በእኛ ትውልድ መሀል የሚታዩና በየወቅቱ እየተገለጡ በማስጨንቅ ላይ ያሉ የመጨረሻ ዘመን ምልክቶች ብዙ ናቸው፡፡እያስጨነቁን ያሉ እንደ ረሀብ፣ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ የእውቅት በፈጣን ሁኔታ መጨመርና ክህደት መብዛት ከመቼውም ይልቅ ተፅእኖ እያደረጉብን ነው፡፡ የአየርና የውሀ ብክለት ከፍተኛ በመሆኑ ሰዎች በዚያ ይሞታሉ፣ በአየር የሚበሩ አእዋፋትና በውሀ ውስጥ የሚኖሩ አሳዎችም በከፍተኛ ቁጥር ሲሞቱ እያየን ነው፡፡ጎርፍና ማእበል፣ድርቅና ረሀብም በየሀገሩ ስለሚያዘወትሩ ብዙ ሰዎች ይጨነቃሉ፣ያልቃሉ፡፡ ያጡ ደሀዎች ይረግፋሉ፣ ሀብታሞች በቅንጦት ይኖራሉ፡፡ ጉልበተኞች ይበድላሉ፣ተጠቂዎች ያለቅሳሉ፡፡ አምልኮዎች ይፈለፈላሉ፣ሀይማኖቶች በየጊዜው ይባዛሉ፣ወንጌልንም የሚሰሙ አሉ፣የሚሰብኩትም አሉ፣የሚያጣምሙትም እንዲሁ አሉ፣ሁሉም በዚህ ሰአት እንዲህ በአለም አሉ፡፡
የመጨረሻውን ዘመን ከሚገልጡ ጥቅሶች ውስጥ 2ጢሞ.3:1-5አንደኛው ነው፡፡በዚህ ቃል ውስጥ የተገለጡነገሮችበትውልዳችን ውስጥ ያሉትን ክስተቶች ከማሳየት በላይበዚህ ትውልድ ያለነውን ክርስቲያኖች ከመቼውም ይልቅ ንቁ እንድንሆን ያሳስቡናል፡፡
የእግዚአብሄር ቃል ዘመኑን እንድናስተውል ምልክቶቹን በማብራራት እያንዳንዳችንን “ይህን እወቅ” ሲል ወደ እኛ ደውል ይደውላል፡፡ምልክቶቹን ስናስተውል ደግሞ “ከእነዚህ ደግሞ ራቅ” ሲል ብርቱ ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል፡-
“ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።”
ከላይ እንደተመለከተው የመጨረሻውን ቀን ዋነኛ ጠባይ ቀኑ በውስጡ የሚያስጨንቅ ዘመን የሚገለጥበት ስለመሆኑ ነው፡፡ በመጨረሻው ቀን (በእግዚአብሄር አቆጣጠር በታወቀው በዚያ ቀን) ውስጥ የሚኖረው ዘመን (ለሰው ልጆች በተፈጠረው ዘመንና ጊዜ) መሽቶ በነጋ ቁጥር የሚወልደውና የሚያሳየው ነገር ሁሉ በውስጡ የሚኖሩትን ፍጥረታት በተለይ የሰውን ልጅ ጭንቅ ጭንቅ የሚያሰኘውና የአእምሮ እረፍት የሚነሳው እንደሆነ ቃሉ ያመለክተናል፡፡
አሁን እኛ ያለንበትን ዘመን ስንመረምር ሰዎች ሁላችን ሀገርና ወገን ሳይለየን ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምእራብ በአንድም በሌላም በሆነ ጭንቀትና መናወጥ ተይዘን ስንናጥ እንደምንኖር ግልፅ ነው፡፡ዘመኑ እንደቃሉ የሚያስጨንቅ ስለመሆኑ ጥርጥር አለን ወይ? በአለም ዙርያ ያሉ አመጾች፣ ህዝብ በህዝብ ላይ ያሉ መነሳሳቶች፣ ህዝብ በመንግስት ላይ የሚያሳየው አመፅናጥላቻ፣አንዱ አንዱን ለበቀል መፈላለግ፣ፍቅር ከሰው መቀነስና እየጠፋ መሄድ፣ሰላም ፈላጊ ሰው በሰላም እጦት ሲደክም ማየት ዘወትር የተለመደ ክስተት ነው፡፡ሁሉ ጉዳይ የሚያሳዝን፣ የሚያሳስብና የሚያስጨንቅ ነው፡፡ እንቅስቃሴዎች በሰጋት የተሞሉ መሆናቸውና እርስ በርስ መተማመን መጥፋቱ በሁሉም የአለም ክፍል የሚታይ ነገር ነው፡፡ የአለም ኢኮኖሚ መናጋት፣ የስራ ማጣት ስጋት፣ የቤተሰብ መበታተንና የትዳር ፍቺ መብዛት ሁሉ በሚያስጨንቀው ዘመን ውስጥ የጎላ ክስተት ነው፡፡