ብዙ ጊዜ ጥቂት ያልነው አነስተኛ ወይም አይን የማይገባና ጉልበቱን ቸል ያልነው ኢምንት ነገር ብዙሀኑን ሰርስሮ በመግባት በክሎና ተሰራጭቶ በራሱ ባህሪ ሲውጠው እናያለን፡፡የእግዚአብሄር ቃል ጥቂት እርሾ ሙሉውን ሊጥ እንደሚያቦካ ያስረዳል፡፡ጥቂት እርሾ ውስጥ ያለ ኮምጣጣ ነገር የመሰራጨት ጉልበቱ ከፍተኛ በመሆኑ ንጹሁንና ትኩሱን (ያልከረመውን) ሊጥ በፍጥነት ያቦካዋል/ያኮመጥጠዋል፡፡ነገሩ በእኛም ህይወት ውስጥ ሲመጣ እንዲሁ ነው፡፡እንደ እርሾው የኮመጠጠና የማይመች ነገር ከእኛ ህይወት ጋር ሲቀላቀል በእጅጉ ይበክለናል፡፡ምናልባት ጥቂት ስለሆነ ቸል ልንለው እንችላለን ወይም ተጽእኖው ወዲያው አይሰማንም ይሆናል፣ግን ሲውል ሲያድር ያመረቅዛል፣ህይወትን በእጅጉ ያጎሰቁላል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል በ1ቆሮ.5‹6-13 ይህንን ያስተምረናል፡-
1Cor 5:6 1ቆሮ.5:6-13 ”መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንዲያቦካ አታውቁምን? እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም።”
ሳናስተውለው በጎ ነው ብለን በሙሉ ልብ የያዝነው እንዲያውም የተመካንበት ነገራችን ቃሉ ፊት ሲቀርብ መልካም እንዳልሆነ እንገሰጻለን፡፡በቃሉ ተቀባይነት እስከሌለውና በእርሱ የተደገፈ እስካልሆነ ድረስ እኛ ጋ ያለው ነገራችን ወደ እግዚአብሄር አያቀርበንም፡፡እርሾ ከአሮጌ ሊጥ ላይ የሚቆነጠር ለአዲሰ(ትኩስ) ሊጥ እንደማብላያነት የምንጠቀመው ማቡኪያ ነው፡፡ሊጥ ሙሉው የቂጣ መጋገሪያ ግብአት በመሆኑ የምንፈልገውን የጣእም ደረጃ እናገኝ ዘንድ ከእርሾ ጋር እንቀላቅለዋለን፡፡
የክርስቲያኖች ማንነት በሊጡ ይመሰላል፡፡አዲሱ ሊጥ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመንና በስሙ የሀጢያት ስርየትን በመቀበል የሚገኝ አዲስ ማንነት ነው፡፡አዲሱ ማንነት አሮጌውን ሰዋችንን አሸንፎ ክርስቶስን ወደ መምሰል የምናድግበት ሂደት ውስጥ አንዳስገባን እናምናለን፡፡እርሾው ግን ከአሮጌው አዳም (ከቀድሞው አለማዊ ህይወትና ማንነት) ተቆንጥሮ ወደ አዲሱ ማንነት ውስጥ የሚገባ ጣልቃ ገብ ባህሪ ነው፡፡ይህ ባህሪ እግዚአብሄር እንድንላበሰው የሚፈልገውን ማንነት የመበከል ጉልበት ያለው ኮምጣጣ ነገር ነው፡፡ጳውሎስ ስላዘነበት እርሾ ሲናገር፡-
1Cor 5:1 1ቆሮ.5:1-5 ”በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና።እናንተም ታብያችኋል፤ ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን? ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ።እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።”
ክርስቶሰ የፋሲካ በግ ሆኖ ታርዶልናል፡፡በፋሲካው የመቅሰፍት ማለፍ የተረጋገጠልንን ሰዎች ነን፡፡ጌታ ታሪካችንን ከእብራውያን የመቅሰፍት ማለፍ ጋር ያስተካከለው ራሱን ለመሰዋት በማቅረብ ነው፡፡ስለዚህ እኛ ግብጽን ካስቀሰፈው ባህሪ አምልጠን ምህረት (ክርስቶስ) ውስጥ ከገባንበት ሰአት አንስቶ ሌላ ማንነት የተላበስን መሆናችንን ባለመዘንጋት ያዳነን ክርስቶስን በህይወታችን ማክበር ይገባናል፡፡የእግዚአብሄር ቃል ለእብራውያን ሲናገር፡-
”ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤታችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ።”(ዘጸ.12:15)
