የአብረሃም ዘር(1…)

የመጨረሻ ዘመን

የአብረሃም ዘር የሚባለው ወገን በትውልድ አንጻር ያየነው እንደሆነ እየተነጋገርን ያለው የአብረሃምን ልጆችና ከርሱ በኋላ የተከተሉት ወገኖችን የትውልድ መስመር ነው፤ የአብረሃም ታሪክ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ትኩረት የተደረገበት መሆኑ መሰረቱ ይህ ሰው ከራሱና ከወገኖቹ ሰዋዊ ፈቃድ ወጥቶ ወደ እግዚአብሄር የዘላለም እቅድ ውስጥ ታዛዥ ሆኖ የገባ በመሆኑ፣ ዘመኑን በሙሉ ለተገለጠለት አምላክ ታማኝ ሆኖ በመኖሩና በቀጣይም የእግዚአብሄር ቃል ኪዳን በርሱና በዘሩ ላይ ስለተነገረ ነው።
‘’አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና፦ እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ አለው። አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው፦እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው፤ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ኪዳን አቆማለሁ፥ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር፥ የከነዓን ምድር ሁሉ፥ ለዘላለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ።’’(ዘፍ. 17:1-8)
አብረሃምና ቤቱ በብሉይ ኪዳን ዘመን በእግዚአብሄር ቃል-ኪዳን ስለተገባለት ከሌሎች የአህዛብ ወገኖች በተለይ ትኩረት ያገኘ ህዝብ ሆኖአል። መጽሃፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ለአብረሃምና ለዘሩ እግዚአብሄር ቃልኪዳን ሲገባ ከቃል-ኪዳኑ የተነሳ የአብረሃም ዘር በሰማይ እንዳሉ ከዋክብት እንደሚበዛ፣ አህዛብን እንደሚወርስና ያዘጋጀለትን የከነአን ምድርም እንደሚያወርሰው ተነግሮታል፤ በዚህ ቃል-ኪዳን አብረሃም ምድራዊውንና ሰማያዊውን ተስፋ እንደተቀበለ እናያለን፤ ምድራዊው ተስፋ ተፈጽሞ ያገኘው የአብረሃም ዘር ከባርነት ምድር ወጥቶ ቃል ወደገባለት ምድር ሲያስገባው ነበር፤ ይህ ምድር በአሁን ሰአት እስራኤልና ፍልስጤም (ሁለቱም ምድሮች) ያሉበትን ስፍራዎች ያጠቃልላል። በእምነት አባትነቱ በኩል ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ የአለም ወራሽ ሆኖአል።
አብረሃም የስጋ ልጆች ወልዶ የነበረ ሲሆን በዋናነት የሚጠቀሱት የአብረሃም ልጆች እስማኤልና ይስሃቅ ናቸው፤ እነዚህ ልጆች እንደ ስጋ ፈቃድ የተወለዱና በተስፋ ቃል የተወለዱ ሁለት ህዝቦች ምሳሌ ሆነዋል፤ እስማኤል የተባለው ልጅ ከአብረሃምና የሳራ ገረድ ከነበረችው ከአጋር የተወለደ ነው፣ ይስሃቅ ደግሞ ከአብረሃምና ከሳራ ተወልዶአል። አብረሃምና ሳራ ልጃቸው ይስሃቅን የወለዱት በእርጅናቸው ዘመን የእግዚአብሄር ቃል-ኪዳን ታምራት በነርሱ ላይ ተከናውኖ ነበር። ይህም የሆነው እግዚአብሄር የገባውን ዘላለማዊ ቃል-ኪዳን በእግዚአብሄር ፈቃድ በተወለደው በይስሃቅ በኩል አስቀጥሎ በክርስቶስ ኢየሱስ ቃልኪዳኑን ሊፈጽም ፈቅዶ ነው። እስማኤል የተወለደው በአብረሃም፣ በሳራና በአጋር ስምምነት (በሰው ፈቃድ) ሲሆን ይስሃቅ የተወለደው እግዚአብሄር ይወለዳል ሲል ቃል ስለገባላቸው (ስለዚህ በእግዚአብሄር ፈቃድ የተወለደ) ነበር።
