የመስቀሉ ቃል አጽንኦት (2..)

የመስቀሉ ቃል
የመስቀሉ ቃል የወንጌል ማእከላዊ መልእክት ሆኖ ሳለ የበዙ አስተማሪዎች ያን ባለማስተዋል ትኩረታቸውን ወደ ሌላ አድርገው በደህንነት ትምህርት ላይ ብዙ ሰዋዊና አጋንንታዊ ትምህርቶች ጣልቃ እንዲገቡ ምክኒያት ሆነዋል። በሌላ በኩል በሃዋርያቱ በኩል ለአለም የደረሰው ወንጌል ያለመቀያየር እንዲቀጥል ከመስራት ይልቅ በተለያዩ ትምህርቶች እንዲበረዝ፣ በወግና በስርአት እንዲታሰር አድርገዋል። የመስቀሉ ቃል በትክክል በሚሰበክበት ስፍራ ሁሉ ነፍሳት ወደ ጌታ መንግስት ይጨመራሉ፤ ህኖም በመጨረሻው ዘመን ላይ እንደመሆናችን በገዛ ምኞታቸው እገዛ እያስተማሩ ያሉ ሰዎች በመብዛታቸው ሰዎች በመስቀሉ ቃል ላይ እምነትን አጥተው ድፍረትን እንዲላበሱ አድርጎአል። የሃዋርያው ጳውሎስ ማስጠንቀቂያ እንዲህ ይላል፦
‘’እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ። እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፥ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፥ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል። ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት:- አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና። ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም።’’ (ቆላ. 2:16-19)
የህይወት ቃል ደብዝዞ በወንጌል አካባቢ የሰው ሥርዓትና ትምህርት ሲበዛ ከአለማዊ ህግጋትና ግብረገብ ወይም ደግሞ የጸባይ ማረሚያ መምሪያ ከመሆን በምንም አይለይም፤ መንፈሳዊነትን ከሚገዛ የወንጌል ትምህርት ይልቅ ይህን ያዝ ያን ልቀቅ፣ ይህን ብላ ያን አትቅመስ፣ ይህን ውሰድ ያን አትንካ በሚሉ አሳሪ ህግጋት ህይወትን የሚያክል ክቡር ነገር ማናወዝ ዞሮ ዞሮ ጽድቅን ቸል ያስብላል። ህሊና ላይ የማይሰራ ስጋ ላይ የሚንጸባረቅ ትእዛዝ ማስፈራሪያ ብቻ እንጂ ነፍስን አያድንም። ይልቁን መዳናችን እንዲጸና በቀራንዮ የተሰቀለው ጌታ ላይ አትኩሮትና እምነታችንን እናድርግ። በሃዋርያት ዘመን ይንጸባረቁ የነበሩ የግሪክና የአይሁድ ሰዎች ልዩ ትምህርት የወንጌል እንቅፋት እንደነበር ቃሉ ያሳያል፦
‘’መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው። ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና።’’ (1ቆሮ. 1:24-27)
ልክ በሃዋርያት ዘመን እንደሆነው ዛሬም የትኩረት አቅጣጫችን ከተሰቀለው ክርስቶስ ላይ ከተነሳ የህይወታችን ዋስትና የሆነው የመስቀሉ ስራ ተዘንግቶ የፈላስፋዎች አሳብ እንደሚወርሰን የትውልዱ ውድቀት ራሱ ምስክር ነው። በትውልዱ ላይ የበረታው ሰዋዊ ትምህርት ከእውነተኛው ሃይማኖት አፈንግጦ የተለያዩ እምነቶች እንዲባዙ ምክኒያት ሆኖአል፤ ክርስቶስን እሰብካለሁ በሚል ማባበያና መሰል መንፈሳዊ አስመሳይነትን በመላበስ የእውነት ደህንነትን ለሚፈልግ ትሁት ህዝብ ታላቅ እንቅፋት ፈጥረው ሰው ሃይማኖት የሚል ስም መስማት እስከሚጠላ ትውልዱን ሰብረዋል። መጽሃፍ ቅዱስ ግን የጸናውን የእግዚአብሄር ቃል በማሰራጨት ትውልዱን ማዳን እንደሚቻል አጽንኦት በመስጠት እውነተኞች የቃሉ አገልጋዮች ያን ይለማመዱ ዘንድ ያመለክታል፦
‘’ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ። አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም።’’ (2ጢሞ. 4:2-5)
1.የጌታ የደህንነት ምስጢር የተገለጠበት ቃል
ደህንነት ከሃይማኖት ጋር ለምን ተያይዞ ቀረበ? አለም በሃይማኖቶች ብዛት በመታጨቅዋ እግዚአብሄር የሚቀበለው ህዝብ አምላኩ በተለይ ከገለጠው እምነት ጋር ተያይዞ እንዲኖር ፈቃዱ በመሆኑ ነው። በየምክኒያቱ ሰውን ለማሳሳት በመናፍስት እገዛ ከሚፈጠሩና ከሚቀነባበሩ ሃይማኖቶች ነጥረን ወጥተን የዘላለም ህይወት ወዳለው እምነት እንድንገባ እግዚአብሄር መንገድ ከፍቶአል።
