ባለፈው ጽሁፍ እንደተጠቀሰው የአብርሃም ዘር አብረሃም ከተለያዩ ሚስቶች የተወለዱለትን ልጆች በሙሉ የተመለከተ ቢሆንም በተለይ ግን እግዚአብሄር ለአብርሃም የገባውን የቃል ኪዳን ተስፋ የወረሰውን ዘር በይስሃቅ በኩል የተጠራውን ወገን ይመለከታል። የአብርሃም ዘር የተባለው ወገን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በገባው ቃል ኪዳን በኩል ለአዲስ ኪዳን የመዳን መንገድ እንደሆነ በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ተቀምጦአል። በማቴዎስ ወንጌል መጀመሪያ ላይ ለማሳየት የተሞከረው የትውልድ መስመር የሚያረጋግጥልን ነገር አለ፦
‘’የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ። አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ … እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት አሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እስከ ባቢሎን ምርኮ አሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኮ እስከ ክርስቶስ አሥራ አራት ትውልድ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።’’ (ማቴ. 1:1-17)
ነገር ግን አብረሃም ተስፋ ከተገባለት ይስሃቅ ሌላ ተስፋውን የማይወርሱ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጪ የሆኑ ልጆች ወልዶአል፤ በአጠቃላይ አብርሃም ከአጋር፣ ከኬጡራና ከሳራ የተወለዱ ስምንት ልጆች ነበሩት (ዘፍ.25)። ታላቁ ልጅ እስማኤል ሲሆን ከሚስቱ ከሣራ አገልጋይ ከአጋር የተወለደ ነበር። ሌሎች ስድስት ልጆች ከኬጡራ ተወለዱ፤ ነገር ግን ለአብረሃም የተገባለት የቃል ኪዳኑ ተስፋ የተላለፈው በእርጅና ዘመንዋ ሣራ ለአብረሃም በወለደችው በሁለተኛው ልጅ በይስሐቅ በኩል ነው። የእግዚአብሄር ተስፋ የሚፈጸመው እግዚአብሄር የተናገረው ነገር ሲሆን ብቻ ነው፤ ለቃሉ የሚተጋ አምላክ የተናገረውን ሊፈጽመውም ይተጋልና፤ ነገር ግን መታገስ በደከመው ሰአት አብረሃም ከዚያ ከተገባለት ተስፋ ወጣ ሲልና የሰው ፈቃድ ውስጥ ሲገባ እንመለከታለን። እግዚአብሄር ግን ሰባቱን ልጆች ሳይመለከት ለሳራ በገባው ተስፋ መሰረት ከይስሃቅ ጋር ቃል ኪዳኑን አጸና።
ወደ ይስሐቅ ስንሄድም ይስሃቅ በተራው ያዕቆብ እና ኤሳው የሚባሉ ሁለት ልጆች ወለደ። በኋላም እስራኤል በመባል የሚታወቀው ያዕቆብ የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አባት ሆነ። እነዚህ አሥራ ሁለቱ ነገዶች የእስራኤልን ሕዝብ መሠረቱ፣ እስራኤል እንደ ህዝብ የእግዚአብሔር የተመረጠ፣ የተለየ ሕዝብ እና የቃል ኪዳኑ ተስፋ ዋና ተቀባይ ሆኖአል።በሮሜ.9 ላይ ሃዋርያው ይህን ሁኔታ እንዲህ ይገልጸዋል፦
