የታላቁ አምላክ ሀይል(1..)

የእውነት እውቀት

የእግዚአብሄር ሀይል ወይም መለኮታዊ ሀይል ከእግዚአብሄር ባህሪያት መሀል አንደኛው ነው፡፡ እግዚአብሄር አምላክ ነው፣ ጌታ ነው፣ መድሀኒት ነው፣ ሁሉን የሚችል፣ ሁሉን የሚገዛ፣ በሁሉ የሚኖር፣ ሁሉን በራሱ፣ ለራሱና ከራሱ ያደረገ ድንቅ አምላክ ነው፡፡ ይህ አምላክ ሁሉን በሀይሉ ያደርጋል፡፡ ሀይሉ ጉልበቱን የማንቀሳቀሻ ብርታቱ ነው፡፡
ዘዳ.10:16፤17”እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ክእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ።” ይላል፡፡
እግዚአብሄር በሀይሉ ፍጥረታትን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶአል፣ የሌለውን እንዲኖር ያልታየውንም እንዲታይ አድርጎአል፡፡ የእግዚአብሄር ሀይል ከሀይላት ሁሉ በላይ የሆነ ነው፤ ሀይል ያላቸው ፍጥረታት ምንጫቸው የእግዚአብሄር ሀይል ነውና፡፡ እግዚአብሄር በመፍጠር ሀይሉ አሁንም ይሰራል፡፡ እንደቃሉ ሲታይ እንዲህ ይላል፡-
”አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፤ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፤ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ።
አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ…”(ነህ.9:6-7)
በአለም ላይ የተለያዩ ተገዳዳሪ ሀይላት አሉ፡፡ በተለይ አጋንንትና ሰይጣን ያን ያደርጉ ዘንድ በሞላ ሀይላቸው ይንቀሳቀሳሉ፤ እግዚአብሄር አቅዶ የሰራውን ሊያበላሹ ሁል ጊዜ ይሰራሉ፡፡ እግዚአብሄር ግን በማዳን ሀይሉ ህዝቡን ከተለያየ የጨለማ አሰራር ይታደጋል፤ ከጠላት ጥቃት፣ ከአመጽ፣ ከሀጢያትና ከሞት ሀይል ያድናል፡፡ ያድናል፣ ያዳናቸውም ከእርሱ ጋር እንዲጉዋዙ ሀይል ያስታጥቃል፤ ለሰው ልጅ ያለውን አሳብ፣ ያሰበውንም እቅድ ይፈጽም ዘንድ ቅዱሳንን በመንፈሱ ይሞላል፡፡
መዝ.68:33-35”በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኃይል ቃል የሆነ ቃሉን፥ እነሆ፥ ይሰጣል። ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ፤ ግርማው በእስራኤል ላይ፥ ኃይሉም በደመናት ላይ ነው። እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፤ የእስራኤል አምላክ እርሱ ኃይልን ብርታትንም ለሕዝቡ ይሰጣል፤ እግዚአብሔርም ይመስገን።”
እግዚአብሄር በቃሉ ውስጥ ባለው ሀይል በኩል እንደተናገረው ይፈጽማል፡፡ በዘፍጥረት መጽሀፍ ውስጥ እግዚአብሄር ሲናገርና የተናገረው ሲሆን ይታያል፡፡ ከአፉ የወጣው ቃል ሁሌም እግዚአብሄር ያሰበውን ያደርጋል፣ ይህ የእግዚአብሄርን ቃል ሀይል ያሳያል፡፡ እግዚአብሄር በብርታቱ ሀይል የፈጠረውን፣ ግን የማይጸናውን ግኡዝ አለም እንደሚያጠፋ ተናግሮአል፡፡
ማቴ.24:29-30 ”ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል”
ፍጥረታት ሲፈጠሩ በተለያየ መንገድ የሚገልጡትን ሀይል በውስጣቸው ተሞልተዋል፤ ተንቀሳቃሾች የሚንቀሳቀሱበትን ሀይል ከእግዚአብሄር ተቀብለዋል፤ የሚሮጡ እንዲሮጡ፣ የሚታገሉ እንዲታገሉ፣ የሚሰሩ እንዲሰሩ፣ የሚበሩ እንዲበሩ፣ የሚያስተውሉ እንዲያስተውሉ፣ የሚማሩ እንዲያውቁ፣ ወዘተ…ፍጥረቶች በተቸራቸው ሀይል ምክኒያት ነገሮችን እንዲያከናውኑ አስችሎአቸዋል፡፡
እግዚአብሄር ለፍጥረቱ በተለያየ መጠን የሰጠው ሀይል ሁሉም ፍጥረት በራሱ ልክና ባለው ሀይል እንዲቆም አስችሎታል፡፡ ስለዚህ አንዱ ፍጥረት ከሌላው በጉልበት የሚለየው በውስጡ በተቀመጠው የሀይል መጠን ምክኒያት ሆኖአል፡፡ የከዋክብት አንዱ ከሌላው በብርሀን ሀይል መለያየት አንድ ምሳሌ ነው፡፡
የእግዚአብሄር ሀይል ይፈጥራል እንጂ አይፈጠርም
ነገሮችን ከባዶ ነገር የሚያወጣ፣ ከሌሉበት ወደ መኖር መሰረታቸው የሚያሻግር፣ በእነርሱ ፈቃድ ሳይሆን በራሱ አሳብና እቅድ በኀይሉ ፈጥሮ ወደ አለም የሚያመጣ አምላክ ኀያል አምላክ የተባለው የአብረሃም፣ የይስሀቅም የያእቆብም አምላክ ነው፡፡
