በመመለስ ውስጥ ከምናገኛቸው አስፈላጊ ነገሮች መሃል የሚከተሉትም ይገኛሉ፦
መመለስ ወደ ጽድቅ ይመለሳል፦
‘’እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም።’’ (ሃስ. 3:21)
የመሸሽ ውጤቱ ብዙ ነው፣ አንዱ ደግሞ ከጽድቅ መውደቅ ነው፣ ጽድቃችን ክርስቶስ ብቻ ስለሆነ ከእርሱ በሸሸን ሰአት ከሰጠን ጽድቅ እየሸሸንና እየራቅን ሄደን በጨለማ ውስጥ የምንሰወር ነው የሚሆነው። ጨለማ የአመጽ፣ የሃጢያትና የመተላለፍ ዋሻ በመሆኑ የእግዚአብሄርን በጎ ነገር ከዚያ ልናገኝ የምንችልበት አጋጣሚ አይኖርም፤ ወደመመለስ ስናመራ ታዲያ ወደ ብርሃን ስለምናመራ በዚያ ውስጥ ኢየሱስን አግኝተን የጠፋብንን የማግኘት አጋጣሚ ይፈጠራል።
‘’ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።’’ (1ቆሮ. 6:9-11)
ከአመጽ ይተርፋል፦
‘’አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና። ብዙ ጊዜ በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት፥ ለሚያርሱአትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል፥ ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና፤እሾህና ኵርንችትን ግን ብታወጣ፥ የተጣለች ናት ለመረገምም ትቀርባለች፥ መጨረሻዋም መቃጠል ነው።’’ (እብ. 6:5-9)
ሰው ወደ ኢየሱስ ሲመጣ ከሞትና ከመርገም የሚያመልጥ ሲሆን ወደ ወጣበት የተረገመ አለም ውስጥ ሲገባ (የመርገም መናፍስት መሃል ሲገኝ) አምልጦት የነበረው ወጥመድ ዳግም ይይዘዋል፣ ይሰብረዋል፣ ያስቀረዋል። ሰው በዚያ በወጥመድ ተይዞ ባለበት ስፍራ ልቡ በአምላክ እርዳታ ከቀና ከዚያ አመጽ መንፈስ ይተርፋል፤ ባለበት ከቀረ የያዘው ይውጠዋል።
ያ ሳይሆን ቀርቶ ሰው እግዚአብሄር የሰጠውን ጸጋ ቸል በማለት፣ አምላኩን በማሳዘን፣ ከርሱ የተቀበለውን ጸጋ ምናምን አድርጎም ቢቆጥር ሌላ መንፈስ ስለሚነዳው በትእቢት ላይ ወድቆ ለመርገም ይጋለጣል። ጸጋው መኖሪያችን እንጂ አቅልለን የምንይዘው ፈጽሞ ሊሆን አይችልም።
ወንድሞችን ያንጻል፦
‘’በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር። ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም። ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ።በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤ ነገር ግን፦ ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።’’ (ገላ. 1:14-24)
ከሞት ወጥመድ ያመለጠ የምስጋና ሰው ይሆናል፤ አይቶት የተመለሰው አስፈሪ ገጠመኝ ያን እንዲፈራ አምላኩን የሙጥኝ እንዲልና አመስጋኝ እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ ዳግም ለተቀበለው ምህረት ስለሚጠነቀቅ ለብዙዎች መነቃቃትን ይፈጥራል።ብዙ አማኞችም ጠፍቶ የነበረው አሁን ግን የተገኘውን እንድማቸውን እየተመለከቱ አባታቸውንና አምላካቸውን ያመሰግናሉ።
ለሌሎች መዳን በር ይከፍታል፦
