መመለስ ከወጡበት፣ ከተዉት፣ ከተሰናበቱት፣ ከተጣሉት፣ ካኮረፉት እንዲሁም ከጣሉት ነገር ሊሆን ይችላል። መመለስ ከወጡበት ነገር ሲሆን ዳግም ወደ ቤት፣ ወደ አገር፣ ወደ ስራ፣ ወደ ልማድ፣ ወደ ካዱት፣ ወደ ረሱት፣ ወደ ጠሉትም ነገር ሁሉ ሊሆን ይችላል። በመመለስ አልፈልግም ብለው ከተዉት ነገር፣ ስራ ወይም ሰው ዳግም የመገናኘት እድል ይፈጥራል። የጠላነው ይሁን የወደድነው በሆነ አጋጣሚ ወይም ተጽእኖ ምክኒያት ትተነው ከተሰናበትነው በሁዋላ ዳግም በመመለስ ልንፈልገውና ልንገናኘው እንችላለን። በመመለስ የተጣላነውን ልማድ (ልምምምድ ጭምር) እና ሰው እንገናኛለን። ካኮረፍነው ሰው (አምላክ ጭምር) ዳግም መዋሃድ የምንችለው በመመለስ ስናምን ብቻ ነው። መመለስ ያጣነውን የኛን የነበረ ነገር ማግኛ ዋነኛ መሳርያ ነው። ሆኖም አሳሳቢው ጥያቄ መመለስ ስለምን አላማ? የሚለው ነው።
መመለስ ክፉም በጎም ጎን አለው፦ ከመጥፎ ነገር ወጥተው ሳለ ወደ ወጡበት ወደዚያ አስከፊ ነገር ዳግም መመለስ ክፋቱን ያባብሳል፣ ጥፋትንም ያፋጥናል። ደግሞ በጎውን ነገር እምቢ ብለው ወደ ሁዋላ ካሉበት ነቅተው (እንደወጡ በዚያው ሳይቀሩ) በጸጸት መመለስ ከቻሉ ወደ ተሻለ ከፍታ ይደርሳሉ። ከዚህ ሌላ መመለስ በብዙ አስገዳጅ ምክኒያቶች ሊሆን እንደሚችል ማየት እንችላለን።
በብዙ መልኩ ከመልካሙ የህይወት ይዘታችን ወደ ሁዋላ ስንመለስ ሊገፋን የሚችለው እያንዳንዱ ምክኒያት የተሻለን ነገር ፍለጋ እንደማይሆን እሙን ነው፦ ከዚህ ይልቅ ወደ አጥፊ አመል መመለስ፣ ወደ ሱስ መመለስ፣ ሌላም ማንነታችን ይበልጥ አዘቅጥ ውስጥ ሊከትና መንፈሳችንን ሊያደቅቅ ወደሚችል አስቀድመን በተለይ ወደ ተውነው መመለስ ተደራራቢ ችግር ውስጥ የሚያስገባ ነው። ከመልካም ህይወት፣ ኑሮ፣ ጸባይና ከመሳሰሉት በጎ ጅማሬዎች ወጥተን እንደሆን ፈጥነንም ሆነ ዘግይተን ወደቀድሞ ሁኔታችን መመለሳችን የሚደገፍ፣ በጎ የሆነ፣ አስተማሪና የሚያንጽ ነው የሚሆነው።
አለምን ከሚያከፉዋት ድርጊቶች መሃል የሰዎች ክፉ አመል አንዱ ነው፤ ሰዎች በሚለማመዱት የክፋት ስራ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ጎረቤትና ማህበረሰባቸውን አልፎም ምድራቸውን ያስጨንቃሉ። ይህን ልማድ ነጥቀው የሚወጡ ግን ታላቅ ለውጥ ወደ ህይወታቸው የሚያመጡ ናቸው።
ሰዎች ከቤተክርስቲያን በጽድቅ ከመኖር ማፈንገጥ ውስጥ ሲወድቁ በተለያየ አቅጣጫ ከእምነት መንሸራተት ያጋጥማል፤ ከዚህ መንፈሳዊ ከፍታ መውረድ ዋጋ ከማስከፈል አልፎ የተሰጠንን ህይወትን ዋጋ እስከሚያስረሳ ድረስ ትልቅ ተጽእኖም የሚያመጣ ነው። በእግዚአብሄር ምህረትና እርዳታ ግን ከጠፋንበት እንመለሳለን፣ ከወደቅንበት እንነሳለን፣ ከጠፋንበት እንገኛለን፤ ይህ ተስፋ የሚያበረታን ነው።
የእስራኤል ህዝብ ግን በዚህ ነገር መጥፎ ታሪክ አለው፦ ከወጣበት የግብጽ ባርነት ምድር ይመለስ ዘንድ በልቡ ከማሰብ አልፎ በምክክር ሴራ ውስጥ ይገባ ዘንድ ፈቅዶ የነበረ ቢሆንም በዚህ እቅዱ የደረሰበት የአምላክ ቁጣ ከጽድቅ መንገድ የመመለስን ዋጋ አመልካች ነው፦
‘’ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን አንሥተው ጮኹ፤ ሕዝቡም በዚያ ሌሊት አለቀሱ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ። በግብፅ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! ወይም በዚህ ምድረ በዳ ምነው በሞትን ኖሮ! እግዚአብሔርም በሰይፍ እንሞት ዘንድ ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሴቶቻችንና ልጆቻችን ምርኮ ይሆናሉ፤ ወደ ግብፅ መመለስ አይሻለንምን? አሉአቸው። እርስ በርሳቸውም፦ ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ።ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ፊት በግምባራቸው ወደቁ።’’ (ዘሁ. 14:1-5)