‘’ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።’’(ይሁ. 1:3)
የመስቀሉን ቃል የሚያበራ ሃይማኖት ከእግዚአብሄር ፍጹም ሆኖ የተሰጠ ነው። አለምም ይህን እምነት የምትቀበለው በመንፈስ ቅዱስ ወንጌል ሲገለጥላት ሲሆን በሌላ በኩል እውነተኛው ሃይማኖት መጋደል ውስጥ የክርስቶስን መስቀል መግለጥ ስላለበት ትግሉ እጅግ ወሳኝ ነው።
ሃዋርያው ጳውሎስ ሰዎች በግራም በቀኝም የሚወጡትን የትምህርት ነፋሶች ተቁዋቁመን፣ አለማዊ ሃይማኖቶችንም ከሚነዱ እውቀቶች ታቅበንና ወደ ጌታ የመስቀል ስራ ዞር ብለን የምንድንበት እውቀት ላይ መጣበቅ እንዳለብን አበክሮ ያስገነዝባል።
‘’ጢሞቴዎስ ሆይ፥ በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ ይህ እውቀት አለን ብለው፥ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና። ጸጋ ከአንተ ጋር ይሁን።’’(1ጢሞ.6:20-21)
ህይወት በማይሰጥ ክርክር፣ ጥልና ጩሀት ላይ ከተመሰረተ አለማዊ ሃይማኖትም መራቅ ተገቢ ነው፤ ትምህርቱ ለዓለም የሚመችና መንፈሳዊነትን የሚያዳክም በመሆኑ በርሱ ላይ ጊዜ ማባከን ተገቢ አይደለም።
‘’አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና። እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር። በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ጊዜ፥ ስለዚህ ክርክር ጳውሎና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቈረጠ።… ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ። ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤ ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም። እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለ ምን ትፈታተናላችሁ? ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን።’’ (ሃስ. 15:1-2፣ 7-11)
2.የሃይማኖት መብዛት ውክቢያ
ለመቁጠር የሚያዳግቱ እጅግ የበዙ የሃይማኖት አይነቶች በምድር ላይ ተዘርተዋል፤ ማን ፈጠራቸው? እንዴትስ ተባዙ? ለሚል ጥያቄ መልስ የሚሆን ሰፊ ትንታኔ ሊያስፈልግ ቢችልም እርግጠኛ ምንጫቸው ላይ ካተኮርን ግን መነሻና መደምደሚያቸው ላይ ልንደርስ እንችላለን፤ ያም መነሻ የእግዚአብሄር ተቃዋሚ መንፈስ መደምደሚያቸውም ራሱ ክፉ መንፈስ ነው።
ለዚህ አሳች የህይወት በራችንን የከፈትንለት እኛው ራሳችን ሰዎች ስንሆን ከሰራነው ስህተታችን ሳንማር ያለንሰሃ የተጉዋዝነው ጉዞ ደግሞ ሃይማኖት በዘፈቀደ እንዲፈለፈልና ተጽእኖውን አሳርፎብን ከአምላካዊ ጎዳና እንዲያስወጣን ሌላ በር ከፍተናል።
በአዳምና ሄዋን ስህተት በምድራችን ላይ ከመጣው እርግማን ባልተናነሰ መልኩ ስህተቱን ለመጠገን የተሄደበት መንገድ የከፋ ስህተት ውስጥ እስገብቶናል፤ እግዚአብሄር አዳምን ሊያናግረው ሲመጣ አዳም ሊሸሸግ ሲሞክር ነበር፤ ስጋዊው መንገድና እውቀቱ ከተበላሸው የሰው ልብ የወጣ ስለነበር ከትውልድ ትውልድ ጥፋት ተከታታይ እንዲሆን አድርጎአል። አስቀድሞ ከዚያ የጀመረው ትምህርት ለመንፈሳዊው ችግር ስጋዊ መፍትሄ ሊሰጥ መሻት ስለነበረው ከግዚአብሄር ይበልጥ የሚያርቅ ውጤት አምጥቶአል።
‘’ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ።’’ (ዘፍ. 3:6-8)
ቀላል ቢመስልም አዳምና ሄዋን እንደ መፍትሄ የፈጠሩት ዘዴ ለሰው ልጆች በሙሉ ከእግዚአብሄር ይልቅ በራስ መደገፍን አስተምሮአል። በራስ መደገፍም የእምነት ጠር ሆኖ ልባችንን የሚያስትና የሚፈታተን ነው።
