የታላቁ አምላክ ሀይል(3..)

የእውነት እውቀት

ወንጌል በሀይል የሚሰበክ የምስራች ቃል ነው፡፡ ወንጌል በውስጡ ሀይል አለበት፣ የእግዚአብሄር ፈቃድ በውስጡ ስላለና እግዚአብሄር የሚሰራበት የመስቀሉ ቃል መገለጫ በመሆኑ፡፡ ወንጌል የጌታን የደህንነት ስራ የሚገልጥ አዋጅ ነው፤ ስለሆነም እግዚአብሄር አለም ሳይፈጠር ቅዱስ ሊሆኑ በተጠሩ ህይወቶች ውስጥ ሊፈጥር ያቀደውን ጽድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ መከራ፣ ሞትና ትንሳኤ በኩል እንደፈጸመው ከፍ አድርጎ የሚያውጅ ቃል ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለሰዎች ሊሰጥ ያዘጋጀው የህይወት እንጀራ የሆነው ስጋና ደሙን የገለጠበት ትምህርትም ነው፡፡ ያም በመሆኑ መድሀኒት በሰው ልጆች መሀል መገኘቱን እግዚአብሄር ለስራ መገለጡንም በወንጌል በኩል ለሰው እየተረከ ይገኛል፡፡ ከሞት ሀይል የምናመልጥበትን የህይወት መንገድ ጠቁዋሚ ሆኖ በማገልገል ላይ ያለው ወንጌል የህይወት እንጀራን ለሰው ልጆች በማሳየትና እርሱም ከሰማይ የወረደ መሆኑን በማሳወቅ ሰዎች ያምኑት ዘንድ የእርሱን ማዳን ማብሰሪያ ሆኖአል፡፡ የምስራቹ አስቀድሞ ለደረሳት ጽዮን የመጣላትን የከበረ ነገር እንድታስተጋባ አስቀድሞ ተነግሮአት እንደነበር ከኢሳ.40:9-11 ቃል ላይ እንመለከታልን፡-
”የምስራች የምትነግሪ ጽዮን ሆይ፥ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጪ የምስራች የምትነግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ድምፅሽን በኃይል አንሺ፤ አንሺ፥ አትፍሪ፤ ለይሁዳም ከተሞች፡- እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለሽ ንገሪ። እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው። መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።” ይላል፡፡
አዋጁ እንደ ሀያል ወደ እስራኤል ሊመጣ ያለው እግዚአብሄር በጽዮን ቀዳሚነት እንዲታወጅ እርሱ ራሱ አዝዞአል፤ ጽዮንም በደስታ ሀይል ተሞልታና በመንፈስ ከፍ ወዳለው የእግዚአብሄር ተራራ ላይ ወጥታ የምስራቹን የምትነግር እንድትሆን ጌታ በመካከልዋ መገለጡን ቃሉ ያሳያል፡፡
በኢሳያስ መጽሀፍ የተነገረው ቃል በደረሰ ጊዜ በእስራኤል ምድር የሆነውን ሉቃ2:8-14 እንዲህ ያበስረዋል፡-
”በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፡- እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፡- ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።”
አዎ የምስራቹ የመጣው በታላቅ ክብር ታጅቦ ነበር፤ ይህ የደህንነት ምስራች ለሰው ልጆች ትልቅ ደስታና ምህረት ያለበት ስለነበረ በብዙ ክብር በሰማይ ሰራዊት ታጅቦ ወደ ሰዎች እንዲደርስ ተገብቶታል፡፡ በመላእክት አጀብ የተገለጠው የምስራቹ ለፍጥረት ሲነገር ዛሬም ከማይታይ ክብር ጋር በአንድነት እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡
የእግዚአብሄር ተግባራዊ የደህንነት ስራ በወንጌል ተመዝግቦ ይገኛል
