የመጨረሻው ዘመን (1…)

የመጨረሻ ዘመን

የመጨረሻው ዘመን የሚመጣበት ጊዜ በተለይ ለጌታ ደቀ መዛሙርት ዋና ጥያቄ ነው፦
‘’እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፡- ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።’’ (ማቴ.24:3)
ጌታም ለጥያቄያቸው ግልጽ መልስ ሰጥቶአል፤ በቃሉ እንደተመለከተው ከርሱ በስጋ በምድር መመላለስ ወቅት አንስቶ መጨረሻው እስከሚሆን ድረስ የሚገለጡትን ታላላቅ ነገሮች በምልክትነት ተቀምጠዋል፤ ስለዚህ በነዚያ ክስተቶች ውስጥ የአሁኑን አለም ሥርዓት ፍጻሜ (ድምዳሜ) ወይም ማብቂያ ጠቋሚ ክንውኖች፣ ክስተቶች፣ ሁኔታዎችና ውሳኔዎችን እናያለን። ዘመናቱ ሩቅ ቢመስሉም እጅግ ልናተኩርባቸው፣ ልንጠነቀቃቸውና በቃሉ ምሪት ማድረግ የሚገባንን የጥንቃቄ እርምጃዎች የሚጠቁሙ ናቸው፤ ጌታ የተናገረበት መንፈስ በአለም ልብ ውስጥ ታሪክ ሆኖ ይተረጎማል፣ ለአማኝ ግን የህልውና ጉዳይ ሊያውም የዘላለም ህይወት ጉዳይ ስለሆነ ትኩረት ይሰጠዋል፤ ስለዚህ የነገረንን በምንም መልኩ ቸል ልንል አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ዘመን በሚለው ጊዜ ውስጥ የአለምን ፍጻሜ ወይም የፍጻሜውን ዘመን እናገኛለን፤ ይህን ብል በመጥራቱ ጊዜውን ከሌሎች ጊዚያቶች እንዲለይ የተለዩ ምልክቶችን አስቀምጦአል (2 ጢሞ.3:1፣ ዳን.8:19) ።
የመጨረሻውን ቀን ለመለየት ምልክት እንደሚሆኑ የተዘረዘሩትን ብዙ ነገሮች የማስጠንቀቂያ ደውል ሆነው ዘወትር በመንፈሳችን እንዲያቃጭሉ ደጋግሞ በተለያዩ መንግዶች ጌታ አስቀምጦአል ( ሉቃ.21:7)።
ክስተቶች ምልክት የሆኑት እንደምን ነው? አንዳንዶችን ለማየት እንሞክር፦
ጦርነት በአለም ስፋት መንሰራፋትና መቀጣጠል። ጌታ ኢየሱስ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እንደሚነሳ አስቀድሞ ተናግሮአል (ማቴዎስ 24:7)። በተመሳሳይም በራእ.6:4 ውስጥ ‘ሰላምን ከምድር ላይ የሚያጠፋ’ ጦርነትን የሚወክል ምሳሌያዊ ፈረሰኛ ይታያል።
የረሃብ(ራብ) መንሰራፋት። ጌታ ኢየሱስ በዝናብ መጥፋት ምክኒያት የምግብ ምርት እጥረት እንደሚኖርና ህዝብ በረሃብ እንደሚጎዳ አስቀድሞ ተናግሮአል ( ማቴዎስ 24:7)። የራእይ መጽሐፍ በ6:8 ላይ ሌላ ምሳሌያዊ ፈረሰኛ ይታያል።
ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጦች መደጋገም። ጌታ ኢየሱስ “በየስፍራው የምድር መናወጥ ይሆናል ብሏል (ማቴዎስ 24:7፤ ሉቃስ 21:11 )። በዓለም ዙሪያ የሚከሰቱት እነዚህ ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጦች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን እየጨመሩና ሥቃይ እየከፋ እንዲሁም ለሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ።