ቀጥሎ በይስሃቅ የትውልድ መስመር የመጡት የያእቆብ ልጆች ሲሆኑ የእስራኤል ህዝብ፣ የይስሃቅ ልጆችና የአብረሃም ዘር ተብለዋል። ይህ የስጋ መስመር አብረሃም በስጋ የወለዳቸውን ልጆች ያመለክታል። ከዚያ ባለፈ ትርጉም ግን የአብረሃም ዘር የሚለው ነገር ከስጋ የዘር መስመር የሚሻገር ነው፤ በመጽሃፍ ቅዱስ ባለው አዲስ ኪዳን ውስጥ ሃዋርያው ጳውሎስ ሲጽፍ በኢየሱስ ላይ እምነታቸውን ያኖሩ ሁሉ የአብረሃም መንፈሳዊ ዘርና የርሱ ወራሽ እንደሆኑ ይናገራል። በገላ 3:29 ላይ አንድ ነገር ተቀምጦአል፣ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፦
ገላ.3:27-29 ‘’ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።’’
ስትድኑ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፤ ቀድሞ የለበሳችሁትን አዳማዊ አሮጌ ማንነት ስታወልቁ አይሁዳዊ ሁኑ የግሪክ ሰው፣ ባሪያ ሁኑ ጨዋ ወንድ ሁኑ ሴት የትኛውም ማንነታችህ/እሴታችሁ ወይም ባህሪያችሁ በክርስቶስ ስጋ በኩል በተከናወነ አሰራር ተሽሮአል፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና፣ ማንነታችሁ ከክርስቶስ በተቀበላችሁት ማንነት ስለተተካ አንድና ልዩ ሆኖአል፣ አንድ መንፈሳዊ ዘር ሆናችኋል። እናንተም ከክርስቶስ የተወለደ ዘር ከሆናችሁ የአብርሃም መንፈሳዊ ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ለአብረሃም የተሰጠውን ወራሾች ናችሁ።
በዚህ ምክኒያት ክርስቲያኖች ከየትኛውም ነገድ ወይም ብሄር ይገኙ በዚህ አሰራሩ ሁሎችም ሰዎች የአብረሃም መንፈሳዊ ቤተሰብ አባል ተደርገዋል ማለት ነው፤ የአብረሃም በመሆናቸውም ለርሱ ከእግዚአብሄር ዘንድ የተነገረውን የተስፋ ቃል ያለምንም ምክኒያትና እንቅፋት ሊወርሱ ችልዋል።
የአብረሃም ዘር የሚለው የእግዚአብሄር አሳብና ምርጫ የሚጠቁመው ባለተስፋው አብረሃምና ከእግዚአብሄር ዘንድ ከተሰጠው የተስፋ ቃል ጋር እንድንገናኝ በመደረጋችን በርሱ መስመር ውስጥ መግባታችንን አመልካች ነው።
የአብረሃም ልጆች የተባሉት ህዝቦች ሁሉ በእምነት የአብረሃም ዘር የሆኑት በአብረሃም እምነት በኩል በመሆኑ በእርሱ ተስፋ ውስጥ (ለእርሱ በተሰጠው ተስፋ ውስጥ) ስፍራ አላቸው።
መጽሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር አብረሃምንና ዘሩን እንደሰማይ ከዋክብት እንደሚያበዛው በቃልኪዳን እንደተናገረው ያሳያል፤ እንዲሁም በዘሩ በኩል የአለም ህዝብ እንደሚባረክ እንዲሁ ቃል ገብቶለታል።
በብሉይ ኪዳን ውስጥ እንደምናየው ከአብረሃም ተከታትለው የተወለዱት ትውልዶች ይስሃቅና የልጅ ልጁ ያእቆብ በኋላም እግዚአብሄር እስራኤል ሲል የጠራው ህዝብ በዚያ በረከት ውስጥ የተካተቱ እንደነበሩ እንመለከታለን። ያእቆብ አስራ ሁለት ልጆችን የወለደ ሲሆን እነዚህ ልጆችም የእስራኤል አስራ ሁለት የነገድ አባቶች የሆኑ ናቸው። እነዚህ የእስራኤል ህዝቦች አይሁድ ወይም እብራውያን ተብለው የሚጠሩ ሲሆን እነርሱም የአብረሃም የስጋ ተውልዶች ናቸው።
ልጆቹ በስጋ ትውልዶች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በአዲስ ኪዳን ሃዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው መንፈሳዊ ዘርንም አመልካች የነበሩ ናቸው (ለመንፈሳዊ ዘር ምሳሌም የነበሩ ናቸው)። በሃዋርያው ጳውሎስ አስተምህሮ ውስጥ እንዳለው ምስጢርም የአብረሃም ዘር የሚለው እውነት ከስጋ የቤተሰብ መስመር ከፍ አድርጎ ጌታ ኢየሱስን በማመን የሚገኝ መንፈሳዊ የትውልድ መስመር እንደሆነም አመልካች ነው፤ እምነታቸውን በጌታ ኢየሱስ ላይ የመሰረቱ ሁሉ ለአብረሃም የተገባው ቃልኪዳን ወራሾች እንደሆኑ ቃሉ ያስረዳል።
