ብዙ ሰዎች መንፈሳዊነትን በሚጋፋ የህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ ራሳቸውን አስገብተው ሳለ ያሉበት ጭልጥ ያለ አለማዊነት ምንም ተጽእኖ እንዳላደረገባቸው ሆነው መንፈሳዊነትን ያለ ችግር ሊኖሩት እንደሚችሉ ለአለም ሊያሳዩ ይሞክራሉ፡፡ዝናቸውን የምንሰማው ዘፋኞች፣ቁማርተኞች፣ሞዴሊስቶች፣ በውጪው አለም ደግሞ እጅግ አስደንጋጭ በሆነ ክፉ ተግባር ውስጥ ያሉ ሰዎች ወደ ቤተ-አምልኮ ሲያዘወትሩ ወይም ፕሮግራሞችን ሲካፈሉ በሚዲያ መስኮት የምናየው ነው፡፡ታዲያ እኛም ያንን እንመለከትና በውኑ ዝነኞች በአምልኮ ስፍራ መታየታቸው ወይም ዘፋኞች ዝናቸውን ተጠቅመው በዘፋኝ መንፈሳቸው ሊዘምሩ መሞከራቸው ወደ እኛ ማስተላለፍ የሚችሉት መንፈሳዊ በረከት ይኖር ይሆንን? መንፈሳዊነታቸውን ለማስመስከር መሞከራቸውና በእግዚአብሄር ተቀባይነት እንዳገኙ ያህል መተማመናቸውስ የሚያሰኬድ ነውን? ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን፡፡በውጪው አለም በግልሙትናቸውም በዘፋኝነታቸውም እኩል ታዋቂ የሆኑ አያሌ ዘፋኞች በዚያው ልክ መዝሙርና አምልኮአቸው ተቀባይነት አግኝቶ ከነተከታዮቻቸው በሚዲያዎች ይታያሉ፡፡ በአምልኮ ስፍራ በመገኘትና በበአላት እለት ከህዝብ ጋር በመሳተፍ ብቻ መንፈሳዊ መሆን ይቻላል የሚል ድምዳሜ ላይ ያሉ ይመስላሉ፡፡
ማንም ቢሆን በአምልኮ ስፍራ ቢገኝ የሚከለክለው የለም፡፡ያ ሁኔታ ስለሚያግዛቸው ይመስላል አለማውያን እግር እንደጣላቸው ወደ ቤተ-እምነት ጎራ የሚሉት፡፡እነርሱም በዚያ የሚሆነውን እያዩ ለመምሰል ይሞክራሉ፡፡እንደዚህ ሆነው አምልኮውን ተሳትፈውት ይመለሳሉ፡-ለመምሰል ዘምረዋል፣አምልከዋል፣ሰግደዋል፣ቃሉን ሰምተዋል (አንዳንዶች ግን ጽድቅ ተርበው እንደሆነ መካድ የለበትም)፡፡
በእነዚህ ሰዎች ዘንድ ያለ ልምድ አማኞችን የመመሳሰል አካሄድ አለው፡፡እንደ አማኝ ራስን በመቁጠር ለመጽናናት መሞከር ይኖራል፣ ነገር ግን አለምንም እግዚአብሄርንም ላለመተው የሚሞክር ህይወት ስለሚንጸባረቅበት ውጤት የለውም፡፡እጃቸው ላይ ባለው ነገር ተማምነው ከመንፈሳውያን ቀድመው ለመታየት ሙከራ የሚያደርጉም አይታጡም፡፡እንዲያውም በመንፈሳዊ ህይወት ደካማ የሆኑ አንዳንዶች ሊመስሉአቸው ይሞክራሉ፡፡
ገላ.5:16 ”ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።”
