የቸርነቱን ደውል አስተውል

የመጨረሻ ዘመን

የእግዚአብሄርን ባህሪ የሚገልጥ አዋጅ እንዲህ ይላል፡-
ዘጸ.34:6-8 ”… እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ።ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጐነበሰና ሰገደ።”
የእግዚአብሄርን ምህረትና ቸርነት የሚያውቁ ቅዱሳን ያን እንደ አላማ ሁልጊዜ ከፍ በማድረግ ያነሳሉ፡፡እኛም በዘመናችን በእግዚአብሄር ታምነን በተጠጋነው ጊዜ ሁሉ የተለማመድነው ብርቱ የማዳን እጁን ሲሆን እሱም በሰላም ሲመራንና ሲያጥረን በርትተን መቆም ችለናል፡፡የኛን ፈቃድ ቸል ብለን የርሱን ለመከተል በመወሰናችን ያገኘናቸው የቸርነቱ ስጦታዎችም የተትረፈረፉ ናቸው፡፡እንዲሁም የእኛን ጉድለት አስተውለን በማየት ወደዚህ አምላክ ፊት ምህረትን ፍለጋ በቀረብን ሰአት የርሱ ፈጣን ምላሽ ከእኛ መቅረብ እጅግ የፈጠነ በመሆኑ በምህረት መትረፍ ብቻ ሳይሆን በቸርነቱም መጎብኘት እንደቻልን ራሳችን ምስክር ነን፡፡ውዱ አምላክ ልጆቹን እጅግ ስለሚወድ እንዲያ ያከብራቸዋል፡፡የእግዚአብሄር ቸርነት ወደተትረፈረፈለት ንጉስ ስንምጣ፡-
1ነገ.3:5-14 ”እግዚአብሔርም በገባዖን ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም፡- ምን እንድሰጥህ ለምን አለ።ሰሎሞንም አለ፡- እርሱ በፊትህ በእውነትና በጽድቅ በልብም ቅንነት ከአንተ ጋር እንደ ሄደ፥ ከባሪያህ ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ቸርነት አድርገሃል፤ ዛሬ እንደ ሆነም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተህ ታላቁን ቸርነትህን አቆይተህለታል። አሁንም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫንና መግቢያን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ። ባሪያህም ያለው አንተ በመረጥኸው ሕዝብህ ስለ ብዛቱም ይቈጠርና ይመጠን ዘንድ በማይቻል በታላቅ ሕዝብ መካከል ነው። ስለዚህም በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፥ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው፤ አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ይፈድ ዘንድ ማን ይችላል?ሰሎሞንም ይህን ነገር ስለ ለመነ፥ ነገሩ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘውእግዚአብሔርም አለው፡- ፍርድን ትለይ ዘንድ ለራስህ ማስተዋልን ለመንህ እንጂ ለራስህ ብዙ ዘመናትን ባለጠግነትንም የጠላቶችህንም ነፍስ ሳትለምን ይህን ነገር ለምነሃልና እነሆ፥ እኔ እንደ ቃል አድርጌልሃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ።ደግሞም ከነገሥታት የሚመስልህ ማንም እንዳይኖር ያልለመንኸውን ባለጠግነትና ክብር ሰጥቼሃለሁ። አባትህም ዳዊት እንደ ሄደ፥ ሥርዓቴንና ትእዛዜን ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴ የሄድህ እንደ ሆነ፥ ዕድሜህን አረዝመዋለሁ።”
ከላይ ባየነው ጥቅስ ውስጥ እግዚአብሄር ሰለሞንን በምህረት ሊያኖረውና ቸርነቱን በህይወት ዘመኑ ሁሉ ሳያቁዋርጥ ሊያሳየው ቃል እንደገባለት የምንመለከተው ነው፡፡ንጉሱ አምላኩን እስከተከተለና ትእዛዙንና ስርአቱን እስከጠበቀ ድረስ የተናገረውን ሊያጸና ቃል ገብቶአል፡፡እግዚአብሄር እንደተናገረው ለንጉስ ሰሎሞን ባደረገ ጊዜ የሰሎሞን ታሪክ ተቀይሮ ነበር፡-
1ነገ.10:23-29 ”ንጉሡም ሰሎሞን በባለጠግነትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ በልጦ ነበር።ምድርም ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረለትን ጥበቡን ይሰማ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ይመኝ ነበር።…. ንጉሡም ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ።ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አገር አስመጣ፤ የንጉሡም ነገዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር።”
