የመጨረሻ ዘመን[4/4]

የመጨረሻ ዘመን

3ኛው የመጨረሻ ቀን ምልክት:- ሰዎች በምኞት የተጠመዱ ይሆናሉ
ትውልዳችንን ከየትኛውም ትውልዶች በተለየ ሁኔታ ምኞት የሚያሩዋሩጠው ትውልድ ነው፡፡እንድንመኝ የሚገፋፉን ነገሮች በደጃችን ያንዣብባሉ፡፡የተለያዩ ማስታወቂያዎች አእምሮአችንን ያስጨንቃሉ፡፡የሚያጉዋጉ ነገሮች በቅርባችን አሉ፡፡የምናየውና የምንሰማው ሁሉ የሚያስጎመጅ ነው፣በቃኝን እንዳንማር ውስጣችንን ዘወትር በፍላጎት ረሃብ ይቦረቡራል፡፡በዚያ ተፅእኖ ምክኒያት ቀልባችን ከምኞቶቻችን መነሳት አይችልም፡፡እንዲያውም ሰው የሚመኘው ሀብት ለማካበትና ብር ለማግኘት ብቻ ሳይሆን በጋብቻ ላይ ይሁን ከጋብቻ ውጪ ለመሴሰን ከፍተኛ ምኞት የሚንፀባረቅበት ጊዜ ነው፡፡አብዛኛው የአለም ህዝብ ትኩረት የሚያደርገው በመንፈሳዊ በረከት ላይ ሳይሆን በስጋዊ ባርኮት ላይ ነው፡፡ይህም ለመንፈሳዊ ዝቅጠት ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ጌታ ሆይ ምራኝ መባሉ ቀርቶ ህገወጥ ስራ እንኩዋን ቢሆን ያለ መሸማቀቅ ያን አድርግልኝ ተብሎ ይፀለያል፡፡”እግዚአብሄር ፀሎታችንን እንዳይሰማና ዝም እንዲል ያደረገው ምንድነው?” ብሎ ዛሬ መጠየቅ መልካም ነው፡፡ የጠላንና ያስጨነቀን ከፊታችን እንዲወገድ ብንፀልይ ምን አለበት? የቀሰፈን ቢቀሰፍ፣ ያሳፈረን ቢያፍር፣ የደበደበን ቢደበደብ እኮ ምን አለበት? ፡- እንዲያ እንመኛለን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ካላወቅን፡፡ እግዚአብሄርንም እናማዋለን ለዚህ ፀሎታችን ባለመመለሱ፡፡
በተለይ በክርስትና ስም በሚንቀሳቀሱ ሀይማኖቶች ውስጥ ሰዎች በምኞት እንዲቃጠሉ የሚገፋፉ ተግባሮችና ስብከቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም ፡-በዚህ ዘመን፡፡ “የብልፅግና ወንጌል” ከጌታ ወንጌል ተገንጥሎ በልዩ መንገድ አማኞችን በትምህርት ያናውዛል፡፡በዚህም እግዚአብሄርን የሚፈልጉ ትኩረታቸውን ወደ ምድራዊ ጥሪት መመኘትና ማለም ውስጥ እንዲሰጥሙ መንገድ ከፋች ሆኖአል፡፡
እስቲ በእውነት እንጠይቅ፡-እግዚአብሄር ለምን አትመኝ አለ? በአጭሩ ምኞት የመውደቂያችን ወጥመድ በመሆኑ!
