መሰረት ማለት?
መሰረት መነሻ ነው፣ መሰረት መቆሚያ ነው፣ መሰረት የእድገት መጀመሪያ ነው፣ መሰረት ስር ነው፣ መሰረት መስፋፊያ ነው፣ መሰረት መታመኛ ነው፣ መሰረት አቁዋም ነው፣ መሰረት መታወቂያ ነው፣ መሰረት ምንጭም ነው።
እያንዳንዱ ነገር መሰረት ያለውና በዚያ ላይ የቆመ፣ የታነጸና ያደገ ነው። ለምሳሌ የምድር መሰረት በእግዚአብሄር ስለተመሰረተ የማይናወጥ ሆኖ ይኖራል። እንዲያውም መሰረቷ ቢናወጥ የሚያናውጣት ሌላ ሃይል ሳይሆን ራሱ የመሰረታት አምላክ ብቻ መሆኑን ቃሉ የናገራል። ሰለስራው ሲናገርም፦
ዕብ.1:10-12 ”… ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም” ይላል።
እግዚአብሄር ለሚወዱት ግን የማትናወጥን ከተማ መስርቶአል። በዕብ.11:8-10 እንደተጥቀሰው፦
”አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።”
ሰው መኖሪያ ቤቱን መገንባት ሲጀምር ከመሰረቱ ይነሳል። መሰረቱ የቤቱን ልክ ይወስናል፣ ጽናት ይወስናል፣ እድሜ ይወስናል። መሰረቱን የጸና ያላደረገ ቤት ሰሪ ኪሳራ ይገጥመዋል። ስለዚህ መሰረት ለሚሰራው ስራ በጽናት መታሰቢያ እንዲኖር የሚያስገድድ ነገር ነው ማለት ነው።
የመንፈሳዊ መሰረቶች ነገር
በ1ቆሮ.3:9-17 ላይ ስለ መንፈሳዊ ነገር ግንባታ ሲናገር፦
”የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል። ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።”
የእምነታችን መሰረት የአዲስ ህይወት መነሻ ይሆነን ዘንድ በእግዚአብሔር ጸጋ በተቀቡና መንፈሳዊ የአናጺ አለቃ በሆኑ ሃዋርያት በጥንቃቄና ፍጹም በሆነ መንገድ ተመስርቶልናል። መሰረቱ በአለም የትምህርት ነፋስ ላንናወጥ መቆሚያ ሆኖ ሳንፍገመገምም እንድንጸና ያደረገ ነው፤ መሰረቱ በመንፈሳዊ ህይወት አድገን እንድንጎለምስ የእድገት መጀመሪያ ሆኖ እያገለገለን ነው፤ መሰረቱ ከኢየሱስ ለሚፈሰው የጸጋ መንፈስ ስር ሆኖ የሚያገለግል ነው። መሰረቱ ላይ ያልቆመ ሃይማኖት የተንሳፈፈ ነው፣ የትምህርት ነፋስም የሚጠርገው ነው፤ የጸናው መሰረት ላይ የታነጸው ግን የሚያድግ ነው፣ የሚሰፋም ጭምር ነው። መሰረት በኢየሱስ ላይ ስለሚያኖር መታመኛ ነው። መሰረት ከኢየሱስና በኢየሱስ የሆነን ነገር ብቻ ስለሚሰጠን የጸና አቁዋም ሆኖ ያገለግለናል። ይህ መሰረት የአማኞች ብቸኛ መታወቂያ ነው፣ በኢየሱስ ትምህርት ላይ የተመሰረቱትን ቀደምት አማኞች ማህበረሰቡ ለይቶ ያውቃቸው እንደነበር ቃሉ ይመሰክራል። ይህ መሰረት ጌታችን ኢየሱስ በመሆኑ የህይወታችን ምንጭም ነው።
ሃዋርያት በትምህርታቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ደህንነት በዚህ አለም ላይ በመትከላቸው የመሰረቱ መስራች ተብለዋል። ይህ መንፈሳዊ መሰረት ለእያንዳንዱ አማኝ የሚበቃ ርስት በመሆኑ እያንዳንዱ በመሰረቱ ላይ የራሱን ቤት እንዲያንጽ ታዞአል። መሰረቱ ኢየሱስ በመሆኑ የመሰረቱ ይዘት አይለወጥም፣ ይልቁንም ቤት ሰሪዎቹ እኛ መንፈሳዊ ቤታችንን በምን እንድናቆመው ማስተዋል ይጠበቅብናል እንጂ። የምንሰራው ቤት ለእግዚአብሄር ማደሪያ ይሁን እንጂ ቤቱ ማለት የእኛ የራሳችን መንፈሳዊ ህይወት ነው። ስለዚህ በምን አይነት ሁኔታና ነገር ህይወታችን እየተገነባ ይሆን? ይሄ ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል፤ ቃሉ ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል ይላልና።