ንጉሱ በሁሉም አቅጣጫ በሚባል ደረጃ ከሚታሰበው በላይ የንብረት በረከት ወደ ጎተራው እስገባ፡፡ብዙዎች ሊያዩት እንኩዋን እስኪጉዋጉ ድረስ የሚስብ የእግዚአብሄር ሞገስ በላዩ ላይ ተገለጠ፡፡ልብ እንበል ለንጉሱ የእግዚአብሄር ቸርነት እንዲህ እንዲበዛለት የሆነው በእግዚአብሄር ፈቃድ ነበር፡፡ከዚያ ትይዩ ግን ይህን ያደረገው አምላክ ከንጉሱ ይጠብቅ የነበረው የህይወት ይዘት እንደነበረ መረሳት የለበትም፡፡በቃሉ ያን አስረግጦ ነግሮታል፡፡
ነገሩን ወደእኛ አምጥተን ብንመለከት ከእግዚአብሄር ጋር ቸርነቱ በዝቶልንና በምህረቱ ተከብበን ስንኖር ዝንጉ መሆን እንደማይገባን ቃሉ እኛንም ያስጠነቅቀናል ማለት ነው፡፡ ያም ከሰውነታችንና ከማንነታችን በላይ የሆነው በጎነቱ በከበበን ጊዜ እኛ ከዚያ የምቾት ክበብ በቶሎ ውጥት ብለን በእግዚአብሄር ፊት በዝቅታ መቅረብ እንዳለብን አመልካች ነው፡፡ይህ ልምምድ በንጉስ ዳዊት ህይወት የነበረ ነው፡፡እግዚአብሄርም ስለንጉሱ በ1ዜና.17:7-27 ውስጥ የተናገረውን ስናይ እንዲህ ይላል፡-
”አሁንም ባሪያዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፡፡ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ። በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደታላላቆች ስም ለአንተ ስም አደርጋለሁ። ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ፥ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፤ እንደቀድሞው ዘመንና በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም፤ ጠላቶችህንም ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ። እግዚአብሔር ደግሞ ቤት እንዲሠራልህ እነግርሃለሁ።ወደ አባቶችህም ትሄድ ዘንድ ዕድሜህ በተፈጸመ ጊዜ ከልጆችህ የሚሆነውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ።እርሱ ቤት ይሠራልኛል፤ ዙፋኑንም ለዘላለም አጸናለሁ።እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ከአንተ አስቀድሞ ከነበረው እንዳራቅሁ፥ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም።”
የእግዚአብሄርን ቸርነትና ምህረት አቀባበልና አያያዝ በተመለከተ ምሳሌ እንዲሆነን የዳዊትና የልጁ የሰለሞንን ህይወት እዚህ ጋ በማነጻጸር ማየት እንችላለን፡፡
ዳዊት በተደረገለት የእግዚአብሄር ምህረትና ቸርነት ተዘናግቶ ከእግዚአብሄር ፊት የሚርቅ ሰው አልነበረም፣ወይም ከምህረቱ ጋር የመጣው ቸርነት አላዘናጋውም፡፡ይልቅ እያነዳንዱ የምህረት ስጦታ ወደ እግዚአብሄር የሚቀርብበት መንገድ ሆኖት ወደ መቅደሱ ያሰገባው እሱ ዝቅ ብሎም ያደረገለትን አምላክ ከፍ እንዲያደርግ ያስችለው ነበር፡፡ያ የዳዊት እንቅስቃሴና ውሳኔ እግዚአብሄርን እንደልቤ እስኪል ያስደሰተው ተግባር ነበር፡፡ዳዊት የእግዚአብሄርን በረከትና የገባለትን የረጅም ዘመን ተስፋ ከነብዩ አፍ ሰምቶ እንዲህ አለ፡-
(ቁ16)”ንጉሡም ዳዊት ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፡- አቤቱ አምላክ ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድር ነው?አምላክ ሆይ ይህ በፊትህ ጥቂት ነበረ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ስለ ባሪያህ ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ እንደ አንድ ባለ ማዕርግ ሰው ተመለከትኸኝ። አንተ ባሪያህን ታውቀዋለህና ለባሪያህ ስለ ተደረገ ክብር ዳዊት ጨምሮ የሚለው ምንድር ነው?አቤቱ፥ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ ታስታውቀው ዘንድ ስለ ባሪያህ እንደ ልብህም ይህን ታአምራት ሁሉ አድርገሃል።አቤቱ፥ እንዳንተ ያለ የለም፥ በጆሮአችንም እንደሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም።”