የዳነ የሌሎች ህመም በብርቱ ስለሚሰማውና እርሱ ራሱ ያን ስለቀመሰ ለነርሱ ይማልዳል፣ አጥብቆም ይጸልያል፣ እግዚአብሄር እርሱን እንደረዳ ስለሚያምንም አምላኩን ስለስራው አስቀድሞ ያመሰግናል፣ ስራውንም በግልጥ ይመሰክራል። ጠፍቶ የተመለሰው ከሞት ወደ ህይወት ስለተመለሰ በሞት አገር ላሉት እጅግ ያዝናል፣ ያለቅሳልም። ከአምላካቸው ተለይተውና በአለም ደን ውስጥ (አለማዊ ስርአት፣ ልማድ፣ አመጻ፣ የመሳሰሉት ውስጥ) ተሰውረው የጠፉትን ያሉበት ድረስ ተከታትሎ የርሱን መዳን ያሳያቸዋል፣ የታደገውን አምላክ መንገዱን ይመራቸዋል፣ የእግዚአብሄርን ምህረት አውጥቶ እየተናገረም የህይወትን ጣእም ያሳያል። መዳን በብዙ መልኩ ወደ ተሻለው ምርጫ እንድናተኩርም ስለሚያደርግ ለሌሎች ትኩረት እንድንሰጥ፣ ለህይወታቸው ግድ እንዲኖረን ያስገድዳል፣ በዚህ የፍቅር ግዴታ የነፍሳት ፍቅር ይዞን ያለንን ለነርሱ እንድናፈስ ያደርጋል።
ከእግዚአብሄር ጋር በንሰሃ እርቅ ያደረጉ በአዲስ ጉጉትና በታደሰ መንፈስ ሲንቀሳቀሱ የደከመን የማንቃት ችሎታ አላቸው፣ የጌታ የምህረት እጅ ስትንቀሳቀስባቸው በጉልህ ስለሚታይ ብዙዎች በአድናቆት እንዲነሱ ያደርጋቸዋል። ሲንቀሳቀሱ ያንቀሳቅሳሉ፣ ሲወጡ ስበው ያወጣሉ፣ ሲያመልኩ ያስመልካሉ፣ ሲመሰክሩ በሃይል ይሆናል፤ አዲስ ሃይል ስለተቀበሉ፣ የአምላካቸው እጅ በምህረት ነጥቃ ስላንቀሳቀሰቻቸው በህይወታቸው አዲስ ታሪክ ይሆንላቸዋል።
ወደ አባቱ ቤት በንሰሃ የተመለሰ የማረው አባቱን ያገለግላል፤ ያዳነውን አምላክ ያመልካል፣ ያስመለጠውን ጌታ ይከተላል፣ ላደሰው ጌታ ይገዛል። መመለስ ነጻነትንም ስለሚያስመልስ በወገኖች መሃል በፍቅር ያመላልሳል፣ የተመለሱ ወገኖቻቸውን በፍቅር ያገለግላሉ።
ከታላቁ ጥፋት የወጡ በትንሹ የተጠየቁትን ሊያደርጉ ፈጽሞ አይሰስቱም፤ የመዳን ታላቅነት ያላስተዋል ግን ማመስገንም ያዳግተዋል። ለዚህ ሰው ግን መዳኑ ፍጹም ሆኖ እንዲበራለትም በንሰሃ የተመለሰ ሰው ትልቅ እገዛ ማድረግ ይችላል።
ለምክር ይጠቅማል፦
በቤተክርስቲያን ለሚያጋጥሙ የተለያዩ የህይወት ገጠመኞች በንሰሃ የተመለሱ ሰዎች ምክር ወሳኝ ነው፤ ለመንሸራተት ዳር ዳር የምትልን ነፍስ መገሰጽ ይችላል፣ የሚጠብቃትን ጨለማ ሊያሳያት ይችላል፣ በርሱ የሆነውን በማሳወቅ በቶሎ ወደ አምላኩ እንዲመለስ ይረዳል።
1.አለማውያን ሰዎች ወደ ጌታ ኢየሱስ ሲመጡ
‘’በዚያችም መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና ያየው ዘንድ ወደ ፊት ሮጦ በአንድ ሾላ ላይ ወጣ። ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና፦ ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው።ፈጥኖም ወረደ በደስታም ተቀበለው።ሁሉም አይተው፦ ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ። ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን፦ ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው። ኢየሱስም፦ እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው።’’(ሉቃ. 19:5-11)
ዘኬዎስ የሚባል የቀራጮች አለቃ ከሰዎች በሚነጥቀው ንብረት ባለ ጠጋ የሆነ ተብሎ በኢያሪኮ ከተማ የሚታማ ሃጢአተኛ ኢየሱስን አግኝቶ ወዲያው ንሰሃ ገባ፣ ወደ አምላኩ ተመለሰ፤ ያ ያልተዋጠላቸው ሊተቹት በጀመረ ጊዜ እርሱ የመለሰው መልስ ከአመጽ ህይወት መመለሱን የሚያንጸባርቅ ነበር፤ አይሁድ በነጣቂነቱ ሲከሱት አዎ ነኝ ግን ከአሁን ጀምሮ (ኢየሱስ ካገኘኝ ጀምሮ) ያሳዘንኩትን ሁሉ በእጥፍ ካሳ እክሰዋለሁ አለ፣ መለወጡንም በትግባር አሳይቶአል።
