የስሜት አግባብነት[2…]

የመጨረሻ ዘመን

መንፈሳዊ ድንዛዜ ስሜትንም ይገድላል/ያደነዝዛል
ውስጣችንን የሚያነቃቃ ነገር በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የጠለቅ ሲሆን ፍላጎታችን የመቀዝቀዝ ሁኔታ ውስጥ ይሆናል፤ የመንፈስ ብርታት ሁለንተናን እንደሚያንቀሳቅስ ሁሉ ቅዝቃዜም መተሳሰር ያመጣል። በመንፈሳዊ ብርታት ውስጥ ስንገኝ የቃሉ ጥማት ይመጣል፣ የጸሎት መንፈስ ይበረታል፣ ቅድስና ገዢ ይሆናል፣ ህይወትም ይጸናል። መንፈሳዊ ቅዝቃዜ የድንዛዜ መገለጫ ሲሆን የሁሉ ነገር ፍላጎትና ጥማት መዘጋትና የፍላጎት ጥማት መዘጋት በመሆኑ የህይወት መናጋትን ተሻግሮ እስከ ኑሮ በሚደርስ ተጽእኖ ስሜቱ ይቆጣጠረናል፤ መንፈሳዊነት በመንፈስ የመለምለም ውጤት ቢሆንም ቅዝቃዜ ሲዘልቀን ከራሳችን አልፎ በዙርያችን ባሉትም ላይ በጎ ያልሆነ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል።
በመንፈሳዊ መነቃቃት ውስጥ ግን የሚሆነውን ነገር በሚከተለው ቃል ላይ እንመልከት፦
‘’የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም አምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሤትም በዓላት ይሆናል፤ ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በብዙ ከተሞች የሚቀመጡ አሕዛብ ገና ይመጣሉ፤ በአንዲትም ከተማ የሚኖሩ ሰዎች፦ እግዚአብሔርን እንለምን ዘንድ፥ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን እንፈልግ ዘንድ ኑ እንሂድ፤ እኔም እሄዳለሁ እያሉ ወደ ሌላ ከተማ ይሄዳሉ። ብዙ ወገኖችና ኃይለኞች አሕዛብ በኢየሩሳሌም የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርንም ይለምኑ ዘንድ ይመጣሉ። የሠራዊትም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ዘመን ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።’’ (ዘካ8:21-23)
ከላይ ቃሉ እንደሚመክረን የውስጥ ስሜት በደስታ የታጀበ እንዲሆንና ህይወት ሳይጎሳቆል በተድላ እንዲመራ ከእግዚአብሄር ጋር ያለንን ቅርበት ማጥበቅ የግድ ይላል፤ ይሁዳ በተከታታይ ጾምና ጸሎት የአምላካቸውን ፊት ሲፈልጉ እርሱም ሲገኝላቸውና ሲባርካቸው እንመለከታለን፤ በጾማቸውና እግዚአብሄርን በመፈለግ ውስጥ የርሱ ሰላም ሲሰፍን ብቻ የውስጥ አስተሳሰብና ስሜት የተረጋጋ፣ የማይዋዥቅ እንዲይውም ለሌላው የተረፈ ህይወት እንደሚያቀዳጅ ከቃሉ እንመለከታለን።
መንፈስ ቅዱስ የተቆጣጠረው ህይወት የሚያሳየውን ፍሬ ቃሉ ሲያመለክት እንዲህ ይላል፦
“የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።” (ገላ.5:22-23 )
በሌላ በኩል መንፈሳዊ ድንዛዜ ሲፈጠር ግን ህይወት ውዥንብር ውስጥ ስለሚገባ ነፍስ የሚያደክም ሁኔታ ውስጥ ትሰጥማለች። ጨለማ፣ ግራ መጋባት እና ተስፋ መቁረጥ ይከታተላል። የመንፈስ ፍሬም ይጠወልጋል። በመንፈሳዊ ህይወታችን ውስጥ ግራ መጋባቶች የሚኖሩባቸው ጊዜያት አሉ፣ እና ሰዎች ሲመክሩ መውጫው መንገድ መረጋጋት ነው፣ ግራ መጋባት አያስፈልግም የሚል ቢሆንም ያ ግን መፍትሄ አይደለም። ለመንፈሳዊ ድንዛዜ ከግራ መጋባት መውጣት ብቻ መፍትሄ አይሆንም፣ የሚባለው መፍትሄ የችግሩን ስር አላገኘምና ፍጹም ውጤት አይገኝም። ሳኦልን ስንመለከት፦