አንዳንድ ዘፋኞች መንፈሳዊነት ከዘፈን ወይም ከሚመሳሰል ስራ ጋር በአብሮነት ሊቀጥል እንደሚችል ሲሰብኩ ይሰማል፡፡ ሌሎች ደግሞ የእግዚአብሄርን ስም ስለጠሩ ብቻ መንፈሳዊነትን የተቀበሉና እግዚአብሄርም የሰማቸው ይመስላቸዋል፡፡ስሙን በጠሩ ጊዜ ወደ እግዚአበሄር የቀረቡ እርሱም ፈጽሞ የተቀበላቸው አድርገው ስለሚቆጥሩ ያለመሸማቀቅ ተግባራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ገላ.5:19-21 ”የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”
አንድ ነገር ማጤን ቢቻል መልካም ይሆናል፡-ማንም ከእግዚአብሄር ያልተወለደ ከሆነ እርሱን እግዚአብሄር አይቀበለውም፣ እግዚአብሄር ልጆቹን ብቻ በመንግስቱ ይቀበላልና፡፡ስለዚህ ለእግዚአብሄር ነገር እውነተኛ ቅናት ያለው ማንም ሰው ቢኖር በእግዚአብሄር ይታወቅ ዘንድ ዳግም ከውሃና ከመንፈስ ይወለድ ዘንድ ይገባል (ዮሀ.3፣3-5)፡፡
በተሳሳተ መንገድ መጉዋዝና ያለማመን ወይም ለወጉ ያህል የሆነ እምነትን መያዝ እንደማያዋጣ አውቆ በህይወት አዲስና እውነተኛ ምእራፍ ለመጀመር መሞከር አስተዋይነት ነው፡፡
የሚዲያዎች አስተዋጽኦ
የሃገራችን ሚደያዎች በበአላት ሰሞን አማኝ ለመምሰል የሚያደርጉት ዝግጅት ሰፊ ነው፡፡የጌታን ልደት፣ስቃዩን፣ሞቱን፣ቀብሩን፣ ትንሳኤውንና የመሳሰለውን እያነሱ ያወራሉ፡- ታሪክ ያጣቅሳሉ፣አንዳንዴ ከመጽሀፍ ቅዱስ እየነካኩ እለቱን ለማዳመቅ ይሞከራሉ፡፡በዝግጅታቸው እለት ያዘፍናሉ፣ይተርካሉ፣ያዘምራሉ፣ይቀልዳሉ፣መንፈሳዊ ነገር ያወራሉ…፡፡ግባቸው መንፈሳዊ ነገሮችን በማስተላለፍና በማስተማር ላይ አያተኩርም፣ ይልቅ የተመልካቹን ጊዜ መቆጣጠርና የአየር ጊዜያቸውን በስኬት ማገባደድ ላይ ትኩረት ይሰጣል፡፡
ከዚህ ሁኔታ በመነሳት መንፈሳዊነት በሚዲያዎች ፊት ምንም ያህል ክብደት እንደሌለው መገንዘብ እንችላለን፣ የአምልኮ ሽሚያቸው ከገበያና ገንዘብን ከመሰብሰብ እንደማያልፍ በግልጽ ስለምናይ፡፡
አንዳንዴ በእኛነታችን ላይ ምንም ነገር አያስከትሉም ብለን የገመትናቸው ነገሮች በሆነ ወቅት ከግምታችን ውጪ ተጽአኖዋቸውን ሲያሳርፉብን ይታያል፡፡በዚህ አለማዊነትና መንፈሳዊ ነገሮች በሚደበላለቁበት ስፍራም (በሚዲያው አካባቢ) የሚሆነው ያ ነው፡፡ምክኒያቱም ሳናስተውል በዚያ አካባቢ የጠራ እውቀትን ፍለጋ የምናማትር ካለን መደናገርና ቆይቶም ቢሆን ተጽእኖ የሚያሳድር ልማድ ስር እንደምንወድቅ እሙን ነው፡፡
