ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ በተባለበት አለም ውስጥ ስኖር ምን መስማት እንዳለብኝና እንደሌለብኝ ማስተዋል የለብኝምን? ለመንፈሳዊ ህይወቴ እንድጠነቀቅ የሚያሳስበኝ አምላክ የድምጾችን ምንጭና አቅጣጫ እንዲሁም ይዘትና ተጽእኖ ስለሚያውቅ ለእኔ ደካማ ሰው ጥንቃቄ ሲል ይህን ማሳሰቢያ አስተላልፎአልና፡፡
አለማችን ውስጥ የተለያየ መንፈስ ያላቸው ድምጾች ቢያንስ ቢያንስ በየሰከንዱ ይፈጠራሉ፤ ሰው ጆሮ የሚደርሱ፣ ተጽእኖ ያላቸውና የሰውን አስተሳሰብ ሊጫኑ የሚችሉ ድምጾችን እንደሰማሁ በግርድፉ ወደ ልቤ የማስገባ ከሆነ ህይወቴን እንደሚያናጉት ምንም ጥርጥር የለውም፡፡መንፈሳዊ ይሁኑ አይሁኑም ወይም አለማዊ ይሁኑ አይሁኑም፣ ብቻ አእምሮን የሚያናጉና ውሳኔን የሚጫኑ እስከሆነ ድረስ አደጋ አላቸው፡፡
ድምጽ (በሰው ልጆች ሊሰማና ሊተረጎም የሚችለው) በነፍስ ላይ ትልቅ ተጽእኖ አለው፡፡ በእለት ተእለት ገጠመኝ በጎ ነገር የሚያስተላልፍ ድምጽን እንደምንሰማ ሁሉ የጥፋት መልእክት የሆነ ድምጽም ወደ ጆሮአችን ይደርሳል፡፡ስለዚህ ወደ ውስጣችን የሚገባ በጎነት የሌለው ድምፅ ነፍሳችንን እያወከ ስሜታችን፣ አስተሳሰባችን ብሎም ማንነታችን ላይ ተጽእኖ ያደርጋል፤ ነገር ግን የምንሰማው መስማት የሚገባንን ነገር ሲሆንና በተገቢው የአሰማም ሁኔታ ላይ ሆነን የሰማነው ሲሆን ያለ ጉዳት የሚያቆም እንዲያውም ጠቃሚና የሚያንጽ ሆኖ አናገኘዋለን፡፡ ሰው ለአሰማም የተጠነቀቀና የተዘጋጀ ይሁን እንጂ ሁሉን እንደ አቀራረቡ ተቀብሎ ያለጉዳት ማስተናገድና መሸኘት ይቻላል፡፡
ህይወትን ከሚጫኑ ድምጾች ጋር በተያያዘ መተኮር ያለባቸው ዋና ዋና ነጥቦች አሉ፤ እነርሱን ቀጥሎ እንመልከት፡-
ድምጽ – ትርጉም ያለው፣ ስፍራ የሚያስለቅቅ፣ አስተሳሰብ የሚጫን፣ የሚያናውጥ ወይም የሚያጸና፣ ተጽእኖ ማሳደር የሚችል ወይም ለህይወታችን መልእክት ይዞ የሚመጣ ማንኛውም ቃል/ንግግር ነው፡፡
የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ – አስተውሎ የሚያደምጥ ለመዳን ብሎ በፈቃዱ ይስማ የሚለውን አሳብ ያሳያል፡፡
ለማን ብዬ ልስማ – እራሴን ለማዳን ስል ለራሴ ብዬ ልስማ፣ ሌሎችን አድን ዘንድም ስለሚባለው ነገር ተጠንቅቄ ልስማ፡፡
ምን ልስማ – ህይወት የሚገኝባቸውን ትምህርቶች ልስማ፡፡
ማንን ልስማ – የህይወት ቃል የሚናገሩ ድምጾችን ልስማ፡፡
እንዴት ልስማ – ለመዳን በተዘጋጀ መንፈስ፣ ቃሉን በማክበርና እግዚአብሄርን በመፍራት ልስማ፡፡
ከየት ልስማ – ከህያው ቃሉ ልስማ፡፡
ማንን አልስማ – ሀሰተኞችን፣ የሚክዱትን፣ የሚዘብቱትንም አልስማ፡፡
እነዚህ ከአሰማማችን ጋር የተያያዙ ሁኔዎች የመስማታችንን እጣ ፋንታና ውጤት የሚወስኑ ናቸው፡፡
የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ
የሚሰማ ጆሮ ድምጽን መለየት ይችል ዘንድ አስተውሎ የሚሰማ ነው፡፡ የሚሰማ ጆሮ ድምጽን መለየት ከሚችል ልቦና ጋር የተያያዘ ሲሆን ልቦናው ያለው ሰውም የጌታን ማስጠንቀቂያ ቸል ሳይል አምላኩን በንቃት መከታተል የሚችል ነው፤ ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ የዚህ አቅም ላላቸው ጆሮዎች የሚሰሙትን በጥንቃቄ እንዲያደርጉት ማስገንዘቢያው ይጣራል፡፡ የጌታ ማስጠንቀቂያ በኛ የማድመጥ አቅምና በሚሰማው የአለም ድምጽ መሃል የሚገባ እንዲሁም ሰዎች ከድምጹ ጋር የምንፈጥረውን የግንኙነት አቅጣጫ የሚያጠራ ነው፡፡ንግግሩ የእኛንም የመስማት አቅም ያውቃል፣ የምንሰማውንም የተጽእኖ ድምጽ ያውቃል፡፡ መስማት ላይ አጥርቶና ለይቶ ማድመጥ እንደሚቸግረን ስለሚያውቅም በአለም ላይ የሚነፍሱ ድምጾች እንዳይቆጣጠሩን በማስጠንቀቂያው ያሳስበናል፡፡
