የታመነው ዜና

የእውነት እውቀት

ወንጌልን እጅግ አስተማማኝ፣ውብና አስደሳች ዜና ያደረገው በጌታ ኢየሱስ የሆነው ጸጋና እውነት በውስጡ በመገለጡ ነው፡፡የጌታ ኢየሱስ ወደ ምደር መምጣት ከመንፈስ አለም ሳይቀር የምስራች ነጋሪዎችን የጋበዘ ነበር፡፡ እነዚህ እንግዶች መናፍሰቶች ቢሆኑም ለሰው ልጅ ተስፋ የሆነ ዜና ስለያዙ ያን የታመነ ዜና ያበስሩ ዘንድ ወደ ምድር ወረዱ፡፡ ስለዚህ ያኔ እንዲህ ሆነ፡-

” በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፡- እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፡- ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።” (ሉቃ2፡8-13)

ለሕዝቡ የሆነ ታላቅ ደስታ፣ መላእክትንም ያስደሰተና ያስመሰገነ ያ ብስራተ-ልደቱ ለእኛ ደግሞ በወንጌል መጣልን፡፡ ወንጌል የደህንነታችን መልካም ዜና ብስራት፣በኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተፈጸመውን የደህንነት ስራም በእምነትና በጸጋ እንድንቀበለው የተነገረ የእውነት አዋጅ፡፡ ይህ የደህንነት ወንጌል ስለዘላለማዊ ህይወት የሚናገር የምስራች ብቻ ሳይሆን እግዚአብሄር የሰውን ልጆች ከሀጢያት፣ከዘላለም ሞት፣ከሰይጣን እና አለምን አሁን ካሸፈነው እርግማን የሚያስመልጥበትን ዘላለማዊ እቅድ የያዘ ሰነድ ሆኖ ወደ አለም የተሰራጨ የሚሰራጭም ነው፡፡

ሰይጣን ሰዎች የክርስቶስን ክብር እንዲያዩ ስለማይፈቅድ የጌታን እውነት ከሚገልጠው ወንጌል እንዲርቁ ምክኒያትን ይደነቅራል፡፡ጌታ ኢየሱሰ ግን ቀርቦ ሰዎችን በወንጌሉ ያድናል፡፡ምንም እንኩዋን ሰዎች በሰይጣን ተንኮል ፈተና ቢደርስባቸውም ጌታ ግን መልክተኞችን በመንፈሱ ሀይል በመላክ ወንጌል በአለም ላይ አንዲሰበክ እያደረገ ይገኛል፡፡

ወንጌል የእውነተኛውን አምላከ መዳን የሚገልጽ ድምጽ እንጂ ሰዋዊ የቃላት ቅንብር አይደለም፣ መረጃም አይደለም፡፡ሰዎች ሰምተው የሚለወጡበት መንፈስ ያለበት ቃል ነው፡፡

“ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና” ሲል በወንጌል ውስጥ ያለውን አሰራር ይናገራል፡፡(1 ተሰ 5 ÷ 5)፡፡

አንደበተ ርቱዕ ሰዎች በሚናገሩት ቃል አሳማኝ በመሆናቸው የሰዎችን ስሜት እና እውቀት በቀላሉ ሊያንቀሳቅሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ሰዎች በዚህ ችሎታቸው ማዳንና ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግስት ማስገባት አይችሉም፤ ከዚህ የተነሳም  ወንጌል ከንግግር ባለፈ በመንፈስና በኃይል በብዙ ማስተዋል ወደ ሰዎች መምጣት አስፈልጎአል፡፡

በሌላ በኩል ወንጌል እግዚአብሄር ከሰዎች ጋር የሚገናኝበት፣ መልእክቱን፣ትእዛዙንና አቅጣጫውን የሚያመላክትበት ዋነኛ መሳርያው ነው፡፡እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር የገለጠበት አንድያ ልጁን (የክብሩ መገለጫ የሆነውን ክቡር ስጋውን) ውርደት ላለበት የሰው ልጅ መፍትሄ፣መክበርያና ከጥፋት የማምለጫ መንገድ እንዲሆን ጨክኖ ለሞት አሳልፎ ሰጥቶታል፡፡እግዚአብሄር የራሴ የሚለው ልጁን ሰውን በመውደዱ ምክኒያት አሳልፎ መስጠቱን ያበሰረን በወንጌሉ  ነው፡፡በ1ቆሮ.15፡1-4 ውስጥ ሲናገር፡-

”ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ።እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ። መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥”

ወንጌል የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን መጽሀፍት ውስጥ ብዙ ቦታ ተጠቅሶአል፡፡ወንጌል በግሪክ ትርጉም መልካም ዜና ወይም የምስራች የሚል ነው፡፡ወንጌል ለሰው ልጆች ከእግዚአብሄር ዘንድ የተላከ የደስታ ዜና እሱም እግዚአብሄር ራሱ በልጁ ሞትና ትንሳኤ የሰራው የደህንነት ስራ ብስራት ነው፡፡

