የአይን ነገር(1…)

የመጨረሻ ዘመን

የአይን ነገር የብዙ ነገር ጉዳይ ነው፡- አይንን አስበን ወደ ምንነቱ፣ ወደ አፈጣጠሩ፣ ወደ ግልጋሎቱ እያነጣጠርን ስናጠና የእርሱን አስፈላጊነት የምናጎላበት ምክንያት ተገቢ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ ባለአይን/ አይናማ ሰው ይህችን አለም በማየት እውቀት ስለሚኖራት የማየት ችግር ካለባቸው አይነስውራን ይልቅ የእርስዋን ግፊት የመቁዋቁዋም አቅሙ ከፍ ያለ ነው፡፡ የተለያዩ እንቅፋቶችን አይናማው ሰው መሻገር የሚችላቸው ቢሆንም የእይታ ግርዶሽ ለገጠመው ግን ፈተና ስለሚሆኑ ህይወቱን አዳጋች ያደርጉታል፡፡
አይን ባለ ብዙ ዘርፍ አገልጋይ ነው፤ አይን ወደ ፊት እንዲያይ ተደርጎ ከሰውነታችን ዋናው ስፍራ ላይ/ፊታችን ላይ ከማገናዘቢያ አእምሮ በቅርብ ርቀት/ የተተከለ ብልት ነው፤ አይን ሁልጊዜ ፊት ለፊት የተፈጥሮ አቅጣጫውን ይዞ ይመለከታል፤ አይን አንገት እየዞረ ሲመራው ደግሞ ዙሪያውን ያያል፤ የአይንን ፊት ለፊት ከመመልከት ጋር አያይዘን እንደ ልማድ የሚያከናውነውን ስናጤን በተለይ የሌሎች ሰዎች ነገር ላይ እንደሚያተኩር መገንዘብ እንችላለን፡፡
አይን ሰውን ከውጪው አለም ጋር ያስተዋውቃል፤ ስለአለምና ስለሰው ያለኝ እውቀት በዋናነት በአይን የገባ ነው፤ ነገር በአይን ይገባል፣ በጎውም ክፉውም ያለመከልከል ወደ ውስጣችን መልእክት ሆኖ ይዘልቃል፡፡ አይን ግን ራሱን አያይም፣አይን እኔ ማን ነኝ፣ ምንድነው የምመስለው የማደርገውስ ሲል አይመራመርም፣ ለውጪው አካል ዋና የምንታይበት ፊታችን ምን እንደሚመስልና ምን እንዳለው እንኩዋን አይቶ መለየት አይችልም፣ ፊታችን ገጻችን ሲሆን እንከኑም ውበቱም ጉልህ ሆኖ ለአለም እየተነበበ ሳለ አይነችን ግን ዞር ብሎ አይመለከተውም፤ ውስጣችንንም እንዲሁ ሊመለከት አይችልም፣ በውስጣችን የሚመላለሰውን አሳብ አያውቅም፣ አእምሮአችን የሳለውን ምስል እንኩዋን ማየት አይችልም፤ ወደ ውጪ እንደሚያየው ወደ ውስጡ አተኩሮ አያጣራም፤ በነፍሳችን ውስጥ የተቀመጠውን አሳብ፣ ስሜትና ፈቃድም አይመረምርም፡፡ ቢሆንም ለአይን የሚሰጠው ስፍራ ታላቅ ነው፣ ምክኒያቱም በዚህ አለም ላለው ነገር ማየት የሁሉ ነገር ቁልፍ ስለሆነ፣ በአለም ውስጥ የሚከናወነው ከትንሽ እስከ ትልቅ ጉዳይ በአይን ታይቶ ውሳኔ ስለሚደረግበት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አብዛኛው እውቀታችን በማየት ላይ ይመሰረታል፤ የእኛ ደህንነት በአብዛኛው በማየት ላይ ስለሚደገፍ አይን በሁሉ ብልት ላይ ይመካል፡፡ ቃሉ አይንና ከአይን ጋር ተያይዞ ስላለው ነገር በማቴ.6:22-23 ውስጥ ይገልጣል፡-
”የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ!”