በሽታ፣.ቸነፈር ወይም አስፈሪ ደዌ ወረርሽኝ ጨምሮ እንደሚከሰት ተነግሮአል።ሉቃ.21:11።
የወንጀል መበራከትና መራቀቅ። ወንጀል ከሰው ልጅ ፍጥረት አንስቶ ያለ የክፋት ስራ ሲሆን ከሰው ልጅ የአእምሮ መላሸቅ የተነሳ የህሊና ተወቃሽነት እየጠፋ ስለሄደ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወንጀል በመጠንም በክፋትም እንዲበዛ አድርጎአል፤ ጌታ ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን የዓመፅ መብዛት እንደሚጨምር ተናግሮአል (ማቴ.24:10)።
የምድር መበላሸት። በራእይ 11:18 ውስጥ እንደምናየው የሰው ዘር ምድርን እንደሚያጠፋ( እንደሚያበላሽ) የትንቢቱ ቃል ያመለክታል። ይህን የሚያደርጉት ሰዎች በአመጽ እና በብልሹ ድርጊቶቻቸው ባህሪያቸውን ብቻ ሳይሆን የከባቢ ምህዳር ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ናቸው።
የባህሪና የአመለካከት መበላሸት። መጽሐፍ ቅዱስ በ2ጢሞ.3:1-4 ላይ ሰዎች የማይመሰገኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ የማይስማሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ በጎነትን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ትዕቢተኞች እንደሚሆኑ ያሳያል፤ እነዚህ ባህሪዎችና አስተሳሰቦች ዘመኑን ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩና ክፉ የሆነ ጊዜ ውስጥ የሚገለጡ ናችው።
የቤተሰብ መበተን/ መፍረስ። ከሰዎች ክፋት የተነሳ በአንድነት ተፈቃቅዶ መኖርና ተቻችሎ በፍቅር መኖር ችግር ላይ ይወድቃል፤ በባህሪ መላሸቅ ምክኒያት ባልና ሚስቶች በትግስት ሆነው ነገሮችን መጋፈጥ በህብረት ቤትን መስራት ይሳናቸዋል፤ ቤተሰብ ጥብቅና የጸና እንዳይሆን ብዙ ሰዎች ለቤተሰባቸው ፍቅር እንደማይኖራቸውና ልጆች ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተነግሮአል።
የእግዚአብሔር ፍቅር ይቀዘቅዛል። ኢየሱስ “የብዙዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” በማለት ተናግሮአል ( ማቴ.24:12 )። ኢየሱስ ይህ እንደሚሆን የተንገረው በብዙ ሰዎች ዘንድ ለአምላክ ያለው ፍቅር በመቀዝቀዙ ነበር። በተመሳሳይም በ2ጢሞ.3:4 በመጨረሻው ዘመን እነዚህ ሰዎች “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ’’ ይላል።
የአስመሳይ ሃይማኖተኞች መበራከት። መጽሐፍ ቅዱስ በ2ጢሞ.3:5 በመጨረሻው ዘመን ሰዎች በአምልኮ መልክ ተሸፍነው እንደሚኖሩ፣ አምላክን የሚያመልኩ እንደሚመስሉ ነገር ግን በእውነተኛ የአቋም ደረጃ ላይ እንደማይኖሩ አስቀድሞ ተናግሯል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ግንዛቤ መጨመር/ የእውቀት መላቅ። የዳንኤል መጽሐፍ ‘በፍጻሜው ዘመን’ ብዙዎች ስለ እነዚህ ትንቢቶች ትክክለኛ ግንዛቤን ጨምሮ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተጨማሪ እውቀት እንደሚያገኙ ትንቢት ተናግሯል፣ ዳን.12:4።