አሮጌው እርሾ ከፋትና ግፍ በውስጡ ይዞአል፡፡ክፋት ከአሮጌው ማንነት (አዳም) ሀጢያትን በሙሉ ማስገባት የሚችል በር ነው፡፡ክፋት በዋናነት የወንድማማችነት ጠር በመሆኑ ወደ ነፍሰገዳይነት ይወረወራል (ወነድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ እንደመሆኑ)፡፡ግፍም እንዲሁ ልብን የሚያደነድን ባህሪ ሆኖ ሰውን የማይገባ ስፍራ እንዲረግጥ ያደፋፍራል፡፡ክርሰቲያኖች በአጠቃላይ በነዚህ አደገኛ የእርሾ ባህሪ ላለመያዝና ከጌታ የተቀበልነውን መልካም ነገር ላለማጣት መጠንቀቅ ይገባናል ማለት ነው፡፡ቅንነትና እውነት ያለው የመስዋእት ቂጣ የሚጋገረው እርሾ ከሌላው አዲስ ሊጥ እንደመሆኑ ለእግዚአብሄር ቅዱስና ህያው መስዋእት የሚሆነው እኛነታችንን ማቅረብ የምንችለው ከአሮጌው ማንነት ተጨልፎ የገባውን ኮምጣጣ ማንነት በማስወገድ የክርስቶስን ማንነት በህይወታችን ስናጎላ ነው፡፡የእግዚአብሄር ቃል በሮሜ12፡1 እንዲህ ይላል፡-
”እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው።”
በሌላ በኩል የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ይዘት በሊጡ/በትኩሱ ሊጥ ይመሰላል፡፡ስለዚህ ቤተክርስቲያን እንደማህበር በውስጡዋ ያሉ ወገኖች በበጎ ህይወት የሚመላለሱባት ልትሆን ይገባል፡፡የክርስቶሰ አካል የሆነችው ይህች ቤተክርስቲያን በበጉ ደም ታጥባ ያለነውር በአምላኩዋ ፊት ስላለች እርሾ ያላቸው ህይወቶች የቅድስና ህይወትዋን ሊያኮመጥጡ ከቶ አይገባም፡፡ሀዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ስለተከሰቱ ተመሳሳይ ህይወቶች ተናግሮአል፡-
”…. ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ።በጠቅላላው የዚህን ዓለም ሴሰኞችን፥ ወይም ገንዘብን የሚመኙትን ነጣቂዎችንም፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩትን አላልሁም፤ ይህስ ቢሆን ከዓለም ልትወጡ ይገባችሁ ነበር።አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ።በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ መፍረድ ምን አግዶኝ? በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን?በውጭ ባሉቱ ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት።”(1Cor 5:6 1ቆሮ.5:6-13)
ሃዋርያው ክፉ የሰራው ሰው ከማህበሩ እንዲወገድ የወሰነው በእርሱ በኩል ወደ ቤተክርስቲያን የገባው እርሾ የቀረውን ንጹህ ሊጥ/ህይወት ሊበክል ስለሚችል ነው፡፡
አማኞች ከምንም በላይ የአምላካችንን ምህረት በማሰብ ሁልጊዜ ወደእርሱ በንሰሃ መመለስን እንዳንዘነጋ፡፡ምክኒያቱም የቃሉ መንፈስ እኛን ከክርስቶስ ነጥሎ ማሳደድ ሳይሆን በየትኛውም መንገድ ወደ ቅድስናው መገኛ ስበን ያስገባነው የአሮጌው አዳም ስራ ፈጥኖ ሳያጠፋን እንዲነቀል ማስቻል ነው፡፡መራራ ስር በጣፋጭ ህይወቶች መሃል በቅሎ የዋሃንን እንዳያስጨንቅ ለእግራችን ቅን መንገድን እንድናደርግም ነው፡፡
ቤተክርስቲያን ጥፋተኞችን አያሳደደች ማቆያ የምትወረውር የህግ አካል ሳትሆን የተሰበሩ ልቦች የሚጠገኑባት የጌታ ማደሪያ ናት፡፡የበጎ ህሊና መሰባሰቢያ ማህበር እንደመሆንዋ ትሁታን በውሰጥዋ በታዛዥነት እንዲኖሩና የጌታ ፊት በእርስዋ እንዲገለጥም ነው፡፡በየትኘውም መልኩ በእርሾው የተበከሉ ህይወቶች በኢየሱስ ደም ዳግም ሊነጹና ወደ ቅድስናው ስፍራ ሊመለሱ የሚችሉበት የማምለጫ በር ከጌታቸው ዘንድ እንዳለ በማስታወስ በንሰሃ ወደዚያ በር ሊቀርቡ አስፈለጊ ነው እንጂ ተግሳጽን መኮብለያ ምክኒያት እንዳያደርጉት ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ያልጠፋነው ከርሱ ምህረት የተነሳ ነውና፡፡
ዕብ.12:4-7 ”ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር። ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል።ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?”