በሌላ በኩል ወንጌል ከአዲስ ኪዳን መጽሀፍት ውስጥ የሚገኙትን አራቱን የወንጌል መጻህፍት ማለትም የማቴዎስ፣የማርቆስ፣የሉቃስና የዮሀንስን መጻህፍት ያመለክታል፡፡ ወንጌል እጅግ አስፈላጊ ከሆነበት ምክኒያት አንዱ የተስፋ ቃል ፍጻሜ ብስራት በመሆኑ ነው፡፡በእብራውያን መልእክት እንደተገለጸው፡-

” ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤…” (ዕብ.1:1-3)

በእርግጥም ወንጌል የእግዚአብሄር አሳብ ከመነሻው እስከ መጨረሻው የተመላከተበት በእርሱም የሚያምኑ ፍጻሜ ተስፋቸውን እንዲያስቡና ዘወትር በናፍቆት እንዲጠባበቁ ማድረግ የሚችል አዋጅ ነው፡፡

2ጢሞ.1፡8-11” እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤ ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥ አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።”

ወንጌል የዘላለም ህይወት የተገለጠበት ምስራች ብቻ አይደለም፡፡ለዘላለም ህይወት የተጠሩ ሁሉ ራሳቸውን ክደው ያዳናቸውን ጌታ እንዲከተሉ የሚያስተምር ታላቅ መመሪያ ነው፡፡ ሀዋርያው ጳውሎስ ወንጌል ለርሱ የህልውናው ምክኒያት ስለመሆኑ ገልጾአል፡፡በእርግጥም ያለጥርጥር ወንጌል እንዳመለከተው እንኖራለን እናልፋለንም፣ በወንጌል እንደተመለከተውም ከስጋ ሞት በሁዋላ የዘላለም ህይወትን በትንሳኤ እንወርሳለን፡፡በሞት ጥላ ውስጥ ያድር የነበረ የሰው ልጅ ተስፋ ወደ ተሞላ የብርሀን ህይወት የገባው ወንጌል ቀድሞ ስለበራለት ብቻ ነው፡፡ይህ የሚያድን ወንጌል በህይወት እየበራ እንዲቀጥል ከትምህርት ነፋስ መጠበቅ ይፈልጋል፡፡

የወንጌል ብርሀን ካልተገለጠ ግን በሰው ልጅ ላይ ዘላለማዊ የህይወት ጥፋት መከተሉ የማይቀር ነው፡፡ወንጌል የእግዚአብሄርን መለኮታዊ ስጦታ ለሰው ያበስራል፡፡መለኮታዊ ስጦታውም ጸጋ ይባላል፡፡ጸጋ የሰው ልጅ በራሱ ጥረት ሊያገኘው ያልቻለው በእግዚአብሄር ቸርነት ምክኒያት ብቻ የሚገኘው ስጦታ ነው፡፡ጸጋ የማንንም አስተዋጽኦ የማይፈልግ ለሰው ልጆች የተዘጋጀ ሙሉ መለኮታዊ ስጦታ ነው፡፡ የሰው ልጅ ስለ ጸጋ በሚኖረው የተሳሳተ አመለካከት ግን ከእግዚአብሄር በነጻ የሚመጣውን ውድ ስጦታ ሳይገለገልበት ይቀራል፡፡በመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ የተከሰተ ችግር ደግሞ ያን ያሳያል፡፡ያኔ አንዳንዶች ከወንድሞች መሀል ተነስተው በጸጋው ስጦታ ላይ ከራሳቸው ፈቃድ የሆነን ነገር ሊደርቡ ሞክረው ነበር፡፡በሐሥ.15፡1 ላይ የሚታይ እንዲህ ያለ ታሪክ አለ፡-

ሐዋ.15:1-2” አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና። እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር።በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ጊዜ፥ ስለዚህ ክርክር ጳውሎና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቈረጠ።”

በቁ.5 ላይ የተጠቀሱት ወንድሞች ቀድሞ ከፈሪሳውያን ወገን የነበሩ ናቸው፡፡እነዚህ ሰዎች በወንጌል ላይ ተቃርኖና ክርክር ሲያነሱ በወንጌል የተገለጠውን የጸጋ ይዘትና ባህሪይ በተቃራኒው እየሞገቱ ነበር፡፡በዚያ የተነሳው ጭቅጭቅ በተመሳሳይ ቆይቶም ጳውሎስን በገላትያ ገጥሞታል፡፡እርሱም በነዚያ ገጠመኞች ላይ ብርቱ ተገሳጽን ያመጣ መልእክት ጽፎአል፡፡በገላ.2፡4-5 ያለው ክፍል እንዲህ ይላል፡-

” ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ። የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም።”

ሀዋርያው ጳውሎስ ወንጌል የሰጠውን የጸጋ ደህንነት ከሰው በሚገኝ የጽድቅ ስራ ሊተኩ እንዳይሞክሩ ለቅዱሳን ጽፎአል፡፡ በሮሜ.4:1-5 ውስጥ እንዲህ አለ፡-

” እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም።መጽሐፍስ ምን አለ? አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።ለሚሠራ ደመወዝ እንደ ዕዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቈጠርለትም፤ነገር ግን ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያደድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል።”