1ጢሞ.4:1-2 ”መንፈስ ግን በግልጥ፡- በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ” ይላል፡፡
ከዚህ ቃል እንደምናየው ወንጌል የምስራችና ሰዎችን በደስታ የሚሞላ ብስራት ብቻ እንደሆነ ማየት ብቻ ሳይሆን ከአጋንንት ትምህርትና ይዞታ እንዲሁም ከአለማዊ ትምህርትና ፍልስፍና ጋር መዋጊያ መንፈሳዊ ሀይልም አድርገን ልንጠቀምበት እንዲገባ ያሳያል፡፡ ይህ እውቀት በአእምሮአችን ላይ የሚከናወነውን የአሳብ ጦርነት የሚያሸንፍና መንፈስ ላይ ያለን የትምህርት ይዞታ ነጻ የሚያወጣ ነው፡፡
ሐዋ.1:8 ”ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።”
የጌታ ትምህርት ሀይል የሚሰጥ ቃል ያለው ቢሆንም ከመንፈስ ቅዱስ ውጪ ሊገለጥና ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ደግሞ ነፍስ ከተያዘችበት አለማዊ ልማድ ነጻ ወጥታ ለእውነት እንድትገዛ እርሱዋን ማስለቀቅ የሚቻለው በዚህ መንገድ የእግዚአብሄር ሀይል በታጠቀው ወንጌል ብቻ ነው፡፡ ይህ እውነት የሚበራልን የአጋንንት ትምህርት እስከምን ድረስ የሰው ልጆችን እንደሚገፋ ስናውቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ለአዳም የተነገረው የእግዚአብሄር ቃል/ ትምህርት አዳምን በኤደን ገነት የሚያኖርና የሚያጸና ነበር፤ ሰይጣን ግን መጥቶ በተጣመመ ትምህርት ከዚያ እውነት እንዲያፈነግጡ አደረገ፡፡ በርሱና በሄዋን ላይ የወረደው ፍርድም ከዘላለም ህይወት ወደ ዘላለም ሞት የሚያሻግር እጅግ አስከፊ ውሳኔ ሆነ፡፡ ወንጌሉ ግን ይህን አጥፊ የሰይጣን ትምህርት በሀይል ይቃወማል፤ አማኞችንም ከእርሱ እንዲጠበቁ ያነቃል፣ ሽንገላውን በእውነት እውቀት ያጋልጣል፡፡ (2ቆሮ.11:1)፡፡
የእግዚአብሄር ቃል በቆላ.2:8 ሲናገር፡-
”እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።” ይላል፡፡
ቃሉ የሰውን አእምሮና መንፈስ ከሚያፈዝ የሰው ወግ፣ ቃሉን ከሚገዳደር አለማዊ ትምህርትና እምነትን ከሚያናጋ ፍልስፍና መራቅ ወደ እነርሱም ከማዘንበል ይልቅ መቆጠብ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡ እነዚህ ሁሉ እውቀቶች ልዩ መንፈስ ያላቸው እንጂ በመንፈስ ቅዱስ ከሚሰበከው እውነት ጋር አንድ አይደሉም፡፡
የስጋ ለባሾች ፈተና ከመንፈስ ጋር በሚደረግ ትግል ላይ ሲወድቅ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የውጊያችን ውጤት ውስን የሚሆነውም የእርሱን አካሄድ በአእምሮ ስለማናስተውለው ነው፤ የመናፍስት እውቀት ረቂቅና ጥልቅ እንደመሆኑ ሌላ የሚረዳን ሀይል ልንቀበል የግድ ይላል፤ ስለዚህ አሸናፊዎች እንዳሰብነው እንድንሆን የመንፈስ ቅዱስ ሀይል ብቸኛ ምርጫ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ከፈተና ባሻገር የሰው ልጆች እውነተኛውን አምላክ አውቀው እንዳይከተሉ አጋንንት በትምህርት ነፋስ በቀላሉ ያስታሉ፤ ይሁን እንጂ ለዚህ የስህተት ትምህርትም መፍትሄ ሆኖ የቆመው ወንጌል ብቻ ነው፡፡ እንደ ሀዋርያትና ነብያት ሁሉ ወንጌል በቃልና በመንፈስ ቅዱስ ሀይል ሲሰበክ አጋንንቶች አእምሮንም ነፍስንም ለቅቀው እስኪሰደዱ ይሸነፋሉ፡፡