‘’በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና። እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።’’
ሃዋርያው ጳውሎስ ለወገኖቹ የሆነውን ቸርንት ሲያስብና እነርሱ ያሉበትን የውድቀት ሁኔታ በጭንቀት ሲያነጻጽር እናያለን፤ የነፍሱ ጥልቅ ስሜት አንዱ በዚህ የአይሁድ አለማመን ችግር ምክኒያት የከበደ ሲሆን የጭንቀቱ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
1. እነዚህ ሰዎች የማይተዋቸው ሲያስባቸውም የሚጨነቅላቸው በሥጋ ዘመዶቹ የሆኑ ህዝቦች ነበሩ።
2. እነዚህ ህዝቦች ወገኖቹ ሲሆኑ ምድሪቱም አገሩ ነበረችና ለነርሱ ጥልቅ ፍቅር ነበረው።
3. እነርሱ የእግዚአብሔር ባለ ተስፋ ህዝቦች ነበሩ።
4. የተስፋ ህዝቦች እንደመሆናቸው ታላላቅ መብቶች፣ ስጥታዎችና መንፈሳዊ ስፍራ የተሰጣቸው ነበሩ፦
– መንፈሳዊ ልጅነት ከእግዚአብሄር የተሰጣቸው ተስፋ ሲሆን የእግዚአብሄር ክብር በሲና ተራራ እነርሱ ብቻ እንዲመለከቱት የታደሉ ህዝቦች ነበሩ።
– ከአብርሃም ጋር የተደረገ ቃል-ኪዳን ወራሾች ነበሩ፤ በዘፍጥረት 12 እና በዘፍጥረት 17 ላይ የተነገሩት ቃል-ኪዳኖች የእስራኤል ውርስ ነበሩ፣ ይህን እንደሚያጸናላቸው ለህዝቡ የግርዘት ቃል-ኪዳን አደረገ ።
– ከዚያም በሲና ተራራ ላይ ሕጉን ሰጣቸው – እንዲህ ዓይነቱ ሕግ በአለም ላይ የትኛውም ህዝብ አልነበረውም፣ አይኖረውምም፤ እውነተኛ አምላክ ብቻ የሚሰጠው ነውና፤ የህጉ መሰጠትም ህዝቡ አምላካቸውን የሚያውቁበትና ከግብጻዊ ስነልቦና፣ ልማድና ባህል ነቅለው ወደ አዲስ ማንነት እንዲገቡ ረድቶአቸው ነበረ። ህጉ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እንደ እስራኤል ያለ ህዝብ ፍጹሙን አምላክ ያመለከ እንደሌለ ያስመሰከረ፣ የእግዚአብሄር ህግም የህይወታቸው መመሪያ እንደሆነ ያረጋገጠ ነበር፤ ህጉን ጠብቀውት ቢሆን በሁዋለኞች ዘመናት የደረሱባቸው መከራዎች፣ ፈተናዎችና ስደቶች ባልሆኑባቸው፣ ለዚህ ማሳያው የህጉ ቃል ራሱ አስቀድሞ በነርሱ ላይ ምስክር መሆኑ ነበር።
ዘዳ.4:5-7 ‘’እነሆ፥ እናንተ ገብታችሁ በምትወርሱአት ምድር ውስጥ እንዲህ ታደርጉ ዘንድ አምላኬ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ ሥርዓትንና ፍርድን አስተማርኋችሁ። ጠብቁአት አድርጉአትም፤ ይህችን ሥርዓት ሁሉ ሰምተው፦ በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና፤አምላካችን እግዚአብሔር በምንጠራው ጊዜ ሁሉ እንደሚቀርበን፥ አምላኩ ወደ እርሱ የቀረበው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው?’’
– በእግዚአብሄር ቃል-ኪዳን ውስጥ በተነገረው መሰረት የተስፋው ቃል ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ፣ ለሕዝቡ፣ ለሙሴ፣ ወዘተ. ለሁሉም ታማኝ ሰዎች ሁሉ ተጨባጭ ነበር።.