የማህበሩ ለቅሶ አንድም ክህደት ያለበት፣ ያለማመንና እግዚአብሄርን ማስቆጣትም የታከለበት ነበር፤ ይህም በእግዚአብሄር ፊት ትልቅ ቁጣን አምጥቶአል። እግዚአብሄር አባቶቻቸውን ወድዶና ቃልኪዳኑን አክብሮ ለልጆቻቸው የተገለጠበትን ታላቅ መገለጥ ችላ በማለት ወደ ሁዋላ ሊያውም ወደ ገዙዋቸው፣ ወደ አስጨነቁዋቸው፣ ትውልዳቸውን ወደፈጁትና ለዘላለም ባሪያ ያደርጉዋቸው ዘንድ ወደ ተማማሉት ጠላቶቻቸው ልባቸውን ማዘንበላቸው ትልቅ ክህደት ነበር።
የተመለሱትን የሚመልሱ መልካም መንፈስ የነበራቸው ከመሃላቸው ስለነበሩ መቅሰፍቱ ተመልሶአል፤ ወደሁዋላ የሚንሸራተቱትን፣ እምነት ባነሰ ጊዜ እምነትን የሚደግፉ ወገኖችን እግዚአብሄር ባያዘጋጅ ኖሮ ትውልድ ይቆረጥ እንደነበር እንመለከታለን።
‘’እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። የሚያጕረመርምብኝን ይህን ክፉ ሕዝብ እስከ መቼ እታገሠዋለሁ? በእኔ ላይ የሚያጕረመርሙትን የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ሰማሁ።እንዲህ በላቸው። እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ የተቆጠራችሁ ሁሉ፥ እንደቁጥራችሁ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ፥ እናንተ ያጕረመረማችሁብኝ፥ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርስዋ አስቀምጣችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም።ምርኮኛ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን አገባቸዋለሁ፥ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ያውቃሉ።እናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ። ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይቅበዘበዛሉ፥ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ግልሙትናችሁን ይሸከማሉ።…. በነጋውም ማልደው ተነሡ፥ ወደ ተራራውም ራስ መጥተው፦ እነሆ፥ መጣን፤ እኛ በድለናልና እግዚአብሔር ወዳለው ስፍራ እንወጣለን አሉ።ሙሴም አለ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይጠቅማችሁም። እግዚአብሔር በእናንተ መካከል አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ።አማሌቃዊና ከነዓናዊ በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋልና እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይሆንም። እነርሱ ግን ወደ ተራራው ራስ ሊወጡ ደፈሩ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ አልተነሡም። በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ አማሌቃዊና ከነዓናዊ ወረዱ፥ መትተዋቸውም እስከ ሔርማ ድረስ አሳደዱአቸው።’’ (ዘሁ. 14:26-45)
