አይን፣ ጆሮና ልብ ተቀናጅተውና በበጎ ልቦና ቁጥጥር ስር ሆነው በህይወታችን ቢሰሩ ህሊና ውጤታማ ስለሚሆን የጽድቅ ፍሬ ያሳያል፤ ለምሳሌ አይን በተገቢው መንገድና በተገቢው ስፍራ ተገቢ ነገር እንዲያይ ቢቃኝ ከፈተና ይጋረዳል፤ ጆሮም ከሚፈትን ድምጽ ቢጠነቀቅ ልብን ከክፉ ውሳኔ ይመልሳል፣ ዛሬም ቀድሞም ከሚሰማው ያልተገባ ነገር የተነሳ ልባችን በተሳሳተ ውሳኔ ሲመራ ስለኖረ ብዙ የህይወት ውጣ ውረድ፣ ፈተናና ስብራት በሰው ልጆች ላይ ደርሶአል፡፡ ስለዚህ ልባችን ከሚፈቅደውና ከሚደገፍበት ነገር ባሻገር የእይታችንና የመስማት ሁኔታችን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ወሳኝ ውጤት የሚፈጥሩ በመሆኑ ቸል ሊባሉ አይገባም ማለት ነው፡፡
ተገቢነት የሌለው እይታ
አጋር የተባለች የሳራ ገረድ በአንድ ወቅት ከእመቤትዋ ለተሰጣት ልዩ እድል ምስጋና ሳይሆን የትእቢት አተያይ በማሳየትዋና ያደረገችው እንቅስቃሴ እመቤትዋን ስላስቆጣ ጥፋት ወለደባት፡፡ አሳዛኝዋ አጋር አጋጣሚውን ሳትጠቀምበት ስለቀረች ተሰደደች፡፡ የስደትዋ ሰበብ የሆነውም የገዛ አይንዋ ነበር፣ እርሱ ከአግባብ ውጪ ስላየና ስለወሰነ ተፈረደባት፡-
ዘፍ.16:5 ”ሦራም አብራምን፡- መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይንዋ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ አለችው።”
አጋር የነበራት የአይን ስህተት ጭንቅ ሲፈጥርባት ከእርስዋ አልፎ ምንም በማያውቀው ልጅዋም ላይ ጥፋት ደቅኖ ነበር፤ ነገር ግን ከኩራት አይን ባሻገር፣ ከመጣባት የጥፋት ውሳኔም ባሻገር የእግዚአብሄር ምህረት ተገልጦ ይታደጋት ዘንድ ሲዘረጋላት እናያለን፡፡ እግዚአብሄር ከልጁዋ ጋር በምድረ-በዳ ጥማት እንዳትጠፋና የተሸሸገን መፍትሄ እንድታስተውል ትእቢትዋን በመግፈፍ አይንዋን ከፍቶላታል፡፡ እንዲህ ለጥፋት የተነሳ አተያይ በእግዚአብሄር ምህረት ብቻ በጎ ማየት ቻለና ሁሉም ደህና ሆነ ማለት ነው፡፡ስለዚህ፡-
”እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጕድጓድንም አየች፤ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች።” (ዘፍ.21:19)
እግዚአብሔር ዓይንን በከፈተ ጊዜ ትእቢትም የለ፣ ጥፋትም የለ፤ ይልቅ የሚያኖር፣ እርካታን የሚያመጣ እይታ ብቻ ይሆናል፡፡
ለሀጢያት መጎምጀት
አንድ በከፍተኛ ስፍራ ያለ ሰው (በሀላፊነት፣ በአመራር፣ በስልጣን፣ በእውቀት) ወርዶ በማይጠበቅ ስፍራ ሲውልና በወረደበት በዚያ ካለው ነገር ጋር የፍላጎት ቁርኝት ለመፍጠር ሲሞክር (መምራት፣ መርዳት ወይም መቆጣጠር የሚገባውን ትቶ ከአግባብ ውጪ በሆነ ግንኙነት/ በአጉዋጉል ግንኙነት ሲተበተብ ሳለ) ጥፋት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ከአንዲት ግብጻዊት እመቤት ታሪክ ማየት ይቻላል፤ እርስዋ አይንዋን በአገልጋይዋ ላይ የጣለችበት አጋጣሚ በተፈጠረ ጊዜ በዚያ እይታ ተነድታ አገልጋይ ብላቴናዋን ልታሳስት ሞክራለች፡-