‘’የእግዚአብሔርም ቃል፡- ሳኦል እኔ ከመከተል ተመልሶአልና፥ ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ ብሎ ወደ ሳሙኤል መጣ። ሳሙኤልም ተቈጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፦ሳሙኤልም በነጋው ሳኦልን ለመገናኘት ማለደ። ሳኦልም ወደ ቀርሜሎስ መጣ፤ እነሆም፥ የመታሰቢያ ዓምድ ባቆመ ጊዜ ዞሮ አለፈ፥ ወደ ጌልገላም ወረደ የሚል ወሬ ለሳሙኤል ደረሰለት። ሳሙኤልም ወደ ሳኦል መጣ፤ ሳኦልም፦ አንተ ለእግዚአብሔር የተባረክህ ሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ አለው። ሳሙኤልም፦ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድር ነው? አለ። ሳኦልም፦ ሕዝቡ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉአቸው ዘንድ መልካሞቹን በጎችና በሬዎች አድነዋቸዋልና ከአማሌቃውያን አምጥተዋቸዋል፤ የቀሩትንም ፈጽመን አጠፋን አለው። ሳሙኤልም ሳኦልን፦ ቆይ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ሌሊት የነገረኝን ልንገርህ አለው፤ እርሱም፦ ተናገር አለው። ሳሙኤልም አለ፦ በዓይንህ ምንም ታናሽ ብትሆን ለእስራኤል ነገዶች አለቃ አልሆንህምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባህ። እግዚአብሔርም፦ ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው ብሎ በመንገድ ላከህ። ለምርኮ ሳስተህ ለምን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህም? ለምንስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረግህ? ሳኦልም ሳሙኤልን፦ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቻለሁ፥ እግዚአብሔርም በላከኝ መንገድ ሄጃለሁ፤ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጥቻለሁ፥ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ። ሕዝቡ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በጌልገላ ይሠዉ ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን በጎችንና በሬዎችን ከምርኮው ወሰዱ አለው።ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።’’ (1ሳሙ. 15:11-22)
እግዚአብሄር ስለ ሳኦል ሲናገር እኔን ከመከተል ተመልሶአል አለ፤ የተመለሰ ሰው በመንፈሱ እንደሚዝል የታወቀ ነው፣ የመለኮት ብርታት ተለይቶታልና፤ ከዚያ ወዲህ ሳኦል ሁሉ ነገር የተመሰቃቀለበት ሆኖ ቀጠለ፣ እውነቱን ከሃሰት መለየት ተሳነው፣ በትክክል የሆነውን መመስከርም አልቻለም፣ ተዛብቶበታልና። እግዚአብሔር፦ ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው ብሎ ሲልከው ለምርኮ ሳስቶ የእግዚአብሔርን ቃል ተላልፎአል፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርጎአል፣ እንዲያም ሆኖ ሳሙኤልን፦ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቻለሁ፥ እግዚአብሔርም በላከኝ መንገድ ሄጃለሁ፤ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጥቻለሁ፥ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ ሲል ጥፋቱን ማየት እስኪያቅተው ተከራክሮአል፣ንሰሃ መግባትም አልቻለም።
መንፈሳዊነትን የሚታገሉ ነገሮች ብዙ ናቸው
ኢያሱ የተባለ ወጣት ከሙሴ ጋር 40 አመት ሲመላለስ ኖሮአል፣ ሙሴንም ዘመኑን ሁሉ አገልግሎአል፤ ሙሴ በሞተ ጊዜ የአመራሩን ስፍራ ወስዶ አገልግሎቱን እንዲቀጥል ሲጠር ፈርቶ ነበር። እስራኤላውያን ክፉ ህዝብ ስለነበሩና ታዛዦች ስላልነበሩ ፈራቸው። በነርሱ ዘንድ ሁልጊዜ ነገሮች አቅጣጫቸውን የሳቱ ሲመስል ወደ ወጡበት ወደ ሁዋላ ተመልክተው ግብጽን ይሹ ወደዚያም መሄድ ይፈልጉ ነበር፣ ይሄም መሻታቸው እግዚአብሄርን እጅግ ሲያስቆጣ ነበር። እንዲያውም ሙሴን ይገድሉት ዘንድ ብዙ ጊዜ አሲረዋል፤ እነዚህ እስራኤላውያን በስጋ አስተሳሰብ ብርቱ፣ ፍላጎታቸው ውስብስብ፣ በመንፈሳዊ ህይወት ግን እጅግ ደካማና አመጸኛ ነበሩ፣ በከፍተኛ ተቃውሞ ውስጥ መዘፈቃቸው የመንፈሳዊ ድንዛዜ ውጤትና የውድቀታቸው ብርታት የፈጠረው ባህሪ በነርሱ ላይ ይታይ ስለነበር ነው፤ በዚህ ምክኒያት የእግዚአብሄርን አላማ ሊያስተውሉ ያልቻሉ ትእዛዙን ከመቀበል ያመጹም ነበሩ፣ በእግዚአብሄር ፈቃድ ላይ እንቅፋት ይሆኑ ነበር፤ ለአባታቸው ለነአብረሃም፣ ለነይስሃቅና ለነያእቆብ እግዚአብሄር የገባውን ቃል ኪዳን ስላላስተዋሉ በርሱ መንገድ ሊጉዋዙ አልቻሉም ነበር። እግዚአብሄር ግን ቃሉን ጠብቆ እነርሱን ወደ ከነአን በትግስት እየመራ አወጣቸው። ኢያሱ እነዚህን ህዝብ አይቶ ፈርቶ ነበር፤ ሙሴ ሞቶአል፣ እርሱ የኢያሱም መሪ ነበር አሁንም የለም፤ ይሄንን ያለ ሙሴ መኖር ሲያስብ የእስራኤላውያንን ክፋትም ሲመለከት የመንፈሳዊ ህይወታቸውን ውድቀት ተመልክቶም አደጋው እጅግ አስፈራው፤ አስቀድሞ ሙሴን እንዴት 40 አመት እንደታገሉትና እንዳሰቃዩት አይቶአል፤ አሁን እግዚአብሄር ጠራውና አመጸኞች ህዝቦቹን ወደ ከነአን ይዘህ ውጣ አለው፤ ስለዚህ ቢፈራና በህዝቡ ምክኒያት ተስፋ ቢቆርጥ እውነቱን ነበር። ያ ሃይለኛ የእግዚአብሄር ሰው ሙሴ ያልቻላቸው ኢያሱ እንዴት ይችላል? የእግዚአብሄር አሳብ ካልገባቸው ከነዚህ ወገኖቹ ጋር እንዴት ሊግባባ ነው? በድንዛዜ ውስጥ ያሉ እነዚህ ወገኖች የተነገረላቸውን የተስፋ ቃል አያውቁምና እንዴት ሊረዱት ነው? ወደ ፊት ሲያይ ደግሞ በከነአን ያሉ አህዛብ ጨካኞች፣ አስፈሪ፣ ክፉና ተዋጊዎች እንደሆኑ አይቶአል፤ ይህ ሁሉ ሆኖ እያለ እግዚአብሄር መጣና ኢያሱን እንዲህ አለው፦
‘’የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ባሪያዬ ሙሴ ሞቶአል፤ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስ ተሻገሩ። ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ።’’(ኢያ1:1-3)
እግዚአብሄር ቃሉን ከጠበቀ መንገዱ እንደሚቀናው ቃል ገብቶለታል። ኢያሱ እግዚአብሄር የሰጠው ሃላፊነት ከባድ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር፤ ስለዚህ አብዝቶ አሳብ ገብቶት ነበር፤ ፈርቶም ነበር፤ ለዚያም ነው እግዚአብሄር ደጋግሞ እንዳይፈራ ያሳሰበው፤ ለዚያም ነው እግዚአብሄር ከርሱ ጋር ሆኖ ሳይተወው በአብሮነት እንደሚሆን ያስታውሰው የነበረው(ኢያ.1:5-9)። ‘’በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም። ለአባቶቻቸው፦ እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል።የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ አይዞህ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?’’
ስለዚህ የሚያስፈራ ሸክም ሲሰጥ እግዚአብሄር በአብሮነት ሊሆንና ሊረዳ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል። እጅግ የፈራውን ኢያሱን ደጋግሞ ሲያደፋፍረው፦ አይዞህ፣ ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ይለው ነበር እግዚአብሄርን የሚያክል አስተማማኝ አምላክ እየተናገረን ስለምን መረጋጋት ተስንኖን ፍርሃት ይወርሰናል? ግልጽ ነው፣ጥቃት ሲኖር፣ መንፈሳችንን ያ የምንፈራው ጥቃት ሲያገኘው፣ የእግዚአብሄር ማጽናናት ሊሰማን ሳይችል ሲቀር ነው፤ ኢያሱ ግን እግዚአብሄር የነገረውን ይዞ ተጉዋዘ፣ እንደተነገረውም ሆነለት፣ እግዚአብሄርን ሰምቶ ነበርና። ኢያሱ እግዚአብሄር የነገረውን ቃል አምኖ ስለነበረ ተስፋውን ይዞ ወደፊት ሊራመድ በቅቶአል። የረገጥከው ምድር ሁሉ ያንተ ይሆናል፣ ያለው ብርቱ የተስፋ ቃል ነበር። ኢያሱም ማድረግ የነበረበት የዚህ ሕግ መጽሐፍ ይዞ፦ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈውን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም ያለውን ይዞ በመጉዋዙ ረጅሙ ጉዞ እንዲሳካለት፣ ውጣ ውረዱ በቁጥጥር ስር ሆኖ ተለኮው እንዲከናወን ሆኖአል። ለዘላለም የህይወት ተስፋ ከተጠራው ከእስራኤል መሃከል መደረግ የነበረውን ነገር አስተውሎ የተመለከተ ካሌብ የተባለ ሰው ብቻ ተገኘ፣ይህን ሰው እግዚአብሄር አግኝቶም ለእርሱ በጎነት ሲያደርግለት ከህዝቡ ታሪክ እንመለከታለን፣ ካሌብ የእግዚአብሄርን የተስፋ ቃል ለመቀበል ልቡን ማስተካከል እንዲገባው ያመነ ሰው ነበር፤ ትእዛዙን በመጠበቅ፣ የራሱን የመራመጃ ጫማ አውልቆ የእግዚአብሄርን በማጥለቅ፣ በቃሉ በመበርታት፣ በመታመንና በድፍረት ከኢያሱ ጋር በመሰለፍም ለኢያሱ የተነገረውን ሁሉ እርሱም ሊያገኝ በቅቶአል። ከመንፈሳዊ ድንዛዜ አምልጠን እግዚአብሄር መመላለስ በሚገባን የህይወት መስመር ውስጥ እንደ ቃሉ ሲያገኘን ከተናገረው ነገር አንዳችም ሳያስቀር እንደሚያወርሰን የካሌብ ህይወት ምስክር ነው። እግዚአብሄርም መስክሮለታል፦ ‘’በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ አሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥ነገሬንም ስላልሰሙ፥ በእውነት ለአባቶቻቸው ማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእነርሱም የናቀኝ ሰው ሁሉ አያያትም፤ ባሪያዬ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ ፈጽሞም ስለተከተለኝ እርሱ ወደ ገባባት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል።’’ አለ እግዚአብሄር (ዘሁ.14:22-25)። መንፈሳዊ ድካም የረጅምና የአጭር ጊዜ ውጤት ያመጣል
ስንደክም ብቻችንን የተጣልን ያለማንም ቅርበት እንዳለን ይሰማናል፣ ይህ ስሜት ሰዎችም እግዚአብሄርም እንደተወን እንዲሰማን ያደርጋል፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የምናስበውም የምናደርገውም ግራ የተጋብ ይሆናል፤ ነገር ግን እግዚአብሄር ከአኛ ጋር እንዳለ ካመንን ለብቻችን ሆነን ሳለ እንኩዋን እንደዚያ እንደሆንን አይሰማንም።