ስሜት ምን?
ማንኛውም ከሰውነታችን ውጪ የሆነ ነገር ተጽእኖው ወደ እኛ ሲመጣ የሆነ የሰውነታችን ክፍል መልስ ይሰጣል፤ ይህ የሚሆነው ያየነው፣ የዳሰስነውና የሰማነው ነገር ትኩረታችንን ስለሳበ ሊሆን ይችላል፤ ሁሌም የነካነው፣ የቀመስነው፣ ያየነውና የሰማነው ነገር እንድንንቀሳቀስ ያስወስነናል፦ አንድ ነገር ቢሸተን እንደሽታው ምንነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንገባለን፤ ሰውነታችንንም የነካን ነገር እንዲሁ ለመልስ እንድንንቀሳቀስ ሊያደርገን ይችላል። የማየት፣ የማሽተት፣ የመስማትና የመቅመስ ችሎታ ያላቸው የአካላችን ክፍሎች ጠንካራ የስሜት ህዋስ ስላላቸው ስሜታችንን ይኮረኩሩታል። በተሰማን ስሜት ምክኒያት የተለያየ አመለካከት እናሳያለን፦ መሳቅ፣ ማልቀስ፣ መውደድ፣ መፍራት፣ መደሰት፣ ተስፋ ማድረግና መቁረጥ ፣ ሌላም ብዙ ነገር በውስጣችን ይፈጠራል። ነገር ግን ሁሉም ቢሆኑ በተገቢው ስፍራ ሊገለጡ እንደ አኩዋሃናቸውም አያያዝ ሊያስፈልጋቸው ግድ ነው። ስሜቶች ሲከሰቱ በስሜት ህዋሶቻችን በኩል አልፈው በአንጎል ላይ መልእክት ሆነው ይደርሳሉ፤ የምናውቃቸው፣ የምንሰማቸው፣ የምናያቸው፣ የምንገናኛቸው ነገሮች በተፈጠረው መልእክት የሚስተናገዱም ይሆናል፡፡ ስሜትን በአካላችን ውስጥ እንዲኖሩ ያደረገው ፈጣሪ አምላክ ነው። ስለዚህ ስሜት አልባነት ፈጽሞ ጤነኝነት አይደለም፡፡ ለምናየውና ለምንሰማው ነገር ስሜታችንን ካልገለጥን ወይ ውስጣችን ካልተነካ የሆነ ችግር በአካላችን በተለይ በአእምሮአችን ላይ እንዳለ ያስታውቃል፡፡
የስሜት አግባብነት
መሳቅ አስፈላጊ ነው፣ ሁሌስ ያስፈልጋል ወይ? የማያስፈልግበት ቀን በእርግጥ ይመጣል:: በሀዘን ወቅት እንዴት ይሳቃል? ያ የጤና አይደለም። ማልቀስ አስፈላጊ ነው፣ በሀዘን፣ በትካዜ፣ በምሬት፣ በመለየትም ከውስጥ በሚፈነቅል ስሜትና ስብር ባለ ስሜት ምክኒያት በለቅሶ ምርር ያለ ሀዘን ይመጣል፡፡ በማያስፈልግ ወቅት፣ ለምሳሌ በደስታ ወቅት ሀዘን የጤና አይደለም፤ በሰርግ፣ በግብዣ በመሳሰሉት በሰዎች ደስታ መሃል ቆዝሞ መቀመጥና አልቃሻ ሆኖ መገኘት አጠያያቂ ነው። ሁሌም የስሜት አግባብነት የጤነኝነት ምልክት የሚሆነው ለዚህ ነው።
መክ.3:4 “ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው”
አንድ አማኝ የስሜት አግባብነትን እንዴት ያስተናግዳል? የእግዚአብሄር ቃል ስሜቱን ሲገራው ብቻ ይሆናል። የአለም ተግዳሮት ስሜታችንን ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን በማድረግ ፈተና ውስጥ ያስገባል፦ ማየት ቢባል የሚገባም የማይገባም ሁሉም ተደበልልቆ አለምን ሞልቶአል፣ መስማት ቢባል የሚሰማው በአብዛኛው ከበጎ ነገር የወጣ በመሆኑ አስጭናቂ ነው። ከዚህ በመነሳት ሊኖረን የሚችለው አስተሳሰብና ስሜት ምን ያህል በፈተና የተሞላ መሆኑን መገመት ይችላል።
ዘመኑ አስጨናቂ ስለመሆኑ ቃሉ ይመሰክራል፤ የሚያስጨንቁን ነገሮች ከስሜታችን አንስተው እስከ ነፍስና መንፈስ በሚደርስ ተጽእኖ የበረቱ ናቸው። ስለዚህ የስሜት አግባብነትን ስናስብ እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች ታሳቢ ልናደርግ ይገባል።
ስሜት መቆጣጠር
ስሜት በአካላችን ላይ ስለተፈጠረ ሀጢያት አይደለም፣ እንዲያውም የስጋችን ህያውነት መለኪያ ነው፤ እግዚአብሄር የፈጠረው ነው። ሆኖም ስሜት ከአግባብ ውጪ ሲሆን፣ ከልክ ሲያልፍና መጠን ሳይበጅለት ሲቀር ግን ለሌላ የማይገባ ሰሜት አሳልፎ ይሰጣል። ብዙ ጊዜ ስሜት ከአግባብ ውጪ ስለሚሆን በርሱ አንታመንም፡፡ ስሜት የሚገራው ሲያጣና ልቅ ሲሆን ወደ ሌላ ስሜት (ምናልባት አላስፈላጊ ወዳልሆነው) ሊያሳልፍ ይችላል። ልያና ራሄል የእስራኤል ህዝቦች ወላጅ እናቶች ስለመሆናቸው መጽሃፍ ቅዱስን የሚያጠና ሁሉ ያውቃል፤ እነዚህ ሴቶች ግን አባታቸው ለአንዱ ለያእቆብ ድሮአቸው ስለነበር ዘመናቸውን ሁሉ ሲቀናኑ እንዲኖሩ ተደርገዋል፤ በአንድ አጋጣሚ የሆነውን ከዚህ ቀጥሎ እንመልከት፦
ዘፍ.30:14-21 “ሮቤል ስንዴ በሚታጨድበት ወራት ወጣ፥ በእርሻም እንኮይ አገኘ፥ ለእናቱ ለልያም አመጣላት። ራሔልም ልያን፦ የልጅሽን እንኮይ ስጪኝ አለቻት። እርስዋም፦ ባሌን መውሰድሽ በውኑ ጥቂት ነገር ነውን? አሁን ደግሞ የልጄን እንኮይ ልትወስጂ ትፈልጊያለሽን? አለቻት። ራሔልም፦ እንኪያስ ስለ ልጅሽ እንኮይ በዚህች ሌሊት ከአንቺ ጋር ይተኛ አለች። ያዕቆብም ሲመሽ ከዱር ገባ፥ ልያም ልትቀበለው ወጣች እንዲህም አለችው። ወደ እኔ ትገባለህ፤ በልጄ እንኮይ በእርግጥ ተከራይቼሃለሁና። በዚያችም ሌሊት ከእርስዋ ጋር ተኛ። እግዚአብሔርም የልያን ጸሎት ሰማ፥ ፀነሰችም፥ አምስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። ልያም፦ ባሪያዬን ለባሌ ስለ ሰጠሁ እግዚአብሔር ዋጋዬን ሰጠኝ አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ ጠራችው። ልያም ደግማ ፀነሰች፥ ስድስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። ልያም፦ እግዚአብሔር መልካም ስጦታን ሰጠኝ፤ እንግዲህስ ባሌ ከእኔ ጋር ይኖራል፥ ስድስት ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስሙንም ዛብሎን ብላ ጠራችው። ከዚያም በኋላ ሴት ልጅን ወለደች፥ ስምዋንም ዲና አለቻት።”
የራሄልን ስስነት/ስሜታዊነት እንዲሁም በቀላሉ መነካት በዚህ ቃል ውስጥ እናያለን፣ ሊያ ልጅ እጅ ላይ ያየችው እንኮይ ትልቅ ነገር ላይሆን ይችላል፣ ግን አይታው ስሜታዊ ሆነች፣ ጎመጀችበትም። ይህንን ያየችው ሊያ ደግሞ አጋጣሚውን ተጠቀመችበት (ቀድሞውንም ባሌን በእህቴ ተነጠቅኩ የሚል ስሜት ስለነበራት)፤ ያእቆብ ኤሳው ወንድሙን እንዴት በምስር ወጥ ብኩርናውን እንዳስለወጠው የምናስታውሰው ነው፤ ሊያም ራሄል እህትዋ ባልዋን በእንኮይ እንድትለውጥ አደረገቻት። የአይን አምሮት የፈጠረው መጎምጀት ራሄል የግልዋ ያደረገችውን ትልቅ ነገር አሳልፋ እንድትሰጥ አደረጋት፤ ሊያ በዚያች እንኮይ የተቀበለችው ያእቆብ ከዚያን ቀን በሁዋላ ለሊያ ሆኖ ብዙ ልጆችን እንድታገኝ ሆነ፣ የራሄልም ተሸናፊነትና ሃዘን የሚበዛ ነበረ።
ከቁጥጥር ውጪ መሆን
የእግዚአብሄር ቃል የማይገራ ስሜት የሚያመጣውን አደጋ ስለሚያውቅ አስቀድሞ መፍትሄውን ያመለክታል፦
1ቆሮ.7:9 “ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ።”
ክርስቲያን ለምን ስጋዊ ፍላጎት አለው አይባልም፤ ለምን መለኮታዊ መፍትሄውን አይቀበልም ይባላል እንጂ። ተቃራኒ ጾታ ላይ ያለው መሳሳብ ለምን አየለበት አይባልም፣ ይልቅ ለምን የመሳሳቡ ስሜት ምኞት ፈጥሮበት በዚያ ከሚቃጠል አያገባም? ነው፤ የቃሉ መፍትሄ እንደሁ ቁርጥ ያለ ነው።
ስሜታዊነት ወደ እብደት ሲመራ ከራስ ውጪ ያደርጋል፤ ሶምሶን አንዲት ፍልስጤማዊት ሴት አየ፣ ስሜቱን ተከተለ፣ ፍላጎቱን ሰማ፣ የአይን አምሮት ከወዳጅ ሰፈር አውጥቶ በስህተት መንገድ እየመራው ጠላት ሰፈር ከተተው። ያ ስሜቱ የመራው አቅጣጫ ወደ ሁዋላ የሚመልስ አልነበረም፤ በስሜት ምሪት የጀመረው ጉዞው መጨረሻ ወፍጮ ፈጪ አድርጎ የጠላቶቹ ባሪያ እስኪሆን አዋረደው፦
“ሶምሶንም ወደ ተምና ወረደ፥ በተምናም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ። ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ፦ በተምና ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ፤ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ አላቸው።አባቱና እናቱም፦ ካልተገረዙት ፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለምን? አሉት። ሶምሶንም አባቱን፦ ለዓይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ አለው።” (መሳ.14:1-3)
ስሜትን ያለመግዛት ራስን ባለመቆጣጠር በኩል እልህ ይፈጥራል። እልህ በአንድ ነገር ላይ (በተለይ በጎ ባልሆነው ላይ ያጣብቅና) መንፈሳዊነትም በዚያ አካሄድ ይጎዳል፤ ስሜታዊነት ግብታዊነት ነውና። እዚያው ፈጠረ እዚያው ፈጸመ የሆነ ችኩል ለሁሉ ችግር ይሆናል። ሶምሶን ለእግዚአብሄር የተለየ ሰው ከመሆኑ ውጪ ግብታዊነትም ነበረበት። በስሜት ዘልሎ የሚገባበት ስፍራ ዋጋ የሚያስከፍለው እንዲያውም ከእርሱ አልፎ ለቤተሰቡና ለወገኖቹ ለእስራኤላውያን ድንጋጤን የጋበዘ ነበረ። ከዚህ ቀጥሎ ባለ ታሪክ ውስጥ ስሜት ያስከተለው ሞትን እናያለን፦
ዘፍ.34:1-2,25-28 “ለያዕቆብ የወለደችለት የልያ ልጅ ዲናም የዚያን አገር ሴቶች ልጆችን ለማየት ወጣች። የአገሩ አለቃ የኤዊያዊ ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት፤ ወሰዳትም ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ አስነወራትም። ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ፥ ብላቴናይቱንም ወደዳት፥ ልብዋንም ደስ በሚያሰኛት ነገር ተናገራት።… ሦስተኛም ቀን በሆነ ጊዜ እጅግ ቆስለው ሳሉ፥ የዲና ወንድሞች የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ፥ ወንዱንም ሁሉ ገደሉ፤ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፥ እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ። የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን ዘረፉ፤በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ።”
ሴኬም በአይኑ በገባ ነገር ብዙ መዘዝ እንደተከተለው ይታያል። ምን እንዳየ ወይም ማንን እንደነካ አላስተዋለም፣ ስሜቱን ብቻ ነው የተከተለው። የስሜቱ አቅጣጫ ሊያን የሚያስነውር ሆነ፣ በዚህ የተቆጡት ወንድሞችዋ ሴኬም፣ ወገኖቹንና ምድራቸውን እንዲያጠፉም ጋበዘ።
ገላ.5:22 “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።”
በሶምሶም ህይወት የእግዚአብሄር መንፈስ ነበር፤ ሶምሶም ግን በእግዚአብሄር ለመመራት ትግስቱም እውቀቱም ስላልነበረው ህይወቱ ላይ መንፈሳዊ ፍሬ አልተፈጠረም፤ የእግዚአብሄርን የመንፈስ ድምጽ ሰምቶ ቢሆን ራሱን የሚገዛበት ሃይል ባገኘ ከጥፋት በተረፈም ነበር።
መንፈሳዊነትና ስሜት
ሰው ምንም በመንፈሳዊ ህይወት የበረታ ቢሆንም ስሜቱ የሞተና የደነዘዘ ነው ማለት አይደለም፤ ግን ይህ መንፈሳዊ ሰው ስሜቱን በቀላሉ የሚገራ ነው፣ ስሜቱ ለጮሀበት ነገር ሁሉ ላሙዋላልህ ወይም ላርካህ ሲል አይጣደፍም ማለት ነው እንጂ። አንድ ነገር መታሰብ ያለበት ነገር መንፈሳዊ ሰው ስሜቱን የሚገራ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚሰማው ሁሉ ትክክል ነው ብሎ ባለማመን ከማመዛዘን ጋር የሚያስተናግደው መሆኑን ነው። መንፈሳዊ ሰው መንፈሳዊ ነገርን ብቻ ሳይሆን የነፍሱ ማደርያ ስጋውም ምን እያሰማው እንደሆነ ማድመጥና በጥንቃቄ ለድምጹ መልስ መስጠት ይገባዋል።
1ቆሮ.7:4-5 “ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ።”
ክርስቲያን ባልና ሚስቶች በዚህ አቅጣጫ ከሚሰማቸው ስጋዊ ስሜት አብልጠው ከፍ ወዳለው መንፈሳዊ ስራ ማመዛዘን መች እንዳለባቸው ማወቅ እንዲገባቸው ሃዋርያው ጳውሎስ ያመለክታል። ስሜት ሊገሰጽ ወይም ልንጠየፈው ያይደለ ግን ልናቅበው ወይም ልንቆጣጠረው እንዲገባ ከቃሉ እንገነዘባለን። ለምሳሌ ባልና ሚስት በጣም ስለሚፋቀሩ በጣም ይቀራረባሉ፣ ስሜት አላቸውና አንዳቸው ለሌላቸው የመፈላለግና ከስሜት በሚመጣ አካላዊ ፍላጎት መፈቃቀድ ይኖራቸዋል፣ ስለዚህ አግባብነቱን ለማረጋገጥና ስሜቱን እንዴት እንደሚያስተናግዱት ያስተውሉ ዘንድ በእግዚአብሄር ቃል የተደገፈ ምሪት እንደተሰጣቸው የምንየው ነው።
መንፈሳዊ ነገር ከስሜት ውጪ የሆነ ህይወት ሲሆን ስሜት በስጋችን ላይ የሚገለጥ ነው፡፡ ስሜት አገባብነት በሌለው አካሄድ ሲስተናገድ ግን መንፈሳዊ ህይወትን ያጠለሻል፤ ያጨልማል፣ ከእግዚአብሄር ፊት ያስወግደዋል።
መዝ.39:1-10 “በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ። ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ ቍስሌም ታደሰብኝ። ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ፤ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ። አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ። እነሆ፥ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው፤ አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ብቻ ነው። በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጣላ ይመላለሳል፤ ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም። አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው። ከኃጢአቴ ሁሉ አድነኝ፥ ለሰነፎችም ስድብ አታድርገኝ። አንተ ሠርተኸኛልና ዝም አልሁ አፌንም አልከፈትሁም። መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ፥ ከእጅህ ብርታት የተነሣ አልቄአለሁና።”
በአጭሩ ስሜትን በመቆጣጠር ከኃጢአት ሁሉ መዳን እንደሚቻል ንጉስ ዳዊት ያሳስባል። እንዳየሁት መጠን አልናገርም፣ ያም የሆነው ያየሁትን ያህል ከተንቀሳቀስኩ ወደ ከፍተኛ ስህተት ስለምገባ ነው የሚል መልእክት ያስተላልፋል፣ ስለዚህ ስሜቴን አፍኜ ዝም ልበል፣ የተቃወመኝ ኃጢአተኛ ያደረገውን አይቻለሁ በዚያ ሳቢያ ልቤ በውስጤ ሞቀብኝ፤ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ ግን ዝም አልሁ አፌንም አልከፈትሁም አለ።
ስሜታችን እንዲገራ ያስፈልጋል
ዕብ.4:12-13 “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።”
በመንፈስ መመላለስ በቃሉ ቁጥጥር ስር ያኖራል፤ ለመሰራት፣ ለመገሰጽ ፈቃደኛ ያደርጋል። እግዚአብሄርን እናምናለንና የቃሉን ተግሳጽ ያለማንገራገር በመቀበል ልብንና ነፍስን መጠበቅ ይቻላል። በቃሉ ያለማመንስ ምን መልክ አለው?
“ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ አይሁዳዊት ከነበረች ድሩሲላ ከሚሉአት ከሚስቱ ጋር መጥቶ ጳውሎስን አስመጣ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ማመን የሚናገረውን ሰማው። እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኵነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ፦ አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ብሎ መለሰለት።”(ሐዋ.24:24-25)
ፊሊክስ ለራሱ የሚመቸውን ለልቡ ደስ የሚያሰኘውንም እየመረጠ ነበር የሚሰማው፤ ሃዋርያው ጽድቅ፣ ራስንም መግዛት ስለሚባሉ ዋና የወንጌል ነጥቦችን ሲያነሳበት መታገስ እንዳቃተው በቃሉ ላይ ይታያል። ራስን መግዛት ትልቅ ጭንቅ የሚሆነው የእግዚአብሄር ነገር ጎልቶ በህይወታችን ሳይወጣ ሲቀር ነው፤ ሰዎች የቃሉ ምሪት ገዝፎና ከብዶ እንደጫና የምንቆጥረው በዚያ ውስጥ የሚሰራልንን አምላክ ለማየት ስለሚያቅት ብቻ ነው። ለምሳሌ የሚከተለው ቃል ለአማኞች ምን ማለት እንደሆነ ማየት ይቻላል፦
2ጴጥ.1:6-7 “በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥
እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።”
ሁልጊዜ በጎ ህሊና በጎነትን ይወልዳል፤ በጎ የሚያደርጉ ልባቸው ስለሚያርፍ፣ ህሊናቸውም ስለሚረካ ያንን ደጋግሞ በመለማመድ ይታደሳሉ፣ ይህ መልካም ነገር ነው። በበጎነት ላይ ግን እውቀት ሊጨመር የግድ ይላል፣ በመንፈሳዊ ህይወት ለማደግ። እውቀትስ የትኛው እውቀት? ሰማያዊ፣ መለኮታዊ፣ ከህያው ቃሉ የሚመነጨው ምሪት ያለበት ህይወትን የሚቀርጽ እርሱን ማለት ነው። ይሄ እውቀት በአንደበት ከምንናገረው በላይ አስፈላጊ፣ የሚቀርጸን፣ ወደ ጌታ የሚያስጠጋን፣ መንፈሳዊነታችንን ስር እንዲሰድ የሚያደርግና የመንፈስ ቅዱስ ምሪት የሚካሄድበት ነው፤ ሆኖም እውቀቱ ብዙ ነገራችንን የሚቃወም ስለሆነ ፈተና ነው፣ ነፍሳችንን ለአምላካችን ሰጥተን በፈቃድ ለጌታ የማንገዛ ከሆነ ማለት ነው፣ እልህ ውስጥ እንዳይከትም ያስፈራል፣ እንደ ስድብ ይቆጠቁጣልና። ያም ሆነ ይህ በእውቀቱ ሳናድግ ራስ መግዛት የሚባለው የመታዘዝ ፍሬ ላይ ፈጽሞ አንደርስም፣ እውቀቱ ነጻ ሳያወጣን ራሳችንን ቅዱስ መስዋእት ማድረግ አይቻልም፣ በእውቀቱ ሳናድግ ፈቃዱን ማክበርም አይቻልም።
ገላ.5:22-23 “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።”