የማይፈሩ ልቦች

የመጨረሻ ዘመን

መንፈሳውያን በእምነት ተመርኩዘው በጽድቅ የሚደፍሩት ድፍረት አለ፡፡ በአምላካቸው ፊት ትሁትና የተገዙ ሆነው ይኖራሉ፤ በእርሱ ላይ ጠንካራ እምነት አላቸው፤ ልባቸው በቃሉ ላይ ሙሉ በመሆኑ ስለቃሉ ድፍረት አላቸው፣ነገር ግን አምላካቸውን የሚፈሩ ናቸው፡፡
በእግዚአብሄር የሚተማመኑ ሰዎች አያፍሩም፤ ”አልፈራም እግዚአብሄር ይረዳኛል” ይላሉ፡፡የታመኑት አምላክ ፈጽሞ ፊት እንደማይነሳቸው እጅግ ስለሚተማመኑ ሞት ፊት እንኩዋን ቢቆሙ በልበ-ሙሉነት አምላካቸውን ይጠራሉ፣ ለዚህ እነ ዳንኤልን ምስክር መጥራት በቂ ነው፡፡ ቃሉ ”የሰው ነፍስ ከአፉ ፍሬ መልካም ነገርን ትጠግባለች” ስለሚል እነርሱም እንዳመኑት ልክ መልካም ነገር ሆኖላቸው ነበር፡፡ እግዚአብሄር በስጋ ደፋሮችን ሳይሆን በርሱ ላይ በእምነት በሚጉዋደዱት ሁሌ ይደሰታል፡፡ የሚፈሩት እነዚህ ልቦች ድፍረታቸው በእምነት ይሁን እንጂ በፊቱ ትህትናን የተሞሉ ናቸው፡፡ ድፍረትና ቅንአት በመንፈስ ሲሆኑ የእግዚአብሄርን ስራ ይሰራሉ፡፡ ሁሌም ግን የስጋ ነገር ጣልቃ እንዳይገባ ጥንቃቄ መኖር አለበት፡፡ በዚህ አካባቢ የተመጣጠነ እውቀት ሊኖር ግድ ነው፡- እምነት በእግዚአብሄር ቃል እውቀት ሲደገፍ ተገቢ ነው፣ የህሊና ቁጥጥር አጥቶ ማስተዋልን የተነጠቀ ከሆነ ግን እምነት መሪ እንደሌለው መርከብ ባሻው መንገድ የሚሄድና የሚጠፋ ነው፡፡
• የማይፈራ ግን የተሰበረ ልብ ምን አይነት ልብ ነው? ደፋር እንዴት ልቡ ይሰበራል?
ይህ ሰው በእግዚአብሄር ፊት ትህትናን ይዞ የሚመላለስ ሲሆን እግዚአብሄር በነገረው፣ ባመለከተውና ባዘዘው ነገር ግን ስለሚታመን ድፍረት አለው፤ ያኔ እግዚአብሄር የነገረውን ሊናገር ይደፍራል፣ እግዚአብሄር አድርግ ሲለው ያለውን ሲያደርግ ያለማቅማማት ሳይፈራ ያደርጋል፡፡ በእግዚአብሄር ፊት የሚፈለገውም ይህ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ይዘህ በእግዚአብሄር ፈቃድ ጉዳይ ደፋር፣ የራስህንና የአለምን ጉዳይ አንስተህ ከሆነ በፊቱ ትሁትና ቁጡብ ሁን ማለት ነው፡፡
ኤር.1:4-7 ”የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ። እኔም፡- ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም አልሁ። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ። ወደምሰድድህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና። ብላቴና ነኝ አትበል።”
ኤርሚያስ በእግዚአብሄር የተለየ ቢሆንም ለማገልገል እጅግ ፈርቶ ነበር፡፡ እግዚአብሄርን መፍራት እንጂ በስራው ብርቱና ድፍረት የተሞላ ሊሆን ተገቢ ስለነበር እግዚአብሄር ሲያበረታው ነበር፡፡
1ዜና.17:24-25 ”የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እርሱ የእስራኤል አምላክ ነው፥ በእውነት የእስራኤል አምላክ ነው ይባል ዘንድ ስምህ ለዘላለም ጽኑና ታላቅ ይሁን፤ የባሪያህም የዳዊት ቤት በፊትህ ጸንቶአል። አምላኬ ሆይ፥ ቤት እንድሠራለት ለባሪያህ ገልጠሃልና ስለዚህ ባሪያህ ወዳንተ ይጸልይ ዘንድ በልቡ ደፈረ።”
ዳዊት ሊያደርግ የደፈረው እግዚአብሄር ይሁንታ የሰጠውን ነገር ብቻ እንደነበር ቃሉ ያመለክተናል፡፡ እግዚአብሄር ባልተናገረው ነገር ላይ መንቀሳቀስ እርሱ አመጽ ያሰኛል፡፡
1ዜና.16:7-11፤ ”በዚያም ቀን ዳዊት በአሳፍና በወንድሞቹ እጅ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ ትእዛዝን ሰጠ። እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙን ጥሩ፤ ለአሕዛብ ሥራውን አውሩ። ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፤ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ። በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው። እግዚአብሔርን ፈልጉት፥ ትጸናላችሁም፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ” አለ፡፡
እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ይጸናሉ/ልባቸው አይፈራም፡፡ ሁልጊዜ ፊቱን ይፈልጋሉ ያገኙታልም። የልብ ደስታ የተቁዋጠረው እግዘአብሄርን በመምረጥና በመፈለግ ላይ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ላይ ያረፉ ልቦች ማመስገን ይችላሉ፣ ስሙን ይጠራሉ እርሱም ይመልስላቸዋል፡፡ መቀኘት፣መዘመርና በህይወታቸው ያደረገውን ታምራት መናገር የሚችሉት ልባቸው በእርሱ ስላረፈ ነው፡፡
• የማይፈራ መንፈሰ- ጠንካራ ልብ
ይህን ልብ እንፍራ፣ እሱ ልበ-ደንዳና ነው፣ አደገኛ ልብ ነው፡፡ ከዚህ ልብ ትእቢት ይወጣል፣ ዞሮ ዞሮ ጥፋት ላይ ሰውን የሚጥል ነውና ያስፈራል፡-
ዘዳ.9:6-8 ”እንግዲህ አንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነህና አምላክህ እግዚአብሔር ይህችን መልካም ምድር ርስት አድርጎ የሰጠህ ስለ ጽድቅህ እንዳይደለ እወቅ። አምላክህን እግዚአብሔርን በምድረ በዳ እንዳስቈጣኸው፤ ከግብፅ አገር ከወጣህበት ቀን ጀምሮ ወደዚህ ስፍራ እስከ መጣችሁ ድረስ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ አስብ፥ አትርሳ። በኮሬብ ደግሞ እግዚአብሔርን አስቈጣችሁ፤ እግዚአብሔርም ሊያጠፋችሁ ተቈጣባችሁ።”
ከግብጽ በትር፣ ስቃይና ክፋት በእግዚአብሄር እጅ ነጻነትን ያገኙ እስራኤላውያን የመረጣቸውን አምላክ ስለተዉ የተፈቱ እስኪያደርጋቸው ድረስ በትር አነሳባቸው፡- የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን እንደ በደሉ እንደ አባቶቻቸው አንገተ ደንዳና ሆኑ፤ እጃቸውን ለእግዚአብሔር እንዲሰጡ ቢመከሩ አልሰሙም፥ ለዘላለም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱ እንዲገቡም የመከራቸውን አልሰሙም፥ እንዲሁም ጽኑ ቍጣውን እንዲመለስ አምላካቸውንም እንዲያመልኩ የነገራቸውን ልብ አላሉም።
2ዜና.30:9 ”…አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነውና፥ ወደ እርሱም ብትመለሱ ፊቱን ከእናንተ አያዞርምና ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኩአቸው ፊት ምሕረትን ያገኛሉ፥ ደግሞም ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ።” ሲል የመከራቸውን ቸል አሉ፣ጥፋትም ተከተላቸው፡፡
ኢዮ.15:20-26 ”ክፉ ሰው ዕድሜውን ሙሉ፥ ከግፈኛ በተመደቡለት በዓመታት ሁሉ በሕመም ይጣጣራል። የሚያስደነግጥ ድምፅ በጆሮው ነው፤ በደኅንነቱም ሳለ ቀማኛ ይመጣበታል። ከጨለማ ተመልሶ እንዲወጣ አያምንም፥ ሰይፍም ይሸምቅበታል። ተቅበዝብዞም፡- ወዴት አለ? እያለ እንጀራ ይለምናል፤ የጨለማ ቀን እንደ ቀረበበት ያውቃል። መከራና ጭንቀት ያስፈራሩታል፤ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ንጉሥ ያሸንፉታል፤እጁን በእግዚአብሔር ላይ ዘርግቶአልና፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ ላይ ደፍሮአልና፥በደንዳና አንገቱና በወፍራሙ በጋሻው ጕብጕብ እየሠገገ ይመጣበታልና”
• የልብ ልእልና -ንጹህና ፍጹም ልብ ማግኘት
ትሁት ልብ ለእግዚአብሄር ቃል የተገዛ ነው፣ ቃሉን የሚያከብር ነው፣ እግዚአብሄርን የሚፈራ ነው፣ በአምላኩ ምህረትም ድፍረት አለው፡፡ ጉዳዩ ያለው ፍጹምነት ላይ አይደለም (በራሱ እንዲያ ሊሆን የሚችል ማን ይሆን?) ይልቅ እግዚአብሄር እንዲለውጠው፣ እንዲሰራውና ፍጹም እንዲያደርገው ተዋርዶ በፊቱ ይቀርባል እንጂ፡፡