ኤር.51:15-17 ”ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ፥ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። ድምጹን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይታወካሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፤ ለዝናብም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል። ሰው ሁሉ እውቀት አጥቶ ሰንፎአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና።”
የእስራኤል ኃይል የተባለውን እውነተኛና የሁሉ ፈጣሪ አምላክ ካላወቅን አሳንሰን በማየት፣ ሀይሉን ውስን በማድረግና ክህደት ውስጥ በመዘፈቅ ከባድ ውድቀት በትውልድ ላይ እናመጣለን፡፡ እግዚአብሄር መፍጠር የሚችል አምላክ ከሆነ ከተፈጠሩ ጋር መደመር ስለምን ተገባው? ይህስ እርሱን ከመካድ በምን ይተናነሳል?
2ዜና.20:5-6 ”ኢዮሣፍጥም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በአዲሱ አደባባይ ፊት ቆመ፤
እንዲህም አለ፡- አቤቱ የአባቶቻችን አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን? የአሕዛብንስ መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኃይልና ችሎታ በእጅህ ነው፥ ሊቋቋምህም የሚችል የለም።”
ኃይልና ችሎታ በእጁ የሆነ እምላክ እጅግ የገዘፉ ፍጥረታትን የፈጠረ ጥቃቅን የሚባሉትንም ያስፈልጋሉ ብሉ ወደ አለም ያመጣ አምላክ እርሱ ራሱ ነው፡- ተራሮችን የሠራ እርሱ ነው፣ ነፋስንም የፈጠረ፥ የልቡንም አሳብ ሳይቀር ለሰው የሚነግር፣ ሰውን ወደ እርሱ ማቅረብ የሚፈቅድ ድንቅ አምላክ ነው፡፡ ንጋትን ጨለማ የሚያደርግ፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ የሚረግጥ ኤልሻዳይ አምላክ እርሱ በመሆኑ ክብሩ ዝቅ ብሎ ከፍጥረታት ጋር አንድ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም፡፡
የእግዚአብሄር ሀይል የሀይላት ሁሉ ምንጭ ነው
እግዚአብሄር የሀይል ምንጭ ከሆነ የሀይል ባለቤትን የሚሻሙ ስለምን በዙ? በሰማይና በምድር ያለው እያንዳንዱ ነገር የእርሱ እጅ ስራ ነው፣ ባለቤቱም እርሱ ነው፣ ምስጋና የሚገባውም እርሱ ነው፡- የሚያውቁት ታላቅነትና ኃይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው ሲሉ ያመልኩታል፤ እርሱ የማይታየው የሰማይ መንግሥት ባለቤት ነው፥ ታላላቅ ፍጥረታት፣ ሰማያትና ሌሎችም ታላላቆች የእርሱን ድምጽ ይሰማሉ፤ እርሱም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያለ ነው፡፡
2ዜና.20:6፤ ”እንዲህም አለ፡- አቤቱ የአባቶቻችን አምላክ ሆይ፥ በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን? የአሕዛብንስ መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኃይልና ችሎታ በእጅህ ነው፥ ሊቋቋምህም የሚችል የለም።”
የእግዚአብሔርን ሃያልነት የቀመሱ ሥራህ ግሩም ነው፣ ኃይልህ ብዙ ሆኖ ሳለም ጠላቶች ዋሽተውብሀል ይላሉ። የታመኑበት ትውልደ ትውልድ ግን ሥራውን ያመሰግናሉ፥ ኃይሉንም ያወራሉ።
1ዜና.29:12”ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው።”
የእግዚአብሄር ሀይል ሀይላትን ይለውጣል፣ ያሸንፋል፣ ያጠፋል
አማልክት ፍጡራን ናቸው፣ ሀይላቸውም የተፈጠረ ነው፤ እነርሱ ሲጠፉም ሀይላቸው ከእነርሱ ጋር ጠፊ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሀይል ግን ዘላለማዊ ነው፡፡ የተፈጠሩትም ሲያልፉ ጸንቶ የሚያሳልፍ እግዚአብሄር ብቻ በመሆኑ በፈቃዱ ሀይሉን አውጥቶ አዲስን ነገር የሚፈጥር አምላክ ነው፡፡
ዘጸ.15:11-15 ”አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው።አሕዛብ ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው።የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞአብን ኃያላን መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ።”