5. ከሌሎች የአለም ህዝቦች በተለየ እስራኤላውያን አባቶች (በጋራ የሚጠሩዋቸው የቀደሙ ትውልዶች እነርሱም ከአብረሃም ጀምሮ የሚጠሩ) ነበሯቸው። ይህ በሌላ አህዛብ የሌለ የነርሱ ብቻ የሆነ የትውልድ አስደናቂ ቅርስ ነበር። እንደዚህ ያለ የአባቶች ትውልድ ዝርዝር ሌላ ምድር ላይ አልነበረም – አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ እና አስራ ሁለቱ አባቶች ደግሞ በታሪካቸው ውስጥ ያሉ ታላላቅ የአባቶች ቤቶች መሪዎች ናቸው።
6. በዘጸአት መጽሐፍ ውስጥ ከምእራፍ 38 ጀምሮ እስከ መጨረሻው እንዲሁም በዘሌዋውያን መጽሐፍ ላይ የተገለጸው ታላቅ የአምልኮ ሥርዓትና በዘኍልቍ መጽሐፍ ውስጥ ያለውን የመቅደስ አገልግሎት ከአህዛብ መሃል እነርሱ ብቻ ከአምላካቸው ተቀብለው ነበር። ያ አገልግሎት እግዚአብሔርን የሚገናኙበት ማእከላዊ ስፍራ ነበረው፤ እግዚአብሔርን በፈለጉ ጊዜ ወደርሱ የሚቀርቡበት ስፍራ ድንኳኑ የተተከለበት ስፍራ ነበረና በእግዚአብሔር ፊት ለስርየትና ለምስጋና የሚሆነውን መስዋእት ለአምላካቸው የሚያቀርቡበት፣ ወደ እግዚአብሔር ሲቀርቡም ሊቀ-ካህናቱን የሚገናኙበት እንደነበረ ከቃሉ እናያለን። አህዛብ ግን እንዲህ ያለ መለኮታዊ ስጦታ ሳይኖራቸው የአጋንንት መፈንጫና መላገጫ ነበሩ። እግዚአብሄር ግን ለአብረሃም ቃል-ኪዳን የገባው ህዝቡን በምህረት፣ በጥበቃና በደስታ ሊመራው በመሃላ በማረጋገጥ ነበር።
7. የመጨረሻና ታላቁ ስጦታቸው ክርስቶስ ነበር፤ ይህ ክርስቶስ በሥጋ መጣ፤ አመጣጡ እንደተስፋው ቃል ነበር፤ እዚህ ላይ የእስራኤላውያን ከማስተዋል መዘግየትና ከእምነት መጉደል ምክኒያት ሆኖ ከእምነት መራቅ ተፈጠረ፣ እስራኤል እንደ ህዝብም የመረጣቸውን ጌታ ሳይቀበሉት ቀሩ፤ ይህ ግን እግዚአብሄር ለአባታቸው የገባውን ቃል-ኪዳን የሚሽር ከቶ አልሆነም፤ የአብረሃም መንፈሳዊ በረከት ለአህዛብም ጭምር ነውና። በእስራኤል ዘንድ ክርስቶስን ያለመቀበል ሁኔታ ግን በሃዋርያው ልብ ውስጥ የማያቋርጥ ሀዘን እና ጭንቅ ሆኖበት እናያለን።
በሌላ በኩል ለአብርሃምና ለዘሩ የተገባውና በዚህ ምድር ሊቀበለው የነበረው የቃል ኪዳን እንደተናገረው ፍጻሜ አግኝቶ የከነዓንን ምድር እንደ ዘላለማዊ ርስት ወርሶ አይተናል፣ አብረአም ብዙ ልጆችን አግኝቶአል፣ በዘሩም የአሕዛብ ሁሉ በረከት ሊሆን በቅቶአል። እነዚህ ተስፋዎች በብዙ አቅጣጫ ለይስሐቅ እና ለያዕቆብ ጸንተዋል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በመልእክቶቹ እስራኤል በምድር ሊቀበለው ከነበረው በረከት ባሻገር ለአብርሃም የተገባ የተስፋ ዘር በመንፈሳዊ ገጹ በኩል እንዳለ ያሳያል። በብሉይ ኪዳን ያልተገለጡ ግን ለአብረሃም የተነገሩ የተስፋ ቃላቶች፣ እነርሱም የአብረሃም ዘር ከሚወርሰው የከነአን ምድር ባለፈ መልኩ እግዚአብሄር ለአብረሃምና ለዘሩ ያዘጋጀው ሰማያዊ አገር እንዳለ የሚያሳይ ነው። ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን አማኞች (አይሁድም ሆኑ አሕዛብ) ሁሎችም የአብርሃም የቃል-ኪዳን ተካፋዮች እንደሚሆኑ ያስረዳል። ቃሉ እንደተናገረው ስጋዊው የተስፋ ዘር ይቀጥል ዘንድ በይስሃቅ በኩል ዘሩ ቀጥሎአል፣ የአብረሃም የስጋ ዘር በተገባለት ቃል-ኪዳን እስራኤል ተብሎ በምድሩ ላይ እየኖረ ነው ይኖራልም፤ ነገር ግን ተስፋው እርሱም የአለም ህዝብ ወራሽ ይሆን ዘንድ መንፈሳዊው ዘር ክርስቶስ አስፈላጊ ነው።