ጌታ ኢየሱስ እንድንሰማ የፈለገው ድምጽ አንድና አንድ ነው፣ እርሱም ቃሉ ነው፡፡ቃሉ ለምን ይሰማ? እርሱ ምክኒያቱን ሲናገር፡-
ዮሐ.12:47-48” ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀው ቢኖር የምፈርድበት እኔ አይደለሁም።
የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል።” ይላል፡፡
በዚህ ምክኒያት ጆሮ ከተከፈተ ለጌታ ቃል ሊከፈት፣ መሰማት ካለበት ቃሉ ሊሰማ ጠቃሚነቱም ለዘላለም ህይወት እንደሆነ በግልጽ ያስገነዝባል፡፡
ማቴ.4:22-25 ”እንዲገለጥ ባይሆን የተሰወረ የለምና፤ ወደ ግልጥ እንዲመጣ እንጂ የተሸሸገ የለም።የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ። አላቸውም፡- ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል።ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፥ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”
ከዚህ ጥቅስ ውስጥ ”የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” የሚለው ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ፈቃዱ ላይ ለተመሰረተው ሰው የአሰማሙን ሁኔታ እንዲቃኝ ያስገነዝባል፡፡ እምነት መልካም ነው፤ ማመን ግን አይን ጨፍኖ በስሜት በመነዳት መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ እምነት ጆሮ ካለው ሚዛናዊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ለመስማት የተስማሙትን ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ… እንዴት እንድትሰሙም ተጠበቁ ይላል፡፡ ጌታ ይህን የሚናገረው ለመንፈሳችን እንደሆነ ማስተዋል ይገባል፡፡ ልጆቹን የሚመራ አምላክ በአካሉ በቤተክርስቲያን ውስጥ ድምጹን ለማንቃት ይልካልና፡፡
ራእ.2:7 ”መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ።” አለ፡፡
ሆኖም የእግዚአብሄር መንፈስ የሚያመጣውን ቃል ካላስተዋልን መንፈሳዊው አለም ላይ ድል የለንም ማለት ነው፡፡ በሰማነው ቃል ምክኒያት መንፈሳዊውን አለም በእምነት መዳሰስና ማስተዋል በቻልን ጊዜ ግን ወደ እግዚአብሄር መጠጋት እንችላለን፡፡ የሚሰማ ጆሮ ለዛሬ ሲል ብቻ ሳይሆን ለዘላለሙ ህይወትም ሲል ይሰማል፣ የእግዚአብሄር ፈቃድ በአሰማማችን ላይ እንዲህ ነው፡፡
ማቴ.13:9-17 ”የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፡- ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም።ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ ነግራቸዋለሁ።መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም።”
ጌታ ኢየሱስ ሲናገር የነበረው አጅግ ብዙ ህዝብ ወደ እርሱ በተሰበሰበ ጊዜ ነበር፡፡ሲናገርም ሁሉ ይሰሙት ነበር፡፡ይሁን እንጂ በማስተዋል ያደምጥ የነበረው ክፍል እጅግ ጥቂቱ ነበር፡፡ ጉባኤው በአንድነት ሆኖ አንድ አይነት ድምጽ ቢሰማም በሞትና በህይወት መሀል እስኪከፈል ተለያይቶአል፡፡ ይህንን እውነታ ነው በዚህ ጥቅስ ውስ|ጥ የምናገኘው፤ ነገሩ ያስደንቃል ፣ያስፈራልም፡፡
ማቴ.13:2-3 ”እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር። በምሳሌም ብዙ ነገራቸው…”
የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ባለ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፡- ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት (የዘሪን ምሳሌ ነግሮአቸው ስለነበር)። እርሱም ሲመልስ ምሳሌ የምናገረው የመንግሥተ ሰማያት ምሥጢር እውቀት ስለተሰጣችሁ ሰምታችሁ ስለምታስተውሉ ነው፥ ለእነርሱ ግን እውቀቱ አልተሰጣቸውም አለ (የመቀበል ፈቃድ ላላሳዩ ጌታ የእውቀቱን በር አይከፍትም)። በዚህ ምክኒያት የመንግስቱ ምስጢር እውቀት ላለው ደግሞ ደጋግሞ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ የምስጢሩ እውቀት ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል አለ (ለአይሁድ ተስፋው ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ እንደተሰጣቸው እናውቃለን፣ ተስፋው በክርስቶስ ተፈጽሞ ያላስተዋሉ ግን ያላቸው ያ ተስፋ ሳይቀር እንደሚወሰድባቸው ጌታ አስጠንቅቆአቸዋል)። ደግሞም እውቀት የሌላቸው የማስተዋል ሀይል የላቸውምና የመንግስተ ሰማይን ነገር እያዩ እንኩዋን በመንፈሳቸው ማስተዋል አይችሉም፣ የመንግስቱን ምስጢር የማወቅ ሀይል በማጣታቸው የጌታን ድምጽ እየሰሙም፣ ስለማይሰሙም አያስተወሉም።ስለዚህ አስቀድሞ በነቢዩ ኢሳያስ ስለእነርሱ የተነገረው ቃል ሲፈጸምባቸው እንመለከታለን፡፡
ሕዝ.3:27፤ ”ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፥ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና አንተ፡- ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- የሚሰማ ይስማ፥ የማይሰማም አይስማ ትላቸዋለህ።”
ለመስማት መፍቀድ ከእግዚአብሄር ዘንድ የማስተዋል ችሎታ እንዲያመጣ በማወቅ እንደ ህጻኑ ሳሙኤል ባለንበት ሆነን ባሪያህ ይሰማልና ተናገር የሚል መሻት ማሳየት ያስፈልጋል፡፡የአብረሃም ዘር ለመስማት ባለመፍቀድ ዓመፀኛ ቤት ሆነው መገኘታቸው አስከፊ ፍርድ ውስጥ ጥሎአቸዋል፡፡
የመንግስተ ሰማያት ምስጢርን የማወቅ ጸጋ በአጋጣሚ የሚታደሉት አይደለም ወይም እግዚአብሄር በዘፈቀደ ሰው ላይ የሚጥለው፣ ያሊያም በአድሎ የሚሰጠው ችሮታ አይደለም፡፡ ምስጢሩ እንቁ የሚያገኘውም ሚሰማው እጣው ያማረለት ሰው ነው፡፡
ኤፌ3:8-10 ”ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ፥ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘላለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለኔ ተሰጠ፤ ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ፥”
መንፈስ ለአብያተ ክረስቲያናት ሲናገር ምስጢሩን ማስተዋል እንዲቻል ለመስማት መቅረብ፣ ድምጹ ወደየግላችን በመንፈስ እንዲመጣ መጠማት፣ የድምጹን አቅጣጫ መለየት፣ ድምጹ ሲመጣም በልብ ሰውሮ መያዝ በርሱ ላይ ተሞርኩዞ መኖርም ጭምር ያስፈልጋል፡፡ይህን በመጠማት በጸሎት መፈለግ ያሻል፡፡ ለህይወታችን ማደግ የሚያስፈልግ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ በቤተ ክርስቲያን በኩል ከሰማያዊ ስፍራ ሲመጣ መስማትና ማየት የሚችሉ የእግዚአብሄር ልጆች ይባረኩበታል፣ ያድጉበታል፣ ይለወጡበታል፣ ይኖሩበታል፡፡ ለዚህ አቀራረብ ያስፈልጋል፤ ጅማሬውም በማስተዋል ከመስማት ነው፡፡ በአለም ያሉ ጠቢባን ግን የእግዚአብሄርን መንግስት ምስጢር ለመፍታት ብዙውን የእድሜአቸውን ክፍል ይሰዋሉ፣ ብዙ ይጽፉበታል፣ ይናገሩታል (አግኝተውትና ተገልጦላቸው ባይሆንም)፡፡ ቢሆንም የቱንም ያህል ይሞክሩ ምስጢሩ ሊፈታ የሚችለው በቤተክርስቲያን በኩል ባለ መገለጥ ብቻ ነው! የህያው አምላክ የድምጹ ምንጭ በዚያ ስለሆነ፡፡