አማልክት የተባሉ መናፍስት በምድር ፊት ተበትነው ባሉ አህዛብ ላይ የሚሰለጥኑ፣ ህይወታቸውን ባርያ ለማድረግ ሁለንተናን የሚቆጣጠሩ፣ ከህያው አምላክ አርቀው እርኩስ መንፈስን የሚያስመልኩ፣ በነጻነት እንዳይኖሩ በባርነት የሚገዙና በምድር ፊት የሚንቀሳቀሱትን ሰዎች በሙሉ የሚያስተደድሩ ክፉ መናፍስት ናቸው፡፡ በጥንቆላ፣ በአስማት፣ በድግምትና በሙዋርት በኩል የሰው ልጆችን መንፈስ ገዝተውና በነፍሱ ላይ ሰልጥነው ባርያ ያደርጋሉ፡፡ እንዲሁም በየስፍራው ላይ የሚገኙና በሰው እጅ የተፈጠሩ የስእል፣ የድንጋይ፣ የእንጨትና የመሳሰሉ ጣኦታትን ሰዎች እንዲያምኑ አእምሮአቸውን ዞር ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉን የሚችለውን አምላክ የሚያመልክ ንጉስ ዳዊት እነዚህ ሁሉ አማልክት በአለም ላይ ቢከማቹ፣ በቁጥርም ብዙ ቢሆኑ ይህን እውነተኛና ቅዱስ አምላክ ሊያህሉ እንደማይበቁ፣ ሊስተካከሉ እንደማይችሉና ከእርሱ ጋር እንደማይቆጠሩ በቃሉ ያሳያል፡፡ እርሱ በቸርነት የተቤዣቸውን ሕዝብ በኃይል መርቶ ወደ ቅዱስ ማደሪያው አግብቶአቸው ነበር። ሀይሉ በአህዛብ ላይ ተገልጦ በአሸናፊነትም መርቶአቸዋል፤ አማልክታቸውን ሰባብሮ ባዶ አድርጎአል፡፡ ሀይሉ ከሀይላቸው በላይ ነውና ሊቁዋቁዋሙት አልቻሉም፡፡ ድምጹን የሰሙ ስለእርሱ ዝና ሰምተው ተንቀጠቀጡ፣ አስፈሪነቱ የምጥ ያህል አስጨናቂ ሆነባቸው፣ ኃያላን በፊቱ መቆም አቅቶአቸው መንቀጥቀጥ ያዛቸው፣ እርሱ ታላቅና ሃያል አምላክ ነውና፡፡
መሳ.5:5-9 ”ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ቀለጡ፥ ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ። በዓናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፥ በኢያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፤ መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር። አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥ ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥ ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም። አዲሶች አማልክትን መረጡ፤ በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፤ በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም። ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥ በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፤ እግዚአብሔርን አመስግኑ።”
ህያዋን በእምነት ሲደክሙና ለታላቅነቱ ክብር ሲነፍጉ ህይወት የሌላቸው ግኡዛን ግን ለእርሱ ድምጽ መልስ ይሰጣሉ፣ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ይፈራሉ፡፡ እስራኤላውን ከእግዚአብሄር ከአምላካቸው በሸሹበት ዘመን ድጋፋቸው የሆነው አምላክ ትቶአቸው ነበርና ጠላትን ተዋግተው ድል ይነሱ የነበሩ ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፣ አለቁም። በንሰሀ መመለስ ትተው ፊታቸውን አዞሩ፣ አዲሶች አማልክትን መረጡ፡፡ ከግብጽ ምድር በጸናች አጅ ያወጣቸውን አምላክ ስለተዉ እርሱም ተዋቸው፣ ይህም ከፍተኛ ኪሳራ እንዳደረሰባቸው ይታያል፡፡
እስራኤላውያን አምላካቸው አንድ ብቻ ሲሆን ከእርሱ በቀር ደግሞ ሌላ እንደሌለ እርሱ ራሱ በቃሉ አስተምሮአቸዋል፡፡ እነርሱ ግን አንድ መሆኑ የበቃቸው አይመስልም፣ ብቸኝነቱ አላረካቸውም፤ ስለዚህ ሌሎች አማልክትን ፈለጉ ተመኙም፣ እርሱን ትተው እነርሱን በመምረጥ ከፊቱ ሸሹ፡፡ እግዚአብሄርን በስራቸው ስላበሳጩት እርሱም ለጠላቶቻቸው ባርነት አሳልፎ ሰጣቸው፣ መሪዎቻቸው እስኪዋረዱ ሀይል እስከማይቀርላቸው አንገታቸውን በጠላቶቻቸው ፊት እንዲደፉ አደረገ፡፡