ዘፍ.39:7 ”ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች። ከእኔም ጋር ተኛ አለችው።”
እንደ ባለስልጣኑ ሚስት ያለ ተገቢ ባልሆነ ስፍራ የሚደረግ የአይን ማንከባለል ክፉ የአይን አምሮትን በሀጢያት እንድንፈጽም ያስገድዳል፤ ስለዚህ አይናችን በማገናዘብ እይታ ካልተያዘና ያየው ሁሉ በልብ ልብ ካልተባለ በቀር ባየው አተያይ ወደ ጥፋት ሊያወርደን ይችላል፡፡ ለዚህም ነው በ1ዮሐ.2:15-16 ላይ የሰፈረው ቃል ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው፡-
”ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።”
የአይን አምሮት ከሄዋን አንስቶ እስከዚህ ትውልድ ድረስ ብዙ ጉድ ያመጣ መተላለፍ ነው፤ አይን እየተከደነ ነገሮችን ማሳለፍ ስላልቻለ/ማጣሪያ ከፊቱ ላይ ስለሌለው/ ያለገደብ ለሀጢያት ተጋልጦአል፡፡ በዚህ ምክኒያት ከአለም ለሚወጣው ማባበልና መጎምጀት አይን መስኮት ሆኖ ልባችንን ወደ ጥፋት ያሳልፋል፣ ተከታዩ ጉድለትም ከሚዛናዊነት ያወጣዋል ማለት ነው፡፡ መቼም ቢሆን ያልተገባ ነገር አካባቢ ሆነን በአይን ትኩረት ተስበንም መመኘት ላይ እየወደቅን፣ ፈተና አይምጣብን የሚል ምኞት ውስጥ ለምን እንገባለን? ተመኝተን እናገኘው ዘንድ በሙሉ ፈቃዳችን እንፈልገዋለንና፤ በአምሮት የጀመረ የሀጢያት ፍላጎትም መላ ስሜታችንን ተቆጣጥሮ ወደ ምኞት በማደግ አድርገው እያለ ያስገድደናልና፣ ያኔ ፈቃደችንንም ገዝቶ ያዝዘዋል፡፡
ማየት፣ ማሰብ፣ መጎምጀትና መመኘት፣ ወደ ድርጊት መገስገስም ሰይጣን በነሄዋን ላይ የዘረጋቸው የማጥመጃ ደረጃዎች ነበሩ፡፡
እግዚአብሄር ደግሞ ሰውን ሊያግዝ ስለሚፈልግና በጽድቅ መንገድ ሊመራው ስለሚፈቅድ በቃሉ ይናገረዋል፣ ለምሳሌ በዘጸ.23:8 ላይ፡-
”ማማለጃን አትቀበል፤ ማማለጃ የዓይናማዎችን ሰዎች ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና።” ይላል፡፡ እግዚአብሄር የሰጠህ አይን ከተፈጠረበት አላማ ውጪ ለምን ዞር ዞር ይላል፣ ይጨፍናል ወይስ ይታወራል? ስለዚህ የዚያ የተሳሳተ ሰበብ በአይን ላይ የተሳሳተ ውጤት ካመጣ መፍሄው መለስ ብሎ ወደ እግዚአብሄር ምክር ማተኮር ብቻ ነው፤ በመመለስ አንደምንድን ቃሉ ተናግሮአልና፡፡
እግዚአብሄር በእይታ ውስጥ ያለን ትኩረት ማግኘት ይፈልጋል
እግዚአብሄር በእይታ ውስጥ ያለንን ትኩረት በማየት ወደ እግዚአብሄር ፈቃድ እንድንመጣና በጽድቅ ብርሀን በተመራ የህይወት ስርአት ውስጥ እንድንመላለስ ማስገንዘቢያዎችን ይገልጥልናል፡፡ አንዳንዴ በእይታችን ሀይል ብቻ በመታመን ምንና እንዴት የተባሉ መልስ ፈላጊ እውነታዎች ዘንግተን ወዳልተፈለገ አቀጣጫ እንገሰግሳለን፡፡ ጠላት ግን በእይታችን ስህተት ተጠቅሞ ከበባ ያደርግብናል፣ የሸምቅብናል፣ ካልነቃን ያጠምደናል አልፎም ያጠፋናል፡፡ ለዚህ ምሳሌ እንዲሆነን ሶምሶን የሆነበትን ማየት ይቻላል፡-