የወንጌል ስርጭት ዓለም አቀፋዊ መሆን። ጌታ ኢየሱስ “ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ብሏል፣ ማቴ.24:14።
የሰዎች ስነምግባር መበላሸትና የስነልቦና ማሽቆልቆል። ጌታ ኢየሱስ ፍጻሜው እየቀረበ መሆኑን የሚያሳዩትን ምልክቶችና ማስረጃዎች ሲገልጽ በአጠቃላይ ሰዎች የእግዚአብሄርን ማስጠንቀቂያ ችላ እንደሚሉ አስቀድሞ ተናግሯል። ( ማቴ.24:37-39 ) ከዚህም በላይ በ2 ጴጥሮስ 3:3፣4 አንዳንዶች በእውነት ላይ እንደሚዘብቱ፣ የጌታን ቃል አቅልለው እንደሚመለከቱት፣ የቃሉንም ማስረጃ እንደሚቃወሙ ጭምር አስቀድሞ ተናግሮአል።
ጥቂቶች ሲቀሩ ሁሉም ትንቢቶች ተፈጽመዋል በሚባል ደረጃ ላይ መገኘታችን። ጌታ ኢየሱስ የመጨረሻው ዘመን ማብቂያው ሰአት ማረጋገጫዎች የትንቢቶች በሙሉ መፈጸም መሆኑን አስገንዝቦአል፤ እነዚህ ትንቢቶች አብዛኞቹ ሲፈጸሙ መጨረሻው እንደሚሆን ተናግሮአል፣ማቴዎስ 24:33።
የመጨረሻውን ዘመን ውስጥ በእርግጠኝነት ነን፦
‘’ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።’’ (2ጢሞ. 3:1)
ሃዋርያው ይህንን እወቅ ሲል መንፈሳዊ ልጁ ለሆነው ጢሞቴዎስ ምን ማወቅ እንዳለበት ከማሳየቱም ሌላ ያወቀውን እውቀት እንዲጠብቅ እንዲሁም ባወቀው ልክ እንዲጠነቀቅ ያስገነዝበዋል፤ እንዲሁም አሁንም ነገም ከቃሉ ጨምሮ ጨምሮ በማወቅ፣ በማስተዋልና በመጠበቅ መዘጋጀት እንዳለበት ያሳስበዋል። አዎ ማወቅ ያለብን ከእግዚአብሄር ቃል እጅግ ብዙ ነገር አለ፤ ከነዚያ መሃል ስለመጨረሻው ዘመን ጠባይ ምን እንደሚመስልና እኛም እንዴት ባለ ጥንቃቄ በእርሱ ውስጥ ልናልፍ እንዲገባን የሚያስገነዝበን እውቀት ነው፤ ስለእግዚአብሄር ባህሪይ አውቀን በተረዳነው መጠን ወደ እርሱ በመቅረብ፣ እያመለክነውና እየተባረክን በፊቱ ልንገኝ ይገባልና።
በአለምስ ፊት፣ በጠላት ዲያቢሎስ ፊትስ? አለም መልኳ ምን ይመስላል፣ በየጊዜው የሚለዋወጠው ጠባይዋስ? ደግሞ እኛስ እንዴት ባለ ሁኔታ ከእርሷ ጋር እንኑር ወይም እየኖርን ነው? ይህ ጥያቄ ከእግዚአብሄር ቃል በምንቀበለው ጥበብ የምንመረምረውና ለመዳናችን የሚሆነውን የምንጠብቀው ነው።
በሌላ በኩል ይህን እወቅ ብሎ ለሁላችን የሚያመለክተን የአማኞች ባህሪ አለ፤ ይህ ባህሪ በሚያስጨንቀው ዘመን ውስጥ ከአለም ጋር እየተዳቀለ አልፎም በአማኞች ህብረት ውስጥ እየተገለጠ ያለና ህብረቱን የሚያስጨንቅ ሳንካ ባህሪይ መሆኑን እንመለከታለን።
