የመሰረቱ ማጠንጠኛ (2…)

የእግዚአብሄር ፈቃድ

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ በመንፈሳዊ ህይወታችን መቆምያ፣ መጽኛችንና እምነታችንን በድል ማጠናቅቅ የሚያስችል የስኬታችን መሰረት ነው። እርሱ ሲናገር ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም ብሎአል። ጌታ ኢየሱስ ለእኛ የሁሉ ነገራችን መሰረት ነው፦
”እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ” (ኤፌ2:10-17)
እኛ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን አዲስ ሰው እንደመሆናችን የማንነታችን መሰረት የሆነ እርሱን በመረዳት ልንከተለውና በእምነት በእርሱ ልንኖር ይገባል።
-እምነት መሰረቱ ክርስቶስ ነው
አህዛብ ወደ እግዚአብሄር መቅረቢያ፣ መታረቂያና ምህረት መቀበያ ተስፋችን ክርስቶስ የሆነበት ምክኒያት ያለ እርሱ ወደ እግዚብሄር የምንቀርብበት ሌላ መንገድ ስለሌለ ነው፤ የጌታችንና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ባይኖር ቁጣው ያጠፋን ነበር፤ የእርሱ ስጋ ባይቆረስ ኖሮ ከባለ ተስፋዎቹ አይሁድ ጋር መንግስቱን የምንካፈልበት መንገድ አይገኝም ነበር። በርሱ የተቀበልነው አዲስ የተስፋ መሰረት ግን የእምነታችን መሰርት ሆኖልናል፦
”እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፥ የምንስት፥ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፥ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፥ የምንጣላ፥ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን። ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው።” (ቲቶ3:3-7)
ጌታ ኢየሱስ የእምነታችን ጀማሪም ፈጻሚም እርሱ ብቻ በመሆኑ እርሱን ከማመን ውጪ ምን ልናደርግ እንችል ኖሮአል?
ራሳችንን መለስ ብለን ስናይ ጌታችንን የምናመሰግንበት ምክንያት እንደምን ታላቅ እንደሆነ እናስተውላለን፦ እንደተባለው በቀደመው ህይወታችን ጽድቅን የማናውቅ፣ አምላክንም የማናውቅ ( የአብረሃምን አምላክ ማለት ነው)፣ ምህረትና ኩነኔን የማናስተውልም ነበርን፤ ስለዚህ ቅዱሱን አምላክ ፈርተንና አስተውለን የማንታዘዝ ነበርን፣ ባሳባችንና በውሳኔያችንም የምንስት ነበርን፣ ለስጋና ለአለም ምኞት ተላልፈን የተሰጠን ነበርን፤ ለልዩ ልዩ የስጋ ፍላጎት መሙያ ለሆነ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ ነበርን፣ የልብ ክፋት የተቆጣጠረንና የእርኩስ መናፍስት መገለጫ በሆነ የምቀኝነት መንፈስ እየተነዳን የምንኖር፣ እርስበርሳችን ከልብ ይቅር የማንባባል በቂም የታጠርን ስለሆንን የምንጣላ ነበርን፣ ደግሞም እርስ በርሳችን የማንስማማ፣ እርቅን የማናውቅና የምንጠላላ ነበርን። ነገር ግን በዚህ አስፈሪ የፍርድ ህይወት ሆነንና ከእግዚአብሄር እጅግ ርቀን ሳለን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ በኩል በተገለጠ ጊዜ ከፈሰሰልን ደምና ከተቆረሰልን ስጋ የተነሳ እርቅ ከአምላካችን ተቀብለን ለመዳን የሆነውን ጸጋም ለማግኘት እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን።
አዎ፣ ጌታ ኢየሱስን የምናምነው መታጠብ የሚገባውን አጥቦ መታደስ የሚገባውንም አድሶ በእግዚአብሄር ፊት ስላቀረበን፣ የመንግስቱ ወራሽ ስላደረገንና የአብረሃም ተስፋ ተካፋዮች እንዲህ ስላደረገን ነው።
-የዘላለም ህይወት መሰረቱ ክርስቶስ ነው
ጌታ ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ አለ፦
”እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” (ዮሐ.6:47-51)