ባለመታዘዝ ምክኒያት የተከተለብን ቅጣትም ልባችንን በንሰሃ ሊመልስ ሲገባ ይህ ያልሆነበት ምክኒያት የፈጠርነው ሰዋዊ መፍትሄ መሸሸጊያችን ስላደረግነው ነበር፤ ለምሳሌ አዳም ራቁቱን እንደነበረ ባወቀ ጊዜ በንሰሃ ልብ ሆኖ አምላኩን ምን ማድረግ እንደነበረበት ምክር አልጠየቀም፣ የራሱን መፍትሄ ያለውን ቅጠል ልብስ አድርጎ አዘጋጀ እንጂ። እግዚአብሄር ግን ከአዳም ከራሱ መፍትሄ የተሻለውን የቁርበት ልብስ ሽፋንና መከለያ አድርጎ ሰጠው።
የአዳም ስህተት የከፋው ካጠፋው ጥፋቱ ያለመመለሱ ብቻ ሳይሆን አዲስ የመፍትሄ መንገድ መቀየሱ ስለነበር ያን ድርብርብ ስህተት አስወግዶ ወደ ትክክለኛው ማንነቱ ይመልሰው ዘንድ መለኮታዊ መፍትሄ ብቸኛው አማራጭ ሆኖአል። የእግዚአብሄር መፍትሄ ችግራችንን፣ ስህተታችንና ድካማችንን፣ እርግማኑንና የወደቀብንን ኩነኔ ከስር ከመሰረቱ አንስቶ ነቅሎና ሽሮ መፍትሄ የሚሰጥ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
የእግዚአብሄር ቃል የአዲስ ኪዳን ትውልድ ራሱን በምን መንገድ ማየት እንዳለበት ምሪት ይሰጣል፤ በኤፌሶን መጽሃፍ ስለኛ መንፈሳዊ ውድቀት፣ ከእግዚአብሄር የራቅንበትን መንገድ፣ እግዚአብሄር ደግሞ ከጥፋት ሊያወጣን ያቀደውን እቅድ፣ በተግባር የገለጠውን ፈቃድም በእውቀቱ ብርሃን በኩል እንድናይ አድርጎአል።
ከመጀመሪያው ሰው አዳም አንስቶ በሰው ላይ የተፈጠረውን የከፋ ሁኔታ ቃሉ በአጽኖት ይገልጸዋል፤ በበደላችንና በኃጢአታችን ምክኒያት በመንፈሳችን ሙታን እንደነበርን በማመልከት፤ ያም ከማስተዋል ውጪ አድርጎ በዚህ ዓለም ኑሮ ስር በተጽእኖ እንድንኖር ስለማድረጉ ያሳያል።
በአለማዊ አስተሳሰብና ልማድ ውስጥ መንፈሳዊ ክልላቸውን ወርሮ የያዘ የጥፋት መንፈስ ሰዎችን ክንጹህ አምልኮ ማገዱ በቃሉ ተመልክቶአል። እግዚአብሄርን ባላወቅንበት ዘመን በእግዚአብሄር ላይ አመጸኞች ሆነንና የማንታዘዝ ሆነን ራሳችንን ለመንፈስ አለቃ አሰራር ሰጥተን ነፍሳችንን ለርሱ እንድትገዛ አሳልፈን ሰጥተናል፤ ባለማስተዋላችንም በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ ለመመላለስ ሳንወድ ተገደናል።
አለም ከእግዚአብሄር መገኛ በራቁና በተለያየ የስጋ ልማድ በሚመሩ ልጆችዋ የምትገለጥ ነች፣ እግዚአብሄር ግን በመስቀል ላይ በተሰራው ስራ ከነርሱ ልማድ ታድጎናል፤ እግዚአብሄር ነጻ ያወጣን ከጽድቅ ከለየን የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ ሲሆን ነፍሳችን በሥጋችን ምኞት ተሸንፋ ስለነበር ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች መሆናችን የተረጋገጠ ነበር። ኤፌ.2:5-6 እግዚአብሄር የሰራውን ስራ ያሳያል፦
‘’ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።’’
እግዚአብሄር ከዘላለም ዘመናት በፊት አቅዶ በመስቀል ላይ የፈጸመው ስራ ለእያንዳንዳችን ይደርስ ዘንድ በስራችን ሚዛን ሳይሆን በጸጋው ስጦታ እንድንቀበለው የፈቀደው ነው፤ ይህን የማዳን ስራ ያመንን ከሞት መንጋጋ ተላቀን አምልጠናል። ይህን የደህንነት ስራ እግዚአብሔር ፈጽሞ ለእኛ በነጻ የሰጠን ስጦታ ነው እንጂ ከእኛ የተዋጣ አንዳች እገዛ አልነበረም፤ የሰው ልጆች ይህን አስተውለን እግዚአብሄርን ማመስገንና ማምለክ እንጂ በምንም ነገር መመካት አንችልም። ቸር አምላክ ግን በአንድያ ውድ ልጁ ላይ መከራና ሞት እንዲያልፍ አድርጎ በርሱ የመስቀል ስራ ምክኒያት በዳግም ልደት ወልዶናልና አዲስ ፍጥረቶቹ ሆነናል፤ ይህን ያደረገውም በአዲስ መንፈስና ተስፋ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ እንድናደርግ ነው።
‘’ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ’’(ኤፌ.2:11-15)