ሕዝ.11:19-20 ”በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ እሰጣለሁ፥ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።”
እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብ፣ ድፍን ያለ ለሰውም ቢሆን አስቸጋሪ ነው፡፡ ፈጣሪውን ሊያውቅ ስለማይችል እርሱን ሊቀርብ ያዳግተዋል፣ የትእቢት ድፍረት ያጠቃዋል፤ እርሱ ቢረዳው፣ ቢያቀርበውና እንደቃል ኪዳኑ በተለወጠ ልብ ቢገኝ ግን ያን ልእልና ይቀበላል፡፡
የስጋ ልብ ሰዎች ከእግዚአብሄር ጋር ተስማምተው ሲሄዱ የሚቀበሉት ልብ ነው፡፡ በእግዚአብሄር የተቃኘና አምላኩ አዲስ አድርጎ የፈጠረው ስለሆነ ከአምላኩ ጋር ተስማምቶ መኖር የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሄር ዳዊትን እንደልቤ ብሎ የተናገረለት ሰው ነበር፡፡ እርሱም እንዲህ ይላል፡-
መዝ.51:10-14 ”አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፥ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ። ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፥ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ። የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከደም አድነኝ፥ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች።”
• ንጹህ ልብ (በመንፈስ መቀደስና በቃሉ ሃይል በመንጻት ይፈጠራል)
የልብ መንጻት በእግዚአብሄር እንድንደገፍና እንድንታመን የሚያደርግ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል/ መንፈስ ማንጻትና መቀደስ የሚችል ሀይል አለው፡፡ ከጌታ ኢየሱስ ጋር በእምነት ደፍረው የተጉዋዙት ሃዋርያት በጌታ ቃል የነጹ በመንፈሱም የተቀደሱ ነበሩ፡፡ በአንድ አጋጣሚ ያን እንዲያስተውሉ የተናገረው ቃል ነበረ፡-
ዮሐ.6:61-64 ”… ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ አላቸው፡- ይህ ያሰናክላችኋልን? እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል? ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው። ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ።” ብሎአል፡፡
• ፍጹም ልብ (በአንድ አምላክ ብቻ በማመን ይፈጠራል)
እግዚአብሄር የህዝቡ ድፍረት ሆኖ ማንም ሊቁዋቁዋም እንዳይችላቸው ያደረገው በፍጹም ልባቸው በተከተሉት ጊዜ ነበር፡፡ ከርሱ ተመልሰው ባፈገፈጉ ወቅት ግን የእግዚአብሄር ሞገስ ከነርሱ ርቆ ስለነበር እጅግ ፈሪዎችና የተጠቁ ነበሩ፡፡ በቃል ኪዳኑ ሲባርካቸው እንዲህ ብሎአል፡-
ዘዳ.28:1-9 ”እንዲህም ይሆናል፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ ብትጠብቅም አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል። የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል፤ ያገኙህማል። አንተ በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ። የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ቡሩክ ይሆናል። እንቅብህና ቡሃቃህ ቡሩክ ይሆናል። አንተም በመግባትህ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ቡሩክ ትሆናለህ። እግዚአብሔርም በላይህ የሚቆሙትን ጠላቶችህን በፊትህ የተመቱ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ መንገድ ይመጡብሃል፥ በሰባትም መንገድ ከፊትህ ይሸሻሉ።…”