መሳ.16:1-5 ”ሶምሶንም ወደ ጋዛ ሄደ፥ በዚያም ጋለሞታ ሴት አይቶ ወደ እርስዋ ገባ። የጋዛ ሰዎችም ሶምሶን ወደ ከተማ ውስጥ እንደ ገባ ሰሙ፥ ከበቡትም፥ ሌሊቱንም ሁሉ በከተማይቱ በር ሸመቁበት። ማለዳ እንገድለዋለን ብለውም ሌሊቱን ሁሉ በዝምታ ተቀመጡ። ሶምሶንም እስከ እኩለ ሌሊት ተኛ፤ እኩለ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ተነሥቶ የከተማይቱን በር መዝጊያ ያዘ፥ ከሁለቱ መቃኖችና ከመወርወሪያውም ጋር ነቀለው፥ በትከሻውም ላይ አደረገ፥ በኬብሮንም ፊት ወዳለው ተራራ ራስ ላይ ተሸክሞት ወጣ በዚያም ጣለው። ከዚህም በኋላ በሶሬቅ ሸለቆ የነበረች ደሊላ የተባለች አንዲት ሴትን ወደደ። የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ወደ እርስዋ ወጥተው። እርሱን ሸንግለሽ በእርሱ ያለ ታላቅ ኃይል በምን እንደ ሆነ፥ እኛስ እርሱን ለማዋረድ እናስረው ዘንድ የምናሸንፈው በምን እንደ ሆነ እወቂ፤ እኛም እያንዳንዳችን ሺህ አንድ መቶ ብር ሺህ አንድ መቶ ብር እንሰጥሻለን አሉአት።”
ሶመሶን ወደ ጋለሞታ ሰፈር ባይሄድ ኖሮ ጋለሞታዋን እንደማያገኛት የታወቀ ነው፤ እሰፈርዋ ድረስ በመሄዱና በእርስዋ እስኪሳብ ድረስ እይታውን በርስዋ ላይ በመጣሉ ወደ እርስዋ ተጠጋ፣ በጠላቶች እስኪከበብ ድረስ አደጋ ገጠመው፤ እንዲያውም ሁዋላ ላይ ጥፋቱን ያፋጠነበት የውድቀቱ መጀመሪያ ይሀው ያለአግባብ የሄደበት አተያይ ሆኖ ተገኘ፡፡
የተስተካከለ እይታ ለፍትህ መስፈን አስፈላጊ ነው
እይታ ለፍትህ ዋና ምስክር ነው፣ በእይታ ላይ ያለው ማረጋገጫ እርግጥ በመሆኑ ሰው አስተውሎ ስላየው ነገር ይመሰክር ዘንድ ይጠየቃል፣ በሰውም በእግዚአብሄርም ዘንድ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ስለ ሰው ጉዳይ እያንዳንዱ ተመልካች ትክክለኛ ምስክር እንዲሆን አስጠንቅቆአል፡-
ዘሌ.5:1 ”ማንም ሰው የሚያምለውን ቃል ቢሰማ፥ ምስክር ሆኖም አንድ ነገር አይቶ እንደ ሆነ ወይም አውቆ እንደ ሆነ ባይናገር፥ ኃጢአት መሥራቱ ነውና በደሉን ይሸከማል።”
ማስጠንቀቂያው ምስክር አይቶ ያስተዋለውን ለእውነተኛ ፍርድ ሊመሰክር ሲገባ ያን ባያደርግ ስላየው ነገር ትክክለኛ ምስክር ባለመሆኑ ይቀጣ የሚል ነው፡፡ በእርግጥ እግዚአብሄር ያሳየንን ነገር በጽድቅ ካልመሰከርን ውሸተኞች መሆናችንና ኃጢአት መሥራታችን እንደሆነ ማወቅ ይገባናል፣ ቅጣቱም ከፍተኛ ነው፡፡
ያልተቃኘ እይታ ደግሞ አለ፤ በዚህ እይታ ጥቃት የሚመጣው የጽድቅ መዳፈን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ንጉስ ሳኦል ከእለታት በአንዱ ቀን ባየው ነገር ደስተኛ ያልሆነበት አጋጣሚ መጣበት፤ ይህ አጋጣሚ አተያዩን አጣሞበታል፤ ሙገሳና ክብር ሊሰጥ የተገባውን ጀግና በምቀኝነት ያየበት አተያይ የጥፋት ውጤትም ነበረው፤ ታሪኩ የሚከተለው ነው፡-
