የማንበቃበት ነገር፡- በእግዚአብሄር መገኛ አካባቢ ይዘን የምንመላለሰው ነገርና አካሄዳችን በማንነታችን የሚደነቃቀፍ ሲሆን፣ የምንመራበት የህይወት መርህ ደካማ ሆኖ ያለን የህይወት ይዘት የማይበቃ ሆኖ ሲቆጠር፣ የእግዚአብሄር ቃል የሚቃወመው የህይወት ይዘት ሲኖረን፣ መርሀችን የተተወ/መታሰቢያ የማይገኝለት መርህ ከሆነ ያም ከአለም ልማድ እንዳንወጣ ካነቀን፣ ከመንፈሳዊ የህይወት ደረጃ የተጣለ/በአለም ብቻ ተቀባይነት ያለው ቃሉ ግን የሚኮንነው ልማድ ካለን፣ የተወገደ/በእኛ ቁጥጥር ስር የሌለ ቀድሞ በጎ ነገራችን የነበረ አሁን ግን የተማረከብን ከሆነ፣ እንዲሁም በምኞት ብቻ ከእኛ ጋር ያለ በአካል ከእኛ የወጣ ነገር ባለቤት ከሆንን የእኛ ነገር ትርጉም የለሽና የማንበቃበትን ነገር የተሸከምን ሰዎች ነን ያሰኛል፡፡
በእግዚአብር ፊት የማንበቃ እንድንሆን የሚያደርጉን የራሳችን ድካሞች አሉ፡፡ በዚህ አንጻር ልናያቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች አሉ፡-
– የኛ የራሳችን ሀጢያት የእኛን ነፍስ የሚያዳክም ነው
ኤር.4:31 ”እንደምታምጥ የበኵርዋንም እንደምትወልድ ሴት ድምፅ ሰምቻለሁና፤ የጽዮን ሴት ልጅ ድምፅ በድካም ይሰልላል፥ እጆችዋንም ትዘረጋለችና። ተገድለው ከሞቱት የተነሣ ነፍሴ ዝላለችና ወዮልኝ! አለች።”
የጽዮን ልጆች አቅም አጥተዋልና ወደ አምላካቸው መቅረብ አልሆነላቸውም፤ ሀጢያት አሸንፎአቸው ከእግዚአብሄር ፊት ዞር ባሉበት ዘመን በሚያስደነግጥ ውድቀት ውስጥ ሆነው ሲጮሁ ይታያሉ፡፡ የጽዮን ልጆች አምላካቸውን መጥራት እስካይችሉ ድምጻቸው አልተሰማም፣ እጃቸውም ወደ እርሱ የመነሳት አቅም አልነበረውም፣ ፍጹም ደክመው ነበርና፡፡ ግን ለምን ያ ሆነባቸው? ዋናው ችግር/ማነቆ የሆነባቸው ሀጢያት ነበር፡- ሀጢያት ነፍስን ከእግዚአብሄር ሀይል ያግዳልና፣ እግዚአብሄርን ከሰው የሚያርቅ የሚያጣላም ነውና፡፡ ከእግዚአብሄር ስለተለዩ፣ ህጉንና ትእዛዙን ችላ ስላሉ፣ የራሳቸውን መንገድ ስለመረጡ እጅግ ደከሙ፤ ወደ አምላካቸው የመጠጋት አቅምም አልነበራቸውም ስለዚህ በከንቱ ጮሁ፡፡
በእርግጥ ሰው በራሱ አቅም ምንም አይነት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ሊያሳካ አይችልም፤ ስለዚህ እግዚአብሄር አቅም ካልሰጠው በራሱ ብቃት ስለማይኖረው ራሱን ከሀጢያት አርቆ ወደ እግዚአብሄር ሊቀርብ ግድ ይለዋል ፡፡ እግዚአብሄርን ያመነ ነገር ግን ከእርሱ በልቡ የራቀ ተጨንቆ እንደ እርጉዝ ቢያምጥም ድምጹ የማይሰማው መንገዱ በሀጢያት ስለተዘጋ ነው፡፡ ሀዋርያው ጳውሎስ ለአማኞች የሚያስተላልፈው ማሳሰቢያ በሀጢያት የሚደነቃቀፉ ሰዎችን ይመለከታል፡-
