የመስቀሉ ቃል አጽንኦት (3..)

የእውነት እውቀት

2.የመስቀሉ ቃል ተስፋ አለበት
ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞቶ እንደሚያድነን በብሉይ ኪዳን መጽሃፍት ላይ ተስፋ ተሰጥቶ ነበር፣ ይህንንም በተለያየ መንገድ አመልክቶአል። መጥቶ ያድናችሁዋል የተባለውም በመስቀሉ ላይ ዋጋ የሚከፍል በመሆኑ ነው።
በኢሳ.25:6-12 ላይ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አንድ ቀን ለእስራኤል ሕዝብ ክርስቶስ በሚሰቀልበት ተራራ ላይ አለም ሳይፈጠር ያቀደውን አስደናቂ የማዳን ስራውን እንደሚገልጥ ተስፋ ይሰጣል፤ ያም የደህንነት መስዋእት ሲሆን መስዋእቱ በእግዚአብሄር በራሱ ስለሚዘጋጅ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ተብሎአል።
ክርስቶስ በቀራኒዮ ላይ የሚፈጽመው መስዋእት ወገኖች በተባሉ እስራኤላውያን ላይ የተጣለውን የእውቀትና የማስተዋል ግርዶሽ፣ ከእስራኤል ውጪ ባለው የተቀረው የአለም ህዝብ ወይም አሕዛብ ላይ የተዘረጋን ያለማወቅ መሸፈኛ እግዚአብሄር እንደሚያጠፋ ተስፋ ሰጥቶአል። ያን ስራ በገለጠ ወቅት በእምነት በተቀበሉት ወገኖች ዘንድ ያለውንም ዋጋ እንዲህ ይለዋል፦
‘’ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል። የእግዚአብሔርም እጅ በዚህ ተራራ ላይ ታርፋለች፥ ጭድም በጭቃ ውስጥ እንደሚረገጥ እንዲሁ ሞዓብ በስፍራው ይረገጣል።’’(ኢሳ. 25:8-10)
አብረሃምም በሞርያ ተራራ በምሳሌ የተቀበለው ምትክ የመስዋእት በግ ስለ ክርስቶስ መታረድ አመልካች ነበር፤ ክርስቶስ በሃጢያት ምክኒያት በሞት ፍርድ ልንሞት የተገባንን የሰው ልጆች ተክቶ እንደሚሰዋ ትንቢቱ አመልካች ነበር፤ አብረሃምም በሩቅ ተመለከተውና አመነ፦
‘’ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን ተናገረው፦ አባቴ ሆይ አለ፦ እርሱም፦ እነሆኝ፥ ልጄ አለው። እሳቱና እንጨቱ ይኸው አለ፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት ነው? አለ። አብርሃምም፦ ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ።እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያውን ሠራ፥ እንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው። አብርሃምም እጁን ዘረጋ፥ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ። የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና፦ አብርሃም አብርሃም አለው፤እርሱም፦ እነሆኝ አለ። እርሱም፦ በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ። አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው። አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል ይባላል።’’(ዘፍ. 22:7-16)
ክርስቶስ የእግዚአብሄር በግ ሆኖ ለእስራኤላውያን መገለጡም እግዚአብሄር በነርሱ ምትክ (እግዚአብሄር ለአባታቸው ይስሃቅ ምትክ መስዋእት አዘጋጅቶ እንዳዳነው ሁሉ) መስዋእት ሆኖ የሚሰዋላቸውን ስጋ እንዳዘጋጀ ማመልከቱ ነበር፤ መልአኩም ለህዝቡ ብስራት የተናገረው ይህንኑ ነው፦
‘’የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ፦ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።’’ (ማቴ.1:18-23)
3.አዋጅ አለበት
‘’ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፥ ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ፥ ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች ወደ እርስዋ ጩኹ። የአዋጅ ነጋሪ ቃል፦ የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ። ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።’’ (ኢሳ. 40:2-5)
የአዋጅ ነጋሪ ቃል ክርስቶስ አዳኝ የሆነ እንዳለና እንደሚመጣ ብስራት ሲናገር ነበር፤ የተመረጠው ህዝብ ግን እግዚአብሄር አስቀድሞ የተናገረውን ሳይቀበል በአመጽ ተነሳስቶ መድሃኒት በሆነ መሲህ ላይ ፈራጅ ሆነ፤ የነቢያት ድምጽ ስለመድሃኒቱ መምጣት በታላቅ ተስፋ ሲናገር ሳለ በዚያው ልክ የህዝቡን ዝግጅት መገለጡ እንደሚፈልግ አስጠንቅቆአል፦
‘’እለፉ፥ በበሮች በኩል እለፉ፤ የሕዝቡንም መንገድ ጥረጉ፤ አዘጋጁ፥ ጐዳናውን አዘጋጁ፥ ድንጋዮቹንም አስወግዱ፤ ለአሕዛብም ዓለማ አንሡ። እነሆ፥እግዚአብሔር ለምድር ዳርቻ አዋጅ እንዲህ ብሎ ነግሮአል። ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ መድኃኒትሽ ይመጣል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ አለ በሉአት። እግዚአብሔር፦ የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም፦የተፈለገች ያልተተወችም ከተማ ትባያለሽ።’’(ኢሳ.62:10-12)
እግዚአብሄር ሲናገር ትውልድ በተያዘበት መንፈስ ተጋርዶ ሳያስተውል እየቀረ እንጂ እርሱ መለኮታዊ እውቀቱን ሰውሮ ያለፈበት ዘመን አልነበረም፤ በተለይ ተስፋ የተቀበሉት እስራኤላውያን እንደታየላቸው ስላልሄዱ፣ እንደነገራቸው ስላልኖሩም በነርሱ በኩል ለአህዛብ ጭምር ሊሆን የታሰበው መንፈሳዊ በረከት ከበዛ ትውልድ ላይ ሳይገለጥ አልፎአል።