የሁለት ጌቶች መሰረት
የገዢነት ስርአት በአገዛዝ ስልጣን ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የገዢው ባህሪ ግን ወሳኝ ነው። ጌትነት በተገዢ ላይ መሰልጠን ሲሆን የተገዢው ፈቃድም ለጌታው የተገዛ ነው። ገዢው ሩህሩህ እንደየሱስ፣ ጨካኝም እንደ ገንዘብ ሊሆን ይችላል። የጌታ መልካምነት በመንፈስ ቅዱስ ሲሰራ የገንዘብ ክፋት በእርኩስ መንፈስ አማካይነት ይገለጣል።
ማቴ.6:24 ”ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።”
ጌታ ኢየሱስ የመልካም ሁሉ መሰረት ሲሆን ጌታ ገንዘብ የሃጢያት ሁሉ መሰረት ነው፤ ዛሬ ጌታ ገንዘብን ክዶ ጌታ ኢየሱስን የሚያነግስ ማን ነው?
በአንድ ወቅት አንድ ገንዘብ ጌታ የሆነበት ሰው ወደ እውነተኛው ጌታ ኢየሱስ መጣ፤ አሳቡ የነበረው በልቡ ያነገሰውንና ጌታ ያደረገውን ገንዘብ በውስጡ ሰውሮ ኢየሱስን ተጭማሪ ለመቀበል ነበረ፤ በልቡ ሁለቱን ጌቶች አስገብቶ በህይወቱ በአንድ ስፍራ እያኖራቸው ሊቀጥል ተመኘ። ከጌታ ኢየሱስ የተነገረው እውነት ግን የልቡን ምኞት ተቃረነበት፣ ሁለተኛውን ጌታ በተጉዋዳኝ ሊያስኬድ እንደማይችል በዚያም ስላወቀ አዘነ።
”እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና፦ ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። እርሱም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና፦ አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው። ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን፦ ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ፦ ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው። ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል አላቸው። እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው፦ እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል? ተባባሉ። ኢየሱስም ተመለከታቸውና፦ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ።” (ማር.10:17-27)
በእርግጥ በእኛ ላይ ከነገሰውና ፊትለፊት ሆኖ ከሚመራን ከገንዘብ ጌትነት መላቀቅ በእግዚአብሄር ብቻ ይቻላል፣ በራስማ አይሞከርም።
1. መልካም መሰረት ክርስቶስ
-ክርስቶስ የእምነታችን መሰረት ነው፦
