ማቴ.13-14 “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።”
የእግዚአብሄር ቃል ከሚገልጠው መንፈሳዊ መንገድ መሃል ቀድሞ የምናገኘው ትልቅ መንገድ ተብሎ የተጠራውን ነው። የመንገዱ መጠን በትልቅነቱና በሚያስተናግደው መንገደኛ ብዛት ተገልጦአል። ይህ መንገድ ትልቅ ይሁን እንጂ ለሰው ልጆች ጥንቃቄ የሚሆን ማንቂያም ሆነ መጠበቂያ ዋስትና የሌለው ነው።እርሱ ሁሉ የመንፈስ አይነት የሚስተናገድበት የህይወት ምርጫ እለበት።ገደብ በሌለው ፍላጎት ለሚጉዋዝ ሰው እንዳሻው እንዲንቀሳቀስ እድል ይሰጣል።በትልቁ መንገድ ውስጥ ብዙዎች በስጋ መንፈስ ተይዘው ይንቀሳቀሳሉ።የዲያቢሎስ ሽንገላ፣አገዛዝና ምሪት በዚያ ትልቅ ተጽእኖ ያደርጋል።እግዚአብሄር በዚያ መንገድ ላይ ስለሌለ ጥፋት ተሞልቶአል።ዋናው ተዋናይ ሸንጋዩ ሰይጣን በመሆኑም ጽድቅ በሚመስሉ ስራዎች የታጀቡ እምነቶችን ይዞአል።መንፈሱ ሰዎችን በዚያ ያተጋል። የሃሰት ትምህርት፣ትንቢት፣ታምራት በዚያ አሉ፣ሰይጣን በመንገዱ ላይ ስላለ።ይህ ትልቁ መንገድ ከሰፊ አማራጭ ጋር በአለም የተንሰራፋ ነው።መንገዱ አጥፊና አታላይ መንፈስ ስለተቆጣጠረው አለምን የገዛም ነው።ሰው ከእግዚአብሄር እርዳታ ውጪ ሲሆን እዚህ መንገድ ውስጥ ስለሚገባ ለሃሰተኛ ሰራተኞችና ለመንፈሳቸው ተጋላጭ የሚሆንበት አልፎም ወደ ጥፋት የሚወርድበት ነው።
ደግሞ ቀጭን መንገድ አለ።ይህ መንገድ አስተማማኝ ህይወትና አምላክ አለበት።መንፈስ የሆነ ጌታ በዚያ መንገድ ላይ ሆኖ እኔ እውነት መንገድም ነኝ ይላል። በእርግጥ መንገዱ ከጠባብ አማራጭ ጋር ያለ ስለሆነ በስጋ ህይወት ለሚመሩ ጭንቅና መራራ ነው።ምኞት ከወዲያ ወዲህ የሚመራቸው፣ በራሳቸው ፈቃድም የሚሰማሩ ሰዎች የጌታን እረኝነት ስለማይቀበሉ በቀጭኑ መንገድ መጽናት ያዳግታቸዋል።ቢሆንም መንገዱ በጌታ ኢየሱስ ለሚታመኑ ሁሉ የሚመች ነው።
የጠበበው መንገድ ለመንፈሳዊው ሰው ሰፊና የበረከት መንገድ ነው።ለስጋዊው ግን የማይመችና የሚጎረብጥ ነው።መንገዱ የእግዚአብሄር ጸጋ የሚገለጥበትና መልካም የህይወት ልምምድ የሚገኝበት በመሆኑ ሲኖርበት አዳጋችነቱ አይታይም፣ሲለማመዱትም አያስጨንቅም። በተለምዶ የያዝናቸው አሮጌ አመለካከቶች ከተገለጡበት ግን ውጤት ሊመጣበት የማይቻል ነው።በአለም ላይ የተለመዱ የህይወት ዘይቤዎች አሉ፣ እነርሱ ቀጭኑ መንገድ ላይ ቢገለጡ ሊጸኑ አይችሉም።
ቀጭኑ መንገድ ጌታ ኢየሱስ የሚገኝበት መንፈሳዊ ክልል ነው።በመንገዱ ሁለት ዳርቻዎች ጽድቅና ቅድስና እንደ አጥር ናቸው።ስለዚህ ማንም አማኝ እነርሱን ማእከል ያላደረገ ህይወት ከሌለው ሊጉዋዝበት አይችልም። መንገዱ ስጋውያንን የሚያስጨንቅ ቢሆንም መንፈሳውያን በስፋት እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል የህይወት ስርአት አለው። መንገዱ ከውጪ ሆኖ ለሚያየው(ከመንፈሱ ክልል ውጪ ላለ ሰው) ይጠብባል፣ የቀጥናልም። ለቀረበው፣ለገባበትና ለፈቀደው ግን ይሰፋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች በመንፈስ ስንጉዋዝ እየሰፋልን (በመንፈስ እየተፍለቀለቅን እንደምንመላለስ) ደክሞን ስንቆም ደግሞ እያጣበበን (በምክርና በተግሳጽ እየያዘን) እንደሚሄድ መገንዘብ አለብን።
በዚህ ዘመን በቀጠነው መንገድ ላይ ለመመላለስ አቅም (የመንፈስ ሀይል) ያስፈልጋል።እንዲሁም የመንገዱን ባህሪይ ማወቅና እርሱን መለማመድ ይጠይቃል።
ጌታ ኢየሱስ በመንገዱ ላይ ካገኘን ጸጋውን ያበዛልናል።ያኔ ህይወቱ የሚያጣብብ ወይም የሚያጨናንቅ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ደስታና በረከት ያለበት ይሆናል።
መዝ.25:8-10 “እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።ገሮችን በፍርድ ይመራል፥ ለገሮችም መንገድን ያስተምራቸዋል።የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው። ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ።”
ጌታ ኢየሱስ የዘላለም ህይወትን በመንገዱ ላይ አኑሮአል።ያን ህይወትም እንድንኖረው የሚመራን እርሱ ራሱ ነው። በመንፈስ ከተመላለስንና በቃሉ መሰረት ከተጉዋዝን ቸርነቱ አይለየንም። መንገዱ በስጋ እቅድ ወይም ፍቃድ ስኬታማ አይሆንም፣ እግዚአብሄርን ለሚጠይቁ፣ፊቱን ለሚሹና በትህትና በፊቱ በሚመላለሱት ዘንድ ግን መንገዱ ክፍት ነው።
መንፈሳዊ ህይወት በስጋ አሳብ ሲጣበብ ያለመመቸትን ይፈጥራል።ያለመረጋጋትና ያለማስተዋል በዚያ ስለሚከተል መንገደኛው ጉዞውን እንዲያቆም ያልያም እንዲያፈነግጥ ያደርገዋል።የእኛ ህይወት ያለ ጌታ ኢየሱስ ምሪት በዚያ መልኩ ልቅ ሲሆን አቅጣጫ የሌለውና መንገጫገጭ የሚያጎሰቁለው ይሆናል።በእንዲህ ያለ አካሄድ ነፍሳችን ሰላሙዋን አጥታ መንፈሳዊ ህይወትን መሸሽ ጀመረች ማለት የጠበበው መንገድ ወደ ዳር ይገፋት ጀምሮአል ማለት ነው።ህይወታችን በመንገዱ ላይ ሆኖ ሳለም ያለ ጌታ ኢየሱስ ጸጋ በስጋ ብቻ ቢታገል ምናችንም ለስኬት አይበቃም።ምክኒያቱም በደከመ መንፈሳዊነት ውስጥ መንፈሳዊ በረከት ስለማይመጣና ድርቀት እየሰፋ ስለሚሄድ ነው።
የቀጠነውን መንገድ አዳጋች የሚያደርግ ምንድነው?
የመጀመሪያው ራስን ያለመስጠት ነው። ራስን መስጠት ለእግዚአብሄር አሰራር ራስን ማዘጋጀት ስለሆነ በተዘጋጀንበት አጋጣሚ ምክኒያት በእግዚአብሄር የታሰበልን ነገር በመንገዳችን ላይ ያገኘናል።ይህ ሳይሆን ሲቀር የመንፈስ ሃይል ያጥረናል፣ ጉዞውም ይበልጥ የተመሰቃቀለ ህይወት ውስጥ ይከተናል።መንፈሳዊ መሻት ደክሞ ከስፍራው ሲወርድ የቀድሞ ልማድ እየተመለሰ ስለሚገዳደር በዚያ ምክኒያት ህይወት ይቀጭጫል።ብዙ ብዙ ያልጠሩ ነገሮች አእምሮአችንን ማስጨነቅ ይይዛሉ።
ከቃሉ ድምጽ ይልቅ አእምሮን የሚሰርቁ፣ የምናያቸው፣ የምንሰማቸው፣ የምንከተላቸው ወይም የምንፈልጋቸው በአለም ያሉ ጉዳዮች እስከምን ድረስ ልባችንን ወርሰዋል? መጠኑ ህይወታችን ምን ያህል በተጸእኖ ስር መዋሉን ይጠቁመናል።
የምንሰማቸው ይጫኑናል? የምናያቸው ያጉዋጉናል? ልባችንን ያጋድሉብናል? አለም ላይ ያሉት እነዚያ ነገሮች በሙሉ መንፈሳዊነትን የሚያናውጡና የሚውጡ በመሆናቸው ሁልጊዜ ጥያቄ ልናነሳባቸው ይገባል። አንድ ሰው በኪሱ ያኖረውን ውድ እቃ ይጠነቀቅ ዘንድ ቶሎ ቶሎ ኪሱን እንዲዳብስ አንድ መንፈሳዊ ሰው በህይወቱ የተቀመጠውን ውድ የእግዚአብሄር ጸጋ (የህይወት መዝገብ) ይጠነቀቅለት ዘንድ ራሱን ሁሌ ሊፈትሽና ሊጠብቅ ይገባል።በተሰመረለት የጽድቅና የቅድስና መስመር ውስጥ ተጠንቅቆ መመላለስም አለበት።
ህይወታችን እንደ እግዚአብሄር ቃል መራመድ ከተሳነው መንገዱ (የክርስትና ህይወት) እየጠበበን ነው ማለት ነው።ከድካማችን በርትተን ህይወቱ የሚጠይቀውን መንፈሳዊነት ማግኘት ከቻልን ግን ቀጭን መንገድ ተብሎ በተጠራው ህይወት ውስጥ በስፋት መንቀሳቀስ እንችላለን።ሳውል ይባል የነበረው ጳውሎስ በመንገዱ ላይ የነበሩትን ክርስቲያኖች አሳደደ።ዛሬም እንዲሁ ሰይጣን በዚህ መንገድ (በተወሰነልን የጽድቅ ህይወት ውስጥ) እንዳንመላለስ በዚህም በዚያም በኩል በማዋከብ ያሳድደናል። እኛ ግን በጌታ ኢየሱስ ጸጋ በርትተን በቃሉ ላይ በመጣበቅ ማሸነፍ እንችላለን።
ክርስቲያኖች ያለ ጌታ ኢየሱስ ምን ማድረግ እንችላለን?
ቃሉ በምሳ.3:5-7 ሲመክረን “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ፤”
በመንገዱ ላይ መጉዋዝ ብቻ ሳይሆን መኖርም የሚሳነው ጉዞአችን ከኢየሱስ ጋር ካልሆነ ነው።ከኢየሱስ ጋር አብሮ ለመሄድ እንደ እርሱ አሳብ መኖር ይጠይቃል፣ ይህም እንደቃሉ መኖር ማለት ነው። የቀጠነው መንገድ በኢየሱስ ለታመነ ሰው የፍርሃት ምንጭ ሳይሆን የደህንነት ካርታው ነው። ጌታ በመንገዱ ላይ የሚያገኛቸው ሰዎች ቃሉ በሚያመለክታቸው አቅጣጫ ስለሚጉዋዙ የሚያሰጋ ነገር አያገኛቸውም።
ዕብ.12:12-13 “ስለዚህ የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጉልበቶች አቅኑ፤ ያነከሰውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ፥ ለእግራችሁ ቅን መንገድ አድርጉ።”
ቃሉ ለእግራችን ቅን መንገድን እንድናደርግ ካዘዘ ያን እንዴት ማሳካት እንደምንችል መፈተሽ ተገቢ ነው።ስለዚህ አንድም ለህይወት መስመራችን የሚመች መልካም ውሳኔ በራሳችን ላይ ስናደርግ በሌላ በኩል በእምነት፣ በቅድስናና በአምልኮ ከእግዚአብሄር ጋር ስንጣበቅና ስንጸና ለእግራችን ቅን መንገድን አደረግን ማለት ነው።አማኞች በዘመናቸው ከሚጋረጠው አለማዊ መንፈስ ጋር ታግለው ለማሸነፍ በመንገዱ ላይ እንዲህ መወሰን ይጠበቅባቸዋል።
የክፋት መንፈስ በአለማውያን ላይ የሚሰራው ሰዎችን በተወሳሰቡ የሃጢያት ልምምዶች በማሰርና እንዳይነቃነቁ አድርጎ መንፈሳቸውን በድን በማድረግ ነው።ሰዎች በዚያ የክፋት መንፈስ ክልል ውስጥ እንዳይገኙና ለመንገዳቸው አቅም እንዲያገኙ አሁንም የመንፈሱ ሀይል በሚገለጥባት ህያው ቤተክርስቲያን ጸጋ መታጀብና መጋረድ ያስፈልጋቸዋል።ለዚያ በነርሱ በኩል ልባቸውን ሊሰጡና ሊፈቅዱ የግድ አስፈላጊ ነው።ያለበለዚያ በህይወት መንገድ ላይ በድል እንዳይራመዱ መንገዱን እጅግ አዳጋች ሊያደርግ ያደባ ያ ጠላት ቅርብ ነው።
በቀጠነው መንገድ ሳንታክት፣ ሳንዝልና ወደ ሁዋላ ሳንል ለመጉዋዝ ምን እናድርግ?
ወገኖች አንዳንድ የመንገዱን ባህሪያት ደጋግመን ልብ ልንል ያስፈልጋል፦
- በቀጠነው መንገድ ላይ ለመሄድ አለም መስፈርቱን ፈጽሞ አታሙዋላም።
- አለማውያን ሊጉዋዙበትም ያዳግታቸዋል።
- መንገዱ መንፈሳዊ አቅም ይጠይቃል።
- በመንገዱ ላይ ለመኖር የጌታ ጸጋ አቅም ይሰጣል።
- የጌታ ፍቅር በመንገዱ ላይ እንድናተኩር ያደርጋል።
- በቀጠነው መንገድ አለማዊ ልማድን ማካሄድ አይቻልም።
- በቀጠነው መንገድ ውስጥ ሊካዱ የሚገባቸው ስጋዊ ልማዶች ናቸው።
- የቀጠነው መንገድ የጌታ ኢየሱስን ፍቅርና ጸጋ ይፈልጋል።
- በቀጠነው መንገድ የመሄድ ጉዳይ የህይወት ጉዳይ በመሆኑ መንገዱን የመረጡ በህይወት ወስነው የሚጉዋዙት ነው።
ራእ. 15:3 3-4 “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፥ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ፥ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፥ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ።”