ሃዋርያው በትቢት መንፈስ ውስጥ ሆኖ የተመለከተው የመጨረሻው ዘመን አሳዛኝና አስደንጋጭ የሆነ የባህሪ ማሽቆልቆል በርሱ ዘመን ከነበረው ይልቅ ወደፊት ባለው ማህበር ውስጥ (ወደዚህኛው ወደኛ ትውልድ አካባቢ) እንዲሁም በውጪ ባሉ ዘንድ የተበላሸ አመል ያላቸው ሰዎች እንደሚበዙና ጣልቃ ገብ ከመሆን አልፈው አስጨናቂዎች እንደሚሆኑ አመልክቶአል። በዘመናት የዳበረው የሰው ልጅ ከንቱ ልምምድ በክፉ ባህሪ ግንባታ ውስጥ በፈጠረው የራሱ ተጽእኖ ምክኒያት ትውልድ እየላሸቀ፣ በጎ ባልሆነ አመል እየተወረሰም ይገኛል፤ ከሰው ራስ ተኮር እውቀትና ራስ ወዳድነት ጋር ይህም ተደባልቆ አስጨናቂ የሆነ ባህሪ ሆኖ እየታየ ነው። ሃዋርያው አገልጋዩንና በርሱ ዘንድ ያሉትን ወንድሞች ከመጨረሻው ዘመን ክፉ ልምምድና ባህሪይ ይታደጋቸው ዘንድ የእውቀት አጥር ሲያጥር በዚህ ክፍል እንመለከታለን።
እንዲሁም ስለጊዜው የተለየ ሁኔታ ሲያመለክተው የሚያስጨንቅ ዘመን ነው የሚመጣውና ይህን እወቅ ይለዋል። በእርግጥ የመጨረሻው ቀን ከያዛቸው ወቅቶች መሃል ጭክን ያለ ክፋት ጉልህ ሆኖ እንደሚወጣ አሳይቶአል፤ ያም ዘመን መለያው የሚያስጨንቅ ነገርና ክፉ የሰዎች ባህሪ የሚገለጥበት ዘመን መሆኑ ነው፤ በሌላ በኩል ከትናንት ይልቅ ነገ ይሻላል የሚባል ክስተት እንደማይመጣና ይህን እንድናውቅ ያመለክታል። ያ ዘመን ሰው ሊኖርበት የሚያቅተው ያልያም በጭንቅ የሚኖርበት ዘመን ነው፤ ዘመኑ የጭንቅ የሆነው በአለም ላይ በሚፈጠሩት የገበያ አቅርቦት እጥረት፣ በንግድና እኮኖሚ የተዛባ መሆንና በሰይፍ ጥፋት በመሳሰለው ብቻ ሳይሆን ከምንም በላይ አስደንጋጭ የሆነ የሰዎች ክፉ አመል እንደሚንሰራፋ የሚያሳይ ነው። በሌላ በኩል ዘመኑን አስጨናቂ የሚያደርጉ ክፉ መንፈሳዊ አስተማሪዎች ስለሚነሱና በብርቱ እውነተኞችን ተመሳስለው ስለሚመላለሱ አማኞች እስከማይለዩዋቸው ድረስም በክፋት ስለሚቀጥሉ እንዲሁም ስተው ስለሚያስቱ ነው፤ የእግዚአብሄር ነቢያት ነን እያሉ በአምላክ ቃል የሚዘብቱትም ከነርሱ መሃል ናቸው፣ እነዚህ በእግዚአብሄር እውቀት ተከልለው የሚመጡ ሃሰተኞች ንጹህ ህሊና ያላቸውን ሰዎች ያረክሳሉ፣ ሃጢያተኞች የንሰሃ በር እንዳይከፈትላቸው ያደርጋሉ፣ በጠማማ ትምህርት እንዲዘፈቁም ያደርጋሉ፣ በዚህ ላይ በክፉ ባህሪ እንዲጠፉ በማድረግ ከእግዚአብሄር ምህረት ጋር እንዲለያዩ ያደርጋሉ።
በሚያቆላምጡ ቃላት የሚገለጡ ክፉዎች ለሰው ነፍስ ጠር ናቸው፤ ሰው ፈርቶ እንዳይጠነቀቃቸው ጽድቅ በሚመስል ሽፋናቸው ያታልሉታል፣ ይሸነግሉታል፣ ያደፋፍሩታልም። የአስመሳይ ሰዎች ንግግር እንደ ጋንግሪን ውስጥ ውስጡን የሚበላ ነው የሚል አባባል አለ። በአጋንንት ትምህርት የተካኑ ሃሰተኛ ወንድሞች ወፍራም ሽፋን ለራሳቸው ያበጁ ናቸው፤ ያን ጽድቅ የሚመስል ነገር ግን በክፋት የተደራረተ ሽፋን ነጥሎና አስተውሎ አመጻቸውን መግለጥ የሚችል የእግዚአብሄር መንፈስ ብቻ ነው። ጌታ ኢየሱስ እስከ መጨረሻው ድረስ የጻፍትና ፈሪሳውያንን ስውር ገመና ሲገልጥባቸው ነበር፤ በህዝቡ ዘንድ የከበሩ ቢሆኑም (በህዝቡ መንፈሳዊ እውቀት ሊፈተሹ አልቻሉምና) በእግዚአብሄር ፊት የህዝቡ ጠላት እነርሱ እንደነበሩ ተመልክቶአል፤ መንግስተ ሰማያትን የሚዘጉ እነርሱ ራሳቸው እንደሆኑም አጋልጦአቸዋል። ክፉዎች ዘዋሪና ተናዳፊ በመሆናቸው በትምህርታቸው የዋሃንን ይመርዛሉ፤ ማንም ይሁን በነርሱ እጅ ውስጥ ካለ በሽንገላቸው የታሰረ ነበር፣ ሃዋርያቶች ከነርሱ አደገኛ ትምህርት ያመለጡት በጌታ ላይ በነበራቸው እምነትና እውቀት ብቻ ነበር።
‘’መንፈስ ግን በግልጥ፦ በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው፥እነዚህ ውሸተኞች መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ።’’ (1ጢሞ.4:1-2)
የእግዚአብሄር መንፈስ በግልጥ ለአማኞች ምን ይናገራል? በዚህ ቃል ውስጥ ያሉ የትንቢት ቃሎች ከራሱ ከእግዚአብሄር የወጡ በመሆናቸው ሰዎች ከፍተኛ ትኩረት በነርሱ ላይ ያደርጉ ዘንድ ይገባል፤ በመንፈስ ቅዱስ የተነገሩና እውነተኛ የሆኑ የማስጠንቀቂያ መልእክቶች በመሆናቸውም በቅርብ በሰዎች ዘመናት ውስጥ ሊሆኑ ያላቸው ናቸው፤ ትንቢቶቹ በአዲስ ኪዳን ዘመን ብቻ ሳይሆን በብሉይ ኪዳን ዘመንም በነቢያት ጭምር በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ተነግረው የነበሩ ናቸው፦የሚያስቱ መናፍስቶች የተጠጉዋቸውና የተቆጣጠሩዋቸው ሰዎች እንደሚነሱ በመጨረሻም በሃሰተኛ መሲህና በሃሰተኛ ነቢይ መንፈስ የተያዙ ሰዎች እንደሚገለጡ እግዚአብሄር አሳስቦአል።
የእግዚአብሄር መንፈስ ትንቢት ያናገራቸው ነቢያት አሉ፤ ለምሳሌ በዳን 7:1 ስለአመጽ ሰው የተተነበየ ቃል አለ፣ እንዲሁም በዳን.11:1 ስለ ሃሰተኛ ነቢይ ተነግሮአል፤ ይህ በጌታ ጭምር የተነገረ በመጨረሻ ዘመን ተነስቶ ብዙዎችን የሚያስት ሃሰተኛ ነቢይ እንደሆነ ተመልክቶአል።
መንፈስ ቅዱስ አተኩሮ እንደሚያመለክተው በመጨረሻው ዘመን ሰዎች በኢየሱስ ላይ ካላቸው እምነት እንደሚንሸራተቱና ሌላ መንፈስ ላይ እንደሚወድቁ የተገለጠ ሆኖአል፤ ጥፋታቸው የሚፋጠነውም ከእምነት ትምህርትና እግዚአብሄርን ከመምሰል ምስጢር ስላፈነገጡ ነው፦ በኋለኛው ዘመን ሰዎች ከእምነት ከማፈንገጣቸው በፊት ከጌታ ኢየሱስ አስተምህሮ ቀድመው ያፈነግጣሉ፣ ያኔ በሰዋዊ አስተምህሮ ይመካሉ፣ በፍልስፍና ይተበተባሉ፤ ከቅዱሳን ማህበርም ቀስበቀስ በልባቸው ይለያሉ፤ አልታዘዝም የሚል መንፈስ ስለሚይዛቸው ያን ያደርጋሉም፤ የአለም መንፈስ በተለያየ መንገድ ስለሚጫናቸውም ይስታሉ፣ የሰይጣን አስተምህሮ በሙሉ በተቆጣጠራቸው ጊዜም ሃሰተኛ መሲህና የሃሰተኛው ነቢይ መንፈስ የሚመራቸው ይሆናሉ።
የእግዚአብሄርን ጸጋ መጣል አደጋ ያለው ነው፣ እግዚአብሄር የሰጠውን የንሰሃ እድል መጣል ትልቅ አደጋ ነው፣ የእግዚአብሄርን ምህረት መጣል ፍጹም ውድቀት ነው፣ የቀመስነውን ሰማያዊ ሃይል ምናምን ማድረግ የተዋጀንበትን ህያው ደም የሚያክፋፋ እውቀት መንዛት ወደማይቀለበስ ዘላለማዊ ጥፋት ውስጥ መስጠም ነው፦
መዝ.19:12-14 ‘’ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ። አቤቱ፥ ረድኤቴ መድኃኒቴም፥ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን።’’
ራስን አውቆ ወደ አምላክ መገስገስና ምህረቱን ሙጥኝ ማለት ግን ምንኛ መታደል ነው።