መዝ.103:15-22 ”… ቃሉን የምትፈጽሙ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ። ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ። ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ። ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ።”
ቃሉን የምትፈጽሙ… የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ… ፈቃዱን የምታደርጉ እርሱ አግዞአችሁዋልና እግዚአብሔርን ባርኩ።… ቃሉን መስማት እንድትችይ ለአንቺም የራራልሽ ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ። በቃሉ ድምጽ ውስጥ ያለውን መልእክት መስማት፣ ሰምቶም ማድረግ፣ አስተውሎ የማድረግ ሀይል የሰጠውን አምላክም መባረክ ከሚያስተውል የእግዚአብሄር ልጅ የሚጠበቅ ስርአት ነው፡፡
ኢሳ.66:1-2፤ ”እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው?እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።”
በእግዚአብሄር ለመሰማትና ለመታየት ልዩ ሰዋዊ እቅድና ብልሀት አይገባም፤ ያን የተከተሉ አልጸደቁም፤ አሳቡ በራሱ ከንቱ ድካም ነው፡፡ ድካሙ ግን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሰዎች በሁላችን ስላለ በእግዚአብሄር ፊት እያንዳንዳችን ጎዶሎ ሆነናል፡፡ ስለዚህ የርሱ ችሎታ በጣም ያስፈልገናል፣ አቀራረባችንን በማስተካከል ሊመለከተን ይገባል፡፡ ስለዚህ መስፈርቱን መጠቀም የፈለገ ቢኖር በፊቱ ትሑት ይሁን፣ ለአምላክነቱ የተሰበረ መንፈሱን ያቅርብ፣ ቃሉንም በመፍራት አመጽን ባራቀ መንፈስም ይጠጋው፣ ይጠብቀውም ከሚገምተው በላይ ሆኖ ያገኘዋል፡፡
ያዕ.1:19-24 ”ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።ቃሉን የሚሰማ ማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል።”
ጆሮው ተከፍቶ እየሰማ ያለ የእግዚአብሄር ልጅ ደግሞ መጠንቀቅ ያለበት ነገር አለው፡- ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ፣ ለቍጣም የዘገየ ሊሆን ይገባዋል እንደተባለ፡፡ ሰው ፈጣን ሰሚ ሳይሆን ፈጣን ተናጋሪ ቢሆን ስቶ ሰውን ያስቆጣል፣ ሰውን ቁጣ/ፈተና ውስጥ የሚከትም የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራም። ይልቅ የእግዚአብሄር ጽድቅ በህይወታችን አብቦ እንዲታይ የስጋ ስራን አስወግደን ነፍሳችንን ማዳን የሚችለውን በውስጣችንም የተተከለውን ቃል በየዋህነት በመታዘዝ እንቀበለው፤ ቃሉን በሰማነው ልክ የምናደርግ እንሁን እንጂ ራሳችን እንደሚመቸን እያጣጣፍነው እንዳንስት፣ ይህ አካሄድ የሚያጠፋን መሆኑ ግልጽ ነውና፡፡ ቃሉን የሚሰማ ግን የማያደርገው ሰው ቃሉ በውስጡ ስለማይተከል ሰምቶ የሚዘነጋ ነው፡፡ ሰምቶ ቃሉ በውስጡ የተተከለው ሰው ደግሞ የቃሉን ድምጽ በመንፈሱ እየሰማ ይደግበት፤ ያለበለዚያ የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት ያየ ዝንጉ ሰው ከመስታወቱ ዞር ሲል ያየውን ነገር እንደሚረሳ እግዚአብሄርን የሚከተለው እሱም እንደዚያ እንዳይሆን።
ነፍሳችንን ማዳን የሚችለው በውስጣችን የተተከለው ቃል ሲጮህ አስተውሎ የሚሰማ የመንፈስ ጆሮ ያስፈልገናል፣ መልካሙ ዜና ደግሞ ከፈለግነውና ከጠየቅነው እግዚአብሄር ያን ሊያበጀው ቃል ኪዳን ሰጥቶናል፣እንዳለውም ያደርገዋል፡-
”የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዓይንን፥ ሁለቱን እግዚአብሔር ፈጠራቸው” እንደተባለ (ምሳ.20:12 )፡፡