1.ደክመው የነበሩ በንሰሃ ሲመለሱ ታላቅ ደስታ በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ ይሆናል
‘’(ጌታ ኢየሱስ) እንዲህም አለ፦ አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን፦ አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገዘቡን በተነ። ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም። ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው።’’(ሉቃ. 15:11-20)
የደከምንበትና የኮበለልንበት ምክኒያት ምንም ይሁን የተመለስንበት አመላለስ ግን ወሳኝና ትርጉም ያለው መሆን አለበት፦ ይህ ልጅ ከአባቱ ቤት ያስኮበለለው ምክኒያት በአባቱ ዘንድ ባለው ሃብት የጥቅም ድርሻ ጉጉትና የራሱን ክፍል ወስዶም እንዳሻው ምኞቱን መሆን ሲሆን በዚህ መሻቱ ያላስተዋለውን የአባቱን ቤት ደስታና ከለላ ጥሶ ስለኮበለለ ምኝቱን ፈጽሞ ሳለ በአባቱ ቤት የነበረው ሞገስ ግን ስለጎደለ እንደቀድሞ የመሆን እድል አጣ፣ ተጎሳቆለ፣ ተመልካችም አልነበረውም፤ ነገር ግን ማስተዋሉ ሲመለስ ጥሎት የመጣው ቤት ክብርና የአባቱ ፍቅር ትዝ ብሎት ንሰሃ ገባ፣ ወደ አባቱ ሊመለስ ተዘጋጀ፣ ያ ውሳኔውም በመጨረሻ አተረፈው።
የጠፋ ሲመለስ በእግዚአብሄር ቤት ብዙ ነገር ይሆናል፦ ወንድሞች በደስታ ይሞላሉ፣ ወንድማችን ጠፍቶ ነበር ተገኘ ሲሉ አምላካቸውን ያመሰግናሉ፣ በሰማይም ታላቅ ደስታ ይሆናል።
ጌታ ኢየሱስም በሉቃ.15:10 ሲናገር እንዲህ አለ፦
‘’እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል’’
መመለስ ቀላል ነገር አይደለም፣ ውጤት አለው፤ ምክኒያቱም በአንድ ሰው መመለስ ምክኒያት የሚመለስ ነገር ይኖራልና፣ ለምሳሌ ሰው በተመለሰ ጊዜ፦
ወደ ልቡ ይመለሳል:-
ያ ልጅ ወደ ልቡ ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። ውሳኔው ቁርጥ ያለና ለውጤት ያንቀሳቀሰው ነበር። በእርግጥ አቅልን ካሳተ መንገድ መመለስ የመለወጥ ጅማሬ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፤ ልባችን ትልቅ የህይወት ክፍል እንደመሆኑ በመመለሳችን አስተሳሰባችን እንዲስተካከል፣ የጠፋንበትን አሳብ ትተን የህይወት ቃል እንድናፈልቅ፣ አዲስ ማንነት የሚያንጽ አስተሳሰብ፣ አፈላለግ፣ ንግግርና አስተሳሰብ እንዲኖረን ያስችላል። ባለመመለስ ልብ ለጠላት ክፍት ሲሆን በመመለስ ግን የጠላትን በር በመዝጋት ክፉውን ከራስ ማራቅ ያስችላል፤ ጠላት የህይወት ማእከል የሆነውን በመቆጣጠር የዘፈቀደ ህይወት እንድንኖርና ከእግዚአብሄር ጋር እንድንጣላ ሲሰራ መመለስና ከአምላክ ጋር እታረቅ ጠላትን የሚያሳጥር ይሆናል።
‘’የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ እናንተም እንቢ አላችሁ፥ነገር ግን፦ በፈረስ ላይ ትቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም አላችሁ፥ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ደግሞም፦ በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን አላችሁ፥ ስለዚህም የሚያሳድዱአችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ። ከአንድ ሰው ዛቻ የተነሣ ሺህ ሰዎች ይሸሻሉ፤ እናንተም በተራራ ራስ ላይ እንዳለ ምሰሶ፥ በኮረብታም ላይ እንዳለ ምልክት ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፥ ከአምስት ሰዎች ዛቻ የተነሣ ትሸሻላችሁ። እግዚአብሔርም የፍርድ አምላክ ነውና ስለዚህ እግዚአብሔር ይራራላችሁ ዘንድ ይታገሣል፥ ይምራችሁም ዘንድ ከፍ ከፍ ይላል፤ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።’’ (ኢሳ. 30:15-18)
ወደ ኢየሱስ ይመለሳል፦
ከኢየሱስ የተጣላና ከአባቱ ቤት የኮበለለ ዱር ይገባና የመናፍስት ጥቃት ተጋላጭ ይሆናል፤ አለምን እንደዚያ ብናያት (መናፍስት የሚመሽጉባትና ቅዱሳንን የሚያጠቁባት ስፍራ እንደመሆንዋ) መከላከያ አጥር ኢየሱስን የተወ ለመናፍስቱ ጥቃት ከመጋለጥ እንደማያመልጥ ሊገነዘብ ተገቢ ነው። እግዚአብሄር አለታችን ነው፣ አምባችን ነው፣ አጥራችን ነው፣ መሸሸጊያም ነው፣ ማምለጫና መታመኛ እርሱ ነው። ወደ እርሱ የተመለሰ የጣለውን የእግዚአብሄር ክብር ይቀበላል፤ ወደ እርሱ የተመለሰ የተገፈፈ ሞገሱን ዳግም ያገኛል፣ ጸጋውን ይቀበላል።
‘’እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም። እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።’’ (እብ. 10:38-41)
ወደ ህይወት ይመለሳል፦
ህይወታችን የተመካው በኢየሱስ ማንነትና እርሱ ከእኛ ጋር በመሆኑ ብቻ ነው፤ ከኢየሱስ በራቅን ወቅት መንፈሱ ከእኛ ስለሚለየን በስጋ መንፈስና በአጋንንት መንፈስ የመጠቃት አጋጣሚ ላይ እንወድቃለን፤ በንሰሃ ስንመለስ ጌታ ኢየሱስ በምህረቱ ይቀበለንና መንፈሱን ይሞላናል፤ መንፈሱ እኛን ህያው በማድረግ በእግዚአብሄር መገኛ ውስጥ ዳግም እንድንመላለስ ያስችለናል። መንፈስ ቅዱስ የሌለው ደረቅ ህይወት በስጋ መንፈስ የሚጎሳቆል በመሆኑ ለተለያየ ጥቃት ተጋላጭ ነው፤ የህይወት አጥሩ ክፍት የሆነ፣ በጠላት የተሰበረና የተማረከ ህይወት አለም ከወዲያ ወዲህ የምታንገላታው ይሆናል፤ ኑሮ አይቀናውም፣ ቢቀናውም ከህሊና ውጪ በሆነ ነገር የሚጠመድ ስለሚሆን ነፍሱ የምትንገላታ ነች።
‘’የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለዚህ እንደ መንገዱ በየሰዉ ሁሉ እፈርድባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ?የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።’’ (ህዝ. 18:30-32)
ወደ ትክክለኛ ውሳኔ ይመለሳል፦
ወደ ልቦና ስንመለስ ያላስተዋልነውን እናስተውላለን፣ የተውነውን እንፈልጋለን፣ የረሳነውን እናስታውሳለን፣ ቸል ያልነውን በቁም ነገር እናየዋለን። ቸልተኝነት በመጥፋት ሲፈጠር ማስተዋል በመመለስ ይገኛል፤ ያፈነገጡ፣ የከዱ ወይም የደከሙ ሰዎች መንፈሳዊ ህይወትን በድርበቡ ወይም በጨለማው የሚመለከቱ ይሆናሉ፤ ያ ተጽእኖ ከጽድቅ ውጪና ከህሊና ውጪ አድርጎ የእግዚአብሄርን ትእዛዝ፣ ምሪት፣ አሳብ በሙሉ ያስረሳል፣ ድፍረትም ያላብሳል። እግዚአብሄር ሲራራ ግን ወደ ልቦና ይመልሳል።
‘’እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን እንዴት ያለ ትጋት፥ እንዴት ያለ መልስ፥ እንዴት ያለ ቁጣ፥ እንዴት ያለ ፍርሃት፥ እንዴት ያለ ናፍቆት፥ እንዴት ያለ ቅንዓት፥ እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል።’’ (2ቆሮ. 7:10-11)