ማቴ.4:23 ”ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር።”
ጌታ ኢየሱስ ወንጌል ሲያስተምር በሀይል የታጀበ ክንዱን ገልጦ በማሳየት ነበር፡፡ ወንጌል የነጻነት ትምህርት እንደመሆኑ ጌታ ኢየሱስ ለህዝቡ ነፍስ መዳን የሚሆነውን ወንጌል ከሰበከ በሁዋላ ለስጋ ፈውስ የሚሆነውንም ሕዝቡን ከደዌና ከሕማም የማላቀቅ ስራ ይሰራ ነበር፡:፡
ዛሬስ ወንጌል እንዴት ይሰበክ? በሃዋርያትና በነብያት መሰረት ላይ መመስረታችንን እርግጠኞች ከሆንን እንደ ጥንቱዋ ቤተክርስቲያን የደህንነት በረከትን በመንፈስ ቅዱስ ሀይል መቀበል ይገባናል፡፡ ለነርሱ የተነገረው ምስክር እንዲህ ስለሚል፡-
”እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን።
ይኸውም፥ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው።እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።” (ኤፌ1:11-14)
አለማዊ ፍልስፍና ግን እውነተኛ ትምህርትንና ያመኑ ወገኖችን ከመንገድ በማስቀረት የታወቀ አንቅፋት ነው፤ ለዚህ ጥፋት እውነተኛ መፈወሻ ቢፈለግ የምናገኘው ነገር ወንጌልን ብቻ ነው፡፡ ፍልስፍና አእምሮን ይዞ አማኝን ከመንገድ የሚያስት ሌላው እንቅፋት ሲሆን በወንጌል የተገለጠው የእግዚአብሄር ሀይል እርሱንም ያሸንፈዋል፡፡
2ቆሮ.10:3-6 ”በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል።”
የእግዚአብሄርን ሀይል መሞላት
ሚክ.3:8፤ ”እኔ ግን በደሉን ለያዕቆብ፥ ኃጢአቱንም ለእስራኤል እነግር ዘንድ በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይልንና ፍርድን ብርታትንም ተሞልቻለሁ።”
የእግዚአብሄር መንፈስ ሲመጣ በህዝቡ መሀል ታላላቅ ስራዎችን ይሰራል፡- መንፈሱ ይፈውሳል፣ ይታደጋል፣ ይቀጣል፣ ይሰብራልም፤ የዲያቢሎስን ስራ ያፈርሳል በደለኞች ላይ ተግሳጽን ያወርዳል፡፡ ስለዚህ ይህን ሀይል ከእግዚአብሄር ስንለምን ከምህረት ጋር፣ ከመፍራትና ከእምነት ጋር መሆን አለበት፡፡
የቀደመውን ዘመን ስንመለከት እግዚአብሄርን ትተው ቅን ፍርድ የጠሉ፣ እውነትን ጠልተውም ቅን የሆነውን ነገር ሁሉ ያጣመሙ የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች በእግዚአብሄር መንፈስ መውረድ ምክኒያት ፍርድ እንዳይወርድባቸው፣ አስቀድመው በንሰሀ እንዲመለሱም ነቢዩ በብርቱ አሰጠንቅቆአቸው ነበር፡፡ በነቢዩ ዘመን እባካችሁ ስሙ ተብለው ሳለ ጆሮአቸውን ወደ እግዚአብሄር ከማዘንበል የመለሱ ሁሉ ምን ያህል ፍርድ እንደተቀበሉ ምድራቸውም ሳትቀር በቅጣት እንደተመታች ቃሉ ይመሰክራል፡፡
በሌላ በኩል የእግዚአብሄርን ሀይል መሞላት የጠላትን ሀይል ለማሸነፍና ጠላትን ከስፍራው ለመንቀል መሳሪያችን ስለሆነ የአማኞች ትልቁ ልመና እርሱን መቀበል መሆን አለበት፡፡ ጌታ ኢየሱስ መንፈሱን ከሁሉ አብልጠን እንድንለምን አሳስቦናል፡፡
ሉቃ11:9-13 ”እኔም እላችኋለሁ፡- ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፍትላችሁማል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?”