ምንም ይሁን ምን ወይም ከየትኛውም የአለም ክፍል ይገኝ ብቻ ከአዳም የተገኘ የሰው ዘር የተባለ በሙሉ የዚህን ምድር ህይወት ይኖር ዘንድ አንዴ ተፈቅዶለታል፤ ህይወቱ ግን ከዚህ ምድር ባሻገር ያለውን ዘላለማዊ ህይወት እንዳያገኝ የዘላለም ፍርድ የሚባል እርግማን ታዝዞበታል። ይህ እርግማን የሃጢያት ውጤት በመሆኑ ሃይሉን የሚሽር አንድ መፍትሄ እስኪገለጥ ድረስ ሰውን የሚያተርፍ መንገድ ለየትኛውም ትውልድ አልነበረም። ሰው በዚህ ብርቱ ፍርድ ውስጥ ሳለ ነው እግዚአብሄር በስጋ የተገለጠው፣ አማኑኤል የሆነው፣ ሰውን ተጠግቶ ሊቀርብና በመሃከሉ አድሮ ወደ እርሱ መምጫን መንገድ ሊዘረጋ የወሰነው፣ ከጨለማ ሊያወጣውና ጸጋን ሊሰጠው የወሰነውም።
ጌታ ኢየሱስ ይህን አስረግጦ ነግሮናል፦
”ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።” (ዮሐ.3:14-17)
የሙሴ ስም እዚህ ስፍራ የተጠቀሰበት ዋና ምክኒያት የጌታ ኢየሱስን በመስቀል ላይ ስለሃጢያተኞች ሲል መዋል በትንቢቱ ያመለከተ ሰው ስለነበረ ነው፤ በሌላ በኩል ሙሴ ሰው ታዝዞ በህይወት መኖር የሚችልበትን ቃል የተቀበለም ሰው ነው። የሙሴን የተሰቀለ እባብ ያመነ ከተናዳፊው እባብ እንደዳነ ሁሉ መስቀል ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን የሚያምን ከዘላለም ሞት የሚድንና የርሱን ህይወት እንደሚካፈል አመልካች ነው፤ ሙሴ ህዝቡ በህይወት ይኖሩበት ዘንድ የተቀበለውን ህግ ቢታዘዙ በህይወት ይኖሩ እንደነበር ሁሉ ለአለም ደህንነት እግዚአብሄር የሰጠውን አንድያ ልጁን የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት ዋስትና አለው።
ዘዳ.4:1-14 ”አሁንም፥ እስራኤል ሆይ፥ እንድታደርጉአቸው በሕይወትም እንድትኖሩ፥ የአባቶቻችሁም አምላክ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፥ የማስተምራችሁን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ። እኔ ያዘዝኋችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም።… እግዚአብሔር:- ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፥ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ ልጆቻቸውንም ያስተምሩ ዘንድ ቃሌን አሰማቸዋለሁ ብሎ በተናገረኝ ጊዜ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በኮሬብ በቆምህበት ቀን ዓይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አስታውቀው። … ታደርጉትም ዘንድ ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን አሥሩን ቃላት ነገራችሁ፤ በሁለቱም በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው።”
ህይወት በአምላክ ዘንድ ያለመጥፋት ነው፤ ይህ ያለመጥፋትም በኢየሱስ ብቻ ሆኖአል፣ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ… ስለሚል፤ ህይወት ከእግዚአብሄር ጋር መኖር ነው (ሮሜ.6:7-8)፣ ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን ስለሚል። ሕይወት መቀበል ብቻ ሳይሆን በሕይወት እንድንኖር ስለሚያስፈልግም በእርሱ አምኖ ከእርሱ ጋር ለሃጢያት መሞት ግድ ነው።
-የቤተክርስቲያን መሰረት ክርስቶስ ነው
ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው መሰረትዋ በሆነው በክርስቶስ ላይ ነው። የቤተክርስቲያን መነሻ ክርስቶስ ነው። ከእርሱው ተነስታ በእርሱ ላይ ታድጋለች፣ እያደገች መጽናት ስትቀጥል መጨረሻዋን በእርሱ ላይ ትደመድማለች።
ማቴ.16:15-18 ”እርሱም፡- እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።”