ለእግዚአብሄር ፍጹም የሆነ ልብ ለርሱ ብቻ የተቀደሰ ልብ ነው፡፡ በቃሉና በመንፈሱ በሚቀደስ ሰው የሚገኝ ልብ ነው፡፡ ይህ ልብ ከአብረሃም አምላክ ሌላ አያምንም ፣ አይከተልም፡፡ ዙፋኑን ሲያስብ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን እርሱን ብቻ ያምናል፡፡ አባቶቹን ሲያስብ እነርሱን ከግብጽ ባርነት ለብቻው እንዳዳነ ያምናል፡፡ ሌላ አምላክ እንደሌለ ከአንዱ በስተቀር አምላክ የሚባል በሰማይም ሆነ በምድር እንደሌለ አጥብቆ ያምናል፣ በዚህ እውቀት ድፍረት አለው፡፡ እግዚአብሄርም እንዲህ ሲል ማረጋገጫ አትሞለታልና፡-
ዘዳ.4:35-40 ”እግዚአብሔርም አምላክ እንደ ሆነ ታውቅ ዘንድ ይህ ለአንተ ተገለጠ፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም። ያስተምርህ ዘንድ ከሰማይ ድምፁን አሰማህ፤ በምድርም ላይ ታላቁን እሳት አሳየህ፤ ከእሳትም ውስጥ ቃሉን ሰማህ። አባቶችህን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ የጸኑትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊትህ እንዲያወጣ፥ አንተንም እንዲያገባህ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ እንዲሰጥህ፥ ከአንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብፅ አወጣህ። እንግዲህ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቅ፥ በልብህም ያዝ። ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆን ዘንድ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዝህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቅ።”
• ሌሎች ደግሞ ደፋሮች ሆነው እግዚአብሄርን አይፈሩም
እግዚአብሄርን ስለማያውቁ ያልያም እያወቁ ስለሚዳፈሩ ጥፋት ውስጥ ይገባሉ፤ እነርሱን እግዚአብሄር ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡ ባለማወቅ ላደረጉት ግን ይራራል፤ ሀዋርያው ”ባለማወቅ ስላደረግኩት ነገር ምህረትን ተቀበልኩ” አለ፡፡
1ሳሙ.2:3-7 ”አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል። ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፤ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል፤ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች። እግዚአብሔር ይገድላል ያድናልም፤ ወደ ሲኦል ያወርዳል፥ ያወጣል። እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል፥ ባለጠጋም ያደርጋል፤ ያዋርዳል፥ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል።”
ልበ-ቅኖች በእግዚአብሄር ላይ ባላቸው ትምክህት በእምነት ልባቸው ሲበረታ አመጸኞች ግን በልብ ኩራት ይታበያሉ፣ የትእቢትን ነገር ይናገራሉ ያደርጋሉም፡፡ ሁኔታ ያመቸ በመሰለ ሰአት ብንታበይና በኩራት ብንናገርም የማይመች ጊዜ ሲተካ ጥልቅ ማፈር ይሆናል፡፡ ሀና እግዚአብሔር አዋቂ እንደሆነና ሥራችንን እንደሚመዝን ስላስተዋለች ተዉ አለች፡፡ ኃያላን የመሰሉ ቆይቶም ቀስታቸው ተሰብሮአል፥ ደካሞች የመሰሉም በእርሱ ጊዜ ኃይል ታጥቀዋል።
• የማይፈሩ ግን ኩሩ ልቦች
መዝ.2:10-12 ”አሁንም እናንት ነገሥታት፥ ልብ አድርጉ፤ እናንት የምድር ፈራጆችም፥ ተገሠጹ። ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፥ ቍጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው።”
