የመስቀሉ ቃል ክርስቶስ የመሰቀሉ አዋጅ ቃል ነው፤ ወደ ቃሉ ውስጥ በጥልቀት ስንመለከት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ስራ የምስራቹን የሚናገረው የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል በሙሉ ነው፤ የመስቀሉ ቃል የእግዚአብሄርን የማዳን ስራ የሚያውጅ ቃል እው፤ በመስቀሉ ቃል ሃጢያተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደዚህ አለም መምጣቱ ተበስሮአል። የመስቀሉ ቃል የገዛ ወገኖቹን ሊያድን ወደነርሱ በስጋ መምጣቱን ያስረዳል። የመስቀሉ ቃል ክርስቶስ ባፈሰሰው ደም ሃጢያታችንን እንደሚያጥብ ይተርካል። ቃሉ ስለክርስቶስ የመስቀል ስራ ሲናገር ስራው ራሱን ለሞት አሳልፎ እስከመስጠት መድረሱን ይገልጣል፤ ክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ ሰውነት እንዲኖር የፈቀደበት፣ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ያደረገበት ምስጢር እንደሆነ ያሳያል።
እርሱ በምድር ላይ ሲመላለስ ክብሩን የተወ ጌታ የተናቀ ከሰውም የተጠላ ነበር፥ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ህመም፣ ድካምና ችግር ስለተሸከመ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው ተባለ፤ ክብሩን የጣለ ጌታ ሰውም ፊቱን እስኪሰውርና ለመስቀል ተላልፎ እስኪሰጥ በሚደርስ ማዋረድ የተናቀ ነበር፥ እስራኤላውያንም ማንነቱ ስላልተገለጠላቸው ሊያከብሩት አልቻሉም።
እርሱ ግን ደዌያችንን የተቀበለ ሕመማችንንም የተሸከመ ጌታ ነው፤ እኛ ደግሞ የሚረዳው አጥቶ በደካማነት እንደ ተመታ፣ በጥፋቱ በእግዚአብሔር እንደ ተቀሠፈ፣ ደህይቶ፣ ተርቦና ተጠምቶ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።
የመስቀሉ ቃል ክርስቶስ ስለራሱ ሳይሆን ስለ መተላለፋችን መቁሰሉን፥ ስለሃጢያቱ ሳይሆን ስለ በደላችን መድቀቁን፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ እንደሆነ (እኛ ከፍርድ እንድንድን እርሱ የኛን ፍርድ መቀበሉን) እና በእርሱም ቍስል እኛ መፈወሳችንን የሚያበስር ነው።
የመስቀሉ ቃል ክርስቶስ ጌታ ስለ እኛ ሲል እስከ መስቀል መሄድ እንዳስፈለገው ያሳያል፤ በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ደም በኩል እንደ በጎች ተቅበዝብዘን የጠፋነውን አግኝቶአል፤ ክርስቶስ መከራውን እስኪቀበል ድረስ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነብሎ ነበር፤ ያንን መፍትሄ ያደርግ ዘንድም እግዚአብሔር የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ (በስጋው ላይ) አኑሮአል።
ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተጨነቆአል፣ ተሰቃይቶአል፤ መከራውን ሲቀበል ንጽህናውን ያስረዳ ዘንድ፣ ፍርድም ከእርሱ እንዲወሰድ ሲል አፉን ለክርክር አልከፈተም፤ ወደ መስቀል ሲሄድ እንደ በግ የዋህ ሆኖ ምን እንደሚገጥመው እንደማያውቅ በመምሰል፣ ለመታረድ ሲወሰድ አራጆቹን እንደማያውቅ ጠቦት ሆኖና በሸላቶቹም ፊት ስለሚሆንበት ነገር መልስ እንደማይሰጥና ዝም እንደሚል የዋህ በግ ሆኖ አፉን አልከፈተም ነበር።