ሮሜ.9:8 ‘’ይህም፥ የተስፋ ቃል ልጆች ዘር ሆነው ይቆጠራሉ እንጂ እነዚህ የሥጋ ልጆች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም ማለት ነው።’’
አብረሃም ሁለት አይነት ልጆች ነበሩት፦ እነርሱም የተስፋ ቃል ልጆችና የሥጋ ልጆች በመባል ተለይተዋል፤ እግዚአብሄርም ዘላለማዊ ቃል-ኪዳኑን ያደረገውና ልጆች ብሎ የጠራቸው እርሱ እንደተናገረው የተወለዱትን (በተስፋ ቃል የተወለዱትን) ነው። የእግዚአብሄር ቃል-ኪዳንም መንፈሳዊ ነውና በእምነት በኩል የአብረሃም ልጆች የሆን በሙሉ የተስፋ ቃል ወራሾች ናቸው።
በአጠቃላይ፣ በስጋ ዘር አንጻር የአብርሃም ልጆች ምድራዊውን በረከት ይወርሱ ዘንድ የልጅነትን መብት ያገኙ ስለሆነ ሁሉ የስጋ ልጅነታቸውን መብት እንደያዙ አሁንም አሉ፤ ነገር ግን በተስፋ ዘር አንጻር ስናይ በአብርሃም እምነት በኩል ወራሽ የሆኑቱ መንፈሳዊ የዘር ግንድ ውስጥ ይገቡ ዘንድ ይገባል፣ እነርሱም ከአህዛብ ወገንና ከአይሁድ ወገን የሆኑ በክርስቶስ ኢየሱስ ያመኑ ናቸው።
‘’እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም።’’ ይላል (ገላ.4:28-31)።
ሁልጊዜ የአብርሃም ዘር ወራሽ የመሆን መንፈሳዊ ጠቀሜታ የአዲስ ኪዳን ትምህርት ምስጢር ነው። በጳውሎስ መልእክቶች መሠረት፣ በመንፈሳዊው መንገድ የአብርሃም ዘር ወራሽ የሚሆኑ ከአስራ ሁለቱ የእስራኤል አባቶች ይወለዱ ወይም ከምድር አህዛብ ወገን ይሁኑ፣ ብቻ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የአብረሃም የተስፋ ዘር ስለሚሆኑ የተሰጠውን ቃል ኪዳን ወራሽ ናቸው። የአብረሃም እምነት በውስጡ ብዙ በረከቶችን ይዞአል፤ የእምነቱን ቁልፍ ገጽታ ስንመለከት የሚከተሉትን እናገኛለን:-
የተስፋ ወራሽነት፡- የተስፋ ወራሽነት እግዚአብሄር አደርግላችሁዋለሁ ብሎ የተናገረውን እንደፈጸመ እኛም ከእርሱ እንደተቀበልን አመልካች ነው፤ በዚህ ምክኒያት ለአብረሃም የተገባው ተስፋ በክርስቶስ የተስፋ ዘር በኩል እውን መሆን ችሎአል፤ ስለዚህ አማኞች ለአብርሃም የተሰጠውን በረከትና ተስፋ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ባላቸው እምነት በኩል ወርሰዋል፣ ይወርሳሉም። እነዚህም በእምነት የመጽደቅ ተስፋ (ሮሜ 4፡13)፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የመሆን ተስፋ (ገላትያ 3፡14)፣ የእግዚአብሔርን ጸጋ የመቀበል ተስፋ (ሮሜ 5፡2) እና የዘላለም ሕይወት ተስፋ (ቲቶ 3፡7) ይገኙበታል።