”ሁለተኛ በእናንተ ዘንድ በነበርሁ ጊዜ እንደ ተናገርሁ አሁንም ደግሞ በሩቅ ስሆን፥ ክርስቶስ በእኔ አድሮ እንዲናገር ማስረጃ ከፈለጋችሁ፥ እንደ ገና ብመጣ እንዳልራራላቸው አስቀድመው ኃጢአት ላደረጉት ለሌሎችም ሁሉ አስቀድሜ ብዬአለሁ፥ አስቀድሜም እላለሁ። ክርስቶስም ስለ እናንተ አይደክምም ነገር ግን በእናንተ ኃይለኛ ነው።” (2ቆሮ.13:2-3)
ሀዋርያው ጳውሎስ አስቀድሞ የሰጠውን ማሳሰቢያ ዳግም አንስቶ ማጠናከር ለምን እንዳስፈለገው ልብ ማለት ያሻል፤ በቅድሚያ ከሚያደክመንና ብቃትን ከሚነሳን ሀጢያት ለምን አልተላቀቅንም? ሁለተኛ ንሰሀ ገብተን ሀይል ከጌታ እንዴት አልተቀበልንም? ተመልካቾች ሀጢያት ባደጉት ላይ እርምጃ እንደወሰደ አይተው ጨካኝ ነው ብለው እንዲመለከቱት ሳይሆን እነሱን ለማዳን በመንገዳቸው ላይ የሚያም የመሰለ እርምጃ ሊወስድና ሊያተርፋቸው እንደቆረጠ ያሳያል፡፡ ታገሱና ተቀጡ፣ ንሰሀ ግቡ፣ እዘኑ፣ አልቅሱ፣ ወደ ጌታ ተጠጉ፣ እርሱ (ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ) የእናንተን ድካም አይቶ ተስፋ አይቆርጥባችሁም፣ በእናንተ ሊሰራና ያሸነፋችሁን አሸንፎ የምትበቁ ሊያደርጋችሁ ቻይ ነው፣ እናንተም ከፈቀዳችሁ በእናንተ የሚሰራ ኃይለኛ ጌታ ነው እያለ ነው።
ደካማ ሰዎች ሁላችን ሆይ! ሀይል የክርስቶስ ነው፣ ስለዚህ የእኛ ሃያል መሆን የሚወሰነው እርሱ በእኛ ሲያድር ነውና ኃጢአት አድርገን ድካም እንዳይይዘን በእግዚአብሄር ቃል የተቀመጠውን ማስጠንቀቂያ እንጠብቅ፡፡
በሮሜ.6:19-22 ውስጥ ሲናገር፡-
”ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ። የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና። እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና። አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው።”
የመንፈሳዊ ህይወት ድካም የአመጻ ብልቶቻችን ጎልተው እንዲወጡና በነፍሳችን ላይ እንዲሰለጥኑ ያደርጋል፡፡ የኃጢአት ባርነት ወደ መንፈሳዊ ሞት ያንደረድራል፣ ከጽድቅ ነፃ በፍርድም ባለ እዳ ደርጋል፤ ስለዚህ የንሰሀ ህይወት እስኪኖረንና ብልቶቻችን ተቀድሰው የአመጻ አካሄድ የሚሻርበት አሰራር እስኪገለጥ ድረስ ድካም በከፍተኛ ሁኔታ መንፈሳዊ ህይወታችንን እንደሚያሰልል መረዳት ተገቢ ነው፡፡ የሀጢያት ባርነት እስራትም ስለሆነ አንገታችንን ወደ እግዚአብሄር እንዳናቀና የሚደፍቅ ሀይል ነው፡፡ ይህን ባርነት በእግዚአብሄር መንፈስ ሀይል በመሻር ነጻ የምንወጣበትን መንገድ ስንፈልግ መንገዱ ከላይ በቃሉ እንደተመለከትነው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በሌላ በኩል ድካማችን እኛን ማሰናከል ብቻ ሳይሆን ለሌሎች እንቅፋት እንዳይሆንም ስጋት ነው፡፡
”ስለዚህ ጌታ ለማፍረስ ያይደለ ለማነጽ እንደ ሰጠኝ ሥልጣን፥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በቁርጥ እንዳልሠራ በሩቅ ሆኜ ይህን እጽፋለሁ።” (2ቆሮ.13:10)