1ሳሙ.18:5-9 ”ዳዊትም ሳኦል ወደ ሰደደው ሁሉ ይሄድ ነበር፥ አስተውሎም ያደርግ ነበር፤ ሳኦልም በጦረኞች ላይ ሾመው፤ ይህም በሕዝብ ሁሉ ዓይን እና በሳኦል ባሪያዎች ዓይን መልካም ነበረ።እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና እየዘፈኑ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሉ ወጡ።ሴቶችም። ሳኦል ሺህ፥ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር።ሳኦልም እጅግ ተቈጣ፥ ይህም ነገር አስከፋው፤ እርሱም። ለዳዊት እልፍ ሰጡት፥ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፤ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት? አለ። ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ተመቅኝቶ ተመለከተው።”
የዳዊት ተግባር በሕዝብ ሁሉ ዓይን እና በሳኦል ባሪያዎች ዓይን መልካም ነበረ፤ ሆኖም ሳኦል ለርሱ መልካም አተያይ አልነበረውም፤ በእርሱ ዘንድ የነበረች የምቀኝነት አይን ስለነበረች ክፉ እንዲያስብና መዘዝ እንዲከተለው አደረገች፤ ሳኦል የክፉ መንፈስ ተጠቂ እስኪሆን አስጠቅታውም ነበር፡፡
በተመሳሳይ እግዚአብሄር እርሱን በተመለከተ ሰው ትክክለኛ ምስክር እንዲሆን ይጠይቃል፡-
ኢሳ.43:12 ”ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ።”
የእግዚአብሄርን ድምጽ የሰማው ባርያ፣ ማዳኑንም ያየው ህዝብ ስለእግዚአብሄር እውነተኛ ምስክር ሊሆን ተጠርቶአል፡፡ እውነተኛ ምስክር እውነተኛውን አምላክ እንደሚያከብር ሁሉ ባዕድ አምላክም እንዲረክስ ያደርጋል፡፡ እንደተባለው የእግዚአብሄር ምስክር ማዳኑን ያየና ድንቅ ቃሉን የሰማው ሰው ነው፤ እኛስ ብንሆን የሰማነው ቃል ማነህ ይለዋል? ያየነው ታምራትስ እግዚአብሄርን ስንት ነህ ይለዋል? እርሱም ሲናገር፡-
”አትፍሩ አትደንግጡም፤ ከጥንቱ ጀምሬ አልነገርኋችሁምን? ወይስ አላሳየኋችሁምን? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? አምባ የለም፤ ማንንም አላውቅም።” (ኢሳ.44:8)
ወደ ትክክለኛ እይታ ምሪት
ትክክለኛ የእይታ መርህ አይናችንን ከማይገባ ነገር አንስተን ወደ ተገቢው ስፍራ እንድንመልስ ያደርጋል፣ ከማይጠቅመው ወደሚጠቅመው፣ ከጠላት ወደ ወዳጅ፣ ከአለም ወደ መንፈሳዊነት… የሚመልስ ነው፡፡ ሙሴ ከእግዚአብሄር ዘንድ ተልኮ ወደ ህዝቡ በመጣ ጊዜ ያን አይነት ልምምድ ህዝቡ እንዲያገኝ መከራቸው፤ እንዲህ ሲል፡-
