ማር.1:1-4 “የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ፦ እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፥ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ።”
መጽሃፍ እንደሚል ኢየሱስ ክርስቶስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ በሰጠው የእግዚአብሔር ወንጌል አስቀድሞ ከጠራቸው ሐዋርያ አልፎ ህዝብን ሊጠራ ተገለጠ። ይህ ጌታ በአህዛብ መሃል በገለጠው ብርሃን በኩልም የዘላለምን ርስት ለአህዛብ ሰጠ።
ሆኖም በየዘመኑ እየተገለጠ በትውልዶች ላይ የሚሰለጥን መናፍስታዊ አሰራር የሰው ልጅ ሊቀበል የተገባው የክብር ህይወት ላይ ታላቅ ግርዶሽ እየፈጠረ እስከዚህ ዘመን ድረስ ኖሮአል ወደፊትም ይኖራል። ወንጌል ምድር ላይ ከሰለጠነው የሞት መንፈስ አሰራር የላቀ ታላቅ ቢሆንም በአለም ላይ የተንሰራፋ አለማዊ ልማድ ግን ሸፍኖ እንዳይሰራ ያደርገዋል፤ ይህም የተገለጠ የክፋት አሰራር በሰው ልብ ውስጥ ደንድኖ በመቀመጥ ብርሃኑ ምድርን እንዳይደርስ ስለሚገዳደር ነው፤ የወንጌል ጉልበት ግን ከፍ ያለ የምስራችና ከጨለማው የላቀ የእውነት ቃል ነው፣ ግን በተጋረደ ልቦና ባልተለወጠም ማንነት እንቅፋት ይገጥመዋል።
በወንጌል ሰማያዊ እውቀት ወደ ብርሃን ወጥቶአል፣ ግን የሰው ያልማወቅና ያለማመን በአንድነት እንቅፋት ሲሆን ይኖራል። ያም ሆኖ የተሰበከው ወንጌል ከሰው አለማመን አልፎ የሰውን አእምሮና ልብ በፍቅር በመማረክ ሃይሉን አሳይቶአል። በወንጌል ስብከት የተገለጠ የምስራች በአለም ላይ የእግዚአብሄርን ማንነትም ያሳያል፤ ወንጌሉ በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ የሚያበራ የምስራች ነው፤ ይህ የእግዚአብሄር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰውነትም የአብረሃም አምላክ ተገለጠ። ቃሉ በ2ቆሮ.5:19 ላይ፦
“እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።” ይላል።
ክርስቶስ ኢየሱስ በስጋ ቃልኪዳን ከተገባለት ከዳዊት ዘር ሊመጣ ችሎአል፤ ክርስቶስ ኢየሱስ እንደሰው ልማድ ከልጅነት እስከ ወንጌል አገልግሎት መጀመሪያ ዘመን ድረስ በአይሁድ መሃል በቁመትም በጸጋም አድጎአል፤ እንደ ሰው ልጅ በሚኖርበት ቤተሰብ መሃል ሆኖ በመታዘዝ አገልግሎአል፤ የወንጌል አገልግሎትን ሲጀምርም የአይሁድን ምድር እየዞረ ህዝቡን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ አገልግሎአል፤ ጊዜው ሲደርስም የቤተመቅደሱን አገልግሎት በሚተካ አሰራር አገልግሎቱን ይፈጽም ዘንድ በሃጢያተኞች እጅ ገብቶ ተሰቃይቶአል፣ ተገረፎአል፣ ተሰቀሎ ሞቶአልም። ትንሳኤ መለኮታዊ ሃይል የተገለጥረበት አሰራር በእግዚአብሄር መንፈስ ለሰው ልጆች ይታወጅ ዘንድም እንደ ቅድስና መንፈስ ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ የተገለጠ ክርስቶስ ኢየሱስ በአለም ይሰበካል።
በእርሱ በተገለጠው መለኮታዊ ስም በጨለማ ውስጥ ይኖሩ በነበሩ አሕዛብ ሁሉ መካከል ሲሰራ ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ለሰዎች ጸጋን ሰጥቶአል። የጸጋው ጉልበት በገለጠው የእውቀት ብርሃን የተጠሩ አስቀድመው ለክብሩ የሆኑት ሃዋርያትና ነብያት ሲሆኑ በነርሱ መካከል ለእግዚአብሄር ሊሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ የተጠሩ አህዛብም ደግሞ ናቸው።
በክርስቶስ ኢየሱስ ህያው ደም የተዋጁ እነዚህ ልጆች በእግዚአብሔር የተወደዱና ቅዱሳን ሊሆኑ የተጠሩ አህዛብና አይሁድን ጨምሮ የዳኑ ወገኖች ሲሆኑ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ከጸኑ በአለም ላይ ከሚሆነው ቁጣ የተጠበቅቁ ይሆናሉ።
ወንጌል የዳኑ የእግዚአብሄር ህዝብ በእርሱ ላይ ተተክለው ይጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታን የሚያካፍል ጸጋ ይሰጣል፤ ጸጋው በብርሃን እየተመላለሱ የምስራቹን የሚያውጁ አገልጋዮችንም በቃል ብርታት ያስታጥቃል።
በአህዛብ ዘንድ ያለ ልማድ ግን በሰይጣናዊ አሰራር የሰለጠነና የተቀረጸ በመሆኑ ያለ ወንጌል እውቀት በክርስቶስ የሆንውን የጽድቅ ልምምድ መቀበል አይችልም፦
ኤፌ2:1-9 “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን የሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።”
ከአህዛብ ልማድ ነጥቆ የሚያወጣው የርሱ ጸጋ በህይወታችን ብዙ ስራ ይሰራል፦ በዋናነት ማንነታችን ላይ የሰለጠነውን የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ በመግረዝ በዚህ ዓለም ካለው ኑሮ ያቆራርጠናል፤ ልባችን ከተሸነፈበትና ባሪያ ከሆነለት የሥጋችን ምኞትም ነጻ አውጥቶ በፊት እንኖርበት የነበረውን ህይወት ያስወግደዋል። ያን ህይወት ጌታ በነርሱ አገልግሎት በኩል እንዲፈጥር ምጥ እንደነበረው ሃዋርያው ሳይገልጽ አላለፈም፣ ያን እንዲህ ይለዋል፦
“ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ዕዳ አለብኝ፤ ስለዚህም በሚቻለኝ መጠን በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቼአለሁ። በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና።” (ሮሜ.1:14-16)
የወንጌል ሃይል ባልዳኑት ብቻ ሳይሆን በዳኑትም ላይ የመስራት ጉልበት ያለው የእግዚአብሄር ቃል ነው። እርሱ ለማዳን አስቀድሞ በጌታ የተሰበከ፣ኁዋላም በሃዋርያትና በየዘመኑ በሚነሱ የቃሉ አገልጋዮች የሚሰበክ የእግዚአብሄር ሃይል ያለበት የደህነንት ምስራች ነው።
1ቆሮ.1:2-9 “በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። በክርስቶስ ኢየሱስ ስላመናችሁ በተሰጣችሁ በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ሁልጊዜ ስለ እናንተ አምላክን አመሰግናለሁ፤ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደ ጸና፥ በነገር ሁሉ በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና። እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤ እርሱም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል። ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።”
በሃዋርያቶች የተሰበከ ወንጌል በቅዱሳን ህይወት ላይ ስለጸና የወንጌሉ ጉልበት አማኞችን በነገር ሁሉ በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ አድርጎአል። ቃሉ እንደሚያመለክተው በወንጌል በኩል በቃልና በእውቀት ባለጠጋ የተደረጉ አማኞች ባለመናወጥና ያለአንዳች የጸጋ ስጦታ መጉዋደል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ የሚጠባበቁ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ በወንጌል በተገለጠ ጸጋ የተጠበቁ ቅዱሳን በነርሱ ያለ የእግዚአብሔር ጽድቅ በላያቸው ሰልጥኖና ልባቸውን ገዝቶ ከእምነት ወደ እምነት እየበረቱ እንዲሄዱ ያደርጋል። ጌታ ኢየሱስ በሰጠው ህይወት ውስጥ የተገለጠ መንፈስ እየመራም ለእግዚአብሄር ወደ ሆነው መንፈሳዊ ከፍታ ያሳድጋል፤ ከፍታውም በእምነት የሚገለጥ፣ በስራውም በቅዱሳን ላይ የእምነት እንቅስቃሴን የሚፈጥር በመሆኑ በየወቅቱ እምነትን የሚያሳድግ ነው።
ብዙ የአህዛብ ሃይማኖቶች መምህራን እነርሱ የሚያስተምሩት ወይም የሚሰብኩት ስብከት ሃይል ኖሮት ሰዎችን የሚጠራና የሚያድን አድርገው ስለሚያምኑ ሰዎች አይታነጹበትም አይጸኑበትምም፤ እንደ ሃዋርያት በሆነ እምነት ያለ የቃሉ አገልጋይ ዘንድ ሊኖር የሚገባ ትምህርት ግን በተሰበከው የእውነት ወንጌል አማካይነት ጌታ ከነርሱ ጋር ተገኝቶ ትምህርታቸውን በሚከተላቸው ስራ ያጸና ነበር። ወንጌልም የጌታ እጅ በምስራቹ በኩል ተገልጣ እንደምትሰራ አብሳሪ ነበር (ማቴ.9:20-35)፦
• እነሆም፥ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ በልብዋ፡- ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ፥ እድናለሁ ትል ነበረችና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና፡- ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች።
• ኢየሱስም ወደ መኰንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፡- ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ አላቸው። በጣምም ሳቁበት። ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፥ ብላቴናይቱም ተነሣች። ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ።
• ኢየሱስም ከዚያ ሲያልፍ ሁለት ዕውሮች፡- የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረን ብለው እየጮሁ ተከተሉት። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፥ ኢየሱስም፡- ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን? አላቸው። አዎን፥ ጌታ ሆይ አሉት። በዚያን ጊዜ፡- እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ። ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ።
• እነርሱም ሲወጡ እነሆ፥ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ጋኔኑንም ካወጣው በኋላ ዲዳው ተናገረ። ሕዝቡም፡- እንዲህ ያለ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልታየም እያሉ ተደነቁ።
ኢየሱስ ደም ይፈሳት የነበረችውን ፈወሳት፣ የሞተችውን ብላቴና አስነሳት፣ ሁለት እውሮች የነበሩትን ሰዎች ፈወሰ፣ ጋኔን ያደረበትን ዲዳም አዳነ፣ በዚያ ሁሉ የእግዚአብሄር ስራ መሃል የነበሩ ፈሪሳውያን ግን፡- በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል አሉ። ኢየሱስ ግን ለክሳቸው ቦታ ሳይሰጥ በከንቱ ክርክራቸው ሳይጠመድም አለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእግዚአብሄር ዘንድ የነበረውን ፈቃድ እየገለጠ፣ በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር። ዛሬ እንዲሁም እስከ አለም ፍጻሜ ድረስም ሰውን ከሃጢያት ነጻ ሊያወጣ የሚችለውንና ከተለያዩ እንቅፋቶች አድኖ ለዘላለም ክብር የሚያደርሰውን ወንጌል እየተከተለ ጌታ በሚመከተሉት ምስክሮች ያጸናው እርሱ ነው፦
ዕብ.2:1-3 “ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል። በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን?ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፥”
ወንጌሉ ግን አምነው እርሱን እንከተላለን ከሚሉት ዘንድ ሳይቀር ተግዳሮት ይገጥመዋል፦
በሮሜ.1:18 ላይ የሚታዩ አማኞች እውነትን በዓመፃ የሚከለክሉ ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ እንደሚገለጥባቸው ቃሉ ያስጠነቅቃል፤ እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና ምክኒያት የላቸውም። በወንጌል የተቀበሉት እውቀት ስለእግዚአብሄር ማንነት የተረከላቸው እውነት የነበረ ቢሆንም በዚያ አምነውና ረክተው መቀመጥ ስላልቻሉ በላያቸው ፍርድ እንደጋበዙ በግልጽ ይታያል።
እግዚአብሄር መንፈስ በመሆኑ ባህሪዎቹ የማይታይ መሆኑን ይገልጻሉ፤ የዘላለም ኃይሉና አምላክነቱ መታየት፣ መዳሰስ ወይም መቀረጽ የማይችሉ ሲሆኑ በእጁ የሰራቸው ፍጥረታት ግን ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ እነዚህን ባህሪዎች ግልጥ ሆነው እንዲታዩ አድርገዋል፤ ስለዚህም እነዚህ በወንጌል የተገለጠውን እውነት አስተውለው ስላላወቁና እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩት፣ ስላላመሰገኑትም የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በክህደታቸው ምክኒያት ተባርከው ገንዘቡ ከመሆን ይልቅ በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ።
ክህደት ሞኝ ስለሚያደርግ ሰይጣን አማኞች እንዲዳፈሩና እንዲጠፉ ያደርግ ዘንድ ውስጣቸውን ያደነድናል፣ አደንቁሮና እንዳያስተውሉ አድርጎ ሳለ ጥበበኞች ነን ብለው ለራሳቸው ማረጋገጫ እንዲሰጡ ያደርጋል። የመንፈሱ ተቃውሞ አይሎ ሲገዛም ሰዎች የማይጠፋውን የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው እንዲለውጡ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ በዚህ አሰራር የተጠቁ ሰዎች እግዚአብሄር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ሁሉ ፈጣሪ፣ ሰማይ ዙፋኑ ምድርም የእግሩ መርገጫ የሆነች ታላቅ ጌታ ሆኖ ሳለ ከነርሱ ልቦና ውስጥ መታሰቢያው ፈዝዞ ያንስባቸዋል፣ በልባቸውም በሚነግስ ባእድ እውቀት ምክኒያት ፈጣሪን በሚንቀሳቀሱ ፍጥረታት ምስል እንዲመስሉት ራሳቸውን ለዚህ እውቀት አሳልፈው ይሰጡታል። ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው። በወንጌል ላይ መነሳት ጥፋቱ በዚያ አያቆምም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ስለሚሰጣቸው እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን የሚያዋርዱ ይሆናል። እንዲሁም ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ የሚሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው የሚለውጡ ይሆናል፤እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ይቃጠላሉ፤ በመጨረሻም ወንዶች በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ይቀበላሉ።
ይህ ሁሉ ለምን እንደሆነ ስናጠና፦
• እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ስለሰጣቸው፤
• ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ስለተሞሉ፤
• የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ በመሆናቸው ነው።
1ጢሞ.6:11 እንደሚል፦
“አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል።”