ማንም በጽድቅ መስመር የሚሄድ ሰው ቢኖር የሌሎችን የህይወት መስመር እንዳያደናቅፍ፣ ግስጋሴን እንዳያሰናክል፣ ስራንም እንዳያፈርስ መጠንቀቅ እንዲገባው ሃዋርያው በራሱ ምሳሌ አድርጎ ሊያሳይ ይሞክራል፡፡ የሙሴ የራሱ ቤተሰቦች በማይመለከታቸው ነገር ውስጥ ገብተው እንቅፋት ሲሆኑበት ነበር፣ ያ ግን ጥቅም ሳይሆን ጉዳት ውስጥ የጣላቸው ውጤት ነበረው፣ መስመራቸውን ስተው ነበርና፡-
ዘኊ.12:1-2 ”ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ። እነርሱም፡- በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን? አሉ፤ እግዚአብሔርም ሰማ።”
– የኛ የራሳችን ሀጢያት የእርሱን ነፍስ አደከመ (ወደ ሞት እንዲወርድ አደረገ)
የእኛ ሀጢያት እኮ እኛን ብቻ አላደከመም፣ እግዚአብሄርንም ጭምር እንጂ፣ ሁለት ታላላቅ ቃላት ይህንን ይላሉ፡-
ኢሳ.7:13-14 ”እርሱም አለ፤- እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ፤ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።”
በመጀመሪያ ሀጢያታችን እኛኑ አድክሞን ከገነት (ከመልካሙ የእግዚአብሄር ጉብኝት ክልል) ወደ መከራ ምድር (አጋንንት ወደ ሰለጠኑበት ስፍራ) ወረወረን፤ ቀጥሎ እግዚአብሄር በደካማ ስጋ ተገልጦ ያድነን ዘንድ ከክብር ስፍራው ወደ ጨለማው አለም እንዲወርድ አስገደደው፤ አማኑኤል እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ሆነ፣ በእኛ መሀል አደረ፣ እኛን (የሀጢያት ባሪያዎችን) በመልክ መሰለ፣ እንዲህም እንደተባለ ፡-
2ቆሮ.5:19-21 ”እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።”
እንዲሁ ደግሞ ሀጠያታችን መለኮት በደካማ ስጋ እንዲገለጥ ብቻ ሳይሆን ስጋውም (ክርስቶስም) በሀጢተኞች በደልና መተላለፍ እንዲደክም የሞት ፍርድም እንዲቀበል አድርጎታል፡-
2ቆሮ.13:4 ”በድካም ተሰቅሎአልና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንደክማለንና፥ ነገር ግን ስለ እናንተ በሆነ በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን።”
ጌታ ኢየሱስ የሚያደክም ነገር በእርሱ ዘንድ ሳይኖር የእኛ ሸክም ግን አደከመው፣ ስለዚህ በድካም ተሰቅሎአል ነገር ግን እኛን ከድካም አውጥቶ በእግዚአብሄር ፊት ብቃት እንዲኖረን ያደርግ ዘንድ በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል፣ በእኛም እየኖረ በሀይል እንድንበረታ ያደርጋል።
– የማንበቃበትን እክል መሻር እንዴት ይቻላል?
