2ኛው የመጨረሻ ቀን ምልክት:- ሰዎች ከእግዚአብሄር ይልቅ ገንዘብና ተድላን ይወዳሉ
በሰዎች ዘንድ (በተለይ በዚህ ዘመን)የምንኖረው ህይወት ሙሉነትመለኪያ የተድላ ጣርያ ወይም ከፍታውናየስኬቱ መጠን ማደግ ነው፡፡ለአለም ሰዎችገንዘብና ንብረት ካለ ህይወት ሙሉ ነው፡፡በዚህ አስተሳሰብ ምክኒያት ብዙዎችለተድላ ህይወት ከምንም በላይ ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ያንን ለማግኘትም ማንኛውንም መስዋእትነት ይከፍላሉ(ገላቸውን ይሸጣሉ፣ሰውን ለገንዘብ ይገድላሉ፣ባልሰሩት ስራ ጉቦ ይበላሉ፣የሰው አካል ሰርቀው እስከመሸጥ ይደርሳሉ…ሌላም ሌላም)፡፡
በሌላ በኩል በክርስትና መጠሪያ ውስጥ ያሉ እምነቶች ትንቢት መናገር የሚያበዙት ተድላን ማእከል ባደረገ መልኩ ሲሆን አማኞቻቸውንም በተድላ ምኞት የናወዘ አድርገዋቸዋል፡፡እነዚያ ሰባኪዎች ባለንብረቶችን በማባበል ይነጥቃሉ፣በማመካኘት ገንዘብ ይዘርፋሉ፣የእግዚአብሄርን ቃል ተተግነው ያስጨንቃሉ፣መንጋውን ይበላሉ፡፡ገንዘብ የሌለው ወይም ምቾት ያለው ኑሮ የሌለው በፀሎት ቤታቸው ደጃፍ እንዳይደርስ የሚያስፈራሩ የሀይማኖት መሪዎች በሀገራችን ብዙ ናቸው፡፡
የአለማውያን እግር ወደ ፀሎት ስፍራ ከሚያመራ ይልቅ ወደ መጠጥ ቤቶች፣ ወደ ዳንስ ቤቶች ያልያም ቁማር ቤቶች መሄድ ይመርጣል፡፡አይናቸውም ከእግዚአብሄር ቃል ይልቅ ልብ ወለድ መፅሀፍትን ማንበብ፣ ስጋን የሚያረክስ ፅሁፍ፣ ስእልና ፎቶ ማየት እንዲሁም ቴሌቪዢን ላይ ተተክሎ መዋል ምርጫ ያደርጋል፡፡እነርሱ ብዙ የመዝናኛ ጊዜን ስለሚወዱ ለእግዚአብሄር ጥቂት ወይም ምንም ጊዜ አይሰጡም፡፡በአለማውያን መንፈስ የተጠመዱ ክርስቲያኖችም አይናቸውን ተክለውና ጆሮአቸውን አዘንብለው በተመስጦና ባለመሸማቀቅ የሚያውኩ፣መንፈስን የሚያስሩና ህሊናን የሚያጎሰቁሉ የቴሌቪዢን ፕሮግራም ይመለከታሉ፡፡አንድ አለማዊ ሰው በማየት የሚደሰትበት የቴሌቪዢን ፕሮግራም ክርስቲያንን መስጦ ከያዘውና ነፍሱን ከማረከው ከአለማዊው ልዩነቱ የቱ ላይ ነው?ዘፈኑም ርኩሰቱም በአንድነት በታጨቁበት የቲቪ ፕሮግራም ላይ ያለምንም ድንጋጤ ተተክሎ ማሳለፍ መጨረሻው ምን ይሆን? በአጠቃላይ የምናያቸው ፊልሞች በሙሉ በሚባል መልኩ በእግዚአብሄር ቃል እርግማን ውስጥ የወደቁ ናቸው፡፡እንዴት አድርገን እነዚህን የእርግማን ስሮች ከቤታችን እንነቃቅላለን?ዘዴው እጅግ ቀላል ነው ግን ውሳኔው የሚያሳምም ነው፡፡እንግዲህ ፍላጎትና ስሜትን አሳምሞ ነፍስን ለማትረፍ ጨከን ያለ ውሳኔ ይጠይቃል፡፡