እግዚአብሄር የመረጠው ህዝብ በጭለማ ታውሮና በሲኦል መሰረት ላይ ቆሞ ባለበት ወቅት እግዚአብሄር ተገለጠና አንድ ታላቅ ተስፋን ለህዝቡ ገባ፤ ያም ተስፋ ከጨለማው መሰረት ወደ ብርሃንና ህይወት ወደ ሆነ መሰረት የሚለውጥ ተስፋ ነበር። ህዝቡ የሚያጠፋውን ካለማወቁ የተነሳ በሚውጠው ጉድጉዋድ ላይ ቆሞ በእርሱ በልብ ሙላት ታምኖአል፤ ይህም የተጠራውን ህዝብ እውርነት የሚገልጥ ጥፋት ነበር። እግዚአብሄር ግን ሩህሩህ በመሆኑ ይህን ጥፋት ሊያፈርስና ለዘላለም የሚቆሙበትን የደህንነት መሰረት (ክርስቶስን) ሊሰጣቸው ቃል ገባ። እንዲህ አለ፦
”ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፦እናንተም፦ ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፥ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፤ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም ስላላችሁ፥ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ፤ የሚያምን አያፍርም። ለገመድ ፍርድን ለቱንቢም ጽድቅን አደርጋለሁ፤ በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፥ ውኆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ። ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፥ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፤ የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ።” (ኢሳ.28:14-18)
በእስራእል ምድር ላይ በኢየሩሳሌም ውስጥ የሚኖሩ እግዚአብሄር ህዝቡን በጽድቅ እንዲመሩ የሾማቸው አለቆች እርሱ እንዲሰማ እስከማይመስላቸው ድረስ ደንዝዘው ይዘብቱ ነበር፤ የሚያይ እግዚአብሄር ግን ሲያይ የህዝቡ ጠላት እንደሚያየው ለክፉ አልነበረም፤ እርሱ በወቅቱ በዙሪያቸው ጉዳይ ብቻ እንደታጠሩት የህዝቡ አለቆች አላደረገም፣ እንደ አምላክነቱ ግን እግዚአብሄር ህዝቡ ከተያዘበት ወጥመድ የሚያመልጥበትን እቅድ አወጣ። አለቆች አሉ፣ ቃልኪዳናችን ከግዚአብሄር ጋር ሳይሆን ከሞት ጋር ነው፤ ይህ ቃል እግዚአብሄርን የሚክድ መንፈስ ሲሆን ህይወታቸውን ደግፎ የያዘውን አምላክ የሚያስቆጣ ድርጊት ሆኖም ነበር። ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለውን መንፈሳዊ ትሥሥር ሲበጥስ ከሞት ጋር ሌላ የግንኙነት ገመድ እንደሚቀጥል ስራቸው ያሳያል። እነዚህ አለቆች የጥፋት ውሳኔ ሞትን ለምን አልፈሩም? የእግዚአብሄር ፍርድ እንዴት ቀለለባቸው? ምንጊዜም ሊመጣ ያለው ፍርድ የሰው ልጅ ካልታየው፣ በአለም ላይ የሚገጥመው ፈተና ካልተሰማውም ከጥፋቱ ጋር ተስማምቶና ተማምሎ ተቀምጦአል ማለት ነው።
የእግዚአብሄር አዋጅ፣ በጽዮን መሰረት ሊጣል እንደሆነ በህዝቡ ጆሮ ተነገረ፦ ጠባብ፣ ስንፍናና ጥፋት ካለበት ሰው ከመሰረተው መሰረት ይልቅ ተስፋ የሚጣልበት ጥብቅና የማይነቃነቅ መሰረት (ክርስቶስ) ለእስራኤል የምስራች ተብሎ ተነገረ። መሰረቱ የሚጣለው በሌላ ስፍራ ሳይሆን አለቆች በዘበቱበት በዚያው በጽዮን አደባባይ ነበር፣ እነዚያ አለቆች ከሞት ጋር ቃለኪዳን በገቡበት ስፍራ/ በዚያው ስፍራ ህይወት ሊመሰረት ተስፋ ገባ።