ይህን መፍትሄ ለማሰብ ከላይ ያየናቸው ምክኒያቶች በቂ ናቸው፡፡ ሆኖም ማስጠንቀቂያ አለ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አጥብቀን እንድንመለከት የሚያደርግ፡-
ዕብ.6:7-9 ”ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት፥ ለሚያርሱአትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል፥ ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና፤ እሾህና ኵርንችትን ግን ብታወጣ፥ የተጣለች ናት ለመረገምም ትቀርባለች፥ መጨረሻዋም መቃጠል ነው። ስለ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ምንም እንኳ እንዲሁ ብንናገር፥ አብልጦ የሚሻለውና ለመዳን የሚሆነው እንዲሆንላችሁ ተረድተናል።”
ይህች መሬት ምን አይነት አፈር ይዛለች? በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ እየጠጣች ሳለ ለሚያርሱአት የምትጠቅምን አትክልት ልታበቅል ብቃት አላት ተብላ ተጠብቃ አልነበር? እርሱዋ ግን ያልተጠበቀውን እሾህና ኵርንችት አውጥታ የተጣለች ልትሆን በቃች፣ መጣልዋ ብቻ ሳይሆን ለንሰሀ በተሰጣት ጊዜ ካልተለወጠች ለመረገም ትቀርባለች፥ መጨረሻዋም መቃጠል ነው። እኛ ግን እንደ መሬትዋ ምሳሌ ከእግዚአብሄር የሚፈስሰውን የጸጋ መንፈስ እየጠጣን ጣፋጭ ፍሬ በማፍራት ፋንታ መራራ የሆነ ነገር እንዳናፈራ እየተጠነቀቅንና የማንበቃበትን እንቅፋት እያስወገድን አብልጦ የሚሻለውና ለመዳን የሚሆነው ነገር እንዲበዛልን መፈለግ ይገባናል።
መርምሩ እራሳችሁን
ፈትሹ እስቲ ራሳችሁን? ምንድነው እንዳትበቁ የሚያደርጋችሁ? የቆምነው በክርስቶስ ሀይማኖት ከሆነ እርግጠኛ ከእርሱ ጋር መሆናችንን በህይወታችን ይዘት ልክ ማረጋገጥ ስለሚገባ ለዚያ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለተሰጠ ሀይማኖት ብቁ መሆንን ዘወትር ራስን በመፈተሸ እናረጋግጥ፡፡
2ቆሮ.13:5-6 ”በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?እኛ ግን የማንበቃ እንዳይደለን ልታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ።”
ጌታ ኢየሱስ በቃሉና በመንፈሱ በእርግጥ በእኛ ዘንድ ከኖረ ብቃታችን እርሱ መሆኑን በእርግጥ መናገር እንችላለን፡፡ ሆኖም ህሊናችን በመንፈስ ቅዱስ ካልተመራና ካልዳኘን አደጋ ውስጥ ነን፤ የቃሉ ብርሀንም እየመራንና እያስተካከለን እንዲኖር ካልፈቀድን አሁንም አደጋ ውስጥ ነንና ቆም ብለን የተበላሸውን ነገራችንን ለይተን እናስተካክል፡፡
መፍትሄ አለ
ክፉ አታድርጉ፣ ድካማችሁን በርሱ በኩል ወደ ሌላው አታሳልፉ
መፈራረድ፣ መወነጃጀል፣ ይቅር አለመባባል፣ ሁከት፣ መለያየት፣ መኮብለል ተራበተራ ወንድሞችን እንዳይገፋ እርስ በርስ መጠባበቅና መተዛዘን እጅግ ተገቢ ነው፡፡
ሮሜ.14:13 ”እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ እርስ በርሳችን አንፈራረድ፤ ይልቁን ግን ለወንድም እንቅፋትን ወይም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖርበት ይህን ቍረጡ።”
ለሀጢያት በመሞትና ለጽድቅ በመኖር ክብሩን አሳዩ
ብቃታችን በጌታ ኢየሱስ ደም ተሸፍነን ወደ እግዚአብሄር መቅረብ እንዲሆንልን ክፋት የሚባልን የልብ ጨለማ አውጥተን ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ክፋት ነፍስን በሀጢያት ያመነችካል፤ ልብ በንሰሀ ወደ አምላክ እንዳይቀርብ ደረቅ ያደርጋል፤ እንዳንሰበርና በተዋረደ መንፈስ ወደ ጌታ እንዳንቀርብ እልሀኛ ሊያደርገን ስለሚችልም በጥንቃቄ ልንመለከተው ይገባል፡፡
2ቆሮ.13:7 ”ክፉ ነገርንም ከቶ እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ እኛ የምንበቃ ሆነን እንገለጥ ዘንድ አይደለም ነገር ግን እኛ ምንም እንደማንበቃ ብንሆን፥ እናንተ መልካሙን ታደርጉ ዘንድ ነው።”
እንዳንበቃ የሚያደርጉን ሀጢያቶችን መለየት
ከአለም ጋር የምንካፈለው ክፉ ልምምድ እውነተኛ ክርስቲያኖችን የሚያደናቅፍ መሆኑን ሀዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ አማኞች ያሳስባል፡፡ ክርስቲያኖች በአለማዊ ልማድ ጸንተው ከኖሩ መራራውን ፍሬ ስለሚያጭዱ ያ አማኞችን የሚያደክም እንቅፋት ነው፡፡
2ቆሮ.12:20 ”ስመጣ፥ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፤ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ”
በመጨረሻ፡- ባለመብቃት ጥፋት ይሆናልና እንጠንቀቅ
ዕብ.6:4-6 ”አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና።”