‘’በዚያም ቀን፦አቤቱ፥ ተቈጥተኸኛልና፥ ቍጣህንም ከእኔ መልሰሃልና፥ አጽናንተኸኛልምና አመሰግንሃለሁ።እነሆ፥ አምላክ መድኃኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌና ዝማሬዬ ነውና፥ መድኃኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም ትላለህ።ውኃውንም ከመድኃኒት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ።በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ። እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናገሩ።ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ።አንቺ በጽዮን የምትኖሪ ሆይ፥ የእስራኤል ቅዱስ በመካከልሽ ከፍ ከፍ ብሎአልና ደስ ይበልሽ እልልም በዪ።’’ (ኢሳ. 12:1-6)
4.ውሳኔ አለበት
‘’እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ እልከኞች፥ ስሙኝ፤ ጽድቄን አቀርባለሁ፥ አይርቅም መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ።’’ (ኢሳ. 46:12-13)
እግዚአብሄር አንድያ ልጁ በመስቀል ሞት እንዲሞት የወሰነው ሰውን ለማዳንና የሃጢያት ምንጭ የሆነውን ሰይጣን ለመቅጣት፣ ወደ ሰው ህይወት የሚያፈሰውን የሃጢያት ጅረትም ለማድረቅ ነው።
‘’የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ። ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ ሁሉ የሆነውን ነገር እናንተ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን። ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን። በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።’’ (ሃስ.10:34-43)
ሰይጣንና ስራውን በመስቀል ላይ በጦር ተወግቶ ባፈሰሰው ደሙ ሊያፈርስ የወሰነ ጌታ በመንፈስ የደረቀውን የሰው ህይወት ደግሞ በሞገሱ ሊጎበኝና በመንፈሱ ሊያረሰርስ ወስኖ ፍቅሩን ገልጦአል፦
‘’በዳዊትም ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የሞገስንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ፤ ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ፤ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል። በዚያ ቀን በመጊዶን ሜዳ እንደ ነበረው እንደ ሐዳድሪሞን ልቅሶ ታላቅ ልቅሶ በኢየሩሳሌም ይሆናል። ምድሪቱም ታለቅሳለች፤ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ የዳዊት ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ የናታን ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ የሌዊ ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ የሰሜን ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፤ የቀሩት ወገኖች ሁሉ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው ያለቅሳሉ።’’ (ዘካ. 12:10-14)
የዳዊት ቤት የተስፋ ቃል ተቀብሎ ሳለ ህዝቡ አይናቸው ስላልተከፈተ በጣሉት ያማረ እጣቸው ፈንታ በሃዘንና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እስከዛሬ ተዘፍቀዋል፤ ከሩቅ ዘመን በሁዋላ አይናቸው ሲከፈት የሰቀሉትን በእንባ እንደሚቀበሉት አስቀድሞ ትንቢቱ ያምለክታል። ይህም ላላመኑት እፍረት ይሆናል፦
‘’ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው። ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።’’ (ዮሃ. 3:13-16)
5.እምነት አለበት
በመስቀል ስለእኛ መተላለፍና ሃጢያት የሞተልንን ጌታ አምነን እለት እለት በእርሱ ህይወት መኖር ይጠበቅብናል፣ ጌታ ኢየሱስ በሰማይ እንደታረደ በግ ሆኖ ቆሞ ያለው በርሱ ስራ መዳንን፣ መትረፍንና መጽደቅን እንድናገኝ በማመን አምነንም ወደ መደናችን ዘወትር በአትኩሮት እንድንመለከት ነው። ወደ ሰማያት ስናቀና የታረደልንን እንድናስብና እንድናሰላስል፣ ስራውን አንስተን እንድናመሰግንና ትምክህታችን እርሱ እንደሆነ እንድናምን ይረዳናል።
‘’በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ። ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም። ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፦ ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፦ ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።’’(ገላ. 3:13-16)
አህዛብ የሆንን እኛ እግዚአብሄር በከፈተልን በር ስለገባን የአብረሃምን ተስፋ ልንቀበል ችለናል፤ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ እርግማናችንን ወስዶልናልና፤ ይህም ለአብረሃም የተናገረው የተስፋ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፤ እውነተኛ አምላክ የተናገረውን የሚሰጥና የሚፈጽም በመሆኑ እምነታችን በእርሱ ላይ ስር ሊሰድና ተስፋችን በህይወታችን እንዲፈጸም ማመን ይገባናል።
ክርስቶስ እርግማናችንን ስለተቀበለ ከእርግማን ነጻ መሆናችን ተረጋገጠ፣ የመንግስቱ ወራሽ የምንሆንበትን የዳግም ልደት አሰራር ገለጠልን። ከውሃና ከመንፈስ የመወለድን ምስጢር አብርቶልን የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል አድርጎና በክርስቶስ ያለውን ህይወት ተካፋይ የምንሆንበትን አሰራርና ሰጥቶን ከእርሱ ጋር ለዘለአለም የምንኖርበትን ተስፋ አተመበን።
‘’ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።’’ (ኤፌ. 2:13-16)