ወደሁዋላ ጥቂት አስርት አመታትን ዞር ብሎ የሚመለከት ካለ ስለዛሬው ዘመን ምን ይሰማዋል?በዚህ ዘመን ባለው የቴክኖሎጂ ከፍታና ባለፀግነት ምክኒያት ዛሬ በቤታችንና በቅፅር ግቢያችን አያሌ እቃዎች ደርድረናል፡፡ኑሮአችን በነርሱ ተቀላጥፈዋል፣ምቾታችን ጨምሮአል፣ያ ግን በእርግጠኝነት አስንፎናል፣እንዲያውም በእግዚአብሄር ላይ የነበረንን እምነት ቀንሶአል፣ፀሎታችንንም ቢሆን አውርዶታል፡፡አስቡት ያኔ የነበረው ጌታ ግን ዛሬም አለ፡፡እንዲያውም ዛሬን ያሳየን፣የዛሬውን ብልፅግና የሰጠን እሱ ነበር፡፡ልዩነቱ ምንድነው?ልዩነቱማ የኛ መቀየር ነው፡፡ያኔ የነበረውን አምልኮ የተቀበለ የክርስቲያኑን ትህትናና ፍለጋ አይቶ በክብሩ የወረደ ጌታ ዛሬስ ያንን መልሶ አይሻውም ወይ?እንደ እውነቱ ከሆነ እግዚአብሄርን ከቴክኖሎጂ እኩል ተለዋዋጭ እያደረግነው እንገኛለን፡፡እኛ ስለተለወጥን እሱም እንዲለወጥ፣እኛ በምቾቶቻችን ስለሰነፍን በስንፍናችን ትክክል እንዲቀመጥ በተግባር መሻታችንን እየነገርነው እንገኛለን፡፡
ያኔ የቤተሰብ አትኩሮት በአንድነት ላይ የተመሰረተ ስለነበረ ያም እግዚአብሄርን ለማምለክ ዋና መሰረት ሆኖ የእግዚአብሄር በረከትን እንዳዘነበ አሁን ግን ቴክኖሎጂ ግለኛነትን በላያችን ፈጥሮና ነጣጣይ ሆኖ ነገሰብን፣ሁላችንን በራስ አለም ተጉዋዢ አደረገን፣ህብረት ሲጠፋ አብሮነትም እየቀነሰ ሲሄድ እግዚአብሄር በህብረት ውስጥ ያስቀመጠው ሁሉ እየቀነሰና እየጠፋ ሄደ፡፡አሁንም ድረስ እየሄደ ነው፡፡በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ነገ የቤተሰብ አምልኮ እንዴት ሊኖር ይችላል? በዚህ ሁኔታ የህብረት አምልኮ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፣ ምክኒያቱም ብዙዎቻችን በቲቪ ፕሮግራም ጊዜያችንን አጣበናል፣የግል ፕሮግራሞ ላይ አተኩረናል፣እንዲያውም የአምልኮና የፀሎት ጊዜዎቻችንን አስማርከናል፡፡የራሳችን የምንላቸው እቅዶች አጣበውናል፡፡የአለም ግሳንግስ ነገሮች ነፍሳችንን በማርከስም በማሰርም ትልቅ ሚና ስለተጫወቱ የተበታተነ መንፈሳችን ወደ እግዚአብሄር ቀርቦ ፀጋው ፊት መገኘት አልተቻለውም፡፡
እንደ እውነቱ ብዙ ሰዎች እየሆነ ባለው ነገር መደናገጥ ወይም መንቃት አይታይባቸውም፡፡ያ ከቀጠለ ደግሞ ትላንትናን በዛሬው እለት እየደግሙት ስለሚሄዱ ለነገ ምንም አይነት ዋስትና ሳያበጁ የቀን ወጥመድ ይይዘቸዋል፣ የሚያልፉበት ገጠመኝምበሙሉ ትርጉም ሳይሰጣቸው አላፊ ይሆናልና አስከፊ ይሆናል፡፡