‘’ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ ኃጢአትንም በሠራ ጊዜ፥ በዚያም ቢሞት፥ እርሱ ባደረገው በደል ይሞታል።ኃጢአተኛውም ከሠራው ኃጢአት ቢመለስ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ይጠብቃል።አስቦ ከሠራው በደል ሁሉ ተመልሶአልና ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።ነገር ግን የእስራኤል ቤት። የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን? የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለዚህ እንደ መንገዱ በየሰዉ ሁሉ እፈርድባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ? የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።’’ (ህዝ. 18:26-32)
የዘላለም ህይወት ያሰጣል፦
‘’… ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው።ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ። እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ? ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና፦ እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ።’’ (ሃስ. 11:15-18)
አዳዲስ ነፍሳት ወደ እግዚአብሄር ሲመለሱ በቤቱ ለቆዩ ልጆቹ መነቃቃት ይፈጥራል፣ እግዚአብሄር በነርሱ ህይወት ያደረገውን ማስታወስና ከየ ስፍራ እንደመለሰም ዳግም ማሰላሰል ፈጥሮ አዲስ ምስጋና፣ ከልብ የሆነ ደስታም ይፈጥራል። ለአዳዲሶች በንሰሃ የጀመረ የህይወት መንገድ ዳግም ከውሃና ከመንፈስ የመወለድ ጸጋን እስኪጎናጸፉ ይመራል፤ የዘላለም ህይወት ለተመለሱ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ ጸጋ ነው፤ ሰዎች ባሉበት የህይወት እስራት ውስጥ ሆነው ልባቸውን ሳያቀኑ ህይወትን ሊያገኙ አይችሉምና።
መዳን ያጎናጽፋል፦
አዲስ ሰው ከምን ከምን ይድናል? አስቀድሞ ከዘላለም ሞት፣ ከዲያቢሎስ እቅድም ነጻ ይወጣል። ነጻነቱም በስጋው ላይ ቀጥሎ ከበሽታ፣ ከድካም፣ ከተለያዩ የማይገቡ ልምምዶች፣ ሱሶች፣ ባህሪዎች ነጻ ይወጣል። እግዚአብሄር ሲያድን አስቀድሞ በመንፈስና በነፍስ ላይ ያለውን እክል፣ ችግር፣ መርገምና የመሳሰሉትን ይሽርልናል፣ ወደ ስጋችን በመቀጠልም ዲያቢሎስ በኛ ላይ የሰራውን ያፈርሳል፣ መዳናችንንም ፍጹም ያደርጋል።
‘’ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።’’(1ቆሮ. 6:9-11)
መዳንን የምንቀበለው አስቀድሞ የመዳን፣ የማምለጥም ሆነ ባሸነፈን ነገር ላይ የበላይነት ስላልነበረን ነው፤ ከላይ የተዘረዘሩት አስቀድሞ የሰለጠኑብን፣ ከእግዚአብሄር ጽድቅ የለዩን የነበሩ ሲሆኑ በአምላካችን አሰራርና በጸጋው ስጦታ የተላቀቅናቸው፣ አሁን ደግሞ በነርሱ ላይ የጸጋ ጉልበት አግኝተን ከበታቻችን ልንገዛቸው የቻልናቸው ናቸው። ባለውለታችን ጌታ ኢየሱስ በእንደዚያ ሁኔታ ከነበርንበት እስር ያወጣን ዘንድ ዋጋ ከፍሎአል፤ የነጻነታችንም አዋጅ ክቃሉ እነሆ በህይወታችን ዘመን ሁሉ እንዲያስተጋባ ሆኖ በእኛ ላይ ታትሞአል። ‘’በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል’’ ይህ ወደ እርሱ የተመለስንበት የድነት አሰራር በእኛ ላይ ጸንቶ እንዲኖር በእኛ ህይወት በጎነቱን የጀመረ አምላክ እስከመጨረሻ ይርዳን። ጸጋው ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።