የመስቀሉ ቃል የእግዚአብሄርን የዘላለም አሳብ የሚገልጠውን መሲህ አመጣጥና ክንዋኔ የሚያበራ ቃል ነው፦ ክርስቶስ ኢየሱስ ዳግም የምንወለድበትንና ከሃጢያት የምንነጻበትን ውኃና ደም ይዞ መጥቶአል፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ የመጣ አይደለም ይላል ቃሉ። ሌሎች በተለያየ ምክኒያትና መንገድ ሲመጡ እርሱ ግን በገዛ ደሙና በገዛ ውኃው እንደመጣ ያበስራል፤ ብሉይ ኪዳን ለእስራኤል ደህንነት የመጣው በእንስሳት ደም በኩል ነበር፤ ካህናትንም የሚያነጻ ንጹህ የምንጭ ውሃ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። በአዲስ ኪዳን ክርስቶስ ኢየሱስ በዘላለም መንፈስ ከጎኑ በፈሰሰ ውኃና ደሙ ከሃጢያታአችን እንድንነጻ አደረገ።
የክርስቶስ ስጋ ከአዳም አባታችን በዘር የተካፈለው እንዳልሆነ ያወቅነውና የተረዳነው የመስቀሉ ቃል ክርስቶስን ስላበራልን ነው፤ አይሁድ ከነርሱ መሃል ከአንዱ ወገን የተወለደ አንድ መልካም ሰው እንደሆነ አድርገው ተመለከቱት እንጂ ከሰማይ ሕያው እንጀራ ሆኖ እንደ ወረደ አላስተዋሉም፤ ሰው ከዚህ ህያው እንጀራ ቢበላ ለዘላለም እንደሚኖር እርሱ ለወገኖቹ የምስራቹን ነግሮአቸው ነበር፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው ያለው ቃል ያሰናከላቸው አይሁድ፣ ተጠራጥረውት፦ ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራክረው ነበር። ጌታ ኢየሱስ ግን ደጋግሞ ያን አስረግጦ ነገራቸው። እንዲያውም የዘላለሙን እንጀራ ባለመብላታቸው ከዘላለም ህይወት ተካፋይ እንደማይሆኑ አመልክቶአቸው ነበር፤ ሲቀጥል እንዲህ አለ፡-
‘’እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል’’ ብሎአል (ዮሃ6:30-63)።
ቃሉ የሚገልጣቸው እውነቶች
ሁላችን የአዳም ልጆች የሆንን ኃጢአት ሠርተናል፣ በሰራነውም ኃጢአት ምክኒያት የእግዚአብሔር ክብር ሊጎድለን በቃ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልነው ቤዛነት ግን መልካምነታችንን ሳይለካ (ያም በእኛ አይገኝምና) ጌታ በሰራልን የመስዋእት ስራ ብቻ በጸጋው ጸድቀናል። በመስቀሉ ላይ ዋጋ ስለተከፈለልን ይህ የምስራች በቃሉ ላይ እንዲህ ይላል፦
‘’ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን።’’
የጸጋው ባለጠግነት ያጎናጸፈን በደሙ በተደረገ ቤዛነታችን እግዚአብሄር እንዲቀበለን ያደረገውን ነው። በዚህም በመስቀል ላይ የፈሰሰው ደም የበደላችን ስርየት ሰጥቶአል።
‘’ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን። እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን።’’ (ራእ.1:6-13)
ሰው ለወደደው በእጁ ካለው ይሰጣል፤ ጌታ ኢየሱስ የሰጠው ግን ራሱን መሆኑ እጅግ ያስደንቃል። እርሱ ነፍሱን አሳልፎ ለሞት እስኪሰጥ ወዶናልና።
‘’በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ። … ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል።’’ (ኤፌ.5:20-26)
የኛ ሰላማዊ ህይወት (ከእግዚአብሄር ጋር በእርቅ የመኖር ሁኔታ) የተረጋገጠው እስከ መስቀሉ መከራ የሚያደርስ ውሳኔ ከእግዚአብሄር አምላክ ስለተወሰነ ነበር፣ ለምን? ስንል፦
‘’የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው። ቃሉ የታመነ ነው።’’ (ቲቶ.3:5)
የክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት ለሚጠፉት ሞኝነት
እግዚአብሄር ቸር የሆነ አምላክ በቸርነቱ አንድ ትልቅ ነገር ስለእኛ አድርጎአል፣ ይሀውም ሰው አጥቶ የነበረውና ትውልድ ሁሉ ሳይቀበል ያለፈው በመጨረሻው ዘመን ግን የተገለጠው ታላቅ ምህረቱ በተግባር መታየቱ ነው፤ በተግባር የታየው ይህ ቸር አምላካዊ ስጦታ ሰውን ከሃጢያት በማጠብና በመንፈስ ቅዱስ በማደስ ወደ መዳን እምጥቶታል።