ዘጸ.14:10-14 ”ፈርዖንም በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ዓይናቸውን አነሡ፥ እነሆም ግብፃውያን በኋላቸው ገሥግስው ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች እጅግ ፈሩ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ። ሙሴንም፡- በግብፅ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው?በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና። ተወን፥ ለግብፃውያን እንገዛ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? አሉት። ሙሴም ለሕዝቡ፡- አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው።”
እስራኤላውያን እጅግ ስለፈሩና እምነታቸው ስለተጉዋደለ አይናቸውን ከጠላታቸው እንቅስቃሴ ላይ ማንሳት አልቻሉም፤ የጠላት እንቅስቃሴ ልባችንን ከአምላካችን ላይ እንድናነሳ በማድረግ፣ በፍርሀት መንፈስ እንድንያዝና በእግዚአብሄር ላይ እንድንጮህ ያደርጋል፤ እንድንጸልይ ሳይሆን እንድናጉረመርም፣ እንድናምን ሳይሆን እንድንጠራጠር በማድረግ የእግዚአብሄር እጅ እንድትሰበሰብ ያደርጋል፡፡ እግዚእብሄር ሲረዳ ግን አተያያችንን እንድናዙዋዙርና ከጠላት ወደ እርሱ አቅጣጫ እንድንመለከት ያደርጋል፣ የታወከው ውስጣችንን በማስከንም እምነትን ይፈጥራል፡፡
ፈርዖን ወደ እነርሱ በቀረበ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በፍርሀት ዓይናቸውን ወደ ጠላታቸው አነሡ፣ ተሸበሩ አለቀሱም፤ ሙሴ ግን ይረጋጉና ወደ ልቦናቸው ይመለሱ ዘንድ ለሕዝቡ፡- አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው። በዚህ ምክሩ የእይታ አቅጣጫቸውን እንዲያስተካክሉ አድርጎአቸዋል፡፡
በሌላ በኩል እይታችን ላይ እግዚአብሄር ገደብ የሚጥልበት ጊዜ እንዳለ ማስተዋል ይገባል፡፡ አለም በብዙ አማራጮች የተከበበች ናት፣ ሰውም በአማራጭዋ የሚጠቀምበት ብልሀት ስላለው የተሸለ ያለውን ይገለገልበታል፤ በእግዚአብሄር ዘንድ ግን አማራጮች ሳይሆኑ እጅግ የተሸሉና የተፈጸሙ ነገሮች ናቸው የሚገኙት፡፡ እግዚአብሄር በራሱም ጉዳይ ቢሆን ከሌሎች ጋር እንዳናስተያየው፣ አማራጭ ወይንም ከእርሱ ጋር የሚመሳሰሉ ይኖራሉ ብለን እንዳንገምት ሲል እይታችን ላይ ማሳሰቢያ ይሰጣል፣ እንዲህም ይላል፡-
”አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም።እጄን ወደ ሰማይ እዘረጋለሁና፥ እንዲህም እላለሁ። ለዘላለም እኔ ሕያው ነኝና” (ዘዳ.32:39-40)
ይህ እይታ መገለጥ የሚጠይቅ እይታ ነው፤ ታላቁን አምላክ የሚያሳውቅ እንደመሆኑ እዩ በሚለው በዚህ የሉአላዊነቱ መገለጥ ላይ በተለይ የመረጠው ህዝብ በውስጡ ከሚኖረው አህዛብ ተለይቶ በከፍታ የሚታወቅ ብቸኛ አምላክ እንዳለው በልቦና አይኑ ጭምር እንዲያየው ያዝዛል፤ እግዚአብሄር በእርግጥም በሚሰራው ስራው ሁሉ ቢገድል፣ ቢያድን፣ ቢመታ ወይም ቢፈውስ ብቸኛ አምላክ እርሱ በመሆኑ እርሱን ተገዳድረው አሳቡን የሚጠመዝዙ እንደሌሉ በአምላክነት ደረጃ እርሱን የሚስተካከሉ እንደማይኖሩም እንድናረጋግጥ ይሻል፡፡