በእርግጥ እግዚአብሄር የሚበልጥ በጎ ነገርን የሚጠብቅልን አምላክ መሆኑን ማወቅ ትልቅ ማስተዋል ነው፡- ትልቅ በረከት ስለሚያስብልን ጸጋውን ሊሰጠን ወደደ፤ ትልቅ ምህረት ሊያደርግልን በስጋ ተገለጠ፤ ትልቅ ማዳን ሊሰጠን በልጁ ደም ምክኒያት ይቅር አለን፤ በታላቅ ምሪት እንድንሄድና በጠላት ሀይል ላይ በበላይነት እንድንራመድም መንፈሱን አፈሰሰልን፡፡ በስጋችን ላይ መሰልጠን እንዴት እንቻል? በአለም ተጽእኖ ላይ እንዴት የበላይ እንሁን? በአጋንንት ሀይል ላይስ እንዴት እንበርታ? በሌላ በምንም ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ብቻ! ያንን የሚያውቅ አምላክም ከስጦታዎች ሁሉ በላጭ ስጦታ የሆነውን መንፈሱን ይሰጠን ዘንድ ወደደ፡፡ የምንመካበት የተስፋ ቃል ራሱ እንዲህ ይላል፡-
”እግዚአብሔር ይላል፡- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።” (ሐዋ.2:17-21)
ጎደሎን የሚሞላ አምላክ መንፈሱን በማፍሰስ ሰውን ሙሉ ያደርጋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሌለበት አማኝ ምን ያህል ከበረከቱ ሩቅ እንደሆነ መንፈሱ በሚሰራው ስራ ይታወቃልና ያንን የበረከት፣ የምህረትና የሀይል መንፈስ እስክንቀበል ፊቱን መፈለግ የግድ ይላል፡፡
እኛ የመጨረሻው ዘመን የደረሰብን ሰዎች ነን፤ እንዲያ ከሆነ ያለ መንፈስ ቅዱስ ዝም ብለን የምንቀመጥበት ዘመን ላይ እንዳልሆንን ማስተዋል አለብን፡፡ እግዚአብሄር በተለይ በዚህ በመጨረሻው ዘመን ታላቁን የሀይል መንፈስ ባመነው ላይ እንዲያው ሊያፈስ ለምን ወደደ? ይህን ብለን መመርመር ተገቢ ነው፡፡ ዘመኑ በተለይ ከትውልዶች መሀል እጅግ አስቸጋሪ ዘመን በመሆኑ፣ ሰይጣንም ወደ ፍርዱ መቃረቢያ እየተጉዋዘ እንደሆነ ስለሚያውቅ ክፋቱን እለት እለት እየጨመረ ስለሚሄድ፣ አማኝም ሀይል ከምንም ጊዜ በላይ ስለሚያስፈልገው፣ የሰው ልጅ በጥበብ የሚልቅበትና በክህደት የሚዘቅጥበት ዘመን እየበዛ ስለሚመጣ፣ ቤተክርስቲያን ደግሞ ይበልጥ ተንቀሳቅሳ ከሰው ልጆች ላይ አጉል እምነትን፣ ፍልስፍና ትምህርትንና የአጋንንት እውቀትን አላቅቃ ነፍሳትን እንድትሰበስብ ለማድረግ መንፈሱ በሀይል መውረድና መስራት አለበት፡፡
ሰው ብዙ ነገር ሊያስደስተው ይችላል፡፡ ከደስታ ሁሉ የላቀው ግን በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ የምንኖረው ህይወት ነው፡፡ እግዚአብሄር እየጎበኘን፣ በቅርብ እያናገረን ከመኖር ይልቅ ምን የበለጠ ደስታ ሊኖር ይችላል? እግዚአብሄርስ በእኛ ደስ እንዴት ይሰኛል? ያለጥርጥር በመንፈሱ ስንሆን ብቻ የሚደሰትበት ህይወት ውስጥ እንኖራለን፡-
ሮሜ.8:8-11 ”በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም። ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።”
በመንፈስ ቁጥጥር ስር ያልሆኑ ነፍሶች በቃሉ ሊገዙ አይችሉም፤ የእግዚአብሄር መንፈስ ያልተቆጣጠራቸው እነርሱ የስጋቸው ፈቃድ የተቆጣጠራቸው ስለሆኑ ከእግዚአብሄር ጋር መራመድ አይችሉምና፤ ፈቃዳቸው ወደራሳቸው ስለሚያዘነብልም የእግዚአብሄር የሆነውን ሊያስተናግዱ ከቶ አይቻላቸውም፡፡ እንዲያውም በእግዚአብሄር ፈቃድና አላማ አቅጣጫ ሳይሆን በተቃራኒው በመቆም ጠላት የመሆን አዝማሚያን ያሳያሉ፡፡ መልካሙና የተሸለው ግን የክርስቶስ መንፈስ በእኛ አድሮ ወደ እግዚአብሄር ፈቃድ ቢመራን ነው፤ የሚበልጠው የእርሱ ወገን መሆናችን ነው፡- ሰውነታችን በኃጢአት ምክንያት የሞተ ይሆን ዘንድ፣ መንፈሳችንም በጽድቅ ምክንያት ሕያው ይሆን ዘንድ፣ ለሚሞተው ሰውነታችንም ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ፡፡