ገላ.4:21-31 እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፥ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ፦ አንዱ ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት ተጽፎአልና። ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአል፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል። ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት። ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፥ ከልጆችዋ ጋር በባርነት ናትና። ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት። አንቺ የማትወልጅ መካን፥ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፥ እልል በዪና ጩኺ፤ ባል ካላቱ ይልቅ የብቸኛይቱ ልጆች በዝተዋልና ተብሎ ተጽፎአል። እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም።
ስለዚህ የአብርሃም ዘር ጽንሰ-ሀሳብ በእስራኤላውያን በኩል ያለውን ሥጋዊ ዘሮቹን እና በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ያሉትን መንፈሳዊ ዘሮቹን ያጠቃልላል። እሱም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ቀጣይነት እና በምድር ላይ ከሚገኙ ወገኖች የተውጣጡ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ ማካተትን ይወክላል።
የአብርሃም ዘር በእስራኤል ሃይማኖት፣ ባህልና ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ማረጋገጫ መሰረት አብርሃም ከእግዚአብሔር የተገባለት ቃል ኪዳን የትልቅ ሕዝብ አባት እንደሚሆን የሚያረጋግጥ ነው። በተለየ ሁኔታ የአብርሃም ዘር የሚያመለክተው ልጆቹን ሲሆን እግዚአብሄር በገባለት ተስፋ አንጻር ስንመለከት ደግም የሚያመለክተው ልጁን ይስሐቅን፣ ያእቆብን እና የእስራኤልን ሕዝብ ነው።
በይስሐቅ በኩል፣ የአብርሃም የዘር ሐረግ ቀጠለ፣ ያእቆብና ኤሳው ተወለዱ፣ ነገር ግን የትውልዱ መስመር ያእቆብ በወለዳቸው ልጆች በአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች በኩል ሆነ። እነዚህ ነገዶች በአይሁድ ህዝብ ታሪክ እና ሃይማኖታዊ ስርአት ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። የአብርሃም፣ የይስሐቅ እና የያዕቆብ ዘሮች (ስማቸው ወደ እስራኤል የተቀየረ) በተለምዶ እስራኤላውያን ተብለው የተጠሩት እነዚህ ናቸው።
ነገር ግን የአብርሃም ዘር የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ ከሥጋዊ የዘር ሐረግ ባሻገር መንፈሳዊ ዘርን ይጨምራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለው አዲስ ኪዳን ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስ የሆኑ አማኞችን የአብርሃም ልጆች እንደሆኑ ይጠቅሳል። ጳውሎስ በክርስቶስ በማመን አይሁድም ሆኑ አሕዛብ የአብርሃም መንፈሳዊ ዘርና በተስፋው መሠረት ወራሾች እንደሆኑ ገልጿል።