ቤተ-ክርስቲያን እንደ እግዚአብሄር ህዝብ በክርስቶስ ፍቅር ላይ ልትመሰረትና እርሱ በሚሰጣት ጸጋ ልታድግ ይገባታል፤ እርሱ የሰላምዋ መሰረት በመሆኑ በቃሉ ላይ በመታነጽ አንዳች ችግር በመሃልዋ ሳይፈጠር አንድነትዋ ተጠብቆ ዳግም እስኪመጣ ልትጸና የግድ አስፈላጊ ነው፤ እርስዋ በጌታ ትምህርት ላይ ስር ሰድዳ ልትኖርና በትምህርት ነፋስ ሳትናወጥ ልትቆም ስለሚያስፈልግ በእርሱ ላይ የሚያጸናትን የጌታ ፈቃድ ልትከተል ይገባል።
ሮሜ.12:1-2 ”እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው።
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።”
ቤተክርስቲያን የአካሉ ብልት ውህደት ሆና ከርስዋ መሃል ካለ አንደኛው ብልት አንጻር ስትታይ አንድ ሰው በመሰረቱ በክርስቶስ ላይ እንዲጸና ፈቃዱን በማወቅና በመረዳት አምላኩን የሚያስደስበትን ነገር ሁሉ መከታተልና መፈጸም ይገባዋል። እግዚአብሄር በዚህ ልጁ የሚደሰተው እርሱ ራሱን በሙሉ ፈቃድ ወደ አምላካዊ ፈቃድ ሲያቀርብና በጸጋው ታግዞ መላ እርሱነቱን (ስጋውን ነፍሱንና መንፈሱን ጨምሮ) ቅዱስ መስዋእት ሊያደርግ ሲወስን ነው። አንድ አማኝ ደቀመዝሙር ሆኖ ለማደግ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማስተዋል ይገባዋል፤ የእግዚአብሄር ፈቃድ ምን እንደሆነ ያውቅም ዘንድ በልቡ መታደስ ሊለወጥ እንደሚገባ ቃሉ ያስተምራል።
1ተሰ.5:22-24 ”ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ። የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል።”
-የፍቅር መሰረቱ ክርስቶስ ነው
ስጋን የሚመች ውዴታ እንዳለ ሁሉ መንፈስ ላይ የሚገለጥ ፍቅርም አለ፤ ፊተኛው ስጋን ለማርካት በስሜት የሚሮጥበት ነው፤ በመንፈስ የሆነ ፍቅር ግን መለኮታዊ ነው፣ ነፍስንና መንፈስን የሚይዝ ሰውን ለአምላክ ሞገስ የሚያዘጋጅ ነው። መለኮታዊ ፍቅር መሰረቱ ክርስቶስ ነው፦
ሮሜ.5:6-8 ”ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።”
ክርስቶስ ሁሉ ነገራችን እንዲሆን ተሰጥቶናል:: በራእ.1:4-6 ሲናገር፦
”…ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።”
መውደድ የቻልነው አስቀድሞ በእርሱ በመወደዳችን ብቻ ነው፤ ኢየሱስ ሲወድ በአንድነት የምንወድበትንም መንፈሱን የሰጣልና። ማንም ሰው ከእግዚአብሄር ውጪ ሆኖ ከእግዚአብሄር የሆነ ፍቅር አለኝ ማለት አይችልም። ፍጹም ፍቅር ከእግዚአብሄር ስለሚገኝ የተጠማ ከእግዚአብሄር ያገኘዋል።
በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም የተባለው እግዚአብሄር በእኛ ሳያፍር በውዴታ ትልቅ የተባለውን ስጦታ (መንፈሱን) በውስጣችን ማፍሰሱ፣ እኛን በፍቅሩ መቀበሉና ወዳጅ ማድረጉ ነው።
እግዚአብሄር መለኮታዊ ፍቅር ሊያሳውቀን፣ ሊያስተምረንና ሊሰጠን ልጁን ወደ አለም ልኮአል። እንግዲህ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ሊሆን ወስኖ በስጋ ከተገለጠና ፍቅሩን ለሰው ልጆች ከሰጠ ከዚህ የክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? ሃዋርያው ጳውሎስ የፍቅሩ ጉልበት ከሚሆንብን መከራ በላይ እንደሆነ ይናገራል፣ ጭንቀት ቢፈጠር ከዚያም በላይ ነው፣ ስለ ስሙ ስደት አለ፣ የፍቅሩ ጉልበት ግን የስደቱን ግፊት እንድንቁዋቁዋም ያስችላል፣ ራብም ቢሆን ይሸነፋል፣ ራቁትነት ቢሆን በፍቅሩ ትግስት የሚታለፍ ነው፣ በተቃዋሚ ምክኒያት ፍርሃት ቢገዛን በፍቅሩ ምክኒያት መታገስ ይሆናል፣ ስለርሱ ሰይፍ ቢከተል በፍቅሩ መስዋእትነትን መቀበል ይቻላል፤ ይህን ስለተረዳን ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው፣ ይላል ሃዋርያው። ጨምሮ ሲናገር፦
”በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።”
”ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።”(ራእ.1:4-6)