በአዲስ ኪዳንም የመሰረቱ ድንጋይ ክርስቶስ እግዚአብሄር ቃል እንደገባው ተገልጦአል፣ ከእርሱ ጋር የነበሩት ሃዋርያቶችም ስለእርሱ በቃላቸው መስክረዋል፦
1ጴጥ.2:4-10 ”በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ፥እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። በመጽሐፍ፦ እነሆ፥ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም:ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ ክብሩ ለእናንተ ለምታምኑት ነው፤ ለማያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የዕንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ፤ የማያምኑ ስለ ሆኑ በቃሉ ይሰናከሉበታልና፤ ለዚህ ደግሞ የተመደቡ ናቸው። እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።”
ሆኖም ታሪክ ራሱን ሲደግም በዚያን ጊዜ (በነቢዩ ዘመን ) እንደነበረው ያለ ትውልድ በአዲስ ኪዳንም በእስራኤል ተፈጥሮ ስለነበር በጌታ ኢየሱስ መገለጥ ያላመኑና የተሰናከሉ እጅግ ብዙ ነበሩ።
-ጸጋ መሰረቱ ክረሰቶስ ነው
ክርስቶስ በመንፈሳዊ ስፍራ የምንቆምበት፣ በህይወት የምንኖርበት፣ በእግዚአብሄር ፊት ያለነቀፋ የምንመላለስበት ብቸኛ መመኪያችን ነው። ስለዚህ በማንኛውም ምክኒያት ይሁን በየትኛውም ጊዜ እርሱ ከእኛ ከተለየ የእኛ መንፈሳዊ ህይወት አበቃለት ማለት ነው። የእስራኤል መሪዎች እንዳሉት ያለክርስቶስ መሆን በሲኦል ደጅ መቆም ነው፣ የህይወት መሰረት እርሱ ከሌለ መቆሚያም አይኖርም። በህይወታችን እርሱ እንዲህ አስፈላጊነቱን የሚያጎላውም ከእርሱ ወደ እኛ የሚፈሰው/ ከሙላቱ ወደ እኛ የሚመጣው የጸጋ ሃይል ነው። ጸጋውን በመንፈሱ የሚሰጠን አምላክ አለምን ወደ ሲኦል ከሚስበው የሞት ሃይል አላቅቆ ወደ እግዚአብሄር መገኛ አካባቢ ከፍ በማድረግ የሚያመላልሰን ጸጋው ሰጥቶናል። ጌታ ኢየሱስ ባያገኘን ጸጋው ከየት ይገኝ ነበር?
ዮሐ.1:14-17 ”ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።”
በአለም ላይ ከባድ ዝለት አለ፦ የምናየው የሚያዝል ነው፣ የምንሰማውም እንዲሁ። ከዚያ ዝለት የሚነጥቀንና እግዚአብሄር በፊታችን ያኖረውን የመንግስቱን ተስፋ የሚያስጭብጠው የጸጋው ጉልበት ነው።
በአለም ላይ ማታለልና ሽንገላ አለ፤ በዚህ መንገድ ህይወታችንን ከእግዚአብሄር ቁርኝት ለመንጠቅ ሰይጣን ይመላለስበታል። የእኛ መመኪያ ያለን ነገር ሳይሆን የጸጋው ሃይል ብቻ ነው። ከዚህ በመለስ ካላስተዋልን በቀር ስጋችን በቀላሉ በአለም አቅርቦት የሚጠለፍ ነው።
አለምን ጠንቅቆ ያልተረዳ አማኝ እጅግ ይጎዳል፤ ምክኒያቱም የምናየው ሁሉ የሚመለከተን ይመስለንና እጃችንን እናስገባበታለን። በአለም በደህንነት መኖር የምንችለው እንደ በጎ ሰው ተገቢውን ነገር በማድረግ ብቻ ነው፣ ተገቢውን ነገር የሚያውቀውም ልንመራበት የሚገባው የእግዚአብሄር ቃል ነው፤ ስለዚህ ስንመላለስ እንዴት ይሁን የሚለውን ቃሉ ያማክረን፣ ሰው አይምራን፣ የራሳችን ስሜት ራሱ እንዲመራንም አንፍቀድ። ይህ ግን ብርቱ ትግል አለው፣ አሸናፊው ግን ጸጋው ነው።