የአብርሃም ዘር ወራሽ የመሆን ጉዳይ በኢስማኤልና በይስሃቅ በኩል ለአይሁድና ለአረቦች በስጋ ተወላጅነት የሚቆጠርላቸው የልጅነት መብት አለ (አይሁድ በይስሃቅ በኩልና አረቦች በእስማኤል በኩል የተቀበሉት ስጋዊ የትውልድ መስመር ነው)፤ ነገር ግን በክርስቶስ ላይ ባለ እምነት አማካይነት ሁሎችም የሰው ዘሮች በአዲስ ልደት ከእግዚአብሄር በመወለድ የአብረሃም ልጆችና መንፈሳዊ ዘር ሆነዋል። ለአይሁድ በተሰጠው የእምነት ተስፋ በኩል ከአብርሃም ጋር ያለው ግንኙነት የሚጸናው ዳግም በመወለድ ሲሆን ያም የተመረጠ የእግዚአብሄር ወገን የሚያደርግ ነው። በክርስትና ውስጥ፣ በክርስቶስ በማመን የምንጎናጸፈው ልጅነት የአብርሃም ወገን የሚያደርግና ክርስቶስን የሚያስለብስ ሲሆን የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ቀጣይነት እና ተፈጻሚነቱን የሚያጎላ ነው።
በአጠቃላይ፣ የአብርሃም ዘር ጽንሰ-ሀሳብ ሁለቱን ማለት ሥጋዊ ዘሮችና በእምነት እና በመንፈሳዊ ውርስ ከእርሱ ጋር አንድ የሆኑትን ወገኖች ያጠቃልላል ማለት ነው። የአብርሃም እምነት እና ከእግዚአብሔር ለእርሱ የተነገሩት ተስፋዎች በመንፈሳዊዎቹም ሆነ በስጋ ዘሮች ላይ ተጽእኖ ስላላቸው በሃይማኖት፣ በባህልና እና በማህበረሰባዊ አንድነት ላይ ጉልህ ተጽእኖ ያደርጋል።
በገላ.4:21-31 የተገለጹት ለአብርሃም የነበሩት ከባሪያይቱና ከጨዋይቱ የሆኑ ሁለት ልጆች የሁለት አለም ማንነት መሰረትና
ምሳሌ ተደርገዋል። የባሪያይቱ ልጅ በሰው ፈቃድ (የሳራ፣ የአጋርና የአብረሃም ስምምነት፣ ምክርና ውሳኔ ያለበት በመሆኑ)
እንደ ሥጋ ተወልዶአል ተባለ፥ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል (በእግዚአብሄር እቅድና ፈቃድ እግዚአብሄር ተናግሮ)
ተወልዶአል። ቃሉ ይህም ነገር ምሳሌ ነው ይላል፦ የእነዚህ ሴቶች ምሳሌነት እግዚአብሄር እንደሰጠው እንደ ሁለቱ ኪዳኖች
ናቸው፤ የመጀመሪያው ኪዳን ምድርን የሚያስወርስ ሲሆን ሁለተኛው ኪዳን ግን ሰማይን የሚያስወርስ ነው። ፊተኛው
ኪዳን ደብረሲና ላይ የተሰጠ ሲሆን ምድራዊ በረከት የሚወርሱ ልጆች ነበሩት፤ ሁለተኛው ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ
ላይ ተሰቅሎና ደሙን አፍስሶ የተሰጠ ኪዳን በመሆኑ በዳግም ልደት በደሙ ታጥበው የነጹና የእግዚአብሄር ልጆች የሆኑ
ልጆች አሉት፤ ከደብረ ሲና የሆነውን ኪዳን የተቀበለችው ሴት ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፥ እርስዋም አጋር ናት። አጋርም
ምድራዊ ኪዳን ተቀብላለች (የዚህን አለም በረከት ከአብረሃም ጋር ተካፍላለች)፤ ይህች አጋር በዓረብ ምድር ያለችው ደብረ
ሲና ናት፤ በዚያች ስፍራ እግዚአብሄር በክብር ወርዶ ህጉን ለህዝቡ ሰጥቶአል፤ ይህም ህዝብ ቃል እንደተገባለት ምድራዊ
ተስፋውን ከነአንን ወርሶአል፤ ስለዚህ ፊተኛውን ኪዳን ስናስብ አሁንም ምድር ላይ ያለችውን ኢየሩሳሌምን እናስባለን፥
ይህች ከተማ ከልጆችዋ ጋር ገና በባርነት ናትና፣ የክርስቶስን ማዳን ስላላገኘች፣ በርሱ በማመን የአብረሃምን የሰማይ ተስፋ
አላገኘችምና ። ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በእግዚአብሄር የተሰራች አገር፣ በክርስቶስ ደም የታጠቡና ዳግም የተወለዱ ልጆች
የሚኖሩባት ከተማ ናት፣ በነጻነት የምትኖርም ናት። ቃሉ በዚህ ክፍል ሲያረጋግጥ እንዲህ ብሎአል፦
‘’እኛም፥ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ
የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ
ልጅ ጋር አይወርስምና ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት። ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ
አይደለንም።’’
‘’ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።’’ (እብ. 12:22-24)