የእስራኤል አምላክ የአህዛብም አምላክ እንደመሆኑ ዛሬም ከእርሱ በቀር አማልክትን መፈለግ፣ እርሱንም ለመመንዘር (ለማባዛት) መሞከር ውድቀት እንደሆነ እንድናስተውል ያስፈልጋል፡፡ የእስራኤል አምላክ የዘላለም አምላክ መነሻና መጨረሻ የሌለው ስለሆነ ከአዲሶችና በቅርብ ከተነሱ አማልክት ጋር እርሱን መቀላቀልና ማመሳሰል ጥፋት ይሆናል፡፡ በአንዱ አምላክ የተጠሩት ህዝብ ግን እርሱን ማምለክ ጥቂት ነገር ሆኖባቸውና ከመከተል ደከሙ፡፡
ኢያ.24:19-21” ኢያሱም ሕዝቡን፡- እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም። እግዚአብሔርን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችሁማል አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፡- እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን አሉት።”
አንድ አምላክን ከማምለክ የሚያግድ ትምህርት የመጀመሪያ ተጽእኖው የድካም መንፈስ ውስጥ መክተት ነው፡፡ ብቸኛውንና ህያው አምላክ ቸል ያሉ የእርሱ ህዝብ በጥፋታቸው ፈዘዙ፣ በጠላትም እጅ ወደቁ፡፡ በዙፋኑ ላይ ብቻውን ከተቀመጠው አምላክ ውጪ ሌላ አምላክ በሰማይ የት አለ? የሌለ አምላክ ማሰላሰል ለመናፍስት ተጽእኖ ያጋልጣል፤ እነዚህ መናፍስት መንፈስን በሚያረክስ አምልኮ ውስጥ በማስገባት ወደ አዲስ አማልክት ይመራሉ፡፡ የሀሰት አምላክ ራእይ በመፍጠርና ቃሉ የማያውቀውን እውቀት በአእምሮ ውስጥ በማስገባት ያረክሳል፡፡ የሀሰት ትንቢቶች እውነተኛውን አምላክ ያስክዳሉ፡፡ ሰዎች እግዚአብሄርን ካልሰሙ የራሳቸውን አሳብ ወደ መስማት ያዘነብላሉ፣ ውስጣቸው የሚመጣውን የመናፍስት ድምጽ እውነት እንደሆነ በመቁጠር በእርሱ ይታለላሉ፡፡ መለኮታዊ ሀይሉ በውስጣቸው እንዳይሰራ በረከሰ እምነትና እውቀት ራሳቸውን ለአጋንንት ያጋልጣሉ፡፡
1ሳሙ.2:1-5” ሐናም ስትጸልይ እንዲህ አለች፡- ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፥ ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ፤ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፤ በማዳንህ ደስ ብሎኛል። እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥ እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና፤ ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም። አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል። ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፤ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል፤ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች።”
የሐና ህይወት በእግዚአብሄር እምነት የታገዘ ነበር፤ ስለሆነም በደስታዋም ሆነ በሀዘንዋ ጊዜ ከእርሱ እጅ የማትወጣ፣ ከፈቃዱ ፈቀቅ የማትልና እርሱን በነገር ሁሉ የምትጠባበቅ እንደነበረች የሚታይ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለልጆቹ የሚያስታጥቀው ሀይል በሀዘን ወቅት የሚያጸና ነው፣ ጠላት አሸነፍኩ ጣልኩ አደከምኩ በሚልበት ሰአት ሀይልን እያደሰ የሚያበረታ እንዲሁም በለቅሶ መሀል የደስታ ዘይትን የሚቀባ ነው፡፡ የበረቱትን ኃያላን አዳክሞ ላዘነው የሰው ልጅ ኃይልን መሙላቱ የእግዚአብሄርን አዋቂነት ይገልጣል፡፡ ሐና ካደከማት ሀዘን ከወጣች በሁዋላ ባቀረበችው ምስጋና ”የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል። ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፤ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል፤ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች።” ስትል ሀያሉን አምላክ ታወድሳለች፡፡
ዘጸ.15:1-3 ”በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው”