ግራ በመጋባት ሰበብ ለዘመናት በላያችን የተሰራው በጎ መንፈሳዊ ስራ ይናዳል
ግራ በመጋባት ውስጣዊ ስሜታችን ሲናወጥ መቆም ሊያቅተን በሚያደርስ መናወጥ ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ግራ መጋባት፣ በተምታታ ሃሳብና ስሜት መያዝ፣ ያለመረጋጋትንም ጭምር ስለሚፈጥር በአንድ መንፈስ መጸለይ እንኩዋን አያስችለንም።
በመንፈሳዊ ህይወት መዛባት ምክኒያት ግራ መጋባት ተፈጥሮ የነፍስ ደጋፊ አሳብ ከተምታታ መንፈሳዊ ሆኖ መቆም አይቻልም። በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው ያለውን የጌታ ትእዛዝ እንዳንጠብቅ ግራ መጋባት ወደ ጠርዝ ይገፋናል። የጌታ ሰላም ግን በዚህ ችግር ላይ ትልቅ መፍትሄ ይሰጣል።
ነገሮችን እንዳመጣጣቸው መመለስ ብቻ ሳይሆን በበጎ ጎናቸው በኩል አብዝተን እንድናያቸው፣ የሚያንጹንን ነገሮች እንድንቀበላቸው፣ ተላምደን እንድንመስላቸው ወይም በተቃርኖ ሳንገጥማቸው ላይደናቀፉም እንድንጠብቃቸው የሚያስችል አንድ የተረጋጋ የነፍስ ስሜትና የመንፈስ በጎነት በውስጣችን ሞልቶ ሲያጸናን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤ መንፈሳችን በእግዚአብሄር ሰላም እርግት ሲል ስሜታችን የጸናና የሰከነ እርጋታችንም ጎልቶ የሚታይ ነው።
ፊል4-9 ‘’ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።’’
ከላይ ባየነው ክፍል ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ የሚለው ቃል ለንግግር ያህል የተባለ ሳይሆን በሚረዳ ጌታ ሲያዙ መሆን የሚቻለውን የውስጣዊ ስሜት ይዞታ ሲያመለክት ነው። የጌታ ደስታ በተነኩ ቁጠር እያለቀሱ በትንሽ ነገር በስሜት መዋጥና መፍነክነክ የሚታይበት የስስ ስሜት ነጸብራቅ ወይም ገጽታ አይደለም። በእግዚአብሄር ጸጋ ስር በመስደድ የሚመጣ እረፍት ውጤት ነው። ነገሮች በህይወታችን እንደማንኛውም ሰው ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። ዋናው ነገር የመጡት ነገሮች አመጣጣቸውን በእግዚአብሄር ፈቃድ በኩል ብናያቸው፣ የሄዱትም በምን መንገድ ሄዱ ብለን በጌታ አሳብ በኩል ብንመዝናቸው ሁሉም ከእርሱ እውቀት ውጪ እንደማይሆኑ እናስተውልና እንረጋጋለን፣ በእርሱ ቃል እንሸነፋለን፣ መንገዱንም እንከተላለን፤ በዚያም እንደማይጥለን በሙሉ ልብ እንተማመናለን። ስለዚህ በሆነው ነገር አሸናፊ አሳብ እንይዛለን፣ ይህን ታላቅ ጌታ የማመስገን መንፈስ ስለሚይዘንም በመንፈስ ደስታ እንሞላለን ማለት ነው።
ጌታ ቅርብ ሲሆን አብሮነቱ ይሰማናል፤ ሁልጊዜም በጌታ ደስተኞች እንሆናለን፤ አብሮነቱ ስለሚሰማን፣ ደህንነታችን የተረግገጠ ስለሆነ፣ እንደሚያየንና እንደሚሰማን ስለምናምን ደስታ ውስጣችን ይፍለቀለቃል፣ ሃይሉ በእኛ ላይ ከሚሆነው በላይ አይሎ የሚሆንብንን ነገር ሁሉ ያሸንፋል፤ በመንፈስ ዘይት ነፍሳችን ስትረሰርስ የአምላክ ጉብኝትም በህይወታችን ሲገለጥ የድል መንፈስ ሁለንተናችንን ስለሚቆጣጠር የሰላም ሁኔታ ይገዛናል።
የደስታ ማማ መውጫ መሰላልም ጸሎት፣ ምልጃና ምስጋና ነው። በነርሱ በኩል ወደ እግዚአብሄር መቅረብ ስለምንችል የእግዚአብሄር ደስታ ያገኘናል። እነዚህ ሶስት መንፈሳዊ ስራዎች በእምነት ሲደረጉ በእኛ ውጤታማ ናቸው፤ አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም እግዚአብሄር ሲሰጠን በአስተሳሰባችን ላይ የሚያይል ሃይል ይቆጣጠረናል፣ ይህ ነው ልባችንና አሳባችንን አስክኖና መንፈሳዊ አድርጎ የሚጠብቀን።
‘’በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።’’(ዮሃ.16:34)
የእግዚአብሄር ሰላም የገዛው ልብና አሳብ ፍሬያማ ነው፦ እውነተኛ የሆነው ነገር ሁሉ የሚታይበት ነው፣ ጭምትነት ያለበት ነገር የተቆጣጠረው ነው፣ ጽድቅ የሆነው ነገር የገዛው ነው፣ ንጹሕ የሆነው ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበት ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበት ነገር ሁሉ ገንዘቡ ይሆናል፤ ሰዎች ያለ እግዚአብሄር እገዛ ሰላም የገዛው ህይወት ተቆጣጥሮአቸው በጎነትና ምስጋና ያለው ህይወት ሊመሩ አይችሉም።
‘’በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ደኅና ሁኑ። ፍጹማን ሁኑ፥ ምክሬን ስሙ፥ በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።’’ (2Cor 13:11)
ቃሉም እንዳረጋገጠው አእምሮን የሚያልፍ ሰላም የምንቀበለው ያን የሚሰጥ ጌታ ከእኛ ጋር ሲሆን ብቻ ነው። አእምሮን የሚያልፍ ሰላም ሰዋዊ አሳብ አመቻችቶ፣ አደራድሮ፣ አስተካክሎ ወይም አረጋግቶ ሊያመጣው ከሚችለው ሰላም እጅግ የላቀ የሰላም አይነት ነው። ይህ ሰላም አስቀድሞ ግለሰብን ያረጋጋል፣ በማህበር ደረጃ በእግዚአብሄር መንፈስ ሃይል የእግዚአብሄር ህዝብ በዚህ የሰላም መንፈስ እንዲያዝ ያደርጋል።
‘’ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።’’(ዮሃ.14:28)
ኢየሱስ ክርስቶስ በዋናነት የመጣበት አላማ ለሃጢያተኞች ምህረት ሰጥቶ ለማዳን ነው፣ በደሙ ሃጥያታችንን አጥቦና አንጽቶ ያለነቀፋ ለማኖር ነው፤ ቀጥሎ በምድር ላይ በሃጢያት ምክኒያት የተከታተለውን ችግር፣ መከራ፣ ሁከት፣ በሽታና ማንኛውም የዲያቢሎስ ጥቃት ለመገሰጽ ነው፤ የታመሙትን ሊፈውስ፣ የጠፉትን ሊያድን፣ ለድሆች መልካም ዜናን ሊናገር፣ ልባቸው የተሰበረውን ሊጠግን፣ ለታሰሩትም ነፃነትን ሊያውጅ፣ እስረኞችን ከጨለማ ሊፈታ ነው። የተዳከመን መንፈስ የርሱ ዘይት ሲፈስበት ነጻ ሊወጣ ይችላል። የዘይቱ ጉልበት በመንፈስ ላይ የተደረበውን ጫና አስወግዶ ዳግም ስለሚያቆም ከርሱ የምንቀበለው የመንፈሱ ጉልበት ብቻ መመኪያ ይሆናል። ደስታ እንደዚያ ነው፣ ሰላም፣ እረፍት፣ መረጋጋት፣ ማስተዋል፣ አለመናወጥ የመሳሰሉት በተለይ አማኝን ከሚያጎሰቁሉ ስሜቶች አውጥቶ በነዚህ የህይወት እርጋታዎች ላይ ለማረፍ የሚያስችል ሌላ መንገድ ሳይሆን የርሱ የመንፈስ ጉልበት የሚሰራው ነው። በዚህ ምክኒያት መሰረታዊ የሆነውን፣ ሰውን ሊያቆመውና ሊረዳው የሚችለውን ነገር እንዲያስብ ሃዋርያው ለወጣቱ አገልጋይ ያመለክተዋል፦
“ስለዚህ ምክንያት፥ እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው፥ እጆቼን በመጫኔ በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታነሣሣ አሳስብሃለሁ። እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና።’’ (2ጢሞ.1:6-7)
ይህን በማለት አንድ እንደ እሳት ያለ መንፈሳዊ ሃይል በውስጣችን ሊነሳሳ፣ ሊቀጣጠልና መበላት ያለበትን የሚያጎድፍ ልማድ ሊያስወግድ እንደሚገባ ቃሉ ያሳየናል።
ቲቶ2:12-13 “ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል”
ስሜት አልባነት፦ መልስ የማይሰጥ፣ የሚንቀረፈፍ ስብእና ውስጥ መግባት
ግራ በተጋባ ህይወት የሚናወጠው የውስጥ ሰውነት ግራ መጋባቱ ካላበቃ መስመሩን ስቶ ጨለማና ሸጥ ውስጥ ይገባል፤ ተስፋውን ይጥልናም እየደበዘዘ በሚሄድ መንፈሳዊ ህይወት አመድ ይለብሳል።
በምድረ በዳና በደረቅ ምድር የተመሰለ ይህ ደካማ ህይወታችን በጌታ መንፈስ ሲጎበኝ ብቻ ደስ ይሰኛል፤ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል፣ መንፈሱ ሲያስውብም እንደ ጽጌ ረዳ ያብባል። ይህ የእግዚአብሄር ተስፋ ነው።
በእምነት መዘርጋት የማይችሉ የደከሙት እጆች እስኪበረቱ፣ ከጸሎት የላሉ ጕልበቶች እስኪጸኑ ድረስ በርትተን ቀና ማለት ከቶ አይቻለንም፤ ከእምነት ወደ ሁዋላ ያለ ፈሪ ልብ በእግዚአብሄር መንፈስ እስኪነካ ጉዞው አዳጋች ይሆናል፣ ድንዛዜው ሌላም እክል አለው፣ መንፈሳዊ አይኖችን ማሳወር ጆሮንም ማደንቆር። ጊዜ ግን ይመጣል፣ ይህ የእግዚአብሄር ምህረት የሚጎበኘን ሰአት ሲሆን በዚያን ወቅት የደረቀብን ነገር ከአምላክ ወንዝ የተነሳ እጅግ ያብባል፣ በደስታና በዝማሬ ልባችን ዳግም ሐሤትን ያደርጋል፣ መንፈሳችን የእግዚአብሔርንም ክብር ተገልጦ ሲሰራ፣ በቤተክርስቲያን ሲመላለስም ያያል።
በሚንቀረፈፍ ስብእና የተጠፈነገ መንፈሳዊ ህይወት በእግዚአብሄር መንፈስ ሃይል ተሃድሶ ውስጥ መግባት አለበት፤ በዚያን ጊዜ አንካሳነቱ ሽሮ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፥ ድዳነቱ ተፈውሶ ምላሱ ይዘምራል፤ በነፍሱ ምድረ በዳ ውኃ፥ በበረሀ ልቡም ላይ የመንፈስ ፈሳሽ ይፈልቃልና።
‘’ደረቂቱ ምድር ኵሬ፥ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ልምላሜና ሸምበቆ ደንገልም ይሆንበታል።
በዚያም ጐዳናና መንገድ ይሆናል እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም፥ ለንጹሐን ግን ይሆናል፤ ተላላፊዎችና ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም። አንበሳም አይኖርበትም፥ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፥ ከዚያም አይገኙም፤ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ፤ እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።’’(ኢሳ.35:1-10)
ቃሉ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ልምላሜና ሸምበቆ ደንገልም ይሆንበታል ይላል። በመንፈስ ፍሬ ልምላሜ ሞልቶ የነበረ ልብ ከወንዝ ፈሳሽ አካባቢ ዞር ካለ የመናፍስት ፈቃድ ማደሪያ መሆኑ እርግጥ ነው፤ የልባችን ዋስትና ጠላታችንን ማሳደጃ ብቻኛው መፍትሄ የእግዚአብሄር መንፈስ ጉብኝት ስለሆነ የእግዚአብሄርን ስጦታ መለመን ከርሱም ጋር መጣበቅ ይገባል ማለት ነው።
ተስፋ ሳይቆርጡ ከደጁ ለማይጠፉ ደካሞች ግን የእግዚአብሄር ጉብኝት አንድ ቀን ይሆናል፣ ከዚህ ቀጥሎ የምናገኘው ታሪክ ይህን የእግዚአሄር ጉብኝት ያሳያል፦
“ደግሞም ወደ ምኵራብ ገባ፥ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ ሊከሱትም፥ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። እጁ የሰለለችውንም ሰው፦ ተነሥተህ ወደ መካከል ና አለው። በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል? አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ። ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቍጣ አያቸው፥ ሰውየውንም፦ እጅህን ዘርጋ አለው።” (ማር.3:1-5)
ጌታ ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ወደ ምኩራብ መጥቶአል፣ ያም ሰው ሳይፈወስ ዘመኑን ገፍቶአል፤ የርሱ የመጎብኛ ቀን እስኪደርስ ግን ምኩራብ አካባቢ ይገኝ ነበር። ይህ ሰው ሙሉ አካል ባለቤት ነው፣ መመላለስ ይችላል፣ ያመልካል፣ ወደ እግዚአብሄር በሙሉ ሃይሉ እንዳይዘረጋ ግን የሰለለች እጁ ትሸመቅቀው ነበር። በአምልኮ ስርአት እጁን ወደ አምላኩ ማንሳት አይችልም፣ በሰለለች እጁ ምክንያት ሙሉ ሃይሉን አውጥቶ መስራትና መንቀሳቀስ ሳይችል ተሸብቦ ኖሮአል። ጌታ ኢየሱስ በጎበኘው ሰአት ግን ያን የተሸመቀቀ እጁን ዘረጋለት፣ ቁጡብ አምልኮውን ሊሽርለት፣ ያነከሰበትን ነገር አነሳለት፤ ሙሉ ሃይሉን የሚጠቀም ሰው አደረገው፣ ከአንካሳነት ፈታው፣ ያን ያደረገውም በተቃዋሚዎቹ ፊት ነበር።
ዛሬም መንፈሳውያን ሆነን ሳለ የእግዚአብሄርን እውቀት እንዳናስተውል የሸፈነብን መጋረጃ ነገር ካለ መፍትሄው የእርሱ ጉብኝት በመሆኑ እርሱን በጸሎት መጠበቅ ይገባናል። በ2ቆሮ.3:14 ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል አለ፦
“ነገር ግን አሳባቸው ደነዘዘ። ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና።”
እስራኤላውያን ባለተስፋ ህዝብ ሆነው ሳለ ትኩረት ባጣ ህይወት ውስጥ በመስጠማቸው የመጎብኛቸው ሰአት በሚያስደንቅ ሁኔታ ሊያመልጣቸው ችሎአል። አሁን ያሉበት ከባድ የድንዛዜ ህይወት የተፈጠረው በውስጥ ሰውነታቸው ላይ የተደረበ፣ መንፈሳቸውን ከማስተዋል የጋረደ መጋረጃ የውስጥ አይናቸውንና ጆሮአቸውን ስለደፈነ ነው። የነርሱ መፍትሄም ክርስቶስ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ቃሉ እነርሱ ሊድኑ የሚችሉት፣ ከድንዛዜያቸው የሚነቁትና ከሙታን ሰፈር የሚውጡት ጌታ ኢየሱስን ሲያገኙ ብቻ እንደሆነ ቃሉ ያስረዳል።
ክርስቶስ የህይወታችን ብርሃን ሲሆን መንቃት ይሆናል፣ ምሪትም ይገኛል
የመንፈሳዊ ህይወት መምታታትና ግርታ፣ ድካምና ድንዛዜ የዋጠው ህይወትም በመንፈሳውያን ላይ ሊፈጠር የሚችል ነገር ሲሆን ካልተቆረጠ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጪ የሚያስወጣ ችግር ነው። ስለዚህ እንዲህ እናድርግ፡
-ኢየሱስ እንዲጎበኝ እንለምን እርሱ ሲመጣ ጎባጣችን ይቃናል
‘’በሰንበትም በአንድ ምኵራብ ያስተምር ነበር። እነሆም፥ ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፥ እርስዋም ጐባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም። ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና፦ አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል አላት፥ እጁንም ጫነባት፤ ያን ጊዜም ቀጥ አለች፥ እግዚአብሔርንም አመሰገነች።’’(ሉቃ. 13:10-13)
ይህች ሴት በክፉ መንፈስ አሰራር ጎብጣለች፣ ከነጉብጥናዋ ግን ወደ እግዚአብሄር ቤት ተመላልሳለች፤ እግዚአብሄር ወደ ቤቴ አትምጪ አላላትም፣ የድካም መንፈስ ግን ሲታገላት ከፊቱ ሊያስቀራት አጉብጦአታል፤ ያች ሴት የልቡዋ ምኞት የሞላው፣ ሙሉ ሰውነትዋ የተረጋገጠውም በጌታ ጉብኝት ወቅት ነበር።
-ብልቶቻችንን ለርኩሰትና ለአመጻ ባሪያ ከማድረግ ለጽድቅ ባርያ አድርጎ ማቅረብ
ሃጢያት የሁሉም ድካማችን ምንጭ ነው፣ አዳክሞም ለጠላት አሳልፎ ያቀርበናል፣ ያን መቀልበሻ መንገድ ራስን ለእግዚአብሄር ማቅረብ ብቻ ነው፦
‘’ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ። የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና። እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና። አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው።’’ (ሮሜ.6:19)
-የጌታ ብርሃን በልባችን ሲበራ የሞተው መንፈሳችን ይነቃል
‘’ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል። እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ’’(ኤፌ.5:15-20)
የጌታ ብርሃን በህይወታችን ፍሬ እንድናፈራ ያደርጋል፣ ፍሬውም በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ውስጥ በመመላለስ የሚገለጥ ነውና እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ ሲል ቃሉ ይመክረናል፤ ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር እንዳንተባበር ከብርሃን ጋር እንድንመላለስም ይመክረናል። ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና ተብሎ ስለተጻፈ።