በ1ነገ.18 ውስጥ እንደምናየው ኤልያስ ከአገርና ከህዝቡ ተነጥሎ በነበረበት ወቅት ከእግዚአብሄር ጋር ስለተጣበቀ በየትኛውም ጊዜ የብቸኝነት ስሜት አልነበረውም፤ እንዲያውም በእግዚአብሄር ስለታመነ 850 ሃሰተኛ ነብያትን ተነስቶ አጠፋ፤ እግዚአብሄር ከእርሱ ጋር እንደሆነ ስለታመነ ልቡ በአጋንንታዊ አሰራሮች ላይ በረታ፣ ጨክኖም የእግዚአብሄር ጠላቶችን አጠፋ። እግዚአብሄር ከእኛ ጋር እንደሆነ ካልታመንን ግን የተለየ ታሪክ ነው የሚሆነው፣ፍርሃት ያጣድፈናል፣ የሰው አተኩሮ ማየት እንኩዋን ያስፈራናል፣ ጨለማ ያስፈራናል፤ ከምንም ነገር በላይ በፍርሃት አሳባችን ይምታታና በስጋት እንቀፈደዳለን፣ ምንም ነገር ይሁን ከሁኔታው ጋር ባይገናኝም ያስደነግጠናል።
ስለ ወደፊትህ ስናስብ ነገሮች ሊጨልሙብን ይችላሉ፣ ተስፋ መቁረጥ ይይዘናል፣ ወደፊት ላለው ኑሮአችን ማቀድ ይሳናናል፣ ስለህይወት ተስፋቢስ ስለምንሆን ባለንበት እንቆማለን (ያለ ራእይ ወደፊት መራመድ ስለማይቻል)፤ በዚህን ሰአት በእጅ ሊኖር የሚችለውን እንኩዋን ልናጣ እንደምንችል ስለሚሰማን አብዝተን እንጨነቃለን፤ ከፊታችን ምን ሊገጥመን እንደሚችል እርግጠኛ ስለማንሆን እንፈራለን፣ እንበረግጋለን።
የሚበጀው መፍትሄ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሄር መደገፍ ነው፤ ነገሮችን ለእግዚአብሄር መተው መልካም ነው፤ እግዚአብሄር ግን በቃሉ ጠባቂያችን መሆኑን ይናገራልና ነቅተን ወደ እርሱ እናተኩር ይገባናል። ሳሙኤል ለንጉስ ሳኦል መንግስቱን በሃጢያቱ ምክኒያት እንደሚነጠቅ በነገረው ጊዜ እጅግ ፈርቶም ነበር፣ ግራ መጋባት ያዘው፣ ሁሉም ነገር ጨለመበት(1 ሳሙ.13:13-14)። ሳሙኤል ያን ከነገረው በሁዋላ ንጉሱ ወደፊት በሚመጡት የንግስናው ዘመናት ሳይቀር መልካም ነገር እንደሌባቸው አወቀ፤ ንጉሱ ያን መትፎ ዜና ከነቢዩ ከሰማ በሁዋላ የሚፈራና የሚጨነቅ ስለነበረ ማንንም አያምንም ነበር፤ እንድያውም ሰዎች በእርሱ ላይ የሚነሱ እስኪመስለው ተጠራጣሪ ሆነ፤ በከንቱ አሳብና ጥርጣሬ ተዳክሞ ጎሰቆለ፣ የሚቀናም ሆነ፤ በዚህ ህይወቱ ብዙ ጥፋቶች ሰራ፣ውደቀቱም ተፋጠነ።
በሃጢያት ቁጥጥር ስር መውደቅ
አዳምና ሄዋን ለመጀመሪያ ጊዜ ክፉና መልካሙን የሚያሳውቀውን ፍሬ እንደበሉ ፍርሃት ወደቀባቸው (ዘፍ. 3:8-10)፤ በእግዚአብሄር ላይ ካመጹ በሁዋላ ፈሪዎችና ከእርሱ የሚሸሹ ሆኑ። በጸጸትና በፍርሃት ህይወታቸው የተጎሳቆለ ሆነ፤ ደግሞ ማንንም የማያምኑ ሆኑ። ሃጢያት በእግዚአብሄር ፊት ፈሪ ያደርጋልና። መንፈሳዊ ህይወቱ የተበላሸበት ሰው መንፈሳዊ ጥንክሬ እንደማይኖረው ከነርሱ ህይወት እንማራለን፤ እነርሱ እግዚአብሄርን የሚፈልጉ፣ ወደ እርሱ የሚጠጉም ሳይሆኑ የሚሸሹ የሆኑት በሃጢያት ምክኒያት ነበር።
መንፈሳዊ ጥንካሬ ማጣት
መንፈሳዊ ጥንካሬ ሲጠፋ ሌሎች ነገሮች ላይ ትኩረታችን ይጠፋል፦ ቤተሰብ፣ ንብረት፣ ገንዘብ፣ ሃላፊነት፣ ሌሎችም ከእኛ ጋር ቢኖሩ ትኩረት ልንሰጣቸው አንችልም። መንፈሳዊነት ሲጎድል ስጋዊነት ከፍ ይላል፣ ስጋዊ ባህሪ ይወጣል፣ ህይወትም ጎስቋላ ይሆናል። በምንም ነገር ላይ ፍላጎት ስለሚጠፋ ከንቱ ነገር የገጥማል። የሰይጣን ግብ ክርስቲያኖች እንደዚያ ደካማና ጉልበት-አልባ ህይወት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፤ ለዚህ የሚያጋልጠው መንፈሳዊ ድክመት ነው። መንፈሳዊ ጥንካሬ ሌላ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን መንፈሳዊ ነገር መታጠቅ ነው፣ ያን ካጣን፣ ከተነጠቅን፣ ካስማረክን፣ ቸል ካልን ብዙ ጥፋት ከክፋት መናፍስት ወደ ህይወታችን መምጣቱ የማይቀር ነው።