መዝ.106:12-17 ”በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ፥ ምስጋናውንም ዘመሩ።ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሡም።በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት።የለመኑትንም ሰጣቸው፤ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ።”
4ኛው የመጨረሻ ቀን ምልክት፡- ሰዎች ትምክህተኛና ኩራተኞች ይሆናሉ
ኩራት ሰይጣንን ከነበረበት የክብር ስፍራ ያስወገደ ምክኒያት ነበር፡፡በእግዚአብሄር ፊት መኩራት ውድቀትን እንደሚያስከትል ካስተዋልን በመጨረሻው ዘመን ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት ኩራተኞች ናቸውና ይህ ውድቀታቸውን እያፋጠነ እንደሚገኝ መመልከት እንችላለን፡፡
በዚህ ዘመን ያለ ዝንባሌ እኔነት የሞላበት በመሆኑ በዚያ ውስጥ መመካትና መኩራት የሚንፀባርቅበትና የእኔ ይሁንልኝ በሚል ዙርያ ትኩረት ያደረገ ግለ-ሰባዊነት የሚታይበት ነው፡፡በሰውም በእግዚአብሄርም ፊት ኩራትን ማንፀባረቅ፣ በሚያስፈልግ ጊዜ ለሰው ከመድረስ መራቅ፣ ራስን ስለሰው ከመስጠት መቆጠብ ሁሉ የዚያ ስሜት ነፀብራቅ ነው፡፡የእኔነት ስሜት ”እኔን እዩ፣እኔን ብቻ ስሙ ወይም እኔን በማንኛውም ምክኒያት ከፍ አድርጉ፣ እኔን ተከተሉ…” ወዘተ አለበት፡፡ይሄን ስሜት ለማጀብም የሚገለጠው ባህሪ ትምክህት ወይም ኩራት ይሆናል፡፡
በኩራትና በትምክህት መንፈስ ሲጠመዱ በአለባበስና በኑሮ ዘይቤ ወጣና ጎላ ብሎ ለመታየት ጥረት ይደረጋል፣ የሰውነት ክፍልን የሚያስቆጥር የተወጣጠረ ልብስ መልበስ፣ በአካል ቅርፅ የተሻሉ እንደሆኑ ለማሳየት መድከምና ሰዎች በዚያ ታይታ በምኞት እንዲሳቡና ምንዝርን እንዲመኙ ለማድረግ መጣጣር አለበት፡፡ይህም በዚህ ዘመን ከህፃን እስከአሮጊት ያለ ሀፍረት የሚከናወን እሽቅድምድም ነው፡፡ምርጥና የተደነቀ መኪና መንዳት፣ እጅግ የተቀናጣ ቤት መገንባት፣ ሰዎች እነሱን ከሌሎች ከፍ አድርጎ ሊያሳይ የሚችልን ነገር ሁሉ መሸመት… የዚህ ዘመን አብይ መገለጫ ነው፡፡በዚህች አለም ላይ የአለምን ትልቅ ገፅታ ለአለም ነዋሪዎች በገዛ ማንነት ላይ እየሞከሩ ለማሳየት መድከም የተያዙበትን መንፈስ አመልካች ብቻ ሳይሆን ይህችን ምድር ብቻ ተስፋ በማድረግ በርሱዋ ላይ ሀሳብን እየጣሉ ስለመሆኑ አመልካች ነገር ነው፡፡
5ኛው የመጨረሻ ቀን ምልክት፡- ልጆች ለወላጆች አይታዘዙም
በዚህ ዘመን ልጆች ወላጆች እንዲሰሙዋቸውና ለስሜቶቻቸው ታዛዥ እንዲሆኑ የሚጫኑዋና አዛዦች ሆነዋል፡፡”ኸረ ልጄ እንዳያዝንብኝ፣ አይ እሷ እንዳታኮርፍ ፈራለሁ ወይም ተዉ ልጆቼ ቁጣን አይወዱም” የሚል ትህትና የሚመስል ነገር ግን የልጅን የወደፊት አቅጣጫ የሚያጣምም የቤተሰብ አስተሳሰብም አለ፡፡ልጆችን መቅጣት ወይም በተግሳፅ መመለስ የማይታሰብ እስኪመስል ድረስ የልጆች የበላይነት ከፍ ብሎ፣ ወላጆች ደግሞ ይህን መንፈስ ተቀብለነው ያልያም ተሸንፈንለት በዘመኑ ውስጥ አንድ የአመፅ መንገድ በራሳችን ፈቃድ ከፍተን እንገኛለን፡፡