ገና ሃጢያተኞች ሳለን፣ ገና ማስተዋሉ ሳይመጣልን፣ ገና ከነእስራታችን ሳለንና ኩነኔ ውስጥ ሆነን እያለ እግዚአብሄር ደህንነትን አወጀልን፤ እርቅንም ሰጠን። አዋጁ መልካምና ለእኛ የምስራች ነው፣ ክርስቶስ በመስቀል ሞቶልሃል የሚልም ነው።
‘’በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር። እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።’’(ኢሳ. 53:8-10)
አይሁድ ግን ክርስቶስ ስለ ሕዝብ ኃጢአት በግፈኞች በትር ተመትቶ በፍርዳቸው ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ አላስተዋሉም፣ እንዲያውም በመስቀሉ ላይ መከራን ሲቀበል ሳለ አሹፈውበታል።
የእግዚአብሄርን አሰራር የማያስተውሉና በፍርድ ስር ያሉ ጨካኝ አይሁዶች ከክፉዎች ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር።
ለምንድን የእግዚአብሔር ኃይል ሆኖአል
የመስቀሉ ቃል ለተቀበልነው የእግዚአብሄር ልጆች መዳን ሰጥቶናል፤ ላመንነው የጌታ ኢየሱስን የፍቅር ክፍያ እንድንቀበል አስችሎናል፤ ይህ በእምነት የተቀበልነው የርሱ የመስቀል ስራ በህይወታችን ውስጥ ምህረት፣ በረከትና ዘላለማዊነትን ተክሎአል። እግዚአብሄር ለእኛ ምህረት እንዲያደርግ ዋጋ ከፍሎአል፣ ያም አንድያ ልጁ ላይ ፍርድ እንዲወድቅ መፍቀዱ ነበር፤ በእርሱ ላይ የወረደው ፍርድ እኛን ነጻ እንድንወጣም አደረገ። በዚህ ውሳኔው እግዚአብሔር እኛን ለማዳን እርሱን በደዌ ያደቅቀው ዘንድ እንደፈቀደ ይታያል፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት እንዲያደርግና ሰዎችን ከማይጠፋ ዘር እንዲወለዱ በማድረግ በነርሱ ህይወት የጀመረውን ስራ በልባቸው አድሮ እንደሚያስቀጥልም ያሳያል። እኛ የምናምን ክርስቶስ ሃጢያተኛ ሆኖ እንደተሰቀለ ሳይሆን በሞቱ ሃጢያታችንን እንደሻረልንና ጽድቅን እንደሰጠን ተረድተናል።
‘’ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን’’ (ሮሜ.5:6-10)
ክርስቶስ የእግዚአብሄር ሃይል ሆኖ ነጻነት ሰጥቶናል፣ በርሱ ያገኘነው ነጻነት በአለምና በአጋንንት ላይ ድል ማድረግን የሚሰጥ፣ ስጋችንንና መንፈሳችንን ለጽድቅ እንድናስገዛ ወደዚያ የሚመራም ነው። ነጻ ህዝብ ከአጋንንት እስራት ነጻ ወጥቶ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላን አጋንንትም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፣ እኛም ይህን አምነናል።
የእግዚአብሄር አሰራር ከአለም ስሌት እጅግ የላቀ በመሆኑ የጥበበኞች ጥበብ ከንቱ ሆኖአል፣ የአስተዋዮችን ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። የመስቀሉ ቃል የሰውን አእምሮ የሚያልፍ ጥበብ ስለተገለጠበት በስጋ ማስተዋል ሊደረስበት ከቶ አልተቻለም፣ በዚህም ምክኒያት የአለም አዋቂ ሊዳስሰውና ሊጨብጠው ባዳገተው መንፈሳዊ እውቀት ተሰናክሎአል፤ ስለመንፈሳዊ ነገር ሳይረዳ በግምት የሚተነትነውና የሚፈላሰፈው የአስተዋዮች ማስተዋል ከፍ ባለው በእግዚአብሄር እውቀት ተሽሮአል፣ እግዚአብሄር እንዲህ ስላለ፦
‘’ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን?በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው። ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፥ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። ነገር ግን፦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው። ነገር ግን፦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው።’’(1ቆሮ.1:22-33)