(ሮሜ 4:13-17)
-የዓለምም ወራሽ እንዲሆን ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠው የተስፋ ቃል በእምነት ጽድቅ ነው እንጂ በሕግ አይደለም። እምነት ሲባል ለአብረሃም የተገባው ቃልኪዳን ሁሉ በክርስቶስ ስራ ውስጥ እንዳለና ያንንም ክርስቶስን በማመን የሚገኝ፣ የአብረሃም ተስፋ ወራሽ መሆን የሚያስችል መሆኑን የሚያሳይ ነው፣
-ከሕግ የሆኑትስ ወራሾች ከሆኑ እምነት ከንቱ ሆኖአል የተስፋውም ቃል ተሽሮአል፤ አብረሃም ግን እግዚአብሄርን አምኖ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ የተቆጠረለት። ዘሩ ወደ ግብጽ ምድር ገብቶ ከመብዛቱና በእስራኤል ስም ከግብጽ ከመውጣቱና ህግን በሲና ተራራ ላይ ከተገለጠው እግዚአብሄር በሙሴ እጅ የተቀበለው ቢያንስ ከ 300 አመት አስቀድሞ ነበር፣ ስለዚህ ሙሴ የተቀበለው ህግ ለአብረሃም የተነገረውን በእምነት ጽድቅን የማግኘት ተስፋ የሚሽር ሳይሆን በክርስቶስ እውን ለሚሆነው የአብረሃም እምነት ሞግዚት ሆኖ መሰጠቱን የሚያመለክት ነው፣
-ስለዚህ ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከአብርሃም እምነት ደግሞ ለሆነ ለዘሩ ሁሉ የተስፋው ቃል እንዲጸና እንደ ጸጋ ይሆን ዘንድ በእምነት ነው፤ እርሱም፦ ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ አብርሃም ባመነው እምነት በኩል (ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ አምላክ ባመነው እምነት ምክኒያት) የሁላችን አባት ነው።
(ገላ.3:6-9)
-እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት የሚለው ማረጋገጫ የሚያሳየው በእግዚአብሄር ችሎታና አሰራር ማመን በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነትን የሚያሰጥና ጽድቅን የሚያሰጥ መሆኑን ነው፣
-‘’እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፦ በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ’’ እንዳለው በአብረሃም እምነት ውስጥ ያሉ በሙሉ እርሱ የተቀበለውን ጽድቅ እንደሚያገኙ እግዚአብሄር ማረጋገጫ ሰጥቶአል፣
-‘’ስለዚህ እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ’’ – ይህ ቃል አማኞችን የሚያጸና እግዚአብሄር ለአብረሃም የነገረውን ተስፋ መፈጸሙንም የሚያረጋግጥ ነው።
(ገላ. 3:14)
-ቃሉ የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደደረሰ ያሳያል።
-(ገላ. 3:27-29)
እግዚአብሄር በገለጠው አሰራር አስቀድሞ የተሰጠው ተስፋ በህይወታችን ፍጻሜ የሚያገኝበትን መንገድ ሲያረጋግጥ እንዲህ አለ፦
‘’ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።’’