙሴም የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ፡- ቅረቡ፥ ወንድሞቻችሁንም ከመቅደሱ ፊት አንሥታችሁ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዱአቸው አላቸው።እነርሱም ቀርበው አነሡአቸው፥ ሙሴም እንዳለ በቀሚሳቸው ከሰፈር ወደ ውጭ ወሰዱአቸው።”
በናዳብና አብዩድ ሕይወት የልብ ኩራት፣ ያለመታገስና ቅንአት ነበር፡፡በዚያ መንፈስ ሆነው የእግዚአብሄርን እሳት ሊያቀርቡ ሞከሩ፣ ሆኖም ሞገስ ሳይሆን መቅሰፍት በራሳቸው ላይ ሳቡ፡፡እግዚአብሄር በአገልግሎት ወደ እርሱ በሚቀርቡ ሁሉ እንደሚቀደስ ተናግሮአልና ያን በማያንጸባርቅ አካሄድ ማገልገል ፍርድ ይጋብዛል፡፡ናዳብና አቢዩድ አስቀድሞ የነበራቸው ልምምድ ብዙ ነበር፡-እግዚአብሄር ህዝቡን ከግብጽ ሲያወጣ ያደረገውን ታላላቅ ታምራት የተመለከቱ ናቸው፤ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በሲና ተራራ ላይ ሲገለጥ አይተዋል፤ሙሴ አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ወጥተው በርሱ ፊት ሰግደዋል፣የእስራኤልን አምላክ አይተዋል፣በዚያ ስፍራ በፊቱ በልተዋል ጠጥተዋልም፡፡ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ እነዚህ ሁለት ሰዎች ልዩ እሳት (መሰዊያ ላይ የሚነደውን የእግዚአብሄር እሳት ሳይሆን እራሳቸው ያዘጋጁትን እሳት) ይዘው አግዚአብሄር ፊት ቀረቡ፡፡ ያቀረቡት እሳት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፣ እንዲያውም ያቀረቡት እሳታቸው ከእግዚአብሄር ዘንድ ሌላ የመቅሰፍት እሳት ጠራባቸው፡፡ ናዳብና አቢዩድ የነበራቸው ታላላቅ የአገልግሎት ልምምድ በመቅሰፍት ከመመታት አላዳናቸውም፡፡ ምክኒያቱም በእግዚአብሄር ፊት ሊያቆማቸው የሚችለው እንደቃሉ የሆነ ግንኙነት እንጂ ያሳለፉት መንፈሳዊ ልምምድ እንዳልሆነ ስላላስተዋሉ ነው፡፡
የኤሊ ስብራት
የኤሊ ከልጆቹ ጋር መጥፋት የቸልተኝነቱ ውጤት ነበር፡፡ቸልተኛ አገልጋይ ለራሱም ለቤተሰቡም ጥፋት ይጋብዛል፡፡ኤሊ ማስጠንቀቂያ የሰማው አስቀድሞ ስለነበር መቅሰፍት ቤቱ ሳይመጣ በፊት በቂ የንሰሀ ጊዜ ነበረው፡፡ያን ጊዜ ተጠቅሞ ቤቱን ማስተካከል ሲችል እርሱ እግዚአብሄር ነው የፈቀደውን ያድርግ አለ፡፡ ካህኑ ከርሱ ዘወትር የሚጠበቀውን ንሰሃና ምህረት ልመና ለራሱና ለልጆቹ አላዋለም፡፡
1ሳሙ.3:11-14፣18፣4፡10-18” እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፡- እነሆ፥ የሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገርን በእስራኤል አደርጋለሁ።በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ አወርዳለሁ፤ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ።ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤት ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ።ስለዚህም የዔሊ ቤት ኃጢአት በመሥዋዕትና በቍርባን ለዘላለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ።… ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፥ አንዳችም አልሸሸገውም። ዔሊም፡- እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።…. ፍልስጥኤማውያንም ተዋጉ፤ እስራኤልም ተመቱ፥ ሁሉም እያንዳንዱ ወደ ድንኳናቸው ሸሹ፤ እጅግም ታላቅ ግድያ ሆነ፥ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኞች ወደቁ።የእግዚአብሔርም ታቦት ተማረከች፥ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ።በዚያም ቀን አንድ የብንያም ሰው ከሰልፍ እየበረረ ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ ወደ ሴሎ መጣ።በመጣም ጊዜ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ተናውጦ ነበርና በመንገድ ዳር በወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር፤ …. ሰውዮውም ዔሊን፡- ከሰልፍ የመጣሁ እኔ ነኝ፥ ዛሬም ከሰልፍ ኮበለልሁ አለ። እርሱም፡- ልጄ ሆይ፥ ነገሩሳ እንዴት ሆነ? አለው።ወሬኛውም መልሶ፡- እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ግድያ ሆኖአል፥ ሁለቱም ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም ታቦት ተማርካለች አለ።ሰውዮውም ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ ዔሊ በበሩ አጠገብ ካለው ከወንበሩ ወደቀ፤ እርሱ ሸምግሎ ደንግዞም ነበርና አንገቱ ተሰብሮ ሞተ።”
የነቆሬ ስብራት
በእግዚአብሄር አገልግሎት አካባቢ የሚከናወን አመጽና ማሳደም ያስቀጽፋል፡፡ያን ያላስተዋሉ እነቆሬ ምድር አፍዋን ከፍታ እነርሱን ለእነርሱም ያለውን ሁሉ ዋጠቻቸው፥ በሕይወታቸውም ወደ ሲኦል ወረዱ፥ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን ስለናቁና ዋናውን ሹም ሊገለብጡ ስላሴሩ በከባድ መቅሰፍት ተመቱ፡፡
ዘኊ.16:1-40 ”የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ ከሮቤልም ልጆች የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን የፋሌትም ልጅ ኦን በሙሴ ላይ ተነሡ። …ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ወሰዱ፤ ከጉባኤው የተመረጡ ዝናቸውም የተሰማ የማኅበሩ አለቆች ነበሩ።በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው፡- ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ።… ሙሴም የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን እንዲጠሩአቸው ላከ፤ እነርሱም፡- አንመጣም፤በምድረ በዳ ትገድለን ዘንድ ወተትና ማር ከምታፈስሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህምን? ደግመህ በእኛ ላይ ራስህን አለቃ ታደርጋለህን? ደግሞ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር አላገባኸንም፥ እርሻና ወይንም አላወረስኸንም፤ የእነዚህንስ ሰዎች ዓይኖቻቸውን ታወጣለህን? አንመጣም አሉ።….ቆሬም ማኅበሩን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእነርሱ ላይ ሰበሰበ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለማኅበሩ ሁሉ ተገለጠ።እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።ሁሉን በቅጽበት አጠፋቸው ዘንድ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ።እነርሱም በግምባራቸው ወድቀው፡- አምላክ ሆይ፥ አንተ የሰው ሁሉ ነፍስ አምላክ፥ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ አንተ በማኅበሩ ሁሉ ላይ ትቈጣለህን? አሉ።እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።ለማኅበሩ፡- ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ዙሪያ ፈቀቅ በሉ ብለህ ንገራቸው።ሙሴም ተነሥቶ ወደ ዳታንና ወደ አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት።ማኅበሩንም፡- እባካችሁ፥ ከእነዚህ ክፉዎች ድንኳን ፈቀቅ በሉ፤ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳትጠፉ ለእነርሱ የሆነውን ሁሉ አትንኩ ብሎ ተናገራቸው።ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ከዙሪያውም ሁሉ ፈቀቅ አሉ፤ ዳታንና አቤሮንም ሴቶቻቸውም ልጆቻቸውም ሕፃናቶቻቸውም ወጥተው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ቆሙ።ሙሴም አለ፡- ይህን ሥራ ሁሉ አደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከኝ እንጂ ከልቤ እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ።እነዚህ ሰዎች ሰው እንደሚሞት ቢሞቱ፥ ወይም እንደ ሰው ሁሉ ቢቀሠፉ እግዚአብሔር አልላከኝም።እግዚአብሔር ግን አዲስ ነገር ቢፈጥር፥ ምድርም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ለእነርሱም ያለውን ሁሉ ብትውጣቸው፥ በሕይወታቸውም ወደ ሲኦል ቢወርዱ፥ ያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደ ናቁ ታውቃላችሁ።እንዲህም ሆነ፤ ይህን ቃል ሁሉ መናገር በፈጸመ ጊዜ ከበታቻቸው ያለው መሬት ተሰነጠቀ፤ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ቤተ ሰቦቻቸውንም፥ ለቆሬም የነበሩትን ሰዎች ሁሉ፥ ዕቃዎቻቸውንም ሁሉ ዋጠቻቸው። እነርሱም ለእነርሱም የነበሩ ሁሉ በሕይወታቸው ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም ተዘጋችባቸው፥ ከጉባኤውም መካከል ጠፉ። በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከጩኸታቸው የተነሣ፡- ምድሪቱ እንዳትውጠን ብለው በረሩ። እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥታ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላች።”
ከነዚህ አሳዛኝ ታሪኮች የምናስተውለው፡-
•ማንም የቆመ ቢመሰለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ የሚለውን ትምህርት
•እጁ ላይ ባለው ነገር ማንም መመካት እንደማያዋጣው፣ ማንም የራሱ የሆነ ስለሌለው
•ሌላውን ካገለገልኩ በሁዋላ ራሴ የተጣልኩ እንዳልሆን ልጠንቀቅ ማለት ተገቢ መሆኑን
•አገልግሎትን እጅግ ማክበር- እርፍ ይዞ ወደ ሁዋላ ማየት ስለማያዋጣ
•የሚገለግለውን ጌታ በማክበር መመላለስ
•በአምላኬ ፊት እንዴት ልቁም ብሎ መጠየቅ? በመፍራትና በመንቀጥቀጥ መዳንንም መፈጸም