የሰውነት መብራት ዓይን ነው በማለት አይን መስኮት ሆኖ ወደ ሰውነት ብርሃን እንደሚያስገባ ያመክታል። ዓይኖቻችን ቢታወሩ ኖሮ “በጨለማ” ውስጥ እንኖር ነበር እንደ ማለት ነው። ዓይንህ መልካም ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል እንዳለው ከዓይን ጤናማነት ጋር ሰውነት የተስተካከለ፣ ሚዛኑን የጠበቀ፣ ደስተኛና ሙሉ ይዘት እንደሚኖረው ያመለክታል፡፡
በብርሃን የተሞላ መሆን እንዴት ይቻላል? ከሙሉ ጨለማ መውጣት ሲቻል፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ጌታ ትክክለኛውን እይታ ሲቸረንና ዓይኖቻችን (በብርሃን በተሞላ ህይወት ሆነን) ወደ ሰማያዊ ነገሮች ሲያተኩሩ ነው፤ ወደ ላይ በማየት ወይም ከምድራዊ ነገሮች ላይ (ከጨለማ የተሞላ ህይወት ወጥተን) ልባችንን ወደ እውነተኛ አምላክ ስናነሳም ነው።
አለማዊው ወራሽና አጥለቅላቂ የሆነው ጨለማ ብርቱ ነው፣ ይህ በአለም ያለ ሰውን ከእይታና ግንዛቤ ውጪ የሚያደርግ ጨለማ፣ ሰውን ከደስታ የሚያርቅ ጨለማ፣ ለአጋንንታዊ ጥቃት አሳልፎ የሚሰጥ ጨለማ ምንኛ ጥልቅ ነው? በስጋዊ ዓይን ምሳሌነት ጌታ ኢየሱስ የሚያሳየን ነገር የውስጥ አይን ካልበራ መንፈሳዊ ህይወት በጨለማ አሰራር ተውጦ ብሩህና በእግዚአብሄር ፊት ሞገስ ያለው ህይወት እንደሚከለክለን ነው፡፡ የዓይኖቻችን እውርነት ራሳችንን እንዳንፈትሽና እንዳንፈትን ስለሚያግድ መላ ሰውነታችን በጨለማ በተመሰለ የሀጢያት ህይወት እንዲወረስ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ከታወርን ጨለማው ያኔ በመላው ሰውነታችን የደነደነ እንዲሁም ጥልቅ ይሆናል።
እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ ይላል የኛ ጌታ፡- ኅሊና ውስጣዊ ተቆጣጣሪ ክፍል በመሆኑና የውስጥ መነጽር ሆኖ የሚያገለግል እንደመሆኑም አላማን፣ ፈቃድንና ስሜትን ይመረምራል፣ መሻትን ያዳምጣል፡፡ ኅሊና የቁጥጥር ማእከል ስለሆነ፣ የሰውን ውስጣዊ ዓላማ፣ ወሰን፣ የሕይወት ግብና ባህሪውን የሚወስን ነው፡፡ ህሊናችንን ስናዳምጥ የተፈጥሮ መርሆችን (እግዚአብሄር በውስጣችን ያተማቸውን ህግጋት) የሚያጎላና የሚያስገዛ ጉልበት፣ አቅጣጫንና ባህሪን ወደ ትክክለኛ አድራሻ የሚያመላክት ምሪት እናገኝበታለን፡፡
ነገር ግን በጎ ህሊና የነሳው ዓለማዊ አስተሳሰብ አጥፊ የግብዝነት መልክ ያለው ነው፤ ይህ ኃጢአት ሰውን ከራሱ ውጪ አድርጎ ለሰይጣን አሰራር የሚሰጥ፣ ምስኪኑ የሰው ልጅም በቀላሉ በጠላቱ የሚጠለፍበት ልማድ ነው፤ ሰይጣን በዚህ ዘዴ ነፍስን በፍጥነት ከእግሩ ስር መጣል ችሎአል፣ አማኝ ነኝ ያለውንም በሀይማኖት ሽፋን ውስጥ እንዲደበቅና አስመሳይ እንዲሆን በማድረግ ጎድቶአል፡፡ ጌታ ኢየሱስ በዚህ አካሄድ እንዳንጠመድ ያስጠነቅቃል፡፡
በህይወታችን የሚታዩ ጊዜአዊ የሆኑ ነገሮች በእኛ ላይ ደስታን መስጠት የሚችሉ ቢመስሉም ዘላቂነት የላቸውም፣ እንዲያውም ዘላለማዊ የሆኑ የእግዚአብሄር ፈቃዶች በህይወታችን እንዳይጸኑ እንቅፋት ይፈጥራሉ፡፡
ከእይታ ጋር የሚገናኙ ነገሮች፡-
የአይን አስፈላጊነት ከፍ የማለቱን ያህል አይንን በተመለከተ የሚፈጠሩ ችግሮች አልጠፉም፡-
አይን ብዙ ችግሮችን የሚቁዋቁዋም ጠንካራ የሰውነት ክፍል ቢሆንም እይታው ግን በቀላሉ በስሜት ሊጠለፍ ይችላል፤ በዚህ በአይን የተስተካከለ አመለካከት ያለመኖር ሳቢያ በሰው ላይ የተከተለ ችግር አለ፣ ለምሳሌ የሄዋን አይን ባደረገው የማይገባ እይታ ምክኒያት በእርስዋ ላይ፣ በባልዋና በትውልዱዋ ላይ የነፍስና የስጋ መርገምን ስቦአል፡-
ዘፍ.3:6-7 ”ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ። የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።”
ሄዋን ዙርያዋን ስትቃኝ በጉዋደኛዋ ግብዣ ያየችው ዛፍ ለአይንዋ አስደሳች ሆኖ ጎምጅታበታለች፣ጠፍታበታለችም፡፡ ደግሞም ለባልዋ ለአዳም ጋብዛው በጠፋችበት ጥፋት እርሱንም አስይዘዋለች፡፡ አይናችን የማይገባ ነገር ካየ የማይገባ እውቀት ለልባችን ያመጣል፡፡ በሰላምና በደስታ ከነአፈጣጠራቸው ሰክነው የኖሩ ሰዎች በአይን በመጣ አጉል እውቀት ወደ ሀዘን ወርደዋል፤ እራቁታቸውን ማየት ባላስፈለገ ህይወት ሲኖሩ ቆይተው በአጉል ሁኔታ በተከፈተ አይን ምክኒያት ተሰናከሉ፤ በዚያ አልቆሙም በዚህ ያልተገባ እውቀት አላስፈላጊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገቡ፣ ያ እንቅስቃሴያቸውም ከእግዚአብሄር ጋር አጣላቸው፡፡
በሄዋን በኩል የገባው መጎምጀት ለሰው ሁሉ የመጎምጀትን አበሳ አስተላልፎአል፡፡ በአይን በኩል ወደ ሰውነት ውስጥ የገባ ሀጢያት ሞትን በመላው የሰው አካል ላይ አስተላልፎአል፡፡ ሰው እየተባዛ በሄደ ልክ ሀጢያትም ያለማቁዋረጥ በአለም ላይ እየተባዛ ሄደ፡፡ በአይን ሰበብ የተወለደ የኃጢአት ስራ እንዲህ ሆኖ ሞትን በሰው ልጅ ላይ አምጥቶአል፡፡
አስተውሎ በማየት መቀበል በረከት
አስተውሎ ማየት ዓይንን አንስቶ ማየት ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሄር ሊባርክ ሲጠራ አይን ላይ የማስተዋል ጥንቃቄ እንድናደርግ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ መፍትሄው የጠራውን አምላክ ድምጽ መለየት ነው፡-
ዘፍ.13:14 ”ሎጥ ከተለየው በኋላም እግዚአብሔር አብራምን አለው፡- ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ”
አብራም ከተጠራበት ጊዜ አስቀድሞ ዓይኑን በማስተዋል የሚያነሳበት አጋጣሚ አላገኘም፣ ከሎጥ ጋር ሲኖሩ ብዙ ክርክር ነበራቸውና አይኑን አርቆ መወርወር ሳይችል ቀርቶ በቅርበት ካለው ችግሩ ጋር ተፋጦ ኖሮአል፡፡ እይታ በጠበበት ህይወት የእግዚአብሄር ራእይ አይታይም፣ ከፈተና ጋርም ተሁኖ አይንን ማንሳት አይቻልም፡፡ አይንን ከሚይዝ ምክኒያት በመነጠል፣ አርቆ እይታን ከሚገድብ ግርዶሽ በመለየት ግን ወደ እግዚአብሄር ራእይ መድረስ ይቻላል፡፡
2ነገ.2:9-12 ”ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፡- ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን አለው፤ ኤልሳዕም፡- መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።እርሱም፡- አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም አለ።ሲሄዱም፡- እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ። ኤልሳዕም አይቶ፡- አባቴ አባቴ ሆይ፥ የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች፥ ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ተረተረው።”
ኤልሳዕ ህልም ነበረው፣ ከእግዚአብሄር ሰው ጋር በኖረበት ዘመን በውስጡ መሻት መፈጠሩ ግልጥ ነበር፤ ከነቢዩ ኤልያስ ጋር እየተጉዋዘ ሳለ ሁሉን ነገር ትቶ እግዚአብሄርን ሊያገለግል ከወጣበት ዘመን ጀምሮ በልቡ ሲመላለስ የነበረው መሻት መልስ የማግኛው ጊዜ መድረሱን በመንፈሱ ስለተረዳ ትክክለኛዋ ሰአት እንዳታመልጠው አጥብቆ መከታተል ያዘ፤ ከክትትሉና ጥንቃቄው በተጨማሪ አስፈላጊ የነበረው ነቢዩ ያስታወቀውን ማድረግ ነበረበትና (ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል ያለው) ያን በፈጸመ ጊዜ ከእግዚአብሄር ዘንድ የጠየቀው ጸሎቱ ተፈጸመለት፡፡
የሚያዩ አይኖችን.. እግዚአብሄር ፈጠራቸው
ምሳ.20:12 ”የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዓይንን፥ ሁለቱን እግዚአብሔር ፈጠራቸው” ይላል፡፡
እግዚአብሄር ያልረዳው እንደምን አድርጎ አስተውሎ ያያል፣ ይሰማልስ? ማየት ካለብን አስፈላጊውንና የእግዚአብሄር አላማ የሚታይበትን ነገር ነው፡፡ መለኮታዊ እውቀቶች በአለም ላይ ምስጢራዊነታቸው ቀጥሎ ሰዎች ከማስተዋል ውጪ ሆነው እንዳይጠፉ እግዚአብሄር አይንንና ጆሮን ይከፍታል፡፡
ማቴ.13:10-17 ”ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፡- ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል :የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም።”
ብዙዎች እስራኤላውያን በጌታ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት እርሱን ሊሰሙትና ሊያዩት መሻቱ አልነበራቸውም፤ ልባቸው ደንድኖ፣ ጆሮአቸው ደንቁሮ፣ አይናቸውም ተጨፍኖ ነበር፤ ይህ በፈቃዳቸው ወድደው ያደረጉት ቸልተኝነትና የፍላጎት ያለመኖር በስጋ እየሰሙ በመንፈስ እንዳያስተውሉ፣ በስጋ አይን እያዩም በመንፈስ እንዳይመለከቱ አግዶአቸዋል፡፡ እግዚአብሄርም ቸልተኝነታቸው ስላስቆጣው በዘመናቸው ሊገለጥላቸው ያስፈልግ የነበረውን የመዳን እውቀት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
እግዚአብሄር በውጪም በውስጥም እይታ ሊባርከን ይፈልጋል
በለአም የሚባል ነቢይ ወደ እግዚአብሄር በተጠጋ ጊዜ አይኑ በሚያስደንቅ ሁኔታ የሚከፈትበትን አጋጣሚ አገኘ፡፡ ይህ ሰው አስፈላጊ የሆነው የውስጥ አይኑ ከመከፈቱ በፊት ግን ስጋዊ አይኑ ወደ እግዚአብሄር ነገር መነሳት ነበረበት፡፡ ስለዚህ ስጋዊ አይኑ የእግዚአብሄር ፈቃድ ወደ ሚፈጸምበት ህዝብ ተመለከተና የውስጥ አይኑ ተከፈተ፣ በመቀጠልም የእግዚአብሄርን ራእይ ያይ ዘንድ ቻለ፡-
ዘኊ.24:2-5 ”በለዓምም ዓይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዱ ተቀምጦ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ መጣ። ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፡- የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ዓይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል። ያዕቆብ ሆይ፥ ድንኳኖችህ፥እስራኤል ሆይ ማደሪያዎችህ ምንኛ ያምራሉ!”
በለዓም ሲናገር መንፈስ እንደመራው ተናገረ እንጂ ከስሜቱ ተነስቶ አልተናገረም። በዚያች ሰአት የእርሱ አይኖች የስጋ አይናቸው ተከፍቶ አለምን እንደሚመለከቱ እንደ ሌሎች የሚያዩ አልሆኑም፡፡ እርሱ ግን እግዚአብሄር ስለረዳው መንፈስ በላዩ መጣ፣ በመንፈስ እየሆነ የነበረውን የእግዚአብሄር ስራም ተመለከተ፡፡
ዋናው ነገር ይህ ነቢይ በመታዘዝ ዓይኑን ባያነሳ ኖሮ ወደ አምላካዊ እይታ ውስጥ ባልገባ፣ የእግዚአብሄር መንፈስም ባላገኘው፣ ያገኘው መንፈስም ዓይኖቹን ሲከፍትለት የእግዚአብሔርን ቃል ባልሰማ፣ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይንም ባላየ ነበረ፡፡ እግዚአብሄር ግን አገዘውና የወደቀው ዓይኖቹ ተከፈቱለት (አይኖቹ አስቀድመው ብዙ የማይገቡ ነገሮች አይተው ነበር)፣ እንዲሁም የያዕቆብን የረጅም ዘመን ራእይ የእስራኤልን ማደሪያዎች ውበትም ተመለከተበት፡፡