ጌታ ኢየሱስ በማር.4:24 ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ ሲል ያስጠነቅቃል።
የሚዲያዎች ቁንጽል መንፈሳዊ እውቀት የጠፉትን አብልጦ የሚያጠፋ፣የሳቱትን አብልጦ የሚያስት ፣እንዲሁም የዘነጋውን እንዳይነቃ የሚያደነዝዝ ነው፡- መንፈሳዊ እውቀት ነው ያልነው ሁሌም በአለም እውቀትና በበአል አጀብ ስለሚከበብና በመዝናኛ ግርግር ስለሚዋጥ ማለት ነው፡፡
የሲኒማ ኢንዱስትሪው ሽሚያ
የሲኒማው ኢንዱስትሪ መንፈሳዊነትን ለመቅረጽ ሲሞክር ይታያል፡፡ብዙ ፊልሞች በክርስቶስ ህይወት ዙርያ ተሰርተዋል፣ እየተሰሩም ነው፡፡የክርስትና ትርክቶችም በፊልም ይዘጋጃሉ፡፡መንፈሳዊ የሚመስሉ ወይም ስም የተሰጣቸው ፊልሞች አላማቸው መንፈሳዊ ትምህርት ማስተማር ሳይሆን ዝናና ከፍተኛ የገንዘብ ገቢ ማግኘት ነው፡፡ስለ-ክርስቶስ ፈተና (ፓሽን ኦፍ ክራይስት በሚል) የተሰራውን ፊልም ማስታወስ ይቻላል፡፡ብዙ ሰው መንፈሳዊ ትምህርቱን ያደንቃል፣ፊልሙን ያዘጋጁት በሙሉ ግን ብዙ ገንዘብ ከሰበሰቡ በሁዋላ የሰሩትን ዘንግተው ወደ ሌላ ገንዘብ ማግኛ ስራቸው ዞረዋል፡፡አዘጋጆቹ የሉም፣ በስራቸው የተመሰጡት ግን ከመንፈሰዊነት ጋር እየታገሉ ከስፍራቸው አልተንቀሳቀሱም፡፡
ዮሐ.4:23-24 ”ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።”
መንፈሳዊ ህይወት በሚታይ ነገር አይነቃቃም፣ በፊልም ትርክት አይሻሻልምም፡፡በሰው እጅ ስራ ከፍ አይልም፡፡መንፈሳዊነት የእግዚአብሄር ቃልና የመንፈሱ ሀይል ውጤት ነው፡፡ቃልና መንፈስ የመታየትና የመዳሰስ ጉዳይ ሳይሆን የእምነትና ለርሱ የመለየት ውሳኔ ነው፡፡በሲኒማ የተዘጋጁ ስለ-ቤተክርስቲያን ወይም ስለ-ክርስቶስ የሚተርኩ ፊልሞች አላማቸው ወይም ውስጣዊ ስሜታቸው ገንዘብ ላይ ያተኮረ ነውና በነርሱ መንፈሳችንን ለማነቃቃት አንድከም፡፡ስራቸው ህይወት አይሆንም፡፡እንዲያውም በነርሱ ከመመሰጥና ከመሳብ ወጥተን መንቃት እንዲሆንልን ፊታችንን ወደ ህያው ቃሉ መመለስ ያስፈልጋል፡፡
ጌታ ኢየሱስ እኔ የነገርኩዋችሁ ቃል አውነት ነው ህይወትም ነው ስላለ ወደ ህያው ጌታ ዞር ማለት ይገባል፡፡ ትኩረትን ወደ ድምጹ ማድረግና በድምጹ አቅጣጫ መራመድ ትክክለኛው ሕይወት የሚገኝበት አካሄድ ነው፡፡
በእውነት ህይወትን የሚሻ ማን ነው? እርሱ የህያው አምላክን ድምጽ ይስማ ይከተልም፣ ከእርሱ ጋር ለዘላለም የሚኖርበትን መንገድ አምላኩ ይገልጥለታል፡፡