ቤተሰቦች በራሳቸው ቸልተኝነት ምክኒያትና በልጆቻቸው መረንነት አንገት ደፍተው ብቻ የሚቆዝሙበት ጊዜ ነው፡፡ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ አንዳንድ ወላጆች የእግዚአብሄር ትእዛዝ የሚወጣው ልጆችን ብቻ የሚመለከት አድርገው ነው፡፡እውነቱ ግን ያ አይደለም፡፡እግዚአብሄር ልጅህን የምትወደው ከሆነ ቅጣው ሲል መውደድ የሚለው የፍቅር ግዴታ ወደ እነርሱ እንደሚጠቁም ማስተዋል አለባቸው፡፡ጥቅሱን ለራሴ ልውሰድና በዚያ እኔም ተጠያቂ እንደሆንኩ እያሰብኩ ቃሉ በህይወቴ ተሳክቶ እኔም ልጄም እስክንተርፍ በፀሎትም በተግሳፅም መትጋት አለብኝ ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ልጆችን በተለያዩ ነገሮች እየሞሉ እዚህ ያደረሱ ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ የሚዲያ ተፅእኖዎችም ናቸው፡፡ልጆቻችንን ከዚያ ተፅእኖ ለማውጣት እንዴት እናድናቸው ብለን በሚገባ ማሰብና መትጋት፣ ከልጆቻችን ጋር በግልፅነት መመካከርም ጭምር አለብን፡፡
የሌሎች ሀገሮች የባህል ወረርሽኝ በቲቪ፣ በፊልምና በመፅሄት ስለሚገባ ያንን የሚያዩና እርሱን ለመኖር የሚለማመዱ ወጣቶች በዘመናዊነት ስም የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል፡፡የእግዚአብሄር ልጆች በዚህ የትውልድ ጥቃት እንዳይጎዱ ወላጆች ልጆቻቸውን በእግዚአብሄር ቃል ማስተማር፣ መምራት፣ ሲያስፈልግ መገሰፅና ሁሉን ጠቃሚ መንገድ በመጠቀም የማዳን ስራ ላይ እንዲጠመዱ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በቤተሰብ ግንኙነት አንፃርም ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጪ የሆነን የወላጅና የልጅ ግንኙነት የሚፈጥሩ አካሄዶችን ማቆም ያስፈልጋል፡፡ራስ መግዛትን እንዲማሩ የልጆች አእምሮ ውስጥ ተቀርፆ የሚቀር ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ለማህበረሰቡ በተለይ ለአዛውንቶች ክብር እንዲሰጡ፣ በሁሉ ታዛዥ እንዲሆኑና ትሁትና እውነተኞች ሆነው እንዲያድጉ የቤተሰብ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡
በመጨረሻው ዘመን ልጆች ያልተገቡ ድርጊቶች ማሳየትና ክብር የሚባል ስሜት ያለመኖር ይታይባቸዋል፡፡ ይህም እግዚአብሄርን ያለመፍራትና ያለማወቅ ውጤት ነው፡፡እግዚአብሄርን የሚፈራ ቤተሰብ ሁሌም የእግዚአብሄርን ትእዛዝ ለልጁ ስለሚያሳውቅ ለመልካም ማህበረሰብ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ቴክኖሎጂው፣ ሳይንስና እውቀቱም እግዚአብሄርን የሚከልል ቁሳዊ ግኝት እየሆነ በማስቸገሩ በዚያ ውስጥ ተጠምደው የሚውሉ ለእግዚአብሄር፣ ለቃሉና ለወላጅ መታዘዝን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዳያዳብሩ ከፍተኛ መሰናክል ይፈጥራል፡፡ ወላጆች ግን ይህን ፈተና በአሸናፊነት ይሻገሩ ዘንድ ልጆቻቸውን በትጋት በክትትልና በጥንቃቄ ሊያሳድጉዋቸው ያስፈልጋል፡፡
1ጴጥ.5:5 እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።