ልጁ ንጉስ ሰለሞን ግን ቸርነቱን ባገነነለት መጠን እንደ አባቱ ዝቅ ብሎ ወደ እግዚአብሄር ለመቅረብ ከመትጋት ይልቅ ወደ ቸልተኝነትና መዘናጋት ውስጥ ሲገባ እንመለከታለን፡፡ያ መዘናጋቱና ቸልተኝነቱ ከምቾቱ ጋር ተዳምረው አይኑን ከእስራኤል አምላክ ላይ እንዲያነሳ አስገድደውታል፡፡በዚያ ሳያበቃም በእግዚአብሄር የተጠሉትን የአህዛብ አማልክት፣ የሚያመልኩቸውንም ሴቶች ልጆች ሚስቶች አድርጎ አበዛ፡፡ቸልተኝነቱ አይኑን በማይረካ የሴሰኝነት ምኞት ሞላው፡፡ሚስቶቹን ባበዛቸው ልክም ልቡን ከእስራኤል አምላክ አስወግደው አሳደዱበት፡፡አግዚአብሄር አስቀድሞ ያስጠነቀቀውን እንዲዘነጋም አደረጉት፡፡ሁዋላም ለቅጣት ዳረጉት፡፡
1ነገ.11:1-6 ”ንጉሡም ሰሎሞን ከፈርዖን ልጅ ሌላ፥ በሞዓባውያንና በአሞናውያን በኤዶማውያን በሲዶናውያንና በኬጢያውያን ሴቶች፥ በብዙ እንግዶች ሴቶች ፍቅር ተነደፈ።እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች፡- አምላኮቻቸውን ትከተሉ ዘንድ ልባችሁን በእውነት ያዘነብላሉና ወደ እነርሱ አትግቡ፥ እነርሱም ወደ እናንተ አይግቡ ካላቸው ከአሕዛብ፥ ከእነዚህ ጋር ሰሎሞን በፍቅር ተጣበቀ።ለእርሱም ወይዛዝር የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶች ሦስት መቶም ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ልቡን አዘነበሉት።ሰሎሞንም ሲሸመግል ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም እንደ ነበረ የሰሎሞን ልቡ እንዲሁ አልነበረም።ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፥ የአሞናውያንንም ርኵሰት ሚልኮምን፥ ተከተለ።ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፥ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን በመከተል ፍጹም አልሆነም።”
ንጉስ ዳዊት የእግዚአብሄር የቸርነት ስራ ድምጽ ፈጥሮ ወደ መገኛው ሲያስገባው ሰለሞን ግን ባለማስተዋሉ ቸርነቱ የምቾትና የተድላ አጥር ሆኖበት ወደ ስጋዊ ፍላጎት አዘነበለ፡፡ዝንባሌው ሌሎች ችግሮችን ወልዶአል፡፡ብዙ ችግርና ከእግዚአብሄር መለየት፣በራሱም ላይ ቁጣን የሚፈጥር አካሄድ የሆነበት በተፈጠረበት የምቾት ብዛት ነው፡፡ምቾት አይኑን ያለቅጥ ከፍቶበት በተቀበለው እንዳይረካና እንዳያመሰግን ሲያደርገው ሌሎች ነውሮችን በስራው ላይ እንዲደራርብ አድርገው ወደ ጥፋት አስገብተውታል፡፡ በበረከት የባረከው እግዚአብሄር በዚህ አካሄዱ አጅግ ተቆጣ፡-
1ነገ.11:7-12 ”በዚያን ጊዜም ሰሎሞን ለሞዓብ ርኵሰት ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለው ተራራ ላይ መስገጃ ሠራ።ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑ መሥዋዕትም ለሚሠዉ ለእንግዶች ሚስቶቹ ሁሉ እንዲሁ አደረገ።ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳይከተል ካዘዘው ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡን አርቆአልና፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ነገር አልጠበቀምና እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተቈጣ። እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው፡- ይህን ሠርተሃልና፥ ያዘዝሁህንም ቃል ኪዳኔንና ሥርዓቴን አልጠበቅህምና መንግሥትህን ከአንተ ቀዳድጄ ለባሪያህ እሰጠዋለሁ።ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም።” አለው፡፡
እኛስ ብንሆን የልባችንን ይዘት ብንመረምር ምን እናገኝበታለን? የእግዚአብሄር ቸርነትን ድምጽ ልባችን በምን አይነት ተግባር ይተረጉመው ይሆን? ወሳኙ የልባችን ዝንባሌ ነው፡-ወሳኙ በእግዚአብሄር ላይ ያለን መታመን ነው፣ ትኩረታችንን የያዘው ፍላጎታችንም ነው፡፡
ሮሜ.2:4-8 ”ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል።”
ስለዚህ ቸርነቱ የማይጠፋ ህይወትን እንድንፈልግ የብርታት ምንጭ እንዲሆነን እንጂ ቁጣና መቅሰፍት የሚስብ እንዳይሆንብን የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት እናክብር፡፡