በዚህ አለም ላይ የምናገኘው ደስታ የቱንም ያህል ከፍ ይበል አስተማማኝ ሊሆን አይችልም፡፡ የትኛውም ምድራዊ ነገር የሚጸና አይደለም፡፡ እግዚእብሄርን በመፍራት ምክኒያት የሚገኝ ምህረት ይዞት በሚመጣው በጎነት ግን ዘላቂ ሰላም፣ በረከትና ደስታ ይፈጠራል፡፡ በኩራት እግዚአብሄር ላይ የታበዩ ፈጥነውም ሆነ ዘግይተው ወደ ሀዘን መግባታቸው አይቀርም፤ እግዚአብሄር ትእቢተኞችን ይቃወማልና፡፡
ምሳ.4:23-27 ”አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና። የአፍህን ጠማማነት ከአንተ አውጣ፥ ሐሰተኞቹን ከንፈሮችም ከአንተ አርቅ። ዓይኖችህ አቅንተው ይዩ፥ ሽፋሽፍቶችህም በቀጥታ ይመልከቱ። የእግርህን መንገድ አቅና፥ አካሄድህም ሁሉ ይጽና። ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፤ እግርህንም ከክፉ መልስ።”
ኩሩና ትእቢት የተሞላ ልብ የማያበላሸው ነገር በእኛ ላይ የለም፡- አፈ ጠማማ ያደርጋል፣ ሀሰተኛ ከንፈር ይፈጥራል፣ ዓይኖቻችን ወደ በጎ ነገር የማያተኩሩ ይሆናሉ፣ እግሮቻችን ወደ መልካም መሄድ ይሳናቸዋል፣ ወዘተ፡፡
• የማይፈሩ ግን በድፍረት ተላላፊ ልቦች
የድፍረት መዘዝ የገባው ንጉስ በትህትና ይለምናል፡-
መዝ.19:12-14 ”ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ። አቤቱ፥ ረድኤቴ መድኃኒቴም፥ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን።”
ንጉሱ ድፍረት ማሰብም መናገርም እጅግ መዘዘኛ እንደሆነ የገባው ስለነበር የሚያስበውም የሚናገረውም ሞገስ እንዲያገኝ አምላኩን ተማጽኖአል፡፡
እንደ ንጉስ ዳዊት ያሉ በእግዚአብሄር የተወደዱ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ትህትና የራቃቸው ማንነቶችም ሞልተዋል፡፡ ምድር በተለያዩ ሰዎች የታጨቀች ስፍራ ነች፡፡ ሰዎች እንደብዛታችን ያለን ባህሪ ይለያያል፡፡ እግዚአብሄር መኖሩን እንኩዋን የሚጠራጠሩ ሰዎች ከምድር ላይ አልጠፉም፤ እነርሱ የሚሆነውን ነገር በሙሉ ከሰዋዊ ጉዳይ ጋር አያይዘው የነገሮችን ምንጭ ጌታ ይዘነጉታል፡፡ በዚህ አሳባቸው የፈጠራቸውን ይበድላሉ፡፡ ከነርሱ ይልቅ ታላቅ አጥፊዎች ደግሞ አሉ፣ እግዚአብሄርን የሚጠሩ በስራቸው ግን የሚክዱት፣ እነዚህ ክፉና ደፋሮች ስለሆኑ አምላካቸውን አይፈሩም፡፡ ስለታገሰ የረሳ፣ ስለጠበቃቸው የማራቸው ይመስላቸዋል፡፡ እነዚህ እግዚአብሄርን የማይፈሩ፣ እንደመሰላቸው የሚናገሩ የሚያደርጉ ቢሆኑም ጊዜያቸው በደረሰ ጊዜ ከፍተኛ ቀወስ ሊያገኛቸው ይችላል፡፡
”በዓለት ንቃቃት ውስጥ የምትቀመጥ፥ የተራራውን ከፍታ የምትይዝ ሆይ፥ ድፍረትህና የልብህ ኵራት አታልለውሃል። ቤትህን ምንም እንደ ንስር ከፍ ብታደርግ፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።” (ኤር.49:16)
• የሚፈሩ ግን የማያስተውሉ ልቦች
ምክኒያታዊ ያልሆነ ፍርሀት ጽድቅ ወይም መንፈሳዊ አይደለም፡፡ አሳባቸውን የማያምኑ፣ጥላቸውን የሚጠራጠሩ ቢኖሩ ይህ ህመም እንጂ የጤና አይደለም፡፡ ትክክለኛ ፍርሀት የፈጠረኝ አምላክ ያየኛል፣ ይሰማኛልም ስለዚህ በአካሄዴ ጥንቁቅ መሆን ይገባኛል የሚል ነው፡፡ በውስጥ በራስ ምክኒያት መበጥበጥና በፍርሀት መበርገግ ሲኖር ግን ከፈጣሪ ጋር የሚገናኝ እንዳልሆነ እንዲያውም የክፉው አሰራር ጥቃት እንደሆነ መጠርጠር ተገቢ ነው፡፡ በእምነት ማነስ ፍርሀት ውስጥ ላሉ ግን እግዚአብሄር የሚያበረታ ተስፋ ይሰጣቸዋል፡-
ኢሳ.35:3-4 ”የደከሙትን እጆች አበርቱ፥ የላሉትንም ጕልበቶች አጽኑ። ፈሪ ልብ ላላቸው፡- እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው።” ይላል፡፡
በመተላለፍ ምክኒያት ለሚጨነቀው ውስጣችን ትክክለኛው መፍትሄ ንሰሃ ስለሆነ ወደ አምላክ ቀርቦ ራስን በማሳየት ምህረትን መለመን ብቻ መፍትሄ አለው፡፡