የአይን አምሮትና የሥጋ ምኞት(1…)

የመጨረሻ ዘመን

የሰው ልጅ በሃጢያት ምክኒያት እግዚአብሄር ካኖረው መንፈሳዊ ስፍራ ሲወድቅ፣ ከጌታ ክብር፣ ድምጽና መገኛ አካባቢ ወዲያው ተባርሮአል፤ ሃጢያት እግዚአብሄር ሊያየው የማይታገሰው አምጽ በመሆኑ አዳም በአምላኩ አካባቢ ከነሃጢያቱ ሊመላለስ አልቻለም ነበር፤ ስለዚህ በሃጢያት በወደቀበት በዚያው ወቅት አዳም ላይ ፍርድ ወድቆበታል፤ በዚያው ወቅት ለአዳም ተሰርቶ የነበረ ስፍራና መልካም ስራም ከርሱ ሃጢያት የተነሳ ተሽሮአል። ከፍርድ በሁዋላ ህይወት ለአዳም አስቸጋሪ አስጨናቂም ሆነ፤ የእግዚአብሄር አብሮነት ራቀው። ስለዚህ ኑሮው በተረገመች ምድር ላይ በመሆኑ እርሱም በመረገሙ ምክኒያት በጎነት ከውስጡ ሊፈልቅ ፈጽሞ አልቻለም፣ ያን ያየ አምላክ እንዲህ አደረገ፦
‘’እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ።’’ (ዘፍ. 6:5-6)
እግዚአብሄር የሰውን አሳብ ሲያይና ልቡን ሲመረምር የሚያመዝነው ወደ ፈጠረው አምላክ ወደ እርሱ ሳይሆን ከርሱ ወዳራቀው ሃጢያት እንደሆነ ሲመለከት አዘነ፤ በንሰሃ ከመጸጸት ይልቅ ይበልጥ በወደቀበት ልምምድ መግፋቱም አሳዘነው።
‘’እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም ተበላሸች፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና። እግዚአብሔርም ኖኅን አለው፦ የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፤ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።’’ (ዘፍ.6:12-13)
የሰው ልጆች ነፍስ ፈጣሪ አምላክ የስጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ ተብሎ ይጠራል፤ ይህ መጠሪያ እርሱን ከሌሎች መንፈስ ከሆኑ ፍጥረታት (ከመላእክትና ከሰዎች መንፈስ) ይለየዋል። እግዚአብሄር የሰው ዘር ባለቤትና ፈጣሪ ሆኖ ሳለ ከነርሱ የሚፈልገውን ታዛዥነት በሰሩት ሃጢያት ምክኒያት ሊያገኝ ስላልቻለ ተለያቸው፤ ሰዎችም ወደርሱ የሚመለሱበትን ልብ ስላላገኙ ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚተላለፍ አመጽ ጸንተው እስከሚጠፉ ድረስ አስከፉት።
በኤር.32:26-27 ውስጥ ‘’የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። እነሆ፥ እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ
እግዚአብሔር ነኝ’’ አለ።
እግዚአብሄር የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ መሆኑን ለምን ያውጃል? ፍጥረት በሙሉ በርሱ ሰሪነት ወደ ህያውነትን እንደመጡ
ያስተውሉ ዘንድና ልባቸውን ወደርሱ እንዲመልሱ ነው፤ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ሳይሆን ባለቤትነቱ የፈጠረው አምላክ ብቻ
እንደሆነ ለማሳየትም ነው፤ ፍጥረት ግን ወደ እርሱ ወደ ፈጠረው ልቡን በመመለስ ፈንታ እየራቀ የሚሄድ ሆኖ ተገኘ።
ሰው ያለፈጣሪው አብሮነት ሰላማዊ ህይወት በዚህ ምድር ላይ መኖር አይችልም፣ ባላንጣ መንፈሳዊ ጠላት ስላለው ይህ
ጠላት ሰው እንዲጠፋ ደግሞም እንዲያጠፋ ሲመራው ኖሮአል፤ ሁሌም ከጥፋት እንዳይወጣ አዘውትሮ የሚስትበትን አሰራር
በየጊዜው ይጥልበታል፣ በሚጠፋበት መንገድም ይመራዋል፤ ውድቀቱን ያፋጥናል፤ ከአምላኩ የሚለያይበትን አሰራር ዘርግቶ
ያሰቃየዋል። ስለዚህ የጠላትን ጥልቅ አሰራር ሳያውቁ ላይ ላዩን መንፈሳዊ ነን እያሉ ይኖሩ ለነበሩ እስራኤላውያን ጌታ
ተናገራቸው፣ እንዲህም አላቸው፦
‘’እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።’’ (ዮሐ.8:44)። ጌታ ኢየሱስ ለምን እንዲህ ተናገረ? ሰይጣን የሃጢያት ምንጭ በመሆኑ፣ የሃጢያት ማስተላለፊያውና የሰውን ነፍስ የሚወጋበት መሳሪያው ከራሱ የፈለቀውና ወደ ሰው ዘር የተሰራጨው የራሱ አመጽ በመሆኑም ነው፤ በርሱ የተመታና የቆሰለ ፈውሱ ሩቅ ነው፣ ምክኒያቱም በርሱ ቁጥጥር ስር የወደቁ የተያዙበትን ክፉ አሰራር እንዳይረዱ አድርጎ ስለሚይዝ በራሱ አስተውሎ የሚያመልጥ አንድም ፍጥረት ስለማይገኝም ነው፤ እስራኤላውያን የተቆጣጠራቸውን መንፈስ
መረዳት አልቻሉምና መድሃኒታቸውን ሲገፉ፣ ሲቃወሙና እርሱን ከምድር ላይ እስከማጥፋት ሲያሴሩ እንመለከታለን።
የሰዎች አሳብ በአጠቃላይ ተበላሽቶ ወደ አምላክ የሚያገናኝ ድልድይ በታጣበት ሁኔታ ውስጥ የሰው ልጆች የህይወት ይዘት በሃጢያት ሲሰቃይ ከማየት በላይ ምን አሳዛኝ ነገር ይኖራል? በቅዱስ ቃሉ ውስጥ ስለእኛ ማንነት ጎልቶ የሚነገረው አዋጅም ይህን ውድቀታችንን ያሳያል፦
በኤፌ.2:1-3 ውስጥ ‘’በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ’’ ብሎ በመሰረታዊነት ህይወታችን በአምላክ ፊት የለየለት ፍርድ ውስጥ እንዳለ ያሳያል፤ ምክኒያቱም በበደልና በሃጢያት ተይዘን ሳለ የተቀደሰ ኑሮ ያለን ሳይሆን በዚህ ዓለም እንዳለው የጥፋትና የውድቀት ኑሮ የምንኖር ነበርንና፤ የማይታዘዙ ልጆች ሲል በሚጠራቸው አመጸኞች ላይ በሚሠራው መንፈስ አለቃ እየተከናወነ ባለ ክፉ አሰራር ቁጥጥር ስር ነበርንና የተሻለ ነገር ከቶ አልነበረንም፤ ቃሉ ሲንገር፦ ‘’በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።’’ ሲል እርግጡን ይነግረናል። ቃሉ በግልጥ እንደሚያሳየን የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ ለመሙላት ስናደርግ የነበረው ድርጊትና ልምምድ እንዲሁም በሥጋችን ምኞት ተይዘን እንኖረው የነበረው ህይወት የሃጢያትና የአጋንንት ባሪያ እንዳደረገን ግልጽ ነው። ለዲያቢሎስ እንድንገዛ ያደረጉንና ለባርነት ያጋለጡን ልምምዶቻችን በሁለትና በሶስት መንገዶች ይገለጣሉ፦
‘’ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።’’ (1ዮሃ.2:15-16)
የአይን አምሮት እንዴት?
የአይን አሮት በአይን የሚገባ ደስ የሚያሰኝ አለማዊ ነገር ሆኖ ፍላጎትና የስሜት ረሃብ ቀስቃሽ ድርጊት ነው፤ ይህ ስሜት ሄዋን ውስጥ ሲፈጠር በእባቡ ፈተና እንድትወድቅ አድርጎአታል። በሃጢያት በወደቀች ሰአትም የዲያቢሎስ ባርያ ወደመሆን ተለወጠች።
የስጋ ምኞት
በሮሜ.8:5-9 ላይ ሲናገር ‘’እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ።ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።’’ ይላል።
ስለዚህ እንደ ሥጋ ፈቃድ መኖር ሲል ሄዋን በተፈተነችበት ሃጢያት ውስጥ የሚያስገባ ድርጊትን ምርጫ አድርጎ መኖርን ስለሚጨምር ይህ የህይወት ጥፋት እንደሆነ ያሳያል።
የስጋ ምኞት ቀላል ነገር አይደለም፤ እርሱ ስጋ ውስጥ ያለ ፍላጎት ነው (በሃጢያት ላይ የወደቀው ሰው ማንነት ውስጥ ያለ ፍላጎት ነው)። ሰዋዊ ፈቃድ ፍላጎታችንን ሲመራም በሃጢያት የተገዛ ህይወት ያኖረናል፤ የእግዚአብሄርን ፈቃድ መከተል በዚያ ህይወት ውስጥ አይቻልም።የስጋ ምኞት አዳማዊ የሆነ አስገዳጅ ውስጣዊ መሻት እንጂ መንፈሳዊ ወይም አጋንንታዊ ወይም መለኮታዊ ፈቃድ አይደለም፤ ይህ አስገዳጅ መሻታችን ግን ለጠላት ሽንገላ በሙሉ ሃይሉ አጋልጦ በመስጠት ከአምላካዊ ፈቃድ ውጪ ያደርገናል።
የአይን አምሮት የጥቃት ጅማሮ
ሰዎች በስጋችን ውስጥ አምሮት የሚባል ስሜት ያይልብናል፤ ይህም ማማር፣ መፈለግ፣ መመኘት፣ መስማት፣ መጓጓት በሚባሉ የውስጥ ፍላጎቶች እንድንያዝ ያደርጋል። የምናየው ነገር ስሜታችንን ይነካና የልባችንን ትኩረት ያገኛል፣ ሃሳባችን ወዳየነው ነገር እንዲሆን በዚያ ላይ እንዲያተኩርም ያደርጋል፤ የአይን አምሮት ሳንመርጥ ያየነውን በከፍተኛ ሁኔታ እንድናተኩርበት ያደርጋል፤ በምናየው ውስጣችን እንዲነሳሳና ፍላጎታችን እንዲጨምር በማድረግም የምናየውን ለማድረግ፣ ለመያዝና ለማግኘት ያንቀሳቅሳል። ፈቃድ የድርጊት ትብብር ነው (ፍላጎቴን በድርጊት መግለጽ እፈልጋለሁ)፤የእሽታ ምልክት ነው (በልብ አሳብ ስምምነት አሳይበታለሁ)፤ሃይሌን አንቀሳቅሳለሁ (ባየሁትና በሰማሁት ነገር ላይ ተስማምቼ አከናውነዋለሁ)፤ ስለዚህ ከፈቃድ የተነሳው ፍላጎታችን በሚያይልበት ጊዜ የጸና ስሜታዊ ረሃብ ይሆንብናል፣ በዚህ ሁኔታ ልባችን ፍላጎታችንን ተከትሎ ያየነውን ያደርግ ዘንድ ዝንባሌ ያሳያል (አምኖን በእህቱ ላይ ያሳየው በጎ ያልሆነ ስሜት ወደ ረሃብ ተለውጦ እስኪታመም ደረሰ፣ ሃጥያት ያደርግ ዘንድም በሙሉ ልቡ ፈቀደ)። ፈቃዳችን ድርጊታችንን ያንቀሳቅሳል፣ ሙሉ ልባችንን ሃይላችንን ተጠቅመን ያየነውን እንድንፈጽም ልባችን ከፈቀደ ሁለንተናችን ይተባበራል፣ ወድቆም ሁለንተናችንን ይበክላል።
‘’ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ለዳዊት ልጅ ለአቤሴሎም አንዲት የተዋበች እኅት ነበረችው፥ ስምዋም ትዕማር ነበረ፤ የዳዊትም ልጅ አምኖን ወደዳት።አምኖንም ከእኅቱ ከትዕማር የተነሣ እጅግ ስለ ተከዘ ታመመ፤ ድንግልም ነበረችና አንዳች ያደርጋት ዘንድ በዓይኑ ፊት ጭንቅ ሆኖበት ነበር። … አምኖንም ትዕማርን። ከእጅሽ እበላ ዘንድ መብሉን ወደ እልፍኙ አግቢው አላት፤ ትዕማርም የሠራችውን እንጎቻ ወስዳ ወንድምዋ አምኖን ወዳለበት እልፍኝ አገባችው። መብሉንም ባቀረበች ጊዜ ያዛትና፦ እኅቴ ሆይ፥ ነዪ ከእኔም ጋር ተኚ አላት። እርስዋ መልሳ፦ ወንድሜ ሆይ፥ አይሆንም፤ እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ዘንድ አይገባምና አታሳፍረኝ፤ ይህንም ነውረኛ ሥራ አታድርግ። እኔም ነውሬን ወዴት ልሸከም? አንተም በእስራኤል ዘንድ ከምናምንቴዎች እንደ አንዱ ትሆናለህ፤ እንግዲህስ ለንጉሡ ንገረው፥ እኔንም አይነሣህም አለችው።ቃልዋን ግን አልሰማም፤ ከእርስዋም ይልቅ ብርቱ ነበረና በግድ አስነወራት፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ። ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፤ አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ። አምኖንም፦ ተነሥተሽ ሂጂ አላት።’’ (2ሳሙ.13:1-17)
ስጋ – አለም – ሰይጣን ሰንሰለት
ይህ አንዱ ከአንዱ የሚያደርገውን ትብብር የሚያሳይ የቅደም ተከተል ድርጊት ያለበት ነው። ስጋ ስሜትን፣ ፍላጎትን፣ (ለምሳሌ የሚያስተክዝ፣ የሚያሳምም፣ የሚርብ ፍላጎትን) ይዞአል፤ ፈቃዳችንን ያንቀሳቅሳል፤ አለምን የሚመኝ ውሳኔ አለው። ይህም አዳም ከጽድቅ ሲወድቅና ከእግዚአብሄር ክብር ሲጣል ይዞት የቀጠለው ማንነትን በሙሉ የሚጠቀልል ነው።የስጋ ምኞትም በውስጣችን ያለ በአይን አምሮት ተማርኮ ፈቃድን የሚያነሳሳና ድርጊትን የሚያንቀሳቅስ አሳብ ነው።
አለም፦ በሰይጣን የተሰሩ የአመጽ ልምምዶች ስለታጨቀበት አንድ በአንድ ለሰው ፍላጎት እንዲመቹ ሆኖ ያቀርባል፣ ያሳያል፣ ይሰጣል፤ ስለዚህ ቃሉ፦ ‘’ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት’’ ነው ይላል።
ሰይጣን ክፉ መንፈስ ነው፦ ይህ የክፋት ምንጭ የሆነ የእግዚአብሄርና የሰው ጠላት ሲሆን አመጽ ማድረግ የሚወድ አጥፊ
መንፈስ ነው። ሰይጣን ሰውን ሲፈትን አተያዩን ያዛባል፤ ጥፋት መርጦ ያሳየዋል (የሚወድቅበትን መርጦ፣ የሚጠመድበትንና
የሚታለልበትንም አዘጋጅቶ ያሳየዋል፣ በአይኑ ላይ አዚም ይሰራል)፤ ትኩረቱን ይስባል (ክፉውን ሲያይ ፈጽሞ እንዳያስተውል
አስመስሎ በአይኑ ላይ በማቅረብ ነው)፤ በጎ አሳብን ይከልላል (ምርጫን ያምታታል)፤ ውሳኔን ያዛባል (ህሊና እንዳይወስን
ያደርጋል)። ይህ ጠላት ወደ ጥፋት ሊያስገባን ሲያቅድ በቅድሚያ ውስጣችንን ያደናግራል፣ በትክክል እንዳናስብ ያደርጋል፣
ያየነውን መልካም ያልሆነ ነገር በአእምሮአችን/በአሳባችን ውስጥ በጎ አስመስሎ ያጎላዋል፣ ህሊናችን የሚናገረውን ምክር፣
ተግሳጽ፣ የእግዚአብሄርም ትእዛዝ፣ ስርአት፣ ህግና ሌላም ምክር እንዳይሰማን ይጋርዳል (አዚም አድርጎ፣ አሳባችንን አሳውሮ፣
አሳባችንን አበላሽቶ ከሚዛን ውጪ ያደርገናል)።
ሰይጣን ሄዋንን ከዛፎች ሁሉ አንድ ዛፍ ላይ እንድታተኩር አደረጋት፣ ልቧ ከዚያ የጥፋትዋ ዛፍ ላይ እንዳይነሳ በተለያዩ አሳቦች፣
መንፈሳዊ ውይይት በሚመስል (የጥፋት ድርድር ሊባል በሚችል የቃላት ልውውጥ) ውስጥ አስጥሞና የማሰብ ሚዛንዋን
አዛብቶ ወደጥፋት ውሳኔ አጣደፋት፣ ቀልቧን እንዳትሰበስብ አደረጋት፣ እንዲሁም ትኩረትዋ ባሳያት ነገር ላይ ብቻ እንዲሆን
ዘበዘባት፤ በዚያ መሃል ህሊናዋ የሚያነሳውን በጎ አሳብ (የእግዚአብሄር ትእዛዝ) ይከላከል ነበር (እያምታታ)፣ በመጨረሻም
ተሳክቶለት ትክክለኛ ውሳኔዋን ከህሊናዋ ደመሰሰ፣ ውሳኔዋንም እስከ ወዲያኛው ሊያዛባ ቻለ።
ዛሬም ሰይጣን ሄዋን ላይ እንዳደረገው እንዳያደርግብን ደግሞ እንዳንስት ስራውን፣ አሳቡንና ፈቃዱን ከእግዚብሄር ቃል መማር ይገባናል፤ አለምም በዲያቢሎስ ስራ የተሞላች በመሆንዋ (ስራዋ ሃጢያት ነውና) በማስተዋል እንኖር ዘንድ ስለአለምና አለማዊነት ከቃሉ መማር ይገባናል። ሰይጣን ዲያቢሎስ በሞት ላይ ስልጣን አለውና ( ሃጢያት በመስራትና በማሰራት ወደ ሞት ፍርድ የመውሰድ ስልጣን አለውና) ቸል የሚባል አይደለም። ነገር ግን በላይ ያለው እሹ እንደሚል እያንዳንዳችን ሰማያዊውን ፈቃድ ልንፈልግና ልንከተል ይገባል። በአለም ካለው ይልቅ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ብንሻ ደስ